የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 28—ሆሴዕ
ጸሐፊው:- ሆሴዕ
የተጻፈበት ቦታ:- ሰማርያ (አውራጃ)
ተጽፎ ያለቀው:- ከክ. ል. በፊት ከ745 በኋላ
ታሪኩ የሚሸፍነው ጊዜ:- ከክ. ል. በፊት ከ804 ቀደም ብሎ እስከ ከክ. ል. በፊት ከ745 በኋላ
የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የመጨረሻዎቹ 12 መጻሕፍት በተለምዶ “ንዑሳን ነቢያት” ወይም “ደቂቀ ነቢያት” በመባል ይጠራሉ። የእነዚህ መጻሕፍት አጠቃላይ ርዝመት ከኢሳይያስ ወይም ከኤርምያስ መጻሕፍት የሚያንስ ቢሆንም ይህ አጠራር የሚሰጡት ጥቅም አነስተኛ መሆኑን አያመለክትም። በዕብራይስጥ ቋንቋ በተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እነዚህ መጻሕፍት እንደ አንድ ጥራዝ ተቆጥረው “አሥራ ሁለቱ መጻሕፍት” በመባል ይጠሩ ነበር። አንዷ ትንሽ ጥቅል ብቻዋን ብትሆን በቀላሉ ልትጠፋ ስለምትችል በዚህ መንገድ አንድ ላይ የተሰበሰቡት እንዳይጠፉ ለማድረግ ተብሎ ሳይሆን አይቀርም። እንደ ሌሎቹ የእነዚህ 12 መጻሕፍት ክፍሎች ሁሉ የመጀመሪያው መጽሐፍም የተሰየመው በጸሐፊው በሆሴዕ ስም ሲሆን ይህ ስም “ያህ ያዳነው፣ ያህ አድኗል” የሚል ትርጉም ያለው ሆሻያ የሚለው መጠሪያ አሕጽሮተ ቃል ነው።
2 በስሙ በተሰየመው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሆሴዕ የብኤሪ ልጅ ከመሆኑ በቀር ስለ እርሱ የተገለጸ ነገር የለም። ትንቢቶቹ ሙሉ በሙሉ ያተኮሩት በእስራኤል ላይ ብቻ ነው ማለት ይቻላል፤ ሆኖም ይሁዳንም እግረ መንገዱን ጠቅሷታል። ሆሴዕ ስለ ኢየሩሳሌም የጠቀሰው ነገር ባይኖርም በእስራኤል ውስጥ ጎላ ብሎ ይታይ የነበረው የኤፍሬም ነገድ በስም 37 ጊዜ ሲጠቀስ የእስራኤል ዋና ከተማ የነበረችው ሰማርያ ደግሞ 6 ጊዜ ተጠቅሳለች።
3 የመጽሐፉ የመጀመሪያ ቁጥር እንደሚገልጸው ሆሴዕ የእስራኤል ንጉሥ ከነበረው ከዳግማዊ ኢዮርብዓም የግዛት ዘመን መገባደጃ አንስቶ እስከ ይሁዳ ንጉሥ እስከ ሕዝቅያስ ዘመን መንግሥት ድረስ በጣም ረዥም ለሆኑ ዓመታት የይሖዋ ነቢይ ሆኖ አገልግሏል። ይህም ከ804 ከክርስቶስ ልደት በፊት አንስቶ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ745 በኋላ እስካሉት ዓመታት ድረስ ያሉትን ከ59 የማያንሱ ዓመታትን ይሸፍናል። ትንቢት በመናገር ያሳለፈው የአገልግሎት ዘመን ከዳግማዊ ኢዮርብዓምና ከሕዝቅያስ የግዛት ዘመንም የተወሰኑ ዓመታትን እንደሚጨምር ምንም አያጠራጥርም። በዚህ ወቅት የነበሩት ሌሎቹ የታመኑ የይሖዋ ነቢያት አሞጽ፣ ኢሳይያስ፣ ሚክያስና ዖዴድ ናቸው።—አሞጽ 1:1፤ ኢሳ. 1:1፤ ሚክ. 1:1፤ 2 ዜና 28:9
4 ይህ የትንቢት መጽሐፍ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በርካታ ጊዜ መጠቀሱ የትንቢቱን እውነተኝነት ያረጋግጣል። ኢየሱስ ራሱ በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚፈጸመው ፍርድ ሲናገር ሆሴዕ 10:8ን በመጥቀስ “በዚያን ጊዜም፣ ተራሮችን፣ ‘ውደቁብን’ ኰረብቶችንም፣ ‘ሰውሩን’ ይላሉ” ብሎ ተናግሯል። (ሉቃስ 23:30) ይኸው ጥቅስ በራእይ 6:16 ላይ በከፊል ተጠቅሶ ይገኛል። ማቴዎስ “ልጄን ከግብፅ ጠራሁት” የሚለው ትንቢት ፍጻሜውን እንዳገኘ ለመግለጽ ሆሴዕ 11:1ን ጠቅሷል። (ማቴ. 2:15) ይሁዳ በምርኮ ከመወሰዷ በፊት ከአሥሩ ነገድ መንግሥት መካከል ብዙ ሰዎች ወደ እርሷ በመሄዳቸውና ልጆቻቸውም ከምርኮ ከተመለሱት ሰዎች መካከል በመገኘታቸው ሆሴዕ መላው የእስራኤል ሕዝብ እንደገና ስለ መቋቋሙ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። (ሆሴዕ 1:11፤ 2 ዜና 11:13-17፤ 30:6-12, 18, 25፤ ዕዝራ 2:70) መጽሐፉ ከዕዝራ ዘመን አንስቶ ‘እግዚአብሔር በሆሴዕ አማካኝነት የተናገረው ቃል’ መሆኑ ታምኖበት በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መካከል ትክክለኛ ቦታውን ይዟል።—ሆሴዕ 1:2
5 ይሖዋ ሆሴዕን ነቢይ አድርጎ ወደ እስራኤል የላከው ለምን ነበር? እስራኤል ከይሖዋ ጋር የገባችውን ቃል ኪዳን በማፍረስ ታማኝነቷን ከማጉደሏም በላይ በበኣል አምልኮ ተበክላ ስለነበር ነው። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላ የሚተዳደሩት በግብርና ነበር፤ ሆኖም በዚህ ጊዜ የከነዓናውያንን አኗኗር ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ የመራቢያ ኃይሎችን የሚወክለው በኣል የተባለው አምላክ የሚመለክበትን ሃይማኖታቸውንም ጭምር መከተል ጀመሩ። በሆሴዕ ዘመን እስራኤላውያን ለይሖዋ አምልኮ ሙሉ በሙሉ ጀርባቸውን ሰጥተው ከቤተ መቅደስ ጋለሞቶች ጋር የጾታ ብልግና መፈጸምን በሚጨምረው ወራዳና ስካር የሞላበት ሥነ ሥርዓት መካፈል ጀምረው ነበር። እስራኤል የብልጽግና ምንጭ በኣል እንደሆነ ትገልጽ ነበር። ለይሖዋ ያላትን ታማኝነት በማጉደሏና ለእርሱ የምትገባ ሆና ባለመገኘቷ ተግሳጽ መስጠቱ አስፈላጊ ነበር። ይሖዋ፣ ያገኘችው ቁሳዊ ንብረት ምንጭ በኣል እንዳልሆነ ሊያሳያት ስለፈለገ ንስሐ ሳትገባ መቀጠሏ ምን ሊያስከትልባት እንደሚችል እንዲያስጠነቅቃት ሆሴዕን ላከው። ዳግማዊ ኢዮርብዓም ከሞተ በኋላ እስራኤል በታሪኳ ከገጠማት ሁሉ የከፋ ጊዜ አሳለፈች። በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት አሦራውያን ሕዝቡን በምርኮ እስከወሰዷቸው ጊዜ ድረስ በእስራኤል ውስጥ በርካታ ገዥዎች የተገደሉበት የሽብር ዘመን ነበር። በዚህም ወቅት አንደኛው ከግብፅ ሌላው ደግሞ ከአሦር ጋር ጥምረት ለመፍጠር የሚፈልጉ ሁለት አንጃዎች እርስ በርሳቸው ይዋጉ ነበር። ሁለቱም ወገኖች ቢሆኑ በይሖዋ ሳይታመኑ ቀርተዋል።
6 የሆሴዕ የአጻጻፍ ስልት ነገሮችን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ብዙውን ጊዜ ለስለስ ያሉና በጥንቃቄ የተመረጡ ቃላትን የሚጠቀም ሲሆን የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነትና ምሕረት በተደጋጋሚ ጊዜያት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። ሕዝቡ ንስሐ እንደገቡ የሚያሳይ ማንኛውንም እርምጃ ሁሉ ጽፏል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ንግግሩ ኃይለኛና ሻካራ ነበር። የአጻጻፍ ስልቱ የሚለዋወጥ ቢሆንም ኃይል አለው። ጠንከር ያሉ ስሜቶችን ከማንጸባረቁም በላይ ከአንዱ ሐሳብ ወደ ሌላው በፍጥነት ይሸጋገራል።
