ምዕራፍ ሦስት
“እርቅ እንፍጠር”
1, 2. ይሖዋ የኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ሕዝብ ገዥዎች ያወዳደራቸው ከማን ጋር ነው? ይህስ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች በኢሳይያስ 1:1-9 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ውግዘት ከሰሙ በኋላ ለማስተባበል ይዳዳቸው ይሆናል። ለይሖዋ ያቀረቧቸውን መሥዋዕቶች ሁሉ በጉራ ለመዘርዘር እንደሚቃጣቸውም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ከኢሳይያስ 1 ቁጥር 10 እስከ 15 ላይ ይሖዋ እንዲህ ላለው አመለካከታቸው የሚሰጠውን ኩምሽሽ የሚያደርግ መልስ እናገኛለን። እንዲህ በማለት ይጀምራል:- “እናንተ የሰዶም አለቆች ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እናንተ የገሞራ ሕዝብ ሆይ፣ የአምላካችንን ሕግ አድምጡ።”—ኢሳይያስ 1:10
2 የሰዶምና ገሞራ ሰዎች የጠፉት ልቅ በሆነው የፆታ ልማዳቸው ምክንያት ብቻ ሳይሆን ልበ ደንዳናና ትዕቢተኛ ስለ ነበሩም ጭምር ነው። (ዘፍጥረት 18:20, 21፤ 19:4, 5, 23-25፤ ሕዝቅኤል 16:49, 50) የኢሳይያስ አድማጮች ከእነዚያ የተረገሙ ከተሞች ሰዎች ጋር መመሳሰላቸው አስደንግጧቸው መሆን አለበት።a የሆነ ሆኖ ይሖዋ የሕዝቡን እውነተኛ ማንነት ያያል። ኢሳይያስም የእነርሱን ‘ጆሮ ለመኮርኮር’ ሲል የአምላክን መልእክት አለዝቦ አይነግራቸውም።—2 ጢሞቴዎስ 4:3 NW
3. ይሖዋ ሕዝቡ የሚያመጣውን መሥዋዕት በተመለከተ “ጠግቤያለሁ” ሲል ምን ማለቱ ነው? ይህስ የሆነው ለምንድን ነው?
3 ይሖዋ ሕዝቡ ያቀርበው ስለነበረው የዘልማድ አምልኮ ምን እንደተሰማው ልብ በል። “የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል? ይላል እግዚአብሔር፤ የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤያለሁ፤ የበሬና የበግ ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም።” (ኢሳይያስ 1:11) ይሖዋ የእነርሱን እጅ እንደማይጠብቅ ዘንግተው ነበር። (መዝሙር 50:8-13) ሰዎች ከሚያመጡለት ነገር መካከል ለእርሱ የግድ የሚያስፈልገው ምንም ነገር የለም። በመሆኑም ሕዝቡ በግማሽ ልብ የሚያቀርቡትን መሥዋዕት በማምጣታቸው ለይሖዋ ውለታ እንደዋሉለት አስበው ከነበረ ተሳስተዋል። ይሖዋ የተጠቀመበት መግለጫ ጠንከር ያለ ነው። “ጠግቤያለሁ” የሚለው መግለጫ “አንገፍግፎኛል” ወይም “ጠግንኖኛል” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። በጣም ብዙ ከመብላትህ የተነሣ ምግብ ለዓይንህ እንኳን አስጠልቶህ ያውቃል? ይሖዋም ስለሚቀርቡት መሥዋዕቶች የተሰማው እንደዚያ ነበር። ፈጽሞ አንገፍግፎት ነበር!
4. ኢሳይያስ 1:12 ሕዝቡ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ መገኘታቸው ከንቱ እንደሆነ ያጋለጠው እንዴት ነው?
4 ይሖዋ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “በእኔ ፊት ልትታዩ ብትመጡ ይህን የመቅደሴን አደባባይ መርገጣችሁን ከእጃችሁ የሚሻ ማን ነው?” (ኢሳይያስ 1:12) ሕዝቡ ‘በይሖዋ ፊት እንዲታይ’ ማለትም በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መቅደስ እንዲመጣ የሚያዝዘው የራሱ የይሖዋ ሕግ አይደለምን? (ዘጸአት 34:23, 24) አዎን፣ ይህን የሚያዝዘው ሕጉ ነው። ይሁን እንጂ እነርሱ ወደዚያ የሚመጡት እንዲሁ በዘልማድ ለንጹህ አምልኮው ሥርዓት የደንቡን ለማድረስ እንጂ ውስጣዊ ግፊታቸው ንጹሕ ሆኖ አልነበረም። ለይሖዋ ግን ወደ ቤተ መቅደሱ መመላለሳቸው አደባባዩን ‘ከመረጋገጥና’ ወለሉን ከማበላሸት የተለየ ፋይዳ አልነበረውም።
5. አይሁዳውያን ያከናውኗቸው የነበሩት አንዳንዶቹ የአምልኮ ድርጊቶች ምንድን ናቸው? እነዚህ ነገሮችስ ለይሖዋ “ሸክም” የሆኑበት ለምንድን ነው?
