ሁለተኛ ነገሥት
17 የይሁዳ ንጉሥ አካዝ በነገሠ በ12ኛው ዓመት የኤላህ ልጅ ሆሺአ+ በሰማርያ ሆኖ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ እሱም ለዘጠኝ ዓመት ገዛ። 2 ከእሱ በፊት የነበሩትን የእስራኤል ነገሥታት ያህል አይሁን እንጂ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። 3 የአሦር ንጉሥ ሰልምናሶር በእሱ ላይ መጣ፤+ ሆሺአም አገልጋዩ ሆነ፤ ገበረለትም።+ 4 ሆኖም የአሦር ንጉሥ ሰልምናሶር ሆሺአ እንዳሴረበት አወቀ፤ ምክንያቱም ሆሺአ ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ሶህ መልእክተኞች ልኮ ነበር፤+ ደግሞም ቀደም ባሉት ዓመታት ያደርግ እንደነበረው ለአሦር ንጉሥ መገበሩን አቁሞ ነበር። ስለሆነም የአሦር ንጉሥ እስር ቤት ውስጥ አስሮ አስቀመጠው።
5 የአሦር ንጉሥ መላ አገሪቱን ወረረ፤ ወደ ሰማርያም መጥቶ ከተማዋን ለሦስት ዓመት ከበባት። 6 ሆሺአ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰማርያን ያዘ።+ ከዚያም የእስራኤልን ሕዝብ ወደ አሦር በግዞት+ በመውሰድ በሃላህ፣ በጎዛን+ ወንዝ አጠገብ በምትገኘው በሃቦርና በሜዶናውያን ከተሞች አሰፈራቸው።+
7 ይህ የሆነው የእስራኤል ሰዎች ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን ቀንበርና ከግብፅ ምድር ነፃ ባወጣቸው በአምላካቸው በይሖዋ ላይ ኃጢአት ስለሠሩ ነው።+ እነሱም ሌሎች አማልክትን አመለኩ፤*+ 8 ይሖዋ ከእስራኤላውያን ፊት ያባረራቸውን ብሔራት ልማዶች ተከተሉ፤ ደግሞም የእስራኤል ነገሥታት ያቋቋሟቸውን ልማዶች ተከተሉ።
9 እስራኤላውያን በአምላካቸው በይሖዋ ፊት ትክክል ያልሆኑ ነገሮችን ያደርጉ ነበር። ከመጠበቂያው ግንብ አንስቶ እስከተመሸገው ከተማ ድረስ በሁሉም ከተሞቻቸው* ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችን ሠሩ።+ 10 በእያንዳንዱ ኮረብታ ላይና በእያንዳንዱ የለመለመ ዛፍ ሥር+ የማምለኪያ ዓምዶችንና የማምለኪያ ግንዶችን*+ ለራሳቸው አቆሙ፤ 11 ይሖዋ ከፊታቸው አሳዶ በግዞት እንዲወሰዱ ያደረጋቸው ብሔራት ያደርጉ እንደነበረው ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ሁሉ የሚጨስ መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር።+ ይሖዋን ለማስቆጣት ክፉ ነገሮችን ማድረጋቸውን ቀጠሉ።
