1 የይሁዳ ነገሥታት+ በሆኑት በዖዝያ፣+ በኢዮዓታም፣+ በአካዝና+ በሕዝቅያስ+ ዘመን የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ራእይ፦+
2 ሰማያት ሆይ፣ ስሙ፤ ምድር ሆይ፣ አድምጪ፤+
ይሖዋ እንዲህ ሲል ተናግሯልና፦
“ወንዶች ልጆችን ተንከባክቤ አሳደግኩ፤+
እነሱ ግን በእኔ ላይ ዓመፁ።+
3 በሬ ጌታውን፣
አህያም የባለቤቱን ጋጣ በሚገባ ያውቃል፤
እስራኤል ግን እኔን አላወቀም፤+
የገዛ ሕዝቤም አላስተዋለም።”
4 ኃጢአተኛ የሆነው ብሔር፣+
ከባድ በደል የተጫነው ሕዝብ፣
የክፉዎች ዘር፣ ብልሹ የሆኑ ልጆች ወዮላቸው!
እነሱ ይሖዋን ትተዋል፤+
የእስራኤልን ቅዱስ አቃለዋል፤
ጀርባቸውን ሰጥተውታል።
5 በዓመፅ ላይ ዓመፅ የምትጨምሩት፣ አሁን ደግሞ ምናችሁ ላይ መመታት ፈልጋችሁ ነው?+
መላው ራስ ታሟል፤
መላው ልብም በበሽታ ተይዟል።+
6 ከእግር ጥፍር አንስቶ እስከ ራስ ፀጉር ድረስ አንድም ጤነኛ የአካል ክፍል የለም።
በቁስልና በሰምበር ተሞልቷል፤ እንዲሁም ተተልትሏል፤
ቁስሉ አልታከመም ወይም አልታሰረም አሊያም በዘይት አለዘበም።+
7 ምድራችሁ ባድማ ሆኗል።
ከተሞቻችሁ በእሳት ጋይተዋል።
የባዕድ አገር ሰዎች ዓይናችሁ እያየ ምድራችሁን ይውጣሉ።+
ባዕዳን እንዳወደሙት ጠፍ መሬት ሆኗል።+
8 የጽዮን ሴት ልጅ በወይን እርሻ ውስጥ እንዳለ መጠለያ፣
በኪያር የእርሻ ቦታ እንዳለ ጎጆ፣
እንደተከበበችም ከተማ ተትታለች።+
9 የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ጥቂት ሰዎች ከጥፋት እንዲተርፉልን ባያደርግ ኖሮ
እንደ ሰዶም በሆንን፣
ገሞራንም በመሰልን ነበር።+
10 እናንተ የሰዶም+ አምባገነኖች፣ የይሖዋን ቃል ስሙ።
እናንተ የገሞራ+ ሰዎች፣ የአምላካችንን ሕግ አዳምጡ።
11 “የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል?”+ ይላል ይሖዋ።
“የሚቃጠሉ የአውራ በግ መባዎችና+ የደለቡ እንስሳት ስብ+ በቅቶኛል፤
በወይፈኖች፣+ በበግ ጠቦቶችና በፍየሎች+ ደም+ ደስ አልሰኝም።
12 በፊቴ ለመቅረብ የምትመጡት፣+
ይህን እንድታደርጉ፣
የቤተ መቅደሴን ግቢ እንድትረግጡ ማን ጠይቋችሁ ነው?+
13 ከንቱ የሆኑትን የእህል መባዎች ከዚህ በኋላ አታምጡ።
ዕጣናችሁ በፊቴ አስጸያፊ ነው።+
የአዲስ ጨረቃ+ በዓልንና ሰንበትን+ ታከብራላችሁ፤ ስብሰባም+ ትጠራላችሁ።
በአንድ በኩል የተቀደሱ ጉባኤዎችን እያከበራችሁ በሌላ በኩል የምትፈጽሙትን አስማታዊ ድርጊት+ መታገሥ አልችልም።
14 የአዲስ ጨረቃ በዓሎቻችሁንና ሌሎች በዓሎቻችሁን ጠልቻለሁ።
ለእኔ ሸክም ሆነውብኛል፤
