የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ሐምሌ 2020
ከሐምሌ 6-12
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 6–7
“አሁን በፈርዖን ላይ የማደርገውን ታያለህ”
(ዘፀአት 6:1) በመሆኑም ይሖዋ ሙሴን “አሁን በፈርዖን ላይ የማደርገውን ታያለህ። በኃያል ክንድ ተገዶ ይለቃቸዋል፤ በኃያል ክንድ ተገዶም ከምድሩ እንዲወጡ ያደርጋቸዋል” አለው።
(ዘፀአት 6:6, 7) “ስለዚህ እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘እኔ ይሖዋ ነኝ፤ ከግብፃውያን ከባድ ሸክም ነፃ አወጣችኋለሁ፤ ከጫኑባችሁም የባርነት ቀንበር አላቅቃችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድና በታላቅ ፍርድ እታደጋችኋለሁ። 7 የራሴ ሕዝብ አድርጌ እወስዳችኋለሁ፤ አምላካችሁም እሆናለሁ፤ እናንተም ከግብፃውያን ከባድ ሸክም ነፃ የማወጣችሁ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ታውቃላችሁ።
it-2 436 አን. 3
ሙሴ
የእስራኤል ሰዎችም ትልቅ ለውጥ አሳይተዋል። መጀመሪያ ላይ ሙሴን አምነውት ነበር፤ ፈርዖን ሥራቸው እንዲከብድ ካደረገ በኋላ ግን በሙሴ ላይ አጉረመረሙ፤ በዚህም ምክንያት ሙሴ ተስፋ ቆርጦ ይሖዋን ተማጸነ። (ዘፀ 4:29-31፤ 5:19-23) በዚህ ጊዜ ሁሉን ቻዩ አምላክ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ይጠብቁ የነበረውን ነገር የሚፈጽምበት ይኸውም እስራኤላውያንን ነፃ በማውጣትና በተስፋይቱ ምድር ኃያል ብሔር አድርጎ በማቋቋም ይሖዋ የሚለውን ስሙን ትርጉም ሙሉ በሙሉ የሚገልጥበት ጊዜ እንደደረሰ በመንገር አበረታታው። (ዘፀ 6:1-8) በዚያን ጊዜም ቢሆን እስራኤላውያን ሙሴን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆኑም። ዘጠነኛው መቅሰፍት ከመጣ በኋላ ግን እስራኤላውያን በሙሴ ሙሉ በሙሉ ተማምነው ተባበሩት፤ በመሆኑም አሥረኛው መቅሰፍት ከመጣ በኋላ ሙሴ ሕዝቡን በማደራጀት “የጦርነት አሰላለፍ ተከትለው” እንዲወጡ ማድረግ ችሏል።—ዘፀ 13:18
(ዘፀአት 7:4, 5) ፈርዖን ግን አይሰማችሁም፤ እኔም በግብፅ ምድር ላይ እጄን አሳርፋለሁ፤ ሠራዊቴን ይኸውም ሕዝቤ የሆኑትን እስራኤላውያንን በታላቅ ፍርድ ከግብፅ ምድር አወጣቸዋለሁ። 5 በግብፅ ላይ እጄን ስዘረጋና እስራኤላውያንን ከመካከላቸው ሳወጣ ግብፃውያን እኔ ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ያውቃሉ።”
it-2 436 አን. 1-2
ሙሴ
በግብፁ ፈርዖን ፊት። አሁን ሙሴና አሮን ‘በአማልክቱ ጦርነት’ ላይ ወሳኝ ሚና መጫወት ጀመሩ። ፈርዖን በአስማተኛ ካህናቱ አማካኝነት (አለቆቻቸው ኢያኔስና ኢያንበሬስ ሳይሆኑ አይቀሩም [2ጢሞ 3:8]) የግብፅ አማልክት በሙሉ ኃይላቸውን አሰባስበው ከይሖዋ ጋር እንዲፋለሙ አደረገ። አሮን በሙሴ ትእዛዝ ፈርዖን ፊት የፈጸመው የመጀመሪያው ተአምር ይሖዋ ከግብፅ አማልክት የላቀ እንደሆነ አረጋግጧል፤ ሆኖም የፈርዖን ልብ ይበልጥ ደነደነ። (ዘፀ 7:8-13) በኋላ ሦስተኛው መቅሰፍት ሲመጣ ግን ካህናቱም ሳይቀሩ “ይህ የአምላክ ጣት ነው!” ብለው ለማመን ተገደዱ። የእባጩ መቅሰፍት ሲመታቸው ደግሞ በጣም ከመቁሰላቸው የተነሳ ሙሴን ለመቃወም በፈርዖን ፊት መቅረብ እንኳ አልቻሉም ነበር።—ዘፀ 8:16-19፤ 9:10-12
