አስቴር
1 ከሕንድ አንስቶ እስከ ኢትዮጵያ* ድረስ ባሉ 127 አውራጃዎች+ ይገዛ በነበረው በአሐሽዌሮስ* ዘመን 2 ይኸውም ንጉሥ አሐሽዌሮስ በሹሻን*+ ግንብ* በሚገኘው ንጉሣዊ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ይገዛ በነበረበት ጊዜ፣ 3 በግዛት ዘመኑ ሦስተኛ ዓመት ላይ ለመኳንንቱና ለአገልጋዮቹ በሙሉ ግብዣ አደረገ። የፋርስና+ የሜዶን+ ሠራዊት፣ ታላላቆቹ ሰዎችና የየአውራጃዎቹ መኳንንት በፊቱ ነበሩ፤ 4 እሱም የክብራማ መንግሥቱን ብልጽግና እንዲሁም የግርማውን ታላቅነትና ውበት ለብዙ ቀናት ይኸውም ለ180 ቀናት ሲያሳያቸው ቆየ። 5 እነዚህ ቀናት ሲያበቁ ንጉሡ ትልቅ ትንሽ ሳይባል በሹሻን* ግንብ* ለተገኘው ሕዝብ ሁሉ በንጉሡ ቤተ መንግሥት የአትክልት ስፍራ ባለው ግቢ ለሰባት ቀን ታላቅ ግብዣ አደረገ። 6 በዚያም ከበፍታ፣ ከጥሩ ጥጥና ከሰማያዊ ጨርቅ የተሠሩ መጋረጃዎች፣ ከፍተኛ ጥራት ካለው ክርና ከሐምራዊ ሱፍ በተሠሩ ገመዶች፣ በእብነ በረድ ዓምዶቹ ላይ በነበሩት የብር ቀለበቶች ላይ ታስረው ነበር፤ ነጭ ነጠብጣብ ያለው ቀይ ድንጋይ፣ ነጭ እብነ በረድ፣ ዕንቁና ጥቁር እብነ በረድ በተነጠፈበት መሬት ላይ ደግሞ ከወርቅና ከብር የተሠሩ ድንክ አልጋዎች ነበሩ።
7 የወይን ጠጅ በወርቅ ጽዋዎች* ቀርቦ ነበር፤ ጽዋዎቹም አንዳቸው ከሌላው የተለዩ ናቸው፤ ከንጉሡም ብልጽግና የተነሳ የቤተ መንግሥቱ የወይን ጠጅ በገፍ ቀርቦ ነበር። 8 የመጠጡ ዝግጅት የተደረገው ማንም ጫና* እንዳይደረግበት ከሚያዘው ደንብ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ነበር፤ ንጉሡ እያንዳንዱ ሰው ደስ ያሰኘውን ማድረግ እንዲችል ለቤተ መንግሥቱ ባለሥልጣናት መመሪያ አስተላልፎ ነበርና።
9 ንግሥት አስጢንም+ በንጉሥ አሐሽዌሮስ ንጉሣዊ ቤት* ውስጥ ለሴቶቹ ታላቅ ግብዣ አድርጋ ነበር።
10 በሰባተኛው ቀን ንጉሥ አሐሽዌሮስ የወይን ጠጅ ጠጥቶ ደስ በተሰኘ ጊዜ የቅርብ አገልጋዮቹ ለነበሩት ሰባት የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት ማለትም ለሜሁማን፣ ለቢዝታ፣ ለሃርቦና፣+ ለቢግታ፣ ለአባግታ፣ ለዜታር እና ለካርካስ 11 ንግሥት አስጢንን የንግሥትነት አክሊሏን* እንዳደረገች ወደ ንጉሡ ፊት እንዲያመጧት ነገራቸው፤ ይህን ያደረገው በጣም ቆንጆ ስለነበረች ሕዝቡና መኳንንቱ ውበቷን እንዲያዩ ነበር። 12 ንግሥት አስጢን ግን ንጉሡ በቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱ በኩል ያስተላለፈውን ትእዛዝ ባለመቀበል ፈጽሞ ለመምጣት ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች። በዚህ ጊዜ ንጉሡ በኃይል ተቆጣ፤ በጣም ተናደደ።