5 ይሖዋ ከዚህም የበለጠ ጠንከር ያለ መግለጫ መጠቀሙ ምንም አያስገርምም! “ምናምንቴውን ቁርባን ጨምራችሁ አታምጡ፤ ዕጣን በእኔ ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ መባቻችሁንና ሰንበታችሁን በጉባኤም መሰብሰባችሁን አልወድድም፤ በደልንም [“ምሥጢራዊ ኃይላችሁን፣ ” NW ] የተቀደሰውንም ጉባኤ አልታገሥም። መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፣ ልታገሣቸውም ደክሜያለሁ።” (ኢሳይያስ 1:13, 14) የእህል ቁርባን፣ ዕጣን፣ ሰንበትና የተቀደሰ ጉባኤ በሙሉ አምላክ ለእስራኤል በሰጠው ሕግ ውስጥ የተጠቀሱ ነገሮች ናቸው። ሕጉ ‘መባቻን’ በሚመለከት እንዲሁ እንዲከበር ብቻ መመሪያ የሚሰጥ ቢሆንም ቀስ በቀስ በአከባበሩ ዙሪያ አንዳንድ ጤናማ ልማዶች እየዳበሩ ሄደው ነበር። (ዘኍልቁ 10:10፤ 28:11) መባቻው እንደ ወርኃዊ ሰንበት የሚታይ ሲሆን ሕዝቡ ከሥራው የሚያርፍበት አልፎ ተርፎም ከነቢያትና ከካህናት ለመማር አንድ ላይ የሚሰበሰብበት ዕለት ነበር። (2 ነገሥት 4:23፤ ሕዝቅኤል 46:3፤ አሞጽ 8:5) እንዲህ ዓይነቶቹን በዓላት ማክበር ስህተት አልነበረውም። ስህተቱ እነዚህን በዓላት ለታይታ ብቻ ብሎ ማድረጉ ነው። ከዚህም በላይ እስራኤላውያን የአምላክን ሕግ በዘልማድ እየጠበቁ ወደ “ምሥጢራዊ ኃይሎች” ዘወር በማለት መናፍስታዊ ድርጊቶችን ጎን ለጎን ያካሂዱ ነበር።b በመሆኑም እነርሱ የሚያቀርቡት አምልኮ ለይሖዋ “ሸክም” ሆኖበት ነበር።
6. ይሖዋ ‘ድካም’ የተሰማው በምን መልኩ ነው?
6 ይሁን እንጂ ይሖዋ ‘ድካም’ ሊሰማው የቻለው እንዴት ነው? በመሠረቱ ‘የእርሱ ኃይል እጅግ ታላቅ ነው፤ አይደክምም ወይም አይታክትም።’ (ኢሳይያስ 40:26, 28) የተሰማውን ስሜት መረዳት እንድንችል ይሖዋ በቀላሉ የሚገባ መግለጫ መጠቀሙ ነው። አንድ ከባድ ነገር ለረጅም ጊዜ ተሸክመህ ቆይተህ በጣም ከመዛልህ የተነሣ ወደዚያ አሽቀንጥረኸው መገላገልን የናፈቅህበት ጊዜ አለ? ሕዝቡ ያከናውነው የነበረውን የግብዝነት አምልኮ በተመለከተ ይሖዋ የተሰማው ልክ እንደዚያ ነበር።
7. ይሖዋ የሕዝቡን ጸሎት መስማት ያቆመው ለምንድን ነው?
7 አሁን ደግሞ ይሖዋ ከየትኛውም የአምልኮ ድርጊት ሁሉ ይበልጥ ቅርበትንና የግል ወዳጅነትን ስለሚያሳየው ድርጊት ይናገራል። “እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፣ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል።” (ኢሳይያስ 1:15) መዳፋቸውን ወደ ላይ አድርገው እጃቸውን መዘርጋታቸው ምልጃ ማቅረባቸውን የሚያሳይ ነው። ይሁንና ሰዎቹ እጃቸው በደም የተሞላ ስለነበር ይህ ድርጊታቸው በይሖዋ ፊት ትርጉም የለሽ ነበር። ዓመፅ በምድሪቱ ተስፋፍቶ ነበር። አቅም የሌላቸውን መጨቆን የተለመደ ነገር ሆኗል። እንዲህ ያሉት ግፈኛና ራስ ወዳድ ሰዎች ይሖዋ በረከቱን እንዲሰጣቸው መለመናቸው ጸያፍ ነገር ነው። ይሖዋ “አልሰማችሁም” ማለቱ ምንም አያስገርምም!
8. ዛሬ ሕዝበ ክርስትና ምን ዓይነት ስህተት እየፈጸመች ነው? አንዳንድ ክርስቲያኖችስ በተመሳሳይ ወጥመድ የሚወድቁት እንዴት ነው?
8 በዘመናችንም ሕዝበ ክርስትና ነጋ ጠባ በምትደግመው ከንቱ ጸሎትም ሆነ በሌሎች ሃይማኖታዊ ‘ሥራዎቿ’ የአምላክን ሞገስ ማግኘት ሳትችል ቀርታለች። (ማቴዎስ 7:21-23) እኛም ተመሳሳይ ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ መጠንቀቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። አልፎ አልፎ አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት ይሠራና ይህንን ሠውሮ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ከፍ ቢያደርግ የሚሠራው ነገር ኃጢአቱን ሊያካክስለት እንደሚችል አድርጎ ያስብ ይሆናል። እንዲህ ያለው የይምሰል ሥራ ይሖዋን ደስ አያሰኘውም። የሚቀጥሉት የኢሳይያስ ጥቅሶች እንደሚያሳዩት ለመንፈሳዊው ሕመም መድኃኒቱ አንድ ብቻ ነው።
ለመንፈሳዊ ሕመም ፍቱን መድኃኒት
9, 10. ንጽሕና ለይሖዋ በምናቀርበው አምልኮ ውስጥ ምን ያህል ቦታ አለው?
