መዝሙር። የአሳፍ+ ማህሌት።
83 አምላክ ሆይ፣ ዝም አትበል፤+
አምላክ ሆይ፣ ጸጥ አትበል፤ ደግሞም ጭጭ አትበል።
2 እነሆ፣ ጠላቶችህ እየደነፉ ነውና፤+
አንተን የሚጠሉ በእብሪት ይመላለሳሉ።
3 በስውር በሕዝቦችህ ላይ የተንኮል ሴራ ይሸርባሉ፤
በውድ አገልጋዮችህ ላይ ይዶልታሉ።
4 “የእስራኤል ስም ተረስቶ እንዲቀር፣
ኑ፣ ሕዝቡን እንደምስስ” ይላሉ።+
5 የጋራ ዕቅድ ይነድፋሉ፤
በአንተ ላይ ግንባር ፈጥረዋል፤+
6 የኤዶምና የእስማኤላውያን ድንኳኖች፣ ሞዓብና+ አጋራውያን፣+
7 ጌባል፣ አሞንና+ አማሌቅ፣
እንዲሁም ፍልስጤም+ ከጢሮስ ነዋሪዎች+ ጋር አበሩ።
8 አሦርም+ ከእነሱ ጋር ተባብሯል፤
ለሎጥ ልጆችም+ድጋፍ ይሰጣሉ። (ሴላ)
9 በምድያም እንዳደረግከው፣
በቂሾንም ጅረት በሲሳራና በያቢን ላይ እንዳደረግከው አድርግባቸው።+
10 እነሱ በኤንዶር+ ተደመሰሱ፤
ለምድርም ፍግ ሆኑ።
11 በመካከላቸው ያሉትን ታላላቅ ሰዎች እንደ ኦሬብና ዜብ፣+
አለቆቻቸውንም እንደ ዘባህና ጻልሙና አድርጋቸው፤+
12 እነሱ “አምላክ የሚኖርባቸውን ቦታዎች እንውረስ” ብለዋልና።
13 አምላኬ ሆይ፣ ነፋስ እያሽከረከረ እንደሚወስደው ኮሸሽላ፣+
ነፋስ እንደሚጠርገው ገለባ አድርጋቸው።
14 ጫካን እንደሚያቃጥል እሳት፣
ተራሮችን እንደሚያነድ ነበልባል፣+
15 አንተም እንዲሁ በሞገድህ አሳዳቸው፤+
በአውሎ ነፋስህም አሸብራቸው።+
16 ይሖዋ ሆይ፣ ስምህን ይሹ ዘንድ፣
ፊታቸውን በኀፍረት ሸፍን።
17 ለዘላለም ይፈሩ፣ ይሸበሩም፤
ውርደት ይከናነቡ፤ ደግሞም ይጥፉ፤
18 ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣+
አዎ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል እንደሆንክ+ ሰዎች ይወቁ።