አንደኛ ሳሙኤል
7 በመሆኑም የቂርያትየአሪም ሰዎች መጥተው የይሖዋን ታቦት በኮረብታው ላይ ወደሚገኘው ወደ አቢናዳብ ቤት+ ወሰዱት፤ የይሖዋን ታቦት እንዲጠብቅም ልጁን አልዓዛርን ቀደሱት።
2 ታቦቱም ወደ ቂርያትየአሪም ከመጣ ረጅም ጊዜ ይኸውም በአጠቃላይ 20 ዓመት አለፈው፤ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ይሖዋን መፈለግ* ጀመረ።+ 3 ሳሙኤልም የእስራኤልን ቤት ሁሉ “በሙሉ ልባችሁ+ ወደ ይሖዋ የምትመለሱ ከሆነ ባዕዳን አማልክትንና+ የአስታሮትን ምስሎች+ ከመካከላችሁ አስወግዱ፤ ልባችሁንም ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ስጡ፤ እሱን ብቻ አገልግሉ፤+ እሱም ከፍልስጤማውያን እጅ ይታደጋችኋል”+ አላቸው። 4 በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን የባአልንና የአስታሮትን ምስሎች አስወግደው ይሖዋን ብቻ አገለገሉ።+
5 ከዚያም ሳሙኤል “እስራኤልን ሁሉ በምጽጳ+ ሰብስቡ፤ እኔም ስለ እናንተ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ”+ አለ። 6 እነሱም በምጽጳ ተሰበሰቡ፤ ከዚያም ውኃ ቀድተው በይሖዋ ፊት አፈሰሱ፤ ያን ዕለትም ሲጾሙ ዋሉ።+ በዚያም “በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርተናል” አሉ።+ ሳሙኤልም በምጽጳ በእስራኤላውያን ላይ ፈራጅ ሆኖ ማገልገል ጀመረ።+
7 ፍልስጤማውያንም እስራኤላውያን በምጽጳ አንድ ላይ መሰብሰባቸውን በሰሙ ጊዜ የፍልስጤም ገዢዎች+ እስራኤልን ለመውጋት ወጡ። እስራኤላውያንም ይህን ሲሰሙ ፍልስጤማውያንን ፈሩ። 8 ስለሆነም እስራኤላውያን ሳሙኤልን “አምላካችን ይሖዋ እንዲረዳንና ከፍልስጤማውያን እጅ እንዲያድነን ወደ እሱ መጮኽህን አታቁም” አሉት።+ 9 ከዚያም ሳሙኤል አንድ የሚጠባ ግልገል ወስዶ ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባ+ አድርጎ አቀረበው፤ ሳሙኤልም ይሖዋ እስራኤላውያንን እንዲረዳቸው ተማጸነ፤ ይሖዋም መለሰለት።+ 10 ሳሙኤል የሚቃጠለውን መባ እያቀረበ ሳለ ፍልስጤማውያን እስራኤላውያንን ለመውጋት ቀረቡ። ይሖዋም በዚያን ዕለት በፍልስጤማውያን ላይ ኃይለኛ የነጎድጓድ ድምፅ ለቀቀባቸው፤+ ግራ እንዲጋቡም አደረጋቸው፤+ እነሱም በእስራኤላውያን ፊት ድል ተመቱ።+ 11 በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሰዎች ከምጽጳ ወጥተው ፍልስጤማውያንን ማሳደዳቸውን ተያያዙት፤ ከቤትካር በስተ ደቡብ እስከሚገኘው አካባቢም ድረስ መቷቸው። 12 ከዚያም ሳሙኤል አንድ ድንጋይ+ ወስዶ በምጽጳ እና በየሻና መካከል አስቀመጠው፤ ስሙንም ኤቤንዔዘር* አለው፤ ይህን ያለው “ይሖዋ እስካሁን ድረስ ረድቶናል”+ ሲል ነው። 13 በዚህ ሁኔታ ፍልስጤማውያን ድል ተመቱ፤ ዳግመኛም ወደ እስራኤላውያን ክልል መጥተው አያውቁም፤+ በሳሙኤል ዘመን ሁሉ የይሖዋ እጅ በፍልስጤማውያን ላይ ነበር።+ 14 በተጨማሪም ፍልስጤማውያን ከእስራኤላውያን ላይ የወሰዷቸው ከኤቅሮን እስከ ጌት ያሉት ከተሞች ለእስራኤላውያን ተመለሱላቸው፤ እንዲሁም እስራኤላውያን በእነዚህ ከተሞች ሥር ያሉትን ክልሎች ከፍልስጤማውያን እጅ አስለቀቁ።
በእስራኤላውያንና በአሞራውያን መካከልም ሰላም ወረደ።+
15 ሳሙኤልም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለእስራኤላውያን ፈራጅ ሆኖ አገለገለ።+ 16 በየዓመቱም በቤቴል፣+ በጊልጋል+ እና በምጽጳ+ በመዘዋወር በእነዚህ አካባቢዎች ሁሉ ለሚገኙ እስራኤላውያን ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። 17 ሆኖም ቤቱ የሚገኘው በራማ+ ስለነበር ወደዚያ ይመለስ ነበር፤ በዚያም ለእስራኤላውያን ፈራጅ ሆኖ አገለገለ። በዚያም ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ።+