እነሱንም ከመሸከሜ የተነሳ ዝያለሁ።
15 እጆቻችሁን ስትዘረጉ
ዓይኖቼን ከእናንተ እሰውራለሁ።+
ጸሎት ብታበዙም እንኳ+
አልሰማችሁም፤+
እጆቻችሁ በደም ተሞልተዋል።+
16 ታጠቡ፤ ራሳችሁንም አንጹ፤+
ክፉ ሥራችሁን ከፊቴ አስወግዱ፤
መጥፎ ድርጊት መፈጸማችሁን አቁሙ።+
17 መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትሕን ፈልጉ፤+
ጨቋኙ እንዲታረም አድርጉ፤
አባት የሌለውን ልጅ መብት አስከብሩ፤
ለመበለቲቱም ተሟገቱ።”+
18 “ኑና በመካከላችን የተፈጠረውን ችግር ተወያይተን እንፍታ” ይላል ይሖዋ።+
“ኃጢአታችሁ እንደ ደም ቢቀላ
እንደ በረዶ ይነጣል፤+
እንደ ደማቅ ቀይ ጨርቅ ቢቀላም
እንደ ነጭ የሱፍ ጨርቅ ይሆናል።
19 እሺ ብትሉና ብትታዘዙ
የምድሪቱን መልካም ፍሬ ትበላላችሁ።+
20 እንቢ ብትሉና ብታምፁ ግን
ሰይፍ ይበላችኋል፤+
የይሖዋ አፍ ይህን ተናግሯልና።”
21 ታማኝ የነበረችው ከተማ+ እንዴት ዝሙት አዳሪ ሆነች!+
ፍትሕ የሞላባትና+
ጽድቅ የሰፈነባት ነበረች፤+
አሁን ግን የነፍሰ ገዳዮች ጎሬ ሆናለች።+
22 ብርሽ እንደ ዝቃጭ ሆኗል፤+
መጠጥሽ በውኃ ተበርዟል።
23 አለቆችሽ ግትሮችና የሌባ ግብረ አበሮች ናቸው።+
ሁሉም ጉቦ የሚወዱና እጅ መንሻ የሚያሳድዱ ናቸው።+
አባት የሌለው ልጅ ፍትሕ እንዲያገኝ አያደርጉም፤
የመበለቲቱም አቤቱታ ወደ እነሱ አይደርስም።+
24 ስለዚህ እውነተኛው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣
የእስራኤል ኃያል አምላክ እንዲህ ይላል፦
“እንግዲያው ስሙ! ባላጋራዎቼን አጠፋለሁ፤
ጠላቶቼንም እበቀላለሁ።+
25 እጄን በአንቺ ላይ አነሳለሁ፤
በመርዝ የማጥራት ያህል ቆሻሻሽን አቅልጬ አወጣለሁ፤
ዝቃጭሽንም ሁሉ አስወግዳለሁ።+
26 መጀመሪያ ላይ እንደነበረው ፈራጆችሽን፣
እንደቀድሞውም አማካሪዎችሽን መልሼ አመጣለሁ።+
ከዚያ በኋላ የጽድቅ መዲና፣ የታመነች ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ።+
27 ጽዮን በፍትሕ፣
የሚመለሱት ነዋሪዎቿም በጽድቅ ይቤዣሉ።+
28 ዓመፀኞችና ኃጢአተኞች በአንድ ላይ ይደቅቃሉ፤+
ይሖዋን የሚተዉም ያከትምላቸዋል።+
29 እናንተ በተመኛችኋቸው ግዙፍ ዛፎች ያፍራሉና፤+
በመረጣችኋቸው የአትክልት ቦታዎች የተነሳም ትዋረዳላችሁ።+
30 ቅጠሉ እንደጠወለገ ትልቅ ዛፍ፣+
ውኃም እንደሌለው የአትክልት ቦታ ትሆናላችሁና።
31 ብርቱውም ሰው እንደ ተልባ እግር ይሆናል፤
የሥራውም ውጤት እንደ እሳት ብልጭታ ይሆናል፤
ሁለቱም አብረው ይቃጠላሉ፤
እሳቱንም ማጥፋት የሚችል ማንም የለም።”