መቅሰፍቶቹ የአንዳንዶችን ልብ አለሰለሱ፤ የአንዳንዶችን ልብ ደግሞ አደነደኑ። ሙሴና አሮን እያንዳንዱ መቅሰፍት ከመድረሱ በፊት መቅሰፍቱ እንደሚመጣ ይናገሩ ነበር። መቅሰፍቶቹ እነሱ በተናገሩት መሠረት መድረሳቸው ሙሴ የይሖዋ ወኪል መሆኑን አረጋግጧል። የይሖዋ ስም ግብፅ ውስጥ በስፋት ታወጀ፤ ይህም የእስራኤላውያንና የአንዳንድ ግብፃውያን ልብ እንዲለሰልስ፣ የፈርዖን እንዲሁም የአማካሪዎቹና የደጋፊዎቹ ልብ ደግሞ እንዲደነድን አድርጓል። (ዘፀ 9:16፤ 11:10፤ 12:29-39) ግብፃውያን አማልክታቸው እንደተቆጡባቸው አላሰቡም፤ ከዚህ ይልቅ በአማልክታቸው ላይ እየፈረደ ያለው ይሖዋ እንደሆነ አውቀው ነበር። ዘጠኙ መቅሰፍቶች ከደረሱ በኋላ “ሙሴ ራሱም ቢሆን በፈርዖን አገልጋዮችና በሕዝቡ ፊት በግብፅ ምድር እጅግ የተከበረ ሰው ሆኖ ነበር።”—ዘፀ 11:3
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 6:3) ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ሁሉን ቻይ አምላክ ሆኜ እገለጥላቸው ነበር፤ ይሖዋ የሚለውን ስሜን በተመለከተ ግን ራሴን ሙሉ በሙሉ አልገለጥኩላቸውም።
it-1 78 አን. 3-4
ሁሉን ቻይ
ይሖዋ ይስሐቅ እንደሚወለድ ለአብርሃም ተስፋ ሲሰጠው “ሁሉን ቻይ አምላክ” (ኤልሻዳይ) የሚለውን ማዕረግ ተጠቅሟል፤ አብርሃም አምላክ ይህን ተስፋ ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል ያለው ስለመሆኑ ታላቅ እምነት ማሳደር ነበረበት። በኋላም አምላክ የአብርሃም ቃል ኪዳን ወራሾች የሆኑትን ይስሐቅንና ያዕቆብን እንደሚባርካቸው በተገለጸበት ወቅት ይህ የማዕረግ ስም ተጠቅሷል።—ዘፍ 17:1፤ 28:3፤ 35:11፤ 48:3
ከዚህ አንጻር ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ሙሴን “ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ሁሉን ቻይ አምላክ (ቤኤልሻዳይ) ሆኜ እገለጥላቸው ነበር፤ ይሖዋ የሚለውን ስሜን በተመለከተ ግን ራሴን ሙሉ በሙሉ አልገለጥኩላቸውም” ብሎታል። (ዘፀ 6:3) ይህ ሐሳብ እነዚህ የቤተሰብ ራሶች ይሖዋ የሚለውን ስም እንደማያውቁ የሚያመለክት ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም እነሱም ሆኑ ከእነሱ በፊት የኖሩ ሰዎች በዚህ ስም አዘውትረው ይጠቀሙ ነበር። (ዘፍ 4:1, 26፤ 14:22፤ 27:27፤ 28:16) እንዲያውም የእነዚህን የቤተሰብ ራሶች ታሪክ በያዘው በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ “ሁሉን ቻይ” የሚለው የማዕረግ ስም የሚገኘው 6 ጊዜ ብቻ ሲሆን ይሖዋ የሚለው የአምላክ የግል ስም ግን በዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ ላይ 172 ጊዜ ይገኛል። ይሁንና እነዚህ የቤተሰብ ራሶች አምላክ “ሁሉን ቻይ” ተብሎ ለመጠራት መብቱም ሆነ ብቃቱ እንዳለው በገዛ ሕይወታቸው ያዩ ቢሆንም ይሖዋ የሚለው የግል ስሙ ያለውን ሙሉ ትርጉምና የሚያስተላልፈውን መልእክት በሕይወታቸው የማየት አጋጣሚ አላገኙም። ዚ ኢለስትሬትድ ባይብል ዲክሽነሪ (ጥራዝ 1 ገጽ 572) ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “[አምላክ] ቀደም ሲል ለቤተሰብ ራሶቹ የተገለጠው ከዘመናት በኋላ ከሚፈጸሙ ተስፋዎች ጋር በተያያዘ ነው፤ በመሆኑም እሱ ማለትም ያህዌ ተስፋዎቹን መፈጸም የሚችል (ሳዳይ የሚለው ቃል አንድ ትርጉም ሊሆን ይችላል) አምላክ (ኤል) እንደሆነ ሊያረጋግጥላቸው ፈልጎ ነበር። በቁጥቋጦው ውስጥ የተገለጠበት መንገድ ግን ይበልጥ ታላቅና ቅርበትን የሚያሳይ ነበር፤ የአምላክ ኃይል እንዲሁም እሱ ያኔም ሆነ ወደፊት አብሯቸው እንደሚሆን የሚገልጸው ማረጋገጫ በደንብ በሚያውቁት ያህዌ በሚለው ስም ውስጥ በአንድ ላይ ተጠቃሏል።”—አርታዒ ጄ. ዲ. ዳግላስ፣ 1980
