ዘፀአት
12 ይሖዋም ሙሴንና አሮንን በግብፅ ምድር እንዲህ አላቸው፦ 2 “ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሆንላችኋል። ከዓመቱም ወሮች የመጀመሪያው ይሆንላችኋል።+ 3 ለመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ እንዲህ ብላችሁ ንገሩ፦ ‘ይህ ወር በገባ በአሥረኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው ለአባቱ ቤት አንድ በግ ይኸውም ለአንድ ቤት አንድ በግ+ ይውሰድ። 4 ሆኖም ቤተሰቡ ለአንድ በግ የሚያንስ ከሆነ እነሱና የእነሱ* የቅርብ ጎረቤቶች በጉን በየቤታቸው ባሉት ሰዎች* ቁጥር ልክ ይከፋፈሉት። በምታሰሉበት ጊዜም እያንዳንዱ ሰው ከበጉ ምን ያህል እንደሚበላ ወስኑ። 5 የምትመርጡት በግ እንከን የሌለበት፣+ ተባዕትና አንድ ዓመት የሞላው መሆን ይኖርበታል። ከበግ ጠቦቶች ወይም ከፍየሎች መካከል መምረጥ ትችላላችሁ። 6 እስከዚህ ወር 14ኛ ቀን+ ድረስ እየተንከባከባችሁ አቆዩት፤ መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ጉባኤም አመሻሹ ላይ* ይረደው።+ 7 ከደሙም ወስደው በጉን በሚበሉበት ቤት በር በሁለቱ መቃኖችና በጉበኑ ላይ ይርጩት።+
8 “‘ሥጋውንም በዚያው ሌሊት ይብሉት።+ ሥጋውን በእሳት ጠብሰው ከቂጣና*+ ከመራራ ቅጠል+ ጋር ይብሉት። 9 የትኛውንም የሥጋውን ብልት ጥሬውን ወይም ቅቅሉን አትብሉ፤ ነገር ግን ጭንቅላቱን ከእግሩና ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት ጥበሱት። 10 እስከ ጠዋት ድረስ ምንም አታስተርፉ፤ ሳይበላ ያደረ ካለ ግን በእሳት አቃጥሉት።+ 11 የምትበሉትም ወገባችሁን ታጥቃችሁ፣ ጫማችሁን አድርጋችሁና በትራችሁን በእጃችሁ ይዛችሁ መሆን አለበት፤ በጥድፊያም ብሉት። ይህ የይሖዋ ፋሲካ* ነው። 12 ምክንያቱም በዚህ ሌሊት በግብፅ ምድር አልፋለሁ፤ ከሰው አንስቶ እስከ እንስሳ ድረስ በግብፅ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ እመታለሁ፤+ በግብፅ አማልክት ሁሉ ላይም የፍርድ እርምጃ እወስዳለሁ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ። 13 ደሙም እናንተ ያላችሁበትን ቤት የሚጠቁም ምልክት ሆኖ ያገለግላል፤ እኔም ደሙን ሳይ እናንተን አልፌ እሄዳለሁ፤ የግብፅን ምድር በምመታበት ጊዜ መቅሰፍቱ መጥቶ እናንተን አያጠፋም።+
14 “‘ይህ ቀን ለእናንተ መታሰቢያ ይሆናል፤ እናንተም በመጪዎቹ ትውልዶቻችሁ ሁሉ የይሖዋ በዓል አድርጋችሁ አክብሩት። ይህን ዘላቂ ደንብ አድርጋችሁ አክብሩት። 15 ለሰባት ቀን ቂጣ ትበላላችሁ።+ አዎ፣ በመጀመሪያው ቀን ከቤታችሁ እርሾ አስወግዱ፤ ምክንያቱም ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ እስከ ሰባተኛው ቀን ድረስ እርሾ የገባበትን ነገር የሚበላ ማንኛውም ሰው* ከእስራኤል መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረጋል። 16 በመጀመሪያው ቀን ቅዱስ ጉባኤ አድርጉ፤ በሰባተኛውም ቀን ሌላ ቅዱስ ጉባኤ አድርጉ። በእነዚህ ቀናት ምንም ዓይነት ሥራ መሠራት የለበትም።+ እያንዳንዱ ሰው* የሚበላውን ነገር ከማዘጋጀት ውጭ ሌላ ምንም ነገር አትሥሩ።