9 ርኅሩኅ የሆነው አምላክ ይሖዋ አሁን ደግሞ በፍቅራዊ ስሜት ይበልጥ ማራኪ በሆነ መንገድ ይናገራቸዋል። “ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግን ተዉ፣ መልካም መሥራትን ተማሩ፣ ፍርድን [“ፍትሕን፣ ”] ፈልጉ፣ የተገፋውን አድኑ፣ ለድሀ አደጉ [“አባት ለሌለው ልጅ፣ ” NW ] ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ።” (ኢሳይያስ 1:16, 17 ) እዚህ ላይ ዘጠኝ ትእዛዛት በተከታታይ ተጠቅሰው እናገኛለን። የመጀመሪያዎቹ አራቱ ኃጢአትን ከማስወገድ ጋር የተያያዙ በመሆናቸው አሉታዊ ሲሆኑ የመጨረሻዎቹ አምስቱ ደግሞ የይሖዋን በረከት ለማግኘት የሚያስችሉ አዎንታዊ እርምጃዎችን እንዲወስዱ የሚያሳስቡ ናቸው።
10 መታጠብና መንጻት የንጹሕ አምልኮ ዋነኛ ክፍል ሆነው ኖረዋል። (ዘጸአት 19:10, 11፤ 30:20፤ 2 ቆሮንቶስ 7:1) ይሁን እንጂ ይሖዋ ይህ ንጽሕና የበለጠ ጥልቀት ያለው እንዲሆንና የአምላኪዎቹ ልብም ንጹሕ እንዲሆን ይፈልጋል። ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕናን መጠበቅ ሲሆን ይሖዋም የጠቀሰው ይህንኑ ነው። በኢሳይያስ ቁጥር 16 ላይ የሚገኙት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ትእዛዛት እንዲሁ ድግግሞሽ እንደሆኑ ተደርገው ሊታዩ አይገባም። ስለ ዕብራይስጥ ሰዋሰው የሚያጠኑ አንድ ሰው እንዳሉት ከሆነ መጀመሪያ የተጠቀሰው “ታጠቡ” የሚለው መግለጫ በቅድሚያ የሚወሰደውን የንጽሕና እርምጃ ሲያመለክት “ሰውነታችሁን አንጹ” የሚለው ሁለተኛው መግለጫ ግን ይህንን ንጽሕና ጠብቆ ለመቆየት የሚደረገውን ቀጣይነት ያለው ጥረት የሚያመለክት ነው።
11. ኃጢአትን ለመዋጋት ምን ማድረግ አለብን? ማድረግ የሌለብንስ ነገር ምንድን ነው?
11 ከይሖዋ ልንደብቀው የምንችለው ነገር የለም። (ኢዮብ 34:22፤ ምሳሌ 15:3፤ ዕብራውያን 4:13) ስለሆነም “የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ” ብሎ ማዘዙ ክፉ ማድረጋችሁን አቁሙ ማለቱ እንጂ ሌላ ነገር ማለት ሊሆን አይችልም። ይህም ከባድ ኃጢአት ሠርቶ ለመደበቅ አለመሞከር ማለት ነው። ምክንያቱም ኃጢአትን መደበቅ ራሱ ኃጢአት ነው። ምሳሌ 28:13 “ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል” በማለት ያስጠነቅቃል።
12. (ሀ) ‘መልካም መሥራትን መማር’ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በተለይ ሽማግሌዎች “ፍትህን ፈልጉ” እና ‘የተገፋውን አድኑ’ የሚሉትን መመሪያዎች ሥራ ላይ ማዋል የሚችሉት እንዴት ነው?
12 ይሖዋ በኢሳይያስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 17 ላይ እንዲወስዱ ካዘዛቸው አዎንታዊ እርምጃዎች ብዙ መማር ይቻላል። “መልካም ሥራ ሥሩ” ብቻ ሳይሆን “መልካም መሥራትን ተማሩ” እንዳለ ልብ በል። በአምላክ ዓይን መልካም የሆነውን ነገር መረዳትና ያንን ለማድረግ መፈለግ የአምላክን ቃል በግል ማጥናትን ይጠይቃል። በተጨማሪም ይሖዋ “ፍትህን አድርጉ” ብቻ ሳይሆን “ፍትሕን ፈልጉ” ነው ያለው። ተሞክሮ ያላቸው ሽማግሌዎች ሳይቀሩ አንዳንድ ውስብስብ ጉዳዮች ሲያጋጥሟቸው ፍትሐዊ የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ለማረጋገጥ በአምላክ ቃል ላይ ጥልቅ ምርምር ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። የእነርሱም ኃላፊነት ቢሆን ቀጥሎ ይሖዋ እንደተናገረው ‘የተገፋውን ማዳንን’ ይጠይቃል። ዛሬ ያሉት ክርስቲያን እረኞች መንጋውን ‘ከጨካኝ ተኩላዎች’ ለመጠበቅ ስለሚፈልጉ እነዚህ መመሪያዎች ለእነርሱም አስፈላጊ ናቸው።—ሥራ 20:28-30
13. አባት የሌላቸውን ልጆችና መበለቶችን በተመለከተ የተሰጠውን ትእዛዝ ዛሬ እኛ በተግባር ልናውል የምንችለው እንዴት ነው?
13 የመጨረሻዎቹ ሁለት ትእዛዛት በአምላክ ሕዝቦች መካከል የሚገኙትንና ይበልጥ ለጥቃት የተጋለጡትን ወላጆች የሌላቸውን ልጆችና መበለቶችን የሚመለከቱ ናቸው። ዓለም እነዚህን ሰዎች መጠቀሚያ ከማድረግ ወደኋላ አይልም። በአምላክ ሕዝቦች መካከል ግን እንደዚያ መሆን የለበትም። አፍቃሪ የሆኑ ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ የሚገኙት ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ወንዶችና ሴቶች ልጆች መጠቀሚያ ሊያደርጋቸውና ሊያበላሻቸው በሚፈልገው በዚህ ዓለም ውስጥ ፍትሕና ጥበቃ እንዲያገኙ በመርዳት ‘ይፈርዱላቸዋል።’ ሽማግሌዎች ‘ለመበለቲቷ ይሟገታሉ’ ወይም እንደ ዕብራይስጡ ቃል ትርጉም ስለ እርሷ ‘ይታገላሉ።’ በእርግጥም ሁሉም ክርስቲያኖች በመካከላችን ላሉት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች መሸሸጊያ እንዲሁም የመጽናኛና የፍትሕ ምንጭ ሆነው መገኘት ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች በይሖዋ ዓይን ውድ ናቸው።—ሚክያስ 6:8፤ ያዕቆብ 1:27
14. በኢሳይያስ 1:16, 17 ላይ የተገለጸው አዎንታዊ መልእክት ምንድን ነው?
