ዘፍጥረት
35 ከዚያ በኋላ አምላክ ያዕቆብን እንዲህ አለው፦ “ተነስተህ ወደ ቤቴል+ ውጣ፤ በዚያም ኑር፤ ከወንድምህ ከኤሳው እየሸሸህ+ ሳለህ ለተገለጠልህ ለእውነተኛው አምላክ በዚያ መሠዊያ ሥራ።”
2 ከዚያም ያዕቆብ ቤተሰቡንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ “በመካከላችሁ ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤+ ራሳችሁን አንጹ፤ ልብሳችሁንም ቀይሩ፤ 3 ተነስተንም ወደ ቤቴል እንውጣ። በዚያም በጭንቀቴ ጊዜ ለሰማኝና በሄድኩበት ሁሉ* ከእኔ ላልተለየው+ ለእውነተኛው አምላክ መሠዊያ እሠራለሁ።” 4 በመሆኑም ባዕዳን አማልክታቸውን በሙሉ እንዲሁም በጆሯቸው ላይ ያደረጓቸውን ጉትቻዎች ለያዕቆብ ሰጡት፤ ያዕቆብም በሴኬም አቅራቢያ ባለው ትልቅ ዛፍ ሥር ቀበራቸው።*
5 በሚጓዙበት ጊዜም አምላክ በዙሪያቸው ባሉት ከተሞች ላይ ሽብር ይለቅባቸው ስለነበር የያዕቆብን ልጆች አላሳደዷቸውም። 6 በመጨረሻም ያዕቆብና አብረውት ያሉት ሰዎች በሙሉ በከነአን ምድር ወደምትገኘው ወደ ሎዛ+ ማለትም ወደ ቤቴል መጡ። 7 እሱም በዚያ መሠዊያ ሠራ፤ የቦታውንም ስም ኤልቤቴል* አለው፤ ምክንያቱም ከወንድሙ በሸሸበት ጊዜ እውነተኛው አምላክ በዚያ ራሱን ገልጦለት ነበር።+ 8 በኋላም የርብቃ ሞግዚት ዲቦራ+ ሞተች፤ በቤቴል አቅራቢያ በሚገኝ የባሉጥ ዛፍ ሥርም ተቀበረች። በመሆኑም ስሙን አሎንባኩት* አለው።
9 ያዕቆብ ከጳዳንአራም እየተመለሰ ሳለ አምላክ ዳግመኛ ተገለጠለትና ባረከው። 10 አምላክም “ስምህ ያዕቆብ ነው።+ ከእንግዲህ ያዕቆብ ተብለህ አትጠራም፤ ከዚህ ይልቅ ስምህ እስራኤል ይባላል” አለው። ስለዚህ እስራኤል ብሎ ጠራው።+ 11 በተጨማሪም አምላክ እንዲህ አለው፦ “እኔ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ።+ ብዛ፣ ተባዛ። ብሔራትና ብዙ ብሔራትን ያቀፈ ጉባኤ ከአንተ ይገኛሉ፤+ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ።*+ 12 ለአብርሃምና ለይስሐቅ የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ዘሮችህም ይህችን ምድር እሰጣለሁ።”+ 13 ከዚያም አምላክ ከእሱ ጋር ሲነጋገርበት ከነበረው ስፍራ ወደ ላይ ወጣ።
14 ስለዚህ ያዕቆብ ከአምላክ ጋር ሲነጋገር በነበረበት ስፍራ ላይ የድንጋይ ዓምድ አቆመ፤ ባቆመውም ዓምድ ላይ የመጠጥ መባና ዘይት አፈሰሰበት።+ 15 ያዕቆብም ከአምላክ ጋር የተነጋገረበትን ስፍራ ቤቴል+ በሚለው በዚያው ስም ጠራው።
16 ከዚያም ከቤቴል ተነስተው ሄዱ። ኤፍራታ ለመድረስ የተወሰነ ርቀት ሲቀራቸው ራሔል ምጥ ያዛት፤ ምጡም እጅግ ጠናባት። 17 ምጡ እጅግ አስጨንቋት ሳለም አዋላጇ “አይዞሽ አትፍሪ፤ ሌላ ወንድ ልጅ ልትገላገዪ ነው” አለቻት።+ 18 እሷ ግን ሕይወቷ ሊያልፍ በማጣጣር ላይ ሳለች* (ሞት አፋፍ ላይ ስለነበረች) የልጁን ስም ቤንኦኒ* አለችው፤ አባቱ ግን ስሙን ቢንያም*+ አለው። 19 ራሔልም ሞተች፤ ወደ ኤፍራታ ይኸውም ወደ ቤተልሔም+ በሚወስደው መንገድ ላይ ተቀበረች። 20 ያዕቆብም በመቃብሯ ላይ ዓምድ አቆመ፤ ይህ የራሔል መቃብር ዓምድ እስከ ዛሬ ድረስ አለ።
21 ከዚያ በኋላ እስራኤል ከዚያ ተነስቶ በመሄድ ከኤዴር ማማ አለፍ ብሎ ድንኳኑን ተከለ። 22 አንድ ቀን፣ እስራኤል በዚያ ምድር ሰፍሮ ሳለ ሮቤል ከአባቱ ቁባት ከባላ ጋር ተኛ፤ እስራኤልም ይህን ሰማ።+
ያዕቆብ 12 ወንዶች ልጆች ነበሩት። 23 ከሊያ የወለዳቸው ወንዶች ልጆቹ የበኩር ልጁ ሮቤል+ ከዚያም ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ይሳኮር እና ዛብሎን ነበሩ። 24 ከራሔል የወለዳቸው ወንዶች ልጆቹ ዮሴፍና ቢንያም ነበሩ። 25 ከራሔል አገልጋይ ከባላ የወለዳቸው ወንዶች ልጆቹ ዳንና ንፍታሌም ነበሩ። 26 ከሊያ አገልጋይ ከዚልጳ የወለዳቸው ወንዶች ልጆቹ ደግሞ ጋድና አሴር ነበሩ። እነዚህ ያዕቆብ በጳዳንአራም ሳለ የወለዳቸው ወንዶች ልጆቹ ናቸው።
27 ከጊዜ በኋላ ያዕቆብ አባቱ ይስሐቅ ወደነበረበት፣ አብርሃምና ይስሐቅ የባዕድ አገር ሰው ሆነው ወደኖሩበት+ በቂርያትአርባ ይኸውም በኬብሮን አካባቢ ወደሚገኘው ወደ ማምሬ መጣ።+ 28 ይስሐቅ 180 ዓመት ኖረ።+ 29 ከዚያም ይስሐቅ የመጨረሻ እስትንፋሱን ተነፈሰ፤ ዕድሜ ጠግቦና በሕይወቱ ረክቶ ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ፤* ልጆቹ ኤሳውና ያዕቆብም ቀበሩት።+