(ዘፀአት 7:1) ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ አንተን ለፈርዖን እንደ አምላክ አድርጌሃለሁ፤ የገዛ ወንድምህ አሮን ደግሞ የአንተ ነቢይ ይሆናል።
it-2 435 አን. 5
ሙሴ
ሙሴ በራሱ የማይተማመን መሆኑ ብቁ እንዳይሆን አላደረገውም። ሆኖም ሙሴ አንደበተ ርቱዕ እንዳልሆነ በመናገር በራሱ እንደማይተማመን አሳየ። ከ40 ዓመት በፊት ራሱን የእስራኤላውያን አዳኝ አድርጎ ያቀረበው ሙሴ በዚህ ወቅት ተለውጦ ነበር። ሙሴ ኃላፊነቱን ላለመቀበል ከይሖዋ ጋር መከራከሩን ቀጠለ፤ በመጨረሻም ከእሱ ይልቅ ሌላ ሰው እንዲልክ ይሖዋን ጠየቀው። አምላክ በዚህ ምክንያት ቁጣው ቢነድም ሙሴን ከመላክ ወደኋላ አላለም፤ ከዚህ ይልቅ የሙሴ ወንድም የሆነው አሮን ቃል አቀባይ እንዲሆንለት አደረገ። በመሆኑም ሙሴ የአምላክ ወኪል እንደነበረ ሁሉ እሱን ወክሎ ለሚናገረው ለአሮን እንደ “አምላክ” ሆነለት። ከእስራኤል ሽማግሌዎችም ሆነ ከፈርዖን ጋር በተገናኙባቸው ወቅቶች አምላክ ለሙሴ መመሪያዎችና ትእዛዞች ከሰጠው በኋላ ሙሴ ደግሞ እነዚህን መመሪያዎች ለአሮን ያስተላለፈ ይመስላል፤ ከዚያም በፈርዖን (ከ40 ዓመት በፊት ሙሴ በሸሸበት ወቅት የነበረው ፈርዖን ተተኪ) ፊት የተናገረው አሮን ሳይሆን አይቀርም። (ዘፀ 2:23፤ 4:10-17) በኋላም ይሖዋ አሮን የሙሴ “ነቢይ” እንደሆነ ተናግሯል፤ ይህም ሙሴ ከአምላክ መመሪያ የሚቀበል የአምላክ ነቢይ እንደነበረው ሁሉ አሮንም የሙሴን መመሪያ መቀበል እንዳለበት ያመለክታል። በተጨማሪም ሙሴ “ለፈርዖን እንደ አምላክ” እንደሚሆን ተነግሮታል፤ ይህም በፈርዖን ላይ መለኮታዊ ኃይልና ሥልጣን ስለሚሰጠው የግብፅን ንጉሥ የሚፈራበት ምክንያት እንደሌለ ያሳያል።—ዘፀ 7:1, 2
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፀአት 6:1-15) በመሆኑም ይሖዋ ሙሴን “አሁን በፈርዖን ላይ የማደርገውን ታያለህ። በኃያል ክንድ ተገዶ ይለቃቸዋል፤ በኃያል ክንድ ተገዶም ከምድሩ እንዲወጡ ያደርጋቸዋል” አለው። 2 ከዚያም አምላክ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እኔ ይሖዋ ነኝ። 3 ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ሁሉን ቻይ አምላክ ሆኜ እገለጥላቸው ነበር፤ ይሖዋ የሚለውን ስሜን በተመለከተ ግን ራሴን ሙሉ በሙሉ አልገለጥኩላቸውም። 4 በተጨማሪም የከነአንን ምድር ማለትም የባዕድ አገር ሰው ሆነው የኖሩባትን ምድር ልሰጣቸው ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ። 5 እንግዲህ አሁን ግብፃውያን በባርነት እየገዟቸው ያሉት የእስራኤል ሰዎች እያሰሙት ያለውን የሥቃይ ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አስባለሁ። 6 “ስለዚህ እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘እኔ ይሖዋ ነኝ፤ ከግብፃውያን ከባድ ሸክም ነፃ አወጣችኋለሁ፤ ከጫኑባችሁም የባርነት ቀንበር አላቅቃችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድና በታላቅ ፍርድ እታደጋችኋለሁ። 