14 ይሖዋ በእነዚህ ዘጠኝ ትእዛዛት አማካኝነት ያስተላለፈው መልእክት እንዴት ጥብቅና አዎንታዊ ነው! አንዳንድ ጊዜ ኃጢአት ውስጥ የወደቁ ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ነገር ማድረግ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። እንዲህ ያለው ሐሳብ ራሱ ተስፋ ያስቆርጣል። ደግሞም ተሳስተዋል። ይሖዋ ማንኛውም ኃጢአተኛ በእርሱ እርዳታ የኃጢአተኛነት ጎዳናውን ትቶ ሊመለስ እንደሚችልና በዚያ ፋንታ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ሊያደርግ እንደሚችል ያውቃል። እኛም ይህን እንድንገነዘብ ይፈልጋል።
ርኅራኄ የተንጸባረቀበት ፍትሐዊ ጥሪ
15. “እርቅ እንፍጠር” የሚለው ሐረግ አንዳንድ ጊዜ የተሳሳተ ትርጉም የሚሰጠው እንዴት ነው? ትክክለኛው ትርጉሙስ ምንድን ነው?
15 አሁን ደግሞ ይሖዋ ይበልጥ ፍቅራዊ በሆነና ርኅራኄ በተንጸባረቀበት ስሜት ተናግሯቸዋል። “ኑና እንዋቀስ [“እርቅ እንፍጠር፣ ” NW ] ይላል እግዚአብሔር፤ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች።” (ኢሳይያስ 1:18 ) በዚህ ግሩም ጥቅስ መክፈቻ ላይ የሚገኘው ጥሪ ብዙውን ጊዜ የተሳሳተ ትርጉም ይሰጠዋል። ለምሳሌ ያህል ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል ሁለቱም ወገኖች አንድ ስምምነት ላይ ለመድረስ ሲሉ ይዘውት የነበረውን አቋም ማላላት ያለባቸው ይመስል ይህን ቃል “እንደራደር” በማለት ተርጉሞታል። ግን እንደዚያ አይደለም! ይሖዋ ዓመፀኛና ግብዝ ከነበረው ከዚህ ሕዝብ ጋር ይቅርና ከማንም ጋር ባለው ግንኙነት ቢሆን የሚነቀፍበት ነገር የለም። (ዘዳግም 32:4, 5) ጥቅሱ የሚናገረው እኩል ሁኔታ ባላቸው ወገኖች መካከል ስለሚደረግ ውይይት ሳይሆን ፍትሕ ለማስጠበቅ ሲባል ስለተሰየመ ችሎት ነው። ይሖዋ እስራኤላውያንን ችሎት ፊት ያቀረባቸው ያህል ነው።
16, 17. ይሖዋ ከባድ ኃጢአቶችን እንኳ ሳይቀር ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆኑን እንዴት እናውቃለን?
16 ይህ የሚያስፈራ ነገር መስሎ ሊታይ ቢችልም ይሖዋ በጣም መሐሪና ርኅሩኅ ዳኛ ነው። ይቅር የማለት ችሎታው አቻ የለውም። (መዝሙር 86:5 NW ) እንደ “አለላ” የሆነችውን የእስራኤል ኃጢአት እንደ “አመዳይ” ሊያነጣው የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። የትኛውም ሰብዓዊ ጥረት፣ ዘዴ፣ ሥራ፣ መሥዋዕት ወይም ጸሎት የኃጢአትን እድፍ ሊያስወግድ አይችልም። ኃጢአትን አጥቦ ማስወገድ የሚችለው የይሖዋ ይቅርታ ብቻ ነው። ይሖዋ ይህን ይቅር ባይነት የሚያሳየው እርሱ ያወጣው መስፈርት ሲሟላ ማለትም እውነተኛና ልባዊ ንስሐ ሲያሳዩ ብቻ ነው።
17 ይህ እውነት በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሣ ይሖዋ በሌላ ምሳሌያዊ መግለጫ በመጠቀም ‘እንደ ደም የቀላችው’ ኃጢአት ቀለም እንዳልተነከረ ‘አዲስ ባዘቶ ጥጥ እንደምትነጣ’ ተናግሯል። ይሖዋ እውነተኛ ንስሐ ገብተን እስካገኘን ድረስ ከባድ የሆኑ ኃጢአቶችን ሳይቀር ይቅር የሚል መሆኑን እንድናውቅ ይፈልጋል። ይሖዋ የእነርሱን ኃጢአት ይቅር እንደማይላቸው የሚሰማቸው ሰዎች ካሉ እንደ ምናሴ ያሉትን ሰዎች ምሳሌ መመርመራቸው የተገባ ይሆናል። ለዓመታት ከባድ ኃጢአት ሲፈጽም ቢቆይም ንስሐ በመግባቱ ይቅርታ አግኝቷል። (2 ዜና መዋዕል 33:9-16) ይሖዋ ከባድ ኃጢአቶች የፈጸሙትን ጨምሮ ሁላችንም ከእርሱ ጋር ‘እርቅ ለመፍጠር’ አሁንም ጊዜ እንዳለን እንድናውቅ ይፈልጋል።
18. ይሖዋ ዓመፀኛ በሆኑት ሕዝቦቹ ፊት ምን ምርጫ አስቀምጧል?
18 ይሖዋ ሕዝቦቹ ምርጫ ማድረግ እንደሚችሉ አስታውሷቸዋል። “እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፣ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እንቢ ብትሉ ግን ብታምፁም፣ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።” (ኢሳይያስ 1:19, 20 ) እዚህ ላይ ይሖዋ ጠበቅ አድርጎ የተናገረው ዝንባሌን በተመለከተ ሲሆን ነጥቡን ለማስጨበጥ ሲል ሌላ ግልጽ ምሳሌ ተጠቅሟል። ይሁዳ የነበራት ምርጫ አንድም መብላት አለዚያም መበላት ብቻ ነበር። ይሖዋን ለማዳመጥና ለመታዘዝ ፈቃደኛ የመሆን ዝንባሌ ካላቸው የምድሪቱን በረከት ይበላሉ። ይሁን እንጂ በዓመፀኛ ዝንባሌያቸው ከገፉበት በጠላቶቻቸው ሰይፍ ይበላሉ! አንድ ሕዝብ ይቅር ባይ የሆነውን አምላክ ምሕረትና በረከት ረግጦ በጠላቶቹ ሰይፍ መበላትን ይመርጣል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። የሆነ ሆኖ በሚቀጥለው የኢሳይያስ ጥቅስ ላይ ማየት እንደሚቻለው የኢየሩሳሌም ምርጫ ይህ ነበር።
ስለተወደደችው ከተማ የወጣ ሙሾ
19, 20. (ሀ) ይሖዋ እርሱን በመክዳታቸው የተሰማውን ስሜት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ‘ጽድቅ በኢየሩሳሌም ያደረው’ እንዴት ነው?