7 ሆሴዕ ገና የነቢይነት ሥራውን ሲጀምር አንዲት “አመንዝራ ሴት” እንዲያገባ ታዝዞ ነበር። (1:2) ይሖዋ ይህን ያደረገበት ምክንያት እንደነበረው ግልጽ ነው። እስራኤል ዝሙት በመፈጸም ታማኝነቷን እንዳጎደለች ሚስት ሆናበት ነበር። ያም ቢሆን ግን ይሖዋ ለእርሷ ያለውን ፍቅር በመግለጽ እንድትመለስ ለማድረግ ይጥራል። የሆሴዕ ሚስት ጎሜር ይህን ሁኔታ ጥሩ አድርጋ የምትወክል ነበረች። ከሁኔታው እንደምንረዳው ታማኝነቷን ያጎደለችው የመጀመሪያው ልጅ ከተወለደ በኋላ ሲሆን ሌሎቹን ልጆች የወለደቻቸው በምንዝር ሳይሆን አይቀርም። (2:5-7) ዘገባው የመጀመሪያው ልጅ ሲወለድ “ወንድ ልጅም [ለሆሴዕ] ወለደችለት” ካለ በኋላ የቀሩት ሁለት ልጆች ስለመወለዳቸው ሲናገር ነቢዩን አለመጥቀሱ ይህንኑ የሚጠቁም ነው። (1:3, 6, 8) ምዕራፍ 3 ቁጥር 1-3 ሆሴዕ ጎሜርን እንደ ባርያ በመግዛት መልሶ እንደወሰዳት የሚናገር ይመስላል፤ ይህም ይሖዋ ሕዝቦቹ ከምንዝር ተግባራቸው ንስሐ ከገቡ በኋላ እነርሱን መልሶ ከመቀበሉ ጋር ይዛመዳል።
8 የሆሴዕ ትንቢት በዋነኝነት የተነገረው አሥሩን ነገድ ላቀፈው ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ሲሆን ይህ መንግሥት በግዛቱ ውስጥ ጎላ ብሎ በሚታየው ነገድ ስም ኤፍሬም በመባልም ተጠርቷል። እስራኤልና ኤፍሬም የሚሉት ስሞች በመጽሐፉ ውስጥ በተወራራሽነት ተሠርቶባቸዋል።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
14 የሆሴዕ መጽሐፍ ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት ባስነገራቸው ትንቢቶች ላይ ያለንን እምነት ያጠነክርልናል። ሆሴዕ እስራኤልንና ይሁዳን በተመለከተ የተናገረው ትንቢት በሙሉ ተፈጽሟል። እስራኤል ፍቅረኞቿ የነበሩት ጣዖት አምላኪ የሆኑት አጎራባች ብሔራት የተዉአት ከመሆኑም በላይ በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት በአሦር አማካኝነት የጥፋትን አውሎ ነፋስ አጭዳለች። (ሆሴዕ 8:7-10፤ 2 ነገ. 15:20፤ 17:3-6, 18) ይሁን እንጂ ሆሴዕ፣ ይሖዋ ለይሁዳ ምሕረት እንደሚያሳያትና በወታደራዊ ኃይል ባይሆንም እንኳ እንደሚያድናት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። ይህም በኢየሩሳሌም ላይ ስጋት ፈጥረው የነበሩትን 185,000 አሦራውያን የይሖዋ መልአክ በገደለበት ጊዜ ፍጻሜውን አግኝቷል። (ሆሴዕ 1:7፤ 2 ነገ. 19:34, 35) ያም ቢሆን ግን በሆሴዕ 8:14 ላይ የተነገረው “እኔ ግን በከተሞቻቸው ላይ እሳትን እለቃለሁ፤ ምሽጎቻቸውንም ይበላል” የሚለው ፍርድ ይሁዳንም ይጨምር ነበር፤ በመሆኑም ናቡከደነፆር ከ609-607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባለው ጊዜ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ባድማ ባደረገበት ወቅት ይህ ትንቢት አሰቃቂ በሆነ መንገድ ፍጻሜውን አግኝቷል። (ኤር. 34:6, 7፤ 2 ዜና 36:19) ሆሴዕ እንደገና ስለመቋቋም የተናገራቸው በርካታ ትንቢቶች ይሖዋ ይሁዳንና እስራኤልን አንድ ላይ በሰበሰበበትና በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት በምርኮ ከነበሩበት ምድር ‘ተመልሰው በመጡበት’ ጊዜ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል።—ሆሴዕ 1:10, 11፤ 2:14-23፤ 3:5፤ 11:8-11፤ 13:14፤ 14:1-9፤ ዕዝራ 2:1፤ 3:1-3
