25 እነዚህም የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ+ ሰዎች የጻፏቸው የሰለሞን ምሳሌዎች ናቸው፦+
2 አንድን ጉዳይ መሰወር ለአምላክ ክብሩ ነው፤+
ጉዳይን በሚገባ መመርመር ደግሞ ለነገሥታት ክብራቸው ነው።
3 ሰማያት ከፍ ያሉ እንደሆኑ፣ ምድርም ጥልቅ እንደሆነች ሁሉ
የንጉሥም ልብ አይመረመርም።
4 የብርን ቆሻሻ አስወግድ፤
ሙሉ በሙሉም የጠራ ይሆናል።+
5 ክፉን ሰው ከንጉሥ ፊት አስወግድ፤
ዙፋኑም በጽድቅ ይጸናል።+
6 በንጉሥ ፊት ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ፤+
ታላላቅ ሰዎችም ባሉበት ስፍራ አትቀመጥ፤+
7 በተከበረ ሰው ፊት ከሚያዋርድህ
እሱ ራሱ “ወደዚህ ከፍ በል” ቢልህ ይሻላልና።+
8 ክስ ለመመሥረት አትቸኩል፤
የኋላ ኋላ ባልንጀራህ ቢያዋርድህ ምን ይውጥሃል?+
9 ከባልንጀራህ ጋር ስለ ራስህ ጉዳይ ተሟገት፤+
ሆኖም በሚስጥር የተነገረህን ጉዳይ አትግለጥ፤+
10 አለዚያ የሚሰማህ ሰው ያዋርድሃል፤
ያናፈስከውንም መጥፎ ወሬ መመለስ አትችልም።
11 በተገቢው ጊዜ የተነገረ ቃል
ከብር በተሠራ ዕቃ ላይ እንዳለ የወርቅ ፖም ነው።+
12 በጥበብ ወቀሳ የሚሰጥ ሰው፣ የሚሰማ ጆሮ ላለው
እንደ ወርቅ ጉትቻና ከጥሩ ወርቅ እንደተሠራ ጌጥ ነው።+
13 ታማኝ መልእክተኛ ለላኩት ሰዎች
በመከር ወቅት እንደሚገኝ የበረዶ ቅዝቃዜ ነው፤
የጌታውን መንፈስ ያድሳልና።+
14 የማይሰጠውን ስጦታ እሰጣለሁ እያለ ጉራውን የሚነዛ ሰው
ዝናብ እንደማያመጣ ደመናና ነፋስ ነው።+
15 በትዕግሥት አዛዥን ማሸነፍ ይቻላል፤
ለስላሳም አንደበት አጥንትን ይሰብራል።+
16 ማር ካገኘህ የሚበቃህን ያህል ብቻ ብላ፤
ከልክ በላይ ከበላህ ሊያስመልስህ ይችላልና።+
17 እንዳይሰለችህና እንዳይጠላህ
ወደ ባልንጀራህ ቤት እግር አታብዛ።
18 በባልንጀራው ላይ በሐሰት የሚመሠክር
እንደ ቆመጥ፣ እንደ ሰይፍና እንደ ሹል ፍላጻ ነው።+
19 በችግር ወቅት እምነት በማይጣልበት ሰው መተማመን፣
እንደተሰበረ ጥርስና እንደሰለለ እግር ነው።
20 ላዘነ ልብ የሚዘምር ሰው፣
በብርድ ቀን ልብሱን እንደሚያወልቅ፣
በሶዳም ላይ እንደተጨመረ ኮምጣጤ ነው።+
21 ጠላትህ ቢራብ ምግብ ስጠው፤
ቢጠማ ውኃ ስጠው፤+
22 ይህን ብታደርግ በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህና፤+
ይሖዋም ወሮታ ይከፍልሃል።
23 የሰሜን ነፋስ ኃይለኛ ዝናብ ያመጣል፤
ሐሜተኛ ምላስም የሰውን ፊት ያስቆጣል።+
24 ከጨቅጫቃ ሚስት ጋር በአንድ ቤት ከመኖር
በጣሪያ ማዕዘን ላይ መኖር ይሻላል።+
25 ቀዝቃዛ ውኃ የዛለችን ነፍስ እንደሚያረካ ሁሉ
ከሩቅ አገር የመጣ መልካም ወሬም እንዲሁ ነው።+
26 ለክፉ ሰው የሚንበረከክ ጻድቅ፣
እንደጨቀየ ምንጭና እንደተበከለ የውኃ ጉድጓድ ነው።
27 ብዙ ማር መብላት ጥሩ አይደለም፤+
የራስንም ክብር መሻት አያስከብርም።+
28 ስሜቱን መቆጣጠር የማይችል ሰው
ቅጥር እንደሌላት የፈረሰች ከተማ ነው።+