19 በወቅቱ የኢየሩሳሌም ክፋት ምን ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር በኢሳይያስ 1:21-23 ላይ በግልጽ ማየት እንችላለን። ቀጥሎ ኢሳይያስ በመንፈስ ተነሳስቶ ሙሾ ወይም እንጉርጉሮ መደርደር ይጀምራል:- “ፍርድ ሞልቶባት የነበረ የታመነችይቱ ከተማ እንዴት ጋለሞታ ሆነች! ጽድቅ አድሮባት ነበር፣ አሁን ግን ገዳዮች አሉባት።”—ኢሳይያስ 1:21
20 የኢየሩሳሌም ከተማ የደረሰባት ውድቀት እንዴት ታላቅ ነው! በአንድ ወቅት የታመነች ሚስት የነበረችው ከተማ አሁን ጋለሞታ ሆናለች። ይሖዋ በኢየሩሳሌም ከዳተኛነት የተሰማውን ሐዘን ከዚህ በተሻለ መንገድ የሚገልጽ ምን ነገር ይኖራል? ይህች ከተማ በአንድ ወቅት “ጽድቅ አድሮባት ነበር።” መቼ? ገና በአብርሃም ዘመን የእስራኤል ብሔር ከመመሥረቱ በፊት ይህች ከተማ ሳሌም ተብላ ትጠራ ነበር። የከተማዋም ገዥ ንጉሥና ካህን ሆኖ የሚያገለግል ሰው ነበር። መልከ ጼዴቅ የሚለው የዚህ ሰው ስም ትርጉም “የጽድቅ ንጉሥ” ማለት ሲሆን የእርሱን ሁኔታ በትክክል የሚገልጽ ስያሜ ነበር። (ዕብራውያን 7:2፤ ዘፍጥረት 14:18-20) ከመልከ ጼዴቅ በኋላ 1, 000 ዓመት ገደማ ቆይቶ ኢየሩሳሌም በዳዊትና በሰሎሞን የንግሥና ዘመን እጅግ ገንና ነበር። በተለይ ነገሥታቶችዋ በይሖዋ መንገድ በመመላለስ ለሕዝቡ ምሳሌ ሆነው በተገኙ ጊዜ “ጽድቅ አድሮባት ነበር።” በኢሳይያስ ዘመን ግን ይህ ሁኔታ የድሮ ትዝታ ብቻ ሆኖ ነበር።
21, 22. ዝገቱና በውኃ የተበረዘው ወይን ምን ያመለክታሉ? የይሁዳ መሪዎች እንዲህ ዓይነቱ መግለጫ የሚገባቸው የሆኑት እንዴት ነው?
21 ለችግሩ በአብዛኛው አስተዋጽኦ ያደረጉት በሕዝቡ መካከል የሚገኙት አለቆች የነበሩ ይመስላል። ኢሳይያስ እንጉርጉሮውን እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ብርሽ ወደ ዝገት ተለወጠ፤ የወይን ጠጅሽ ከውኃ ጋር ተደባለቀ። አለቆችሽ ዓመፀኞችና [“እልከኞችና፣ ” NW ] የሌቦች ባልንጀሮች ሆኑ፤ ሁሉ ጉቦ ይወድዳሉ፣ ዋጋም ለማግኘት ይሮጣሉ፤ ለድሀ አደጉ አይፈርዱም፣ የመበለቲቱም ሙግት ወደ እነርሱ አይደርስም።” (ኢሳይያስ 1:22, 23 ) ተከታትለው የተጠቀሱት ሁለት ግልጽ ምሳሌዎች ቀጥሎ የሚነገረውን ነገር እንድንጠብቅ አእምሮአችንን ያዘጋጃሉ። ምድጃው አጠገብ የተቀመጠው አንጥረኛ በቀለጠው ብር ላይ ያሰፈፈውን ቁሻሻ ገፍፎ ይጥለዋል። የእስራኤል አለቆችና መሳፍንት እንደ ብሩ ሳይሆን እንደ ቁሻሻው ሆነው ነበር። መወገድ ነበረባቸው። በውኃ ተበርዞ ጣዕሙን ካጣ ወይን ምንም አልተሻሉም። እንዲህ ያለውን መጠጥ ከመድፋት የተሻለ ምርጫ አይኖርም!
22 አለቆቹን በተመለከተ እንዲህ ዓይነት መግለጫ መሰጠቱ ተገቢ የሆነው ለምን እንደሆነ ኢሳይያስ 1 ቁጥር 23 ይጠቁመናል። የሙሴ ሕግ የአምላክ ሕዝቦች ከሌሎች የተለዩና የላቀ ደረጃ ያላቸው እንዲሆኑ አስችሏቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል አንደኛው መንገድ ወላጆች የሌሏቸው ልጆችና መበለቶች ጥበቃ እንዲያገኙ በማድረግ ነበር። (ዘጸአት 22:22-24) በኢሳይያስ ዘመን ግን አባት የሌለው ልጅ ትክክለኛ ፍርድ ማግኘት የሚችልበት ተስፋ አልነበረውም። መበለቲቱም ብትሆን ስለ እርሷ የሚቆረቆር ይቅርና ጉዳይዋን እንኳ በቅጡ የሚሰማት ሰው ማግኘት አትችልም ነበር። እነዚህ መሪዎችና መሳፍንት ጉቦና ገጸ በረከት በማሳደድ እንዲሁም የሌቦች ግብረ አበር በመሆንና ለወንጀለኞች እየተከላከሉ ተጠቂዎቹ እንዲሰቃዩ በማድረግ የራሳቸውን ጥቅም በማሳደድ የተጠመዱ ይመስላል። ከሁሉ የከፋው ደግሞ በኃጢአት ጎዳናቸው “እልከኞች” ሆነው መገኘታቸው ወይም መደንደናቸው ነው። እንዴት የሚያሳዝን ሁኔታ ነው!