7 የራሴ ሕዝብ አድርጌ እወስዳችኋለሁ፤ አምላካችሁም እሆናለሁ፤ እናንተም ከግብፃውያን ከባድ ሸክም ነፃ የማወጣችሁ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ መሆኔን በእርግጥ ታውቃላችሁ። 8 ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ለመስጠት እጄን አንስቼ ወደማልኩላቸው ምድር አስገባችኋለሁ፤ ርስት አድርጌም እሰጣችኋለሁ። እኔ ይሖዋ ነኝ።’” 9 ከዚያም ሙሴ ለእስራኤላውያን ይህን መልእክት ነገራቸው፤ እነሱ ግን ተስፋ ከመቁረጣቸውና አስከፊ ከሆነው የባርነት ሕይወታቸው የተነሳ ሊሰሙት ፈቃደኞች አልሆኑም። 10 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 11 “ወደ ግብፁ ንጉሥ ወደ ፈርዖን ገብተህ እስራኤላውያንን ከምድሩ እንዲያሰናብታቸው ንገረው።” 12 ሆኖም ሙሴ “እንግዲህ እስራኤላውያን ሊሰሙኝ ፈቃደኛ አልሆኑም፤ ታዲያ የመናገር ችግር ያለብኝን እኔን፣ ፈርዖን እንዴት ብሎ ሊሰማኝ ይችላል?” በማለት ለይሖዋ መለሰ። 13 ይሖዋ ግን እስራኤላውያንን ከግብፅ ምድር ለማውጣት ለእነሱና ለግብፁ ንጉሥ ለፈርዖን ማስተላለፍ ያለባቸውን ትእዛዝ ለሙሴና ለአሮን በድጋሚ ነገራቸው። 14 የአባቶቻቸው ቤት መሪዎችም እነዚህ ናቸው፦ የእስራኤል የበኩር ልጅ የሮቤል ወንዶች ልጆች ሃኖክ፣ ፓሉ፣ ኤስሮን እና ካርሚ ነበሩ። እነዚህ የሮቤል ቤተሰቦች ናቸው። 15 የስምዖን ወንዶች ልጆች የሙኤል፣ ያሚን፣ ኦሃድ፣ ያኪን፣ ጾሃር እና ከአንዲት ከነአናዊት የወለደው ሻኡል ነበሩ። እነዚህ የስምዖን ቤተሰቦች ናቸው።
ከሐምሌ 13-19
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 8–9
“ኩራተኛው ፈርዖን ሳያውቀው የአምላክን ዓላማ አስፈጸመ”
(ዘፀአት 8:15) ፈርዖንም ችግሩ ጋብ ማለቱን ባየ ጊዜ ልቡን አደነደነ፤ ልክ ይሖዋ እንደተናገረውም እነሱን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም።
it-2 1040-1041
ግትርነት
ይሖዋ የሰው ልጆችን የያዘበትን መንገድ ስንመለከት የተለያዩ ግለሰቦችም ሆኑ ብሔራት ሞት የሚገባቸው ቢሆኑም ትዕግሥት በማሳየት ሳይጠፋ እንዳቆያቸው እናስተውላለን። (ዘፍ 15:16፤ 2ጴጥ 3:9) አንዳንዶች ለምሕረት የሚያበቃ ሥራ በመሥራት ለትዕግሥቱ ጥሩ ምላሽ ቢሰጡም (ኢያሱ 2:8-14፤ 6:22, 23፤ 9:3-15) ሌሎች ግን በይሖዋና በሕዝቡ ላይ ይበልጥ ልባቸውን አደንድነዋል። (ዘዳ 2:30-33፤ ኢያሱ 11:19, 20) ይሖዋ ሰዎች ግትር እንዳይሆኑ ስለማይከለክላቸው ‘ልባቸውን እንዳደነደነ’ ወይም ‘ግትር እንዲሆኑ እንደፈቀደ’ ተደርጎ ተገልጿል። በግትሮች ላይ የበቀል እርምጃ በሚወስድበት ጊዜ ታላቅ ኃይሉ ይገለጣል እንዲሁም ስሙ ይታወጃል።—ከዘፀ 4:21፤ ዮሐ 12:40 እና ሮም 9:14-18 ጋር አወዳድር።
(ዘፀአት 8:18, 19) አስማተኞቹ ካህናትም ተመሳሳይ ነገር ለመፈጸምና በሚስጥራዊ ጥበባቸው ትንኞች እንዲፈሉ ለማድረግ ሞከሩ፤ ሆኖም አልቻሉም። ትንኞቹ ሰዉንም እንስሳውንም ወርረው ነበር። 19 በመሆኑም አስማተኞቹ ካህናት ፈርዖንን “ይህ የአምላክ ጣት ነው!” አሉት። የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፤ ልክ ይሖዋ እንዳለውም እነሱን አልሰማቸውም።
(ዘፀአት 9:15-17) እስካሁን እጄን ዘርግቼ አንተንም ሆነ ሕዝብህን አጥፊ በሆነ መቅሰፍት በመታኋችሁ ነበር፤ አንተም ከምድር ገጽ ተጠራርገህ በጠፋህ ነበር። 16 ሆኖም ኃይሌን እንዳሳይህና ስሜ በመላው ምድር እንዲታወጅ ስል በሕይወት አቆይቼሃለሁ። 17 ሕዝቤን አለቅም በማለት አሁንም በእነሱ ላይ እንደታበይክ ነህ?
