የማቴዎስ ወንጌል
3 በዚያ ወቅት መጥምቁ ዮሐንስ+ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ፤+ 2 “መንግሥተ ሰማያት ስለቀረበ ንስሐ ግቡ” ይል ነበር።+ 3 “አንድ ሰው በምድረ በዳ ‘የይሖዋን* መንገድ አዘጋጁ፤ ጎዳናዎቹንም አቅኑ’+ በማለት ይጮኻል” ተብሎ በነቢዩ ኢሳይያስ የተነገረለት እሱ ነው።+ 4 ዮሐንስ ከግመል ፀጉር የተሠራ ልብስ ይለብስ፣ ወገቡም ላይ የቆዳ ቀበቶ ይታጠቅ ነበር።+ ምግቡ አንበጣና የዱር ማር ነበር።+ 5 በኢየሩሳሌምና በመላዋ ይሁዳ እንዲሁም በዮርዳኖስ ዙሪያ ባለው ክልል ሁሉ የሚኖሩ ሰዎች ወደ እሱ ይመጡ ነበር፤+ 6 ደግሞም ኃጢአታቸውን በግልጽ እየተናዘዙ ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በእሱ ይጠመቁ* ነበር።+
7 ብዙ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን+ ወደሚያጠምቅበት ቦታ ሲመጡ ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የእፉኝት ልጆች፣+ ከሚመጣው ቁጣ+ እንድትሸሹ ያስጠነቀቃችሁ ማን ነው? 8 እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አፍሩ። 9 ‘እኛ እኮ አባታችን አብርሃም ነው’ ብላችሁ አታስቡ።+ አምላክ ለአብርሃም ከእነዚህ ድንጋዮች ልጆች ሊያስነሳለት እንደሚችል ልነግራችሁ እወዳለሁ። 10 መጥረቢያው ዛፎቹ ሥር ተቀምጧል። ስለዚህ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ተቆርጦ እሳት ውስጥ ይጣላል።+ 11 እኔ በበኩሌ ንስሐ በመግባታችሁ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤+ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይበረታል፤ እኔ ጫማውን ለማውለቅ እንኳ ብቁ አይደለሁም።+ እሱ በመንፈስ ቅዱስና+ በእሳት+ ያጠምቃችኋል። 12 ላይዳውን* በእጁ ይዟል፤ አውድማውንም ፈጽሞ ያጸዳል፤ ስንዴውንም ወደ ጎተራ ያስገባል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።”+
13 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ።+ 14 ዮሐንስ ግን “በአንተ መጠመቅ የሚያስፈልገኝ እኔ ሆኜ ሳለ አንተ ወደ እኔ ትመጣለህ?” ብሎ ሊከለክለው ሞከረ። 15 ኢየሱስም መልሶ “ግድ የለም እሺ በለኝ፤ በዚህ መንገድ ጽድቅ የሆነውን ሁሉ መፈጸማችን ተገቢ ነው” አለው። በዚህ ጊዜ ዮሐንስ ፈቀደለት። 16 ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃው ወጣ፤ እነሆ፣ ሰማያት ተከፈቱ፤+ የአምላክም መንፈስ በእሱ ላይ እንደ ርግብ ሲወርድ አየ።+ 17 ደግሞም “በጣም የምደሰትበት+ የምወደው ልጄ ይህ ነው”+ የሚል ድምፅ ከሰማያት ተሰማ።+