ይሖዋ ሕዝቡን ያጠራል
23. ይሖዋ ስለ ባላጋራዎቹ የሚሰማው ስሜት ምንድን ነው?
23 ይሖዋ ሥልጣናቸውን በዚህ መልኩ አላግባብ እየተጠቀሙ እንዲቀጥሉ አይፈቅድላቸውም። ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ስለዚህ የእስራኤል ኃያል፣ እውነተኛው ገዥ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል:- እንዲያማ ከሆነ፣ ከባላጋራዎቼ እገላገላለሁ፣ ጠላቶቼንም እበቀላለሁ።” (ኢሳይያስ 1:24 NW ) እዚህ ላይ ይሖዋ እውነተኛ ጌትነቱንና ታላቅ ኃይሉን በሚያሳዩ ሦስት ስያሜዎች ተጠርቷል። “እንዲያማ ከሆነ” የሚለው ጠንከር ያለ አነጋገር ይሖዋ በቁጭት እርምጃ ለመውሰድ ቆርጦ መነሳቱን የሚያሳይ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት እንዳለ ደግሞ ጥርጥር የለውም።
24. ይሖዋ ለሕዝቡ ሊያከናውነው ያሰበው የማንጠር ሥራ ምንድን ነው?
24 ሕዝቦቹ ራሳቸው ለይሖዋ ጠላት ሆነውበት ነበር። በእርግጥም መለኮታዊ የበቀል እርምጃ ይገባቸዋል። ይሖዋም ‘ይገላገላቸዋል’ ወይም በሌላ አባባል ያስወግዳቸዋል። ይህ ማለት ግን በስሙ የተጠራውን ሕዝብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያጠፋል ማለት ነውን? እንደዚያ ማለት አይደለም። ይሖዋ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “እጄንም በአንቺ ላይ አመጣለሁ፣ ዝገትሽንም በጣም [“በመርዝ፣ ” NW ] አነጻለሁ፣ ቆርቆሮሽንም [“ቁሻሻሽን ” ] ሁሉ አወጣለሁ።” (ኢሳይያስ 1:25) አሁን ደግሞ ይሖዋ እንደ ምሳሌ የተጠቀመው ማዕድን የማንጠር ሥራን ነው። የጥንቶቹ አንጥረኞች ዝገቱን ውድ ከሆነው ማዕድን ለመለየት ብዙውን ጊዜ መርዝ ይጨምሩ ነበር። በተመሳሳይም ይሖዋ ሕዝቡን ሙሉ በሙሉ ክፉ እንደሆነ አድርጎ ስለማይመለከት ‘በመጠን ይቀጣቸዋል።’ ከመካከላቸው የሚያስወግደው ለመማርና ለመታዘዝ ፈቃደኛ ያልሆኑትንና በእልከኝነት የሚቀጥሉትን “ቆሻሻ” ሰዎች ብቻ ነው።c (ኤርምያስ 46:28) ኢሳይያስ በዚህ መንገድ ታሪኩ ሳይፈጸም ወደፊት የሚሆነውን ነገር አስቀድሞ የመጻፍ አጋጣሚ አግኝቶ ነበር።
25. (ሀ) ይሖዋ በ607 ከዘአበ ሕዝቡን ያነጠረው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ በዘመናችን ሕዝቡን ያነጠረው መቼ ነው?
25 በእርግጥም ይሖዋ እንደ ዝገት ያሉትን ብልሹ መሪዎችና ሌሎች ዓመፀኞች በማስወገድ ሕዝቡን አንጥሯል። በ607 ከዘአበ ማለትም ከኢሳይያስ ዘመን በኋላ ብዙ ጊዜ ቆይቶ ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷም ሌላ ነዋሪዎቿ በባቢሎን ለ70 ዓመት ግዞት ተዳርገዋል። ይህም ከዚያ በኋላ ብዙ ቆይቶ አምላክ ከወሰደው ሌላ እርምጃ ጋር የሚመሳሰልባቸው አንዳንድ መንገዶች አሉ። በባቢሎን በግዞት ከቆዩ ከረጅም ጊዜ በኋላ በሚልክያስ 3:1-5 ላይ የሚገኘው ትንቢት አምላክ እንደገና የማንጠር ሥራ እንደሚሠራ ይገልጻል። ይህም፣ ይሖዋ አምላክ ‘ከቃል ኪዳኑ መልእክተኛ’ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሆኖ ወደ መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ የሚመጣበትን ጊዜ የሚጠቁም ነው። ይህ የሆነው በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ እንደሆነ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። ይሖዋ ክርስቲያን ነን የሚሉትን ሁሉ የመረመረ ሲሆን እውነተኞቹን ከሐሰተኞቹ ለይቷቸዋል። ውጤቱስ ምን ነበር?
26-28. (ሀ) ኢሳይያስ 1:26 የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? (ለ) ይህ ትንቢት በእኛ ዘመን ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? (ሐ) ይህ ትንቢት ዛሬ ሽማግሌዎችን ሊጠቅማቸው የሚችለው እንዴት ነው?