it-2 1181 አን. 3-5
ክፋት
በተጨማሪም ይሖዋ አምላክ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ክፉዎች ሳያውቁት የእሱን ዓላማ እንዲፈጽሙ ያደርጋል። ክፉዎች አምላክን የሚቃወሙ ቢሆኑም እንኳ አምላክ አገልጋዮቹ ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው መጽናት እንዲችሉ በክፉዎች ላይ ገደብ መጣል እንዲሁም እንዲህ ያሉ ክፉ ሰዎች የሚያደርጉት ነገር እንኳ የእሱን ጽድቅ አጉልቶ እንዲያሳይ ማድረግ ይችላል። (ሮም 3:3-5, 23-26፤ 8:35-39፤ መዝ 76:10) ምሳሌ 16:4 ይህን ሐሳብ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ ማንኛውንም ነገር ያዘጋጀው ለራሱ ዓላማ ነው፤ ክፉውም ሰው እንኳ በመዓት ቀን እንዲጠፋ ያደርጋል።”
ይሖዋ በባርነት የተያዙትን እስራኤላውያንን እንዲለቅ በሙሴና በአሮን አማካኝነት የጠየቀው ፈርዖን ለዚህ ምሳሌ ይሆናል። ይህን ግብፃዊ መሪ ክፉ ያደረገው አምላክ አይደለም፤ ሆኖም በሕይወት እንዲቀጥል ፈቅዶለታል፤ እንዲሁም ክፋቱና ሞት የሚገባው መሆኑ እንዲታይ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። ይሖዋ ይህን ያደረገበት ዓላማ በዘፀአት 9:16 ላይ ተገልጿል፦ “ኃይሌን እንዳሳይህና ስሜ በመላው ምድር እንዲታወጅ ስል በሕይወት አቆይቼሃለሁ።”
በግብፅ ላይ የደረሱት አሥር መቅሰፍቶች እንዲሁም የፈርዖንና የሠራዊቱ በቀይ ባሕር መደምሰስ የይሖዋን ኃይል አስደናቂ በሆነ መንገድ ያሳያሉ። (ዘፀ 7:14–12:30፤ መዝ 78:43-51፤ 136:15) ከበርካታ ዓመታት በኋላም እንኳ በዙሪያ ያሉት ብሔራት ስለዚህ ጉዳይ ያወሩ ነበር፤ በመሆኑም የአምላክ ስም በመላው ምድር ታውጇል። (ኢያሱ 2:10, 11፤ 1ሳሙ 4:8) ይሖዋ ፈርዖንን ወዲያውኑ ገድሎት ቢሆን ኖሮ ለራሱ ክብር ማስገኘትና ሕዝቡን ነፃ ማውጣት ያስቻለው ይህ አስደናቂ የኃይሉ መገለጫ ሊታይ አይችልም ነበር።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 8:21) ሕዝቤን የማትለቅ ከሆነ ግን በአንተ፣ በአገልጋዮችህና በሕዝብህ ላይ እንዲሁም በቤቶችህ ውስጥ ተናካሽ ዝንብ እለቃለሁ፤ ዝንቦቹም በግብፅ ያሉትን ቤቶች ይሞላሉ፤ አልፎ ተርፎም የቆሙበትን መሬት ይሸፍናሉ።
it-1 878
ተናካሽ ዝንቦች
በግብፅ ላይ ከደረሰው አራተኛ መቅሰፍት (በጎሸን በሚኖሩት እስራኤላውያን ላይ ያልደረሰው የመጀመሪያው መቅሰፍት) ጋር ተያይዞ የተጠቀሰው የዕብራይስጥ ቃል ከነፍሳት መካከል የትኛውን እንደሚያመለክት በእርግጠኝነት አይታወቅም። (ዘፀ 8:21, 22, 24, 29, 31፤ መዝ 78:45፤ 105:31) አሮቭ የሚለው ቃል “ተናካሽ ዝንብ” (NWT)፣ “ዝንብ” (የ1954 ትርጉም፣ አዲሱ መደበኛ ትርጉም) እና “የውሻ ዝንብ” (የ1879 ትርጉም) ተብሎ ተተርጉሟል።
“ተናካሽ ዝንብ” የሚለው አገላለጽ እንስሳትንና ሰዎችን በመንደፍ ደማቸውን የሚመጥጡ ዝንቦችን ሊያመለክት ይችላል። አንዳንድ ተናካሽ ዝንቦች በዕጭነታቸው ወቅት በእንስሳትና በሰዎች አካል ውስጥ ጥገኛ ተሕዋስያን ሆነው ይኖራሉ፤ ሰዎችን የሚያጠቁት የዝንብ ዓይነቶች የሚኖሩት በሞቃታማ አካባቢዎች ነው። በመሆኑም የተናካሽ ዝንቦች መቅሰፍት በግብፃውያንና በከብቶቻቸው ላይ ከባድ ሥቃይ አልፎ ተርፎም ሞት አስከትሎ መሆን አለበት።