12 ይሖዋ “አታድርጉ!”+ ያላቸውን ነገር በማድረግ አስጸያፊ የሆኑ ጣዖቶችን* አገለገሉ፤+ 13 ይሖዋ በነቢያቱ ሁሉና በእያንዳንዱ ባለ ራእይ+ አማካኝነት እስራኤልንና ይሁዳን “ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ!+ አባቶቻችሁን ባዘዝኳቸውና በአገልጋዮቼ በነቢያት በኩል ለእናንተ በሰጠሁት ሕግ መሠረት ትእዛዛቴንና ደንቦቼን ጠብቁ” በማለት በተደጋጋሚ ያስጠነቅቃቸው ነበር። 14 እነሱ ግን አልሰሙም፤ በአምላካቸው በይሖዋ እንዳላመኑት አባቶቻቸው እነሱም ግትሮች ሆኑ።*+ 15 ሥርዓቶቹን፣ ከአባቶቻቸው ጋር የገባውን ቃል ኪዳንና+ እነሱን ለማስጠንቀቅ የሰጣቸውን ማሳሰቢያዎች ችላ አሉ፤+ ደግሞም ይሖዋ የእነሱን ምሳሌ እንዳይከተሉ ያዘዛቸውን+ በዙሪያቸው ያሉትን ብሔራት በመምሰል ከንቱ ጣዖቶችን ተከተሉ፤+ እነሱ ራሳቸውም ከንቱ ሆኑ።+
16 የአምላካቸውን የይሖዋን ትእዛዛት በሙሉ ተዉ፤ ለራሳቸውም ከብረት የተሠሩ ሁለት የጥጃ ሐውልቶችን* አበጁ፤+ የማምለኪያም ግንድ*+ ሠሩ፤ ለሰማያት ሠራዊት ሁሉ ሰገዱ፤+ እንዲሁም ባአልን አገለገሉ።+ 17 ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም ለእሳት አሳልፈው ሰጡ፤+ ሟርተኞችና ጠንቋዮች ሆኑ፤+ ይሖዋንም ያስቆጡት ዘንድ በእሱ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሰጡ።*
18 በመሆኑም ይሖዋ በእስራኤል ላይ እጅግ ተቆጣ፤ ስለሆነም ከፊቱ አስወገዳቸው።+ ከይሁዳ ነገድ ሌላ ማንንም አላስቀረም።
19 የይሁዳም ሰዎች ቢሆኑ የአምላካቸውን የይሖዋን ትእዛዛት አልጠበቁም፤+ እነሱም እስራኤላውያን በተከተሏቸው ልማዶች ተመላለሱ።+ 20 ይሖዋም የእስራኤልን ዘሮች ሁሉ ተወ፤ ከፊቱም እስኪያስወግዳቸው ድረስ አዋረዳቸው፤ ለሚበዘብዟቸውም ሰዎች አሳልፎ ሰጣቸው። 21 እስራኤልን ከዳዊት ቤት ለየ፤ እነሱም የናባጥን ልጅ ኢዮርብዓምን አነገሡት።+ ሆኖም ኢዮርብዓም እስራኤላውያን ይሖዋን ከመከተል ዞር እንዲሉና ከባድ ኃጢአት እንዲሠሩ አደረገ። 22 የእስራኤልም ሰዎች ኢዮርብዓም የፈጸማቸውን ኃጢአቶች ሁሉ ሠሩ።+ ከዚያ ዞር አላሉም፤ 23 ይህም የሆነው ይሖዋ በአገልጋዮቹ በነቢያት ሁሉ አማካኝነት በተናገረው መሠረት እስራኤልን ከፊቱ እስኪያስወግድ ድረስ ነው።+ በመሆኑም እስራኤላውያን ከገዛ ምድራቸው ወደ አሦር በግዞት ተወሰዱ፤+ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ ይገኛሉ።
24 የአሦርም ንጉሥ ሰዎችን ከባቢሎን፣ ከኩታ፣ ከአዋ፣ ከሃማትና ከሰፋርዊም+ አምጥቶ በእስራኤላውያን ምትክ በሰማርያ ከተሞች አሰፈራቸው፤ እነሱም ሰማርያን ወርሰው በከተሞቿ መኖር ጀመሩ። 25 በዚያ መኖር እንደጀመሩ አካባቢ ይሖዋን አይፈሩም* ነበር። በመሆኑም ይሖዋ በመካከላቸው አንበሶችን ላከባቸው፤+ እነሱም የተወሰኑ ሰዎችን ገደሉ። 26 የአሦርም ንጉሥ እንዲህ ተብሎ ተነገረው፦ “በግዞት ወስደህ በሰማርያ ከተሞች እንዲሰፍሩ ያደረግካቸው ብሔራት የዚያች ምድር አምላክ እንዴት እንደሚመለክ* አላወቁም። ስለዚህ በመካከላቸው አንበሶችን ላከባቸው፤ አንዳቸውም የዚያች ምድር አምላክ እንዴት እንደሚመለክ ስለማያውቁ አንበሶቹ እየገደሏቸው ነው።”