26 ይሖዋ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጣል:- “ፈራጆችሽንም እንደ ቀድሞ አማካሪዎችሽንም እንደ መጀመሪያው ጊዜ መልሼ አስነሣለሁ፤ ከዚያም በኋላ የጽድቅ ከተማ የታመነችም ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ። ጽዮን በፍርድ ከእርስዋም የሚመለሱ በጽድቅ ይድናሉ።” (ኢሳይያስ 1:26, 27 ) ይህ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው በጥንቷ ኢየሩሳሌም ላይ ነው። ግዞተኞቹ በ537 ከዘአበ ወደ ተወደደችው ከተማቸው ከተመለሱ በኋላ እንደ ቀድሞው የታመኑ ፈራጆችና አማካሪዎች ተነስተው ነበር። ነቢያቱ ሐጌና ዘካርያስ፣ ካህኑ ኢያሱ፣ ጸሐፊው ዕዝራና ገዥው ዘሩባቤል ወደ ምድራቸው የተመለሱት የታመኑ ቀሪዎች በአምላክ ጎዳና እንዲጓዙ አመራር ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ በ20ኛው መቶ ዘመን ደግሞ የሚበልጠውን ፍጻሜውን አግኝቷል።
27 በዚህ ዘመን ያሉት የይሖዋ አገልጋዮች በ1919 የፈተናውን ጊዜ አልፈው ብቅ ብለዋል። የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎን መንፈሳዊ ግዞት ነፃ ወጥተዋል። በታመኑት ቅቡዓን ቀሪዎችና በሕዝበ ክርስትና ከሃዲ ቀሳውስት መካከል ያለው ልዩነት ግልጽ ሆኖ ነበር። አምላክ ‘ፈራጆችና አማካሪዎችን’ ማለትም የአምላክን ሕዝብ በሰው ወግ ሳይሆን በቃሉ ላይ ባለው መሠረት የሚመክሩ የታመኑ ወንዶችን በማስነሳት ሕዝቡን በድጋሚ ባርኳል። ዛሬም ቢሆን ቁጥራቸው እየተመናመነ ከመጣው ‘ታናሽ መንጋም’ ሆነ የእነርሱ ባልንጀሮች ከሆኑት ቁጥራቸው እያደገ ከሄደው “ሌሎች በጎች” መካከል በሺህ የሚቆጠሩ እንዲህ ዓይነት ወንዶች አሉ።—ሉቃስ 12:32፤ ዮሐንስ 10:16፤ ኢሳይያስ 32:1, 2፤ 60:17፤ 61:3, 4
28 ሽማግሌዎች የጉባኤውን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕና ለመጠበቅ ሲሉ አልፎ አልፎ “ፈራጆች” ሆነው የሚያገለግሉበት ጊዜ እንዳለ አይዘነጉም። የአምላክን ምሕረትና ሚዛኑን የጠበቀ ፍትሕ በመኮረጅ ነገሮችን በአምላክ መንገድ መሥራት መቻላቸው ከልብ ያሳስባቸዋል። ይሁንና በአብዛኛው “አማካሪዎች” ሆነው ያገለግላሉ። ይህ ደግሞ ፈላጭ ቆራጭ መሳፍንት ከመሆን ፈጽሞ የተለየ መሆኑ ግልጽ ነው። እንዲያውም ‘ማኅበሮቻቸውን በኃይል የሚገዙ’ እንዳይመስሉ እንኳ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ።—1 ጴጥሮስ 5:3
29, 30. (ሀ) ከማንጠር ሥራው ተጠቃሚ መሆን የማይፈልጉትን ሰዎች በተመለከተ ይሖዋ ምን ተናግሯል? (ለ) ሕዝቡ በዛፎቹና በአትክልት ስፍራቸው ‘የሚያፍሩት’ እንዴት ነው?
29 በኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ የተጠቀሰውን “ዝገት” በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ከአምላክ የማንጠር ሥራ ለመጠቀም ፈቃደኛ የማይሆኑ ሰዎች ምን ይደርስባቸዋል? ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “በደለኞችና ኃጢአተኞች ግን በአንድነት ይሰበራሉ፣ እግዚአብሔርንም የሚተዉ ይጠፋሉ። በወደዳችኋት የአድባር ዛፍ ታፍራላችሁና፣ ስለ መረጣችኋትም አትክልት እፍረት ይይዛችኋልና።” (ኢሳይያስ 1:28, 29) እስከ መጨረሻ ድረስ የነቢያቱን መልእክት ቸል በማለት በይሖዋ ላይ የሚያምጹና በእርሱ ላይ ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎች “ይሰበራሉ” ‘ይጠፋሉም።’ ይህ የተፈጸመው በ607 ከዘአበ ነው። ይሁን እንጂ ስለ ዛፍና አትክልት የተጠቀሰው ነገር ምን ትርጉም አለው?
30 አይሁዳውያን ከጣዖት አምልኮ ጋር በተያያዘ ሥር የሰደደ ችግር ነበረባቸው። ብዙውን ጊዜ ዛፎች፣ የአትክልት ቦታዎችና ጫካዎች የሚዛመዱት ርካሽ ከሆኑ ድርጊቶቻቸው ነው። ለምሳሌ ያህል የበኣልና የሚስቱ የአስታሮት አምላኪዎች በደረቅ ወቅቶች ሁለቱ አማልክት ሞተው እንደሚቀበሩ ያምናሉ። እነዚህ አማልክት ከሙታን ተነስተው ግንኙነት እንዲያደርጉና ወዲያውም ለምድሪቱ ልምላሜ እንዲመጣ ለማነሳሳት ሲባል ጣዖት አምላኪዎቹ በጫካዎቹ ወይም የአትክልት ሥፍራዎቹ ውስጥ በሚገኙ “ቅዱስ” ዛፎች ሥር ልቅ የሆነ የፆታ ብልግና ይፈጽሙ ነበር። ምድሪቱ ዝናብና ልምላሜ ስታገኝ የሚመሰገኑት የሐሰት አማልክቱ ናቸው። ጣዖት አምላኪዎቹም አጉል እምነቶቻቸው ትክክል እንደሆኑ ማረጋገጫ እንዳገኙ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ዓመፀኞቹን ጣዖት አምላኪዎች ሲያጠፋቸው የሚያስጥላቸው የጣዖት አምላክ አይኖርም። ዓመፀኞቹ ምንም ማድረግ በማይችሉት በእነዚህ ዛፎችና የአትክልት ቦታዎች ‘ያፍራሉ።’
31. ጣዖት አምላኪ የሆኑት ሰዎች ከእፍረትም የከፋ ምን ነገር ይገጥማቸዋል?