(ዘፀአት 8:25-27) በመጨረሻም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ጠርቶ “ሂዱ፤ በምድሪቱም ለአምላካችሁ መሥዋዕት ሠዉ” አላቸው። 26 ሙሴ ግን እንዲህ አለው፦ “ይሄማ ተገቢ አይደለም፤ ምክንያቱም እኛ ለአምላካችን ለይሖዋ መሥዋዕት የምናደርገው ነገር ለግብፃውያን አስጸያፊ ነው። ታዲያ ግብፃውያን የሚጸየፉትን መሥዋዕት እዚያው እነሱ እያዩን ብናቀርብ አይወግሩንም? 27 ስለዚህ ወደ ምድረ በዳው የሦስት ቀን መንገድ እንጓዛለን፤ በዚያም አምላካችን ይሖዋ ባለን መሠረት ለእሱ መሥዋዕት እናቀርባለን።”
የዘፀአት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
8:26, 27—ሙሴ የእስራኤላውያን መሥዋዕት “በግብፃውያን ዘንድ አስጸያፊ” እንደሚሆን የተናገረው ለምንድን ነው? ግብፅ ውስጥ በርካታ እንስሳት ይመለኩ ነበር። በመሆኑም ሙሴ፣ እንስሳትን መሥዋዕት እንደሚያደርጉ መግለጹ ለይሖዋ ለመሠዋት እንዲሄዱ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝና አሳማኝ እንዲሆን ያደርገዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፀአት 8:1-19) ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ገብተህ እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 2 እነሱን ለመልቀቅ አሁንም ፈቃደኛ የማትሆን ከሆነ ምድርህን በሙሉ በእንቁራሪት መቅሰፍት እመታለሁ። 3 የአባይም ወንዝ በእንቁራሪቶች ይሞላል፤ እነሱም ወጥተው ወደ ቤትህ፣ ወደ መኝታ ክፍልህ ይገባሉ፤ አልጋህም ላይ ይወጣሉ፤ እንዲሁም ወደ አገልጋዮችህ ቤቶች ይገባሉ፤ ሕዝብህም ላይ ይወጣሉ፤ መጋገሪያ ምድጃዎችህና ቡሃቃዎችህም ውስጥ ይገባሉ። 4 እንቁራሪቶቹ በአንተ፣ በሕዝብህና በአገልጋዮችህ ሁሉ ላይ ይወጡባችኋል።”’” 5 በኋላም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አሮንን እንዲህ በለው፦ ‘እጅህን ሰንዝረህ ወንዞቹን፣ የአባይ ወንዝ የመስኖ ቦዮቹንና ረግረጋማ ቦታዎቹን በበትርህ በመምታት እንቁራሪቶቹ በግብፅ ምድር ላይ እንዲወጡ አድርግ።’” 6 ስለዚህ አሮን በግብፅ ውኃዎች ላይ እጁን ሰነዘረ፤ እንቁራሪቶቹም እየወጡ የግብፅን ምድር መውረር ጀመሩ። 7 ይሁን እንጂ አስማተኞቹ ካህናትም በሚስጥራዊ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር ፈጸሙ፤ እነሱም እንቁራሪቶች በግብፅ ምድር ላይ እንዲወጡ አደረጉ። 8 ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ጠርቶ “ሕዝቡ ለይሖዋ መሥዋዕት እንዲያቀርብ መልቀቅ ስለምፈልግ እንቁራሪቶቹን ከእኔም ሆነ ከሕዝቤ ላይ እንዲያስወግድ ይሖዋን ለምኑልኝ” አላቸው። 