27 በዚህ ጊዜ የአሦር ንጉሥ “ከዚያ በግዞት ከወሰዳችኋቸው ካህናት መካከል አንዱ ተመልሶ አብሯቸው በመኖር የዚያች ምድር አምላክ እንዴት እንደሚመለክ ያስተምራቸው” ሲል አዘዘ። 28 ስለሆነም ከሰማርያ በግዞት ከወሰዷቸው ካህናት መካከል አንዱ ተመልሶ በመምጣት በቤቴል+ መኖር ጀመረ፤ እሱም ይሖዋን እንዴት መፍራት* እንዳለባቸው ያስተምራቸው ጀመር።+
29 ይሁንና እያንዳንዱ ብሔር የየራሱን አምላክ* በመሥራት ሳምራውያን ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች ላይ በሠሯቸው ቤቶች ውስጥ አስቀምጦ ነበር፤ እያንዳንዱ ብሔር በሚኖርባቸው ከተሞች ውስጥ እንዲህ አደረገ። 30 በመሆኑም የባቢሎን ሰዎች ሱኮትቤኖትን፣ የኩት ሰዎች ኔርጋልን፣ የሃማት+ ሰዎች ደግሞ አሺማን ሠሩ፤ 31 አዋውያንም ኒብሃዝን እና ታርታቅን ሠሩ። ሰፋርዊማውያን+ ደግሞ አድራሜሌክና አናሜሌክ ለተባሉት የሰፋርዊም አማልክት ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ነበር። 32 ይሖዋን ይፈሩ የነበረ ቢሆንም ከሕዝቡ መካከል፣ ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች የሚያገለግሉ ካህናትን ሾሙ፤ እነዚህ ካህናትም ከፍ ባሉት የማምለኪያ ቦታዎች በሚገኙት የአምልኮ ቤቶች የእነሱ አገልጋዮች ሆኑ።+ 33 በአንድ በኩል ይሖዋን ይፈሩ ነበር፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከመፈናቀላቸው በፊት የነበሩባቸው ብሔራት ያመልኩ እንደነበረው* የራሳቸውን አማልክት ያመልኩ ነበር።+
34 እስከ ዛሬ ድረስ አምልኳቸውን የሚያከናውኑት በፊት ያደርጉት እንደነበረው* ነው። ይሖዋን የሚያመልክ* ብሎም ደንቦቹን፣ ድንጋጌዎቹን እንዲሁም ይሖዋ እስራኤል የሚል ስም ላወጣለት ለያዕቆብ+ ልጆች የሰጣቸውን ሕግና ትእዛዝ የሚከተል አንድም ሰው አልነበረም። 35 ይሖዋ ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን በተጋባበት ወቅት+ እንዲህ ሲል አዟቸው ነበር፦ “ሌሎች አማልክትን አትፍሩ፤ አትስገዱላቸው፤ አታገልግሏቸው፤ አትሠዉላቸው።+ 36 ከዚህ ይልቅ መፍራት+ ያለባችሁ በታላቅ ኃይልና በተዘረጋ ክንድ ከግብፅ ምድር ያወጣችሁን ይሖዋን ነው፤+ መስገድ ያለባችሁ ለእሱ ነው፤ መሠዋት ያለባችሁም ለእሱ ነው። 37 የጻፈላችሁን ሥርዓቶች፣ ድንጋጌዎች፣ ሕግና ትእዛዛት ምንጊዜም በጥንቃቄ ጠብቁ፤+ ሌሎች አማልክትን አትፍሩ። 38 ደግሞም ከእናንተ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አትርሱ፤+ ሌሎች አማልክትንም አትፍሩ። 39 ይልቁንም ከጠላቶቻችሁ ሁሉ እጅ የሚታደጋችሁ እሱ ስለሆነ መፍራት ያለባችሁ አምላካችሁን ይሖዋን ነው።”
40 እነሱ ግን አልታዘዙም፤ አምልኳቸውንም የሚያከናውኑት በፊት ያደርጉት እንደነበረው* ነው።+ 41 እነዚህ ብሔራት ይሖዋን ይፈሩ+ የነበረ ቢሆንም የራሳቸውን የተቀረጹ ምስሎችም ያገለግሉ ነበር። ልጆቻቸውም ሆኑ የልጅ ልጆቻቸው እስከ ዛሬ ድረስ የሚያደርጉት አባቶቻቸው እንዳደረጉት ነው።