17 “‘የቂጣን በዓል አክብሩ፤+ ምክንያቱም በዚህ ቀን ሠራዊታችሁን ከግብፅ ምድር አወጣለሁ። እናንተም ይህን ዕለት በመጪዎቹ ትውልዶቻችሁ ሁሉ ዘላቂ ደንብ አድርጋችሁ አክብሩት። 18 በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም ከ14ኛው ቀን ምሽት አንስቶ እስከ ወሩ 21ኛ ቀን ምሽት ድረስ ቂጣ ትበላላችሁ።+ 19 ለሰባት ቀናት እርሾ የሚባል ነገር በቤታችሁ ውስጥ አይገኝ፤ ምክንያቱም እርሾ ያለበትን ነገር የሚበላ ማንኛውም ሰው የባዕድ አገር ሰውም ሆነ የአገሩ ተወላጅ፣+ ያ ሰው* ከእስራኤል ማኅበረሰብ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረጋል።+ 20 እርሾ ያለበት ምንም ነገር አትብሉ። በቤታችሁ ሁሉ ቂጣ ብሉ።’”
21 ሙሴም ወዲያው የእስራኤልን ሽማግሌዎች+ በሙሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ሂዱ፣ ለየቤተሰባችሁ የሚሆን ጠቦት መርጣችሁ የፋሲካን መሥዋዕት እረዱ። 22 ከዚያም አንድ እስር ሂሶጵ ወስዳችሁ በሳህን ባለው ደም ውስጥ ከነከራችሁ በኋላ ደሙን በበራችሁ ጉበንና በሁለቱ መቃኖች ላይ እርጩት፤ ከእናንተም መካከል አንድም ሰው እስኪነጋ ድረስ ከቤቱ መውጣት የለበትም። 23 ይሖዋ ግብፃውያንን በመቅሰፍት ሊመታ በሚያልፍበት ጊዜ በበራችሁ ጉበንና በሁለቱ መቃኖች ላይ ያለውን ደም ሲያይ ይሖዋ በእርግጥ በሩን አልፎ ይሄዳል፤ የሞት መቅሰፍቱ* ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይፈቅድም።+
24 “እናንተም ይህን ነገር ለእናንተና ለልጆቻችሁ ዘላቂ ሥርዓት አድርጋችሁ አክብሩት።+ 25 ልክ ይሖዋ በተናገረው መሠረትም ወደሚሰጣችሁ ምድር በምትገቡበት ጊዜ ይህን በዓል አክብሩ።+ 26 ልጆቻችሁ ‘ይህን በዓል የምታከብሩት ለምንድን ነው?’ ብለው ሲጠይቋችሁ+ 27 እንዲህ በሏቸው፦ ‘ግብፃውያንን በመቅሰፍት በመታበት ጊዜ በግብፅ ያሉትን የእስራኤላውያንን ቤቶች አልፎ በመሄድ ቤቶቻችንን ላተረፈልን ለይሖዋ የሚቀርብ የፋሲካ መሥዋዕት ነው።’”
ከዚያም ሕዝቡ ተደፍቶ ሰገደ። 28 እስራኤላውያንም ሄደው ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዳዘዛቸው አደረጉ።+ ልክ እንደተባሉት አደረጉ።
29 እኩለ ሌሊት ላይ ይሖዋ፣ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን የበኩር ልጅ አንስቶ በእስር ቤት* እስከሚገኘው እስረኛ የበኩር ልጅ ድረስ በግብፅ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ መታ፤ የእያንዳንዱን እንስሳ በኩርም መታ።+ 30 ከዚያም ፈርዖን በዚያ ሌሊት ተነሳ፤ እሱ ብቻ ሳይሆን አገልጋዮቹ ሁሉና ሌሎቹ ግብፃውያን በሙሉ ተነሱ፤ ሰው ያልሞተበት አንድም ቤት ስላልነበር በግብፃውያን መካከል ታላቅ ዋይታ ሆነ።+ 31 እሱም ወዲያውኑ ሙሴንና አሮንን በሌሊት ጠርቶ+ እንዲህ አላቸው፦ “ተነሱ፣ እናንተም ሆናችሁ ሌሎቹ እስራኤላውያን ከሕዝቤ መካከል ውጡ። ሂዱ፣ እንዳላችሁት ይሖዋን አገልግሉ።+ 32 ባላችሁትም መሠረት መንጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ይዛችሁ ሂዱ።+ እኔን ግን ባርኩኝ።”