9 ከዚያም ሙሴ ፈርዖንን እንዲህ አለው፦ “እንቁራሪቶቹ ከአንተ፣ ከአገልጋዮችህ፣ ከሕዝብህና ከቤቶችህ ይወገዱ ዘንድ አምላክን እንድለምንልህ የምትፈልገው መቼ እንደሆነ የመወሰኑን ጉዳይ ለአንተ ትቼዋለሁ። እንቁራሪቶቹ በአባይ ወንዝ ውስጥ ብቻ ተወስነው ይቀራሉ።” 10 እሱም “ነገ ይሁን” አለው። በመሆኑም ሙሴ እንዲህ አለው፦ “እንደ አምላካችን እንደ ይሖዋ ያለ ማንም እንደሌለ እንድታውቅ ልክ እንዳልከው ይሆናል። 11 እንቁራሪቶቹ ከአንተ፣ ከቤቶችህ፣ ከአገልጋዮችህና ከሕዝቦችህ ይወገዳሉ። በአባይ ወንዝ ውስጥ ብቻ ተወስነው ይቀራሉ።” 12 ሙሴና አሮንም ከፈርዖን ፊት ወጥተው ሄዱ፤ ሙሴም ይሖዋ በፈርዖን ላይ ያመጣቸውን እንቁራሪቶች አስመልክቶ ወደ እሱ ጮኸ። 13 ይሖዋም ሙሴ እንደጠየቀው አደረገ፤ እንቁራሪቶቹም በየቤቱ፣ በየግቢውና በየሜዳው መሞት ጀመሩ። 14 እነሱም እንቁራሪቶቹን በየቦታው ከመሯቸው፤ ምድሪቱም መግማት ጀመረች። 15 ፈርዖንም ችግሩ ጋብ ማለቱን ባየ ጊዜ ልቡን አደነደነ፤ ልክ ይሖዋ እንደተናገረውም እነሱን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም። 16 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አሮንን እንዲህ በለው፦ ‘በትርህን ሰንዝረህ የምድርን አቧራ ምታ፤ አቧራውም በመላው የግብፅ ምድር ላይ ትንኝ ይሆናል።’” 17 እነሱም እንዲሁ አደረጉ። አሮን በእጁ የያዘውን በትር ሰንዝሮ የምድርን አቧራ መታ፤ ትንኞቹም ሰዉንም እንስሳውንም ወረሩ። በምድሪቱ ያለው አቧራ ሁሉ በመላው የግብፅ ምድር ላይ ትንኝ ሆነ። 18 አስማተኞቹ ካህናትም ተመሳሳይ ነገር ለመፈጸምና በሚስጥራዊ ጥበባቸው ትንኞች እንዲፈሉ ለማድረግ ሞከሩ፤ ሆኖም አልቻሉም። ትንኞቹ ሰዉንም እንስሳውንም ወርረው ነበር። 19 በመሆኑም አስማተኞቹ ካህናት ፈርዖንን “ይህ የአምላክ ጣት ነው!” አሉት። የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፤ ልክ ይሖዋ እንዳለውም እነሱን አልሰማቸውም።
ከሐምሌ 20-26
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 10–11
“ሙሴና አሮን ታላቅ ድፍረት አሳይተዋል”
(ዘፀአት 10:3-6) በመሆኑም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ገብተው እንዲህ አሉት፦ “የዕብራውያን አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ለመሆኑ ለእኔ ለመገዛት ፈቃደኛ የማትሆነው እስከ መቼ ነው? እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 4 አሁንም ሕዝቤን ለመልቀቅ ፈቃደኛ የማትሆን ከሆነ ግን በነገው ዕለት በግዛትህ ላይ አንበጦችን አመጣለሁ። 5 አንበጦቹም ምድሪቱን ይሸፍናሉ፤ መሬቱንም ማየት አይቻልም። እነሱም ከበረዶው ያመለጠውንና የቀረላችሁን ነገር ሁሉ ሙልጭ አድርገው ይበሉታል፤ በመስክ ላይ እየበቀሉ ያሉትን ዛፎቻችሁን በሙሉ ይበሏቸዋል። 6 አንበጦቹ አባቶችህና አያቶችህ በዚህች ምድር ላይ መኖር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ አይተውት በማያውቁት ሁኔታ ቤቶችህን፣ የአገልጋዮችህን ቤቶች ሁሉና የግብፅን ቤቶች ሁሉ ይሞላሉ።’” እሱም ይህን ከተናገረ በኋላ ፊቱን አዙሮ ከፈርዖን ፊት ወጥቶ ሄደ።