15 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን የጻፉት ሰዎች የሆሴዕን ትንቢቶች ጠቅሰው የጻፏቸውን ሐሳቦች መመርመራችን በጣም ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ በተናገረበት ጊዜ ሆሴዕ 13:14ን ጠንከር ባለ መንገድ ተጠቅሞበታል:- “ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? ሞት ሆይ፤ መንደፊያህስ የት አለ?” (1 ቆሮ. 15:55) ጳውሎስ ይሖዋ ለምሕረት ዕቃዎች ያሳየውን ይገባናል የማንለውን ደግነቱን ጎላ አድርጎ ሲገልጽ ሆሴዕ 1:10 እና 2:23ን ጠቅሷል:- “በሆሴዕ እንዲህ እንደሚል፤ ‘ሕዝቤ ያልሆኑትን፣ “ሕዝቤ” ብዬ እጠራቸዋለሁ፤ ያልተወደደችውንም “የተወደደችው” ብዬ እጠራለሁ።’ ደግሞም፣ ‘“ሕዝቤ አይደላችሁም”፤ ተብሎ በተነገራቸው በዚያ ቦታ፣ “የሕያው እግዚአብሔር ልጆች” ተብለው ይጠራሉ።’” (ሮሜ 9:25, 26) ጴጥሮስ ይህንኑ የሆሴዕ ጥቅስ እንደሚከተለው ሲል በሌላ መንገድ ገልጾታል:- “ቀድሞ የእርሱ ወገን አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆናችኋል፤ ቀድሞ ምሕረትን አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል።”—1 ጴጥ. 2:10
16 በመሆኑም የሆሴዕ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው በዘሩባቤል ዘመን ቀሪዎቹ በመመለሳቸው ብቻ ሳይሆን ይሖዋ፣ ‘የተወደዱ የሕያው አምላክ ልጆች’ የሆኑትን መንፈሳዊ ቀሪዎች በምሕረቱ በሰበሰበበት ጊዜም ጭምር ነው። የአምላክ መንፈስ እነዚህ ሰዎች የሚፈልግባቸውን ብቃት ለሆሴዕ አሳይቶት ነበር። ሊያሟሉት የሚገባው ብቃት ለይስሙላ በሚከናወን ሥርዓት የሚቀርብ አምልኮ አይደለም፤ ሆሴዕ 6:6 እንዲህ ይላል:- “ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፣ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እሻለሁና።” ይህንኑ ጥቅስ ኢየሱስም በማቴዎስ 9:13 እና 12:7 ላይ ደግሞታል።
17 በሆሴዕ ሕይወት በገሃድ የተፈጸመው የአመንዝራይቱ ሚስት ምሳሌ ይሖዋ እርሱን ትተው ጣዖት በማምለክና የሐሰት አምልኮ በመከተል መንፈሳዊ ምንዝር የሚፈጽሙ ሰዎችን እንደሚጸየፍ ያሳያል። ተደናቅፈው ስህተት የሚፈጽሙ ሁሉ እውነተኛ ንስሐ ገብተው ወደ ይሖዋ መመለስና ‘የከንፈራቸውን ፍሬ’ ማቅረብ ይገባቸዋል። (ሆሴዕ 14:2፤ ዕብ. 13:15) እነዚህ ሰዎች ከመንፈሳዊ እስራኤል ልጆች ቀሪዎች ጋር አንድ ላይ በመሆን በሆሴዕ 3:5 ላይ በሚገኘው ስለ አምላክ መንግሥት በተነገረው በሚከተለው ትንቢት ፍጻሜ ሊደሰቱ ይችላሉ:- “ከዚያ በኋላ እስራኤላውያን ተመልሰው አምላካቸውን እግዚአብሔርንና ንጉሣቸውን ዳዊትን ይፈልጋሉ፤ በመጨረሻውም ዘመን በመንቀጥቀጥ ወደ እግዚአብሔርና ወደ በረከቱ ይመጣሉ።”