33 ግብፃውያኑም “በዚህ ዓይነት እኮ ሁላችንም ማለቃችን ነው!”+ በማለት ሕዝቡ በአስቸኳይ ምድሪቱን ለቆ እንዲሄድላቸው ያጣድፉት ጀመር።+ 34 ስለዚህ ሕዝቡ ያልቦካውን ሊጥ በየቡሃቃው አድርጎ በልብሱ ከጠቀለለ በኋላ በትከሻው ተሸከመው። 35 እስራኤላውያንም ሙሴ የነገራቸውን አደረጉ፤ የብርና የወርቅ ዕቃዎችን እንዲሁም ልብሶችን እንዲሰጧቸውም ግብፃውያንን ጠየቁ።+ 36 ይሖዋም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት ሞገስ ሰጣቸው፤ በመሆኑም የጠየቁትን ሁሉ ሰጧቸው፤ ግብፃውያኑንም በዘበዟቸው።+
37 ከዚያም እስራኤላውያን ከራምሴስ+ ተነስተው ወደ ሱኮት+ ሄዱ፤ ልጆችን ሳይጨምር እግረኛ የሆኑት ወንዶች ወደ 600,000 ገደማ ነበሩ።+ 38 ከእነሱም ጋር እጅግ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ*+ እንዲሁም መንጎችና ከብቶች ይኸውም እጅግ ብዙ እንስሳ አብሮ ወጣ። 39 እነሱም ከግብፅ ይዘው በወጡት ሊጥ ቂጣ ጋገሩ። ይህም የሆነው ሊጡ ስላልቦካ ነበር፤ ምክንያቱም ከግብፅ እንዲወጡ የተደረገው በድንገት ስለነበር ለራሳቸው ስንቅ ማዘጋጀት አልቻሉም።+
40 በግብፅ የኖሩት እስራኤላውያን+ የኖሩበት ዘመን 430 ዓመት ነበር።+ 41 አራት መቶ ሠላሳው ዓመት በተፈጸመበት በዚያው ዕለት መላው የይሖዋ ሠራዊት ከግብፅ ምድር ወጣ። 42 ይህ ሌሊት ይሖዋ ከግብፅ ምድር ስላወጣቸው የሚያከብሩት ሌሊት ነው። ይህ ሌሊት መላው የእስራኤል ሕዝብ በመጪዎቹ ትውልዶች ሁሉ ለይሖዋ የሚያከብረው ሌሊት ነው።+
43 ከዚያም ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “የፋሲካው ደንብ ይህ ነው፦ ማንኛውም የባዕድ አገር ሰው ከፋሲካው አይብላ።+ 44 ሆኖም አንድ ሰው በገንዘብ የተገዛ ባሪያ ካለው ግረዘው።+ መብላት የሚችለው ይህ ከሆነ ብቻ ነው። 45 ሰፋሪና ቅጥር ሠራተኛ ከዚያ ላይ መብላት የለባቸውም። 46 በአንድ ቤት ውስጥ መበላት አለበት። ከሥጋውም ላይ የትኛውንም ቢሆን ከቤት ውጭ ይዘህ አትውጣ፤ ከአጥንቱም አንዱንም አትስበሩ።+ 47 መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ይህን በዓል ማክበር አለበት። 48 በመካከላችሁ የሚኖር የባዕድ አገር ሰው ካለና ለይሖዋ ፋሲካን ማክበር ከፈለገ የእሱ የሆኑት ወንዶች ሁሉ መገረዝ አለባቸው። ከዚያ በኋላ በዓሉን ለማክበር መቅረብ ይችላል፤ እሱም እንደ አገሩ ተወላጅ ይሆናል። ነገር ግን ማንኛውም ያልተገረዘ ሰው ከፋሲካው ምግብ መብላት አይችልም።+ 49 ለአገሩ ተወላጅም ሆነ በመካከላችሁ ለሚኖር የባዕድ አገር ሰው ሕጉ አንድ ዓይነት ነው።”+
50 በመሆኑም እስራኤላውያን በሙሉ ይሖዋ ሙሴን እና አሮንን እንዳዘዛቸው አደረጉ። ልክ እንደተባሉት አደረጉ። 51 በዚሁ ቀን ይሖዋ እስራኤላውያንን ከነሠራዊታቸው ከግብፅ ምድር አወጣቸው።