31 ይሁንና ጣዖት አምላኪ የሆኑ አይሁዳውያን ከኃፍረትም የከፋ ነገር ይደርስባቸዋል። ቀጥሎ ደግሞ ይሖዋ ምሳሌውን ትንሽ ለወጥ በማድረግ ጣዖት አምላኪዎቹን ራሳቸውን ከዛፍ ጋር አመሳስሏቸዋል። “ቅጠልዋ እንደ ረገፈ ዛፍ፣ ውኃም እንደሌለባት አትክልት ትሆናላችሁና።” (ኢሳይያስ 1:30) ሞቃታማና ደረቅ የሆነ የአየር ጠባይ ላለው መካከለኛው ምሥራቅ ይህ ምሳሌ ፍጹም ተስማሚ ነው። ውኃ ሳያገኝ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ የሚችል ዛፍ ወይም የአትክልት ስፍራ የለም። እነዚህ ዕጽዋት ይደርቁና ለእሳት የተጋለጡ ይሆናሉ። በመሆኑም በኢሳይያስ 1 ቁጥር 31 ላይ የሚገኘው ምሳሌ ይፈጸማል ማለት ነው።
32. (ሀ) በኢሳይያስ 1 ቁጥር 31 ላይ የተጠቀሰው ‘ኃያል’ ሰው ማን ነው? (ለ) ‘የተልባ እግር ጭረት’ የሚሆነው በምን መንገድ ነው? የሚያቃጥለውስ “የእሳት ብልጭታ” ምንድን ነው? ውጤቱስ ምን ይሆናል?
32 “ኃይለኛውም እንደ ተልባ ጭረት፣ ሥራውም እንደ ጠለሸት [“እሳት ብልጭታ፣ ” የ1980 ትርጉመ ] ይሆናል፤ አብረውም ይቃጠላሉ እነርሱንም የሚያጠፋ የለም።” (ኢሳይያስ 1:31) ይህ ‘ኃያል ሰው’ ማን ነው? የዕብራይስጡ መግለጫ የሚያመለክተው ጥንካሬንና ብልጽግናን ነው። ባለጠጋ ስለሆነና በራሱ ስለሚመካ የሐሰት አማልክት ተከታይ የሚናገር ይመስላል። እንደ እኛ ዘመን ሁሉ በኢሳይያስም ዘመን ይሖዋን የተዉና ንጹህ አምልኮውን ገሸሽ ያደረጉ ብዙ ሰዎች ነበሩ። አንዳንዶች እንዲያውም የተሳካላቸው መስለው ይታዩ ነበር። ይሁንና ይሖዋ እንዲህ ያሉት ሰዎች እንደ “ተልባ ጭረት” ልፍስፍስና ደረቅ እንደሆኑና ገና እሳት ሲሸትታቸው ጥምልምል ብለው እንደሚጠፉ ያህል እንደሆኑ ተናግሯል። (መሳፍንት 16:8, 9) የጣዖት አምላኪው እንቅስቃሴ ውጤት የሆኑት ነገሮች ማለትም የጣዖት አማልክቱ፣ ሀብቱ ወይም በይሖዋ ፋንታ አምልኮ የሚያቀርብለት ነገር እንደ “እሳት ብልጭታ” ይሆናል። የእሳት ብልጭታውም ሆነ የተልባ እግር ጭረቱ ማንም ሊያጠፋው በማይችል እሳት ይበላሉ ወይም ይጠፋሉ። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የይሖዋን ፍጹም ፍርድ ሊቀለብስ የሚችል አካል የለም።
33. (ሀ) ስለመጪው ፍርድ የሚነገረው የማስጠንቀቂያ መልእክት የአምላክን ምሕረት የሚያሳይ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ ለሰው ዘር የዘረጋው አጋጣሚ ምንድን ነው? ይህስ እያንዳንዳችንን የሚነካን እንዴት ነው?
33 መጨረሻ ላይ የተጠቀሰው ይህ መልእክት በኢሳይያስ 1 ቁጥር 18 ላይ ከተጠቀሰው የምሕረትና የይቅር ባይነት መልእክት ጋር ይጣጣማልን? ምንም ጥያቄ የለውም! ይሖዋ አገልጋዮቹ እንዲህ ያሉትን የማስጠንቀቂያ መልእክቶች በጽሑፍ እንዲያሰፍሩና እንዲናገሩ ያደረገው መሐሪ በመሆኑ ነው። ደግሞም ‘ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዲጠፋ’ አይፈልግም። (2 ጴጥሮስ 3:9) በመሆኑም ዛሬ እያንዳንዱ እውነተኛ ክርስቲያን ንስሐ የሚገቡ ሰዎች ከዚህ ታላቅ ምሕረት ተጠቃሚ በመሆን ለዘላለም መኖር ይችሉ ዘንድ ዛሬ የአምላክን የማስጠንቀቂያ መልእክት ለሰው ዘር የማወጅ መብት አግኝቷል። ይሖዋ ጊዜው ከማለፉ በፊት ሰዎች ከእርሱ ጋር ‘እርቅ የሚፈጥሩበትን’ አጋጣሚ መፍቀዱ እንዴት ያለ ደግነት ነው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የጥንቶቹ አይሁዳውያን ወግ እንደሚለው ከሆነ ክፉ የነበረው ንጉሥ ምናሴ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ በመጋዝ ተሰንጥቆ እንዲሞት አድርጓል። (ከዕብራውያን 11:37 ጋር አወዳድር።) አንድ ጽሑፍ እንደገለጸው ከሆነ በኢሳይያስ ላይ ሞት ለማስፈረድ ሲል አንድ ሐሰተኛ ነቢይ “ኢየሩሳሌምን ሰዶም፣ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን አለቆች ደግሞ የገሞራ ሕዝብ ብሎ ጠርቷቸዋል” የሚል ክስ አቅርቦበታል።
b “ምሥጢራዊ ኃይሎች” ለሚለው ፍቺ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ጎጂ የሆነ” “ድብቅ ነገር” እና “የሚያምታታ” የሚልም ትርጉም አለው። ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት እንደሚለው ከሆነ ዕብራውያን ነቢያት “ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም ያስከተለውን ክፉ ውጤት” ለማውገዝ በዚህ ቃል ተጠቅመዋል።
c “እጄንም በአንቺ ላይ አመጣለሁ” የሚለው መግለጫ ይሖዋ ሕዝቡን ከመደገፍ ዘወር በማለት እንደሚቀጣቸው የሚያሳይ ነው።