13 ከዚያም ንጉሡ ስለ ቀድሞው ዘመን* ጥልቅ ማስተዋል ያላቸውን ጥበበኛ ሰዎች አማከረ (ንጉሡ የሚያጋጥሙት ነገሮች ሕግንና የፍርድ ጉዳዮችን ጠንቅቀው በሚያውቁ ሰዎች ሁሉ ፊት የሚቀርቡት በዚህ መንገድ ነበርና፤ 14 የቅርብ ሰዎቹም ካርሼና፣ ሼታር፣ አድማታ፣ ተርሴስ፣ ሜሬስ፣ ማርሴና እና ሜሙካን ነበሩ፤ እነዚህ ንጉሡ ፊት መቅረብ የሚችሉና በመንግሥቱ ውስጥ ከፍተኛውን ቦታ የያዙ ሰባቱ የፋርስና የሜዶን መኳንንት+ ናቸው)። 15 ንጉሡም እንዲህ ሲል ጠየቀ፦ “ንጉሥ አሐሽዌሮስ በቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱ በኩል ያስተላለፈውን ትእዛዝ ባለማክበሯ በሕጉ መሠረት በንግሥት አስጢን ላይ ምን ቢደረግ ይሻላል?”
16 በዚህ ጊዜ ሜሙካን በንጉሡና በመኳንንቱ ፊት እንዲህ አለ፦ “ንግሥት አስጢን የበደለችው ንጉሡን ብቻ አይደለም፤+ ከዚህ ይልቅ መኳንንቱን ሁሉና በመላው የንጉሥ አሐሽዌሮስ አውራጃዎች የሚኖሩትን ሕዝቦች ሁሉ ነው። 17 ሌሎች ሚስቶች ሁሉ ንግሥቲቱ ያደረገችውን ነገር ማወቃቸው ስለማይቀር ባሎቻቸውን ይንቃሉ፤ ደግሞም ‘ንጉሥ አሐሽዌሮስ ንግሥት አስጢንን በፊቱ እንዲያቀርቧት አዝዞ ነበር፤ እሷ ግን አልቀረበችም’ ይላሉ። 18 በዚህ ቀን ንግሥቲቱ ያደረገችውን ነገር የሰሙ የፋርስና የሜዶን ልዕልቶች ለንጉሡ መኳንንት ሁሉ ተመሳሳይ መልስ ሊሰጡ ነው፤ ይህም ከፍተኛ ንቀትና ቁጣ ያስከትላል። 19 በመሆኑም ንጉሡ መልካም መስሎ ከታየው አስጢን፣ ንጉሥ አሐሽዌሮስ ፊት ዳግመኛ እንዳትቀርብ የሚያዝዝ ንጉሣዊ አዋጅ ያውጣ፤ ይህም የማይሻር ሆኖ+ በፋርስና በሜዶን ሕጎች ውስጥ ይካተት፤ ንጉሡም የእቴጌነት ክብሯን ከእሷ ለተሻለች ሴት ይስጥ። 20 ንጉሡም የሚያወጣው አዋጅ ሰፊ በሆነው ግዛቱ ሁሉ ሲነገር ትልቅ ትንሽ ሳይል ሁሉም ሚስቶች ባሎቻቸውን ያከብራሉ።”
21 ይህ ሐሳብ ንጉሡንና መኳንንቱን ደስ አሰኛቸው፤ ንጉሡም ሜሙካን እንዳለው አደረገ። 22 በመሆኑም እያንዳንዱ ባል በቤቱ ውስጥ ጌታ እንዲሆንና* በራሱ ሕዝብ ቋንቋ እንዲናገር የሚያዝዝ ደብዳቤ ለመላው የንጉሡ አውራጃዎች+ ላከ፤ ደብዳቤውም ለእያንዳንዱ አውራጃ በየራሱ ጽሑፍ፣* ለእያንዳንዱም ሕዝብ በገዛ ቋንቋው የተዘጋጀ ነበር።