27 ነገ በሚሆነው ነገር አትመካ፤
ቀን የሚያመጣውን አታውቅምና።+
2 የገዛ አፍህ ሳይሆን ሌላ ሰው ያመስግንህ፤
የገዛ ከንፈርህ ሳይሆን ሌሎች ያወድሱህ።+
3 ድንጋይ ከባድ ነው፤ አሸዋም ሸክም ነው፤
የሞኝ ሰው ትንኮሳ ግን ከሁለቱም ይከብዳል።+
4 ንዴት ጨካኝ ነው፤ ቁጣም ጎርፍ ነው፤
ይሁንና ቅናትን ማን ሊቋቋም ይችላል?+
5 ከተሰወረ ፍቅር ይልቅ የተገለጠ ወቀሳ ይሻላል።+
6 የወዳጅ ማቁሰል ከታማኝነት የሚመነጭ ነው፤+
የጠላት መሳም ግን የበዛ ነው።
7 የጠገበ ሰው ከማር እንጀራ የሚገኝን ማር አይፈልግም፤
የተራበ ግን የሚመር ነገር እንኳ ይጣፍጠዋል።
8 ከቤቱ ወጥቶ የሚባዝን ሰው
ከጎጆዋ ወጥታ እንደምትባዝን ወፍ ነው።
9 ዘይትና ዕጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፤
በቀና ምክር ላይ የተመሠረተ ጥሩ ወዳጅነትም እንዲሁ ነው።+
10 መከራ ባጋጠመህ ቀን የራስህንም ሆነ የአባትህን ወዳጅ ትተህ
ወደ ገዛ ወንድምህ ቤት አትግባ፤
ሩቅ ቦታ ካለ ወንድም ይልቅ በቅርብ ያለ ጎረቤት ይሻላል።+
11 ልጄ ሆይ፣ ለሚነቅፈኝ መልስ መስጠት እችል ዘንድ
ጥበበኛ ሁን፤+ ልቤንም ደስ አሰኘው።+
12 ብልህ ሰው አደጋ አይቶ ይሸሸጋል፤+
ተሞክሮ የሌለው ሰው ግን ዝም ብሎ ይሄዳል፤ መዘዙንም ይቀበላል።
13 አንድ ሰው ለማያውቀው ሰው ዋስ ከሆነ ልብሱን ውሰድበት፤
ይህን ያደረገው ለባዕድ ሴት ብሎ ከሆነ መያዣውን ውሰድ።+
14 ሰው በማለዳ ድምፁን ከፍ አድርጎ ባልንጀራውን ቢባርክ
እንደ እርግማን ይቆጠርበታል።
15 ጨቅጫቃ ሚስት በዝናባማ ቀን ያለማቋረጥ እንደሚያንጠባጥብ ጣሪያ ናት።+
16 እሷን መግታት የሚችል ሁሉ ነፋስን መግታት፣
ዘይትንም በቀኝ እጁ መጨበጥ ይችላል።
17 ብረት ብረትን እንደሚስል ሁሉ
ሰውም ጓደኛውን ይስለዋል።+
18 የበለስን ዛፍ የሚንከባከብ ፍሬዋን ይበላል፤+
ጌታውንም የሚንከባከብ ክብር ይጎናጸፋል።+
19 ውኃ የሰውን ፊት እንደሚያንጸባርቅ ሁሉ፣
የሰውም ልብ የሌላ ሰው ልብ ነጸብራቅ ነው።
20 መቃብርና የጥፋት ቦታ አይጠግቡም፤+
ልክ እንደዚሁም የሰው ዓይን ፈጽሞ አይጠግብም።
21 ማቅለጫ ለብር፣ ምድጃ ለወርቅ ነው፤+
ሰውም በሚቀበለው ውዳሴ ይፈተናል።
22 ሞኝን ሙቀጫ ውስጥ ከተህ በዘነዘና ብትወቅጠውና
እንደ እህል ብታደቀው እንኳ
ሞኝነቱ ከእሱ አይወገድም።
23 የመንጋህን ሁኔታ በሚገባ እወቅ።
በጎችህን በደንብ ተንከባከብ፤+
24 ሀብት ለዘላለም አይኖርምና፤+
አክሊልም ከትውልድ እስከ ትውልድ ጸንቶ አይኖርም።
25 ሣሩ በቦታው የለም፤ አዲስ ሣርም በቅሏል፤
በተራሮች ላይ ያለው ተክልም ተሰብስቧል።
26 የበግ ጠቦቶች ለልብስ፣
አውራ ፍየሎችም ለመሬት መግዣ ይሆኑልሃል።
27 ደግሞም አንተንና ቤተሰብህን ለመመገብ፣
ልጃገረዶችህንም በሕይወት ለማኖር የሚያስችል በቂ የፍየል ወተት ይኖርሃል።