በድፍረት በመስበክ ኢየሱስን ምሰሉ
6 ሙሴ፣ ፈርዖንን ባነጋገረበት ወቅት ያሳየውን ድፍረትም እንመልከት፤ ራ የተባለው የፀሐይ አምላክ ልጅ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ የነበረው ፈርዖን የአማልክት ወኪል ሳይሆን እሱ ራሱ አምላክ እንደሆነ ይታሰብ ነበር። እንደ ሌሎች ፈርዖኖች ሁሉ ይህ ንጉሥም የራሱን ምስል ሳያመልክ አልቀረም። ፈርዖን፣ እሱ የተናገረው ነገር ሁሉ እንዲፈጸም የሚጠብቅ ፈላጭ ቆራጭ መሪ ነበር። ኃያል፣ እብሪተኛና ግትር የነበረው ፈርዖን የሚያደርገውን ነገር ሌሎች እንዲነግሩት አይፈልግም ነበር። በእረኝነት ሥራ የተሰማራውና ትሑት ሰው የነበረው ሙሴ ሳይጋበዝ እንዲሁም ፈርዖን ሊያየው እንደማይፈልግ እያወቀ በተደጋጋሚ ጊዜያት ይህን ንጉሥ ማነጋገር ነበረበት። ሙሴ የሚናገረው መልእክት ምን ነበር? በግብጽ ላይ አውዳሚ መቅሰፍቶች እንደሚመጡ መናገር ነበረበት። ንጉሡን የጠየቀውስ ምን ነበር? በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የፈርዖን ባሪያዎች አገሪቱን ለቅቀው ለመውጣት ፈቃድ እንዲሰጣቸው ፈልጎ ነበር! ታዲያ ሙሴ ይህን መልእክት ለመናገር ደፋር መሆን አስፈልጎት ነበር? ምንም ጥርጥር የለውም!—ዘኍ. 12:3፤ ዕብ. 11:27
(ዘፀአት 10:24-26) ከዚያም ፈርዖን ሙሴን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ሂዱ፣ ይሖዋን አገልግሉ። በጎቻችሁና ከብቶቻችሁ ብቻ እዚሁ ይቀራሉ። ልጆቻችሁም አብረዋችሁ መሄድ ይችላሉ።” 25 ሙሴ ግን እንዲህ አለው፦ “እንግዲያውስ ለመሥዋዕቶችና ለሚቃጠሉ መባዎች የሚሆኑትን እንስሳት አንተው ራስህ ትሰጠንና ለአምላካችን ለይሖዋ መሥዋዕት አድርገን እናቀርባቸዋለን። 26 ከብቶቻችንም አብረውን መሄድ አለባቸው። አምላካችንን ይሖዋን ስናመልክ ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹን መሥዋዕት አድርገን ስለምናቀርብ አንድም እንስሳ እዚህ መቅረት የለበትም፤ ደግሞም እኛ ራሳችን ለይሖዋ አምልኮ ምን መሥዋዕት ማቅረብ እንዳለብን የምናውቀው እዚያ ስንደርስ ነው።”
(ዘፀአት 10:28) ስለሆነም ፈርዖን “ከፊቴ ጥፋ! ዳግመኛ ፊቴን ለማየት እንዳትሞክር፤ ፊቴን የምታይበት ቀን መሞቻህ እንደሚሆን እወቅ” አለው።
(ዘፀአት 11:4-8) ሙሴም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እኩለ ሌሊት ገደማ በግብፅ መሃል እወጣለሁ፤ 5 በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን የበኩር ልጅ አንስቶ የወፍጮ መጅ እስከምትገፋው ባሪያ የበኩር ልጅ ድረስ በግብፅ ምድር ያለ በኩር ሁሉ ይሞታል፤ የእንስሳም በኩር ሁሉ ይሞታል። 6 በመላው የግብፅ ምድርም ከዚያ በፊት በጭራሽ ሆኖ የማያውቅ ከዚያ በኋላም ፈጽሞ ዳግመኛ የማይከሰት ታላቅ ዋይታ ይሆናል። 7 ሆኖም ይሖዋ በግብፃውያንና በእስራኤላውያን መካከል ልዩነት ማድረግ እንደሚችል እንድታውቁ በእስራኤላውያን ላይ፣ በሰዎቹም ሆነ በእንስሶቻቸው ላይ ውሻ እንኳ አይጮኽም።’ 8 አገልጋዮችህም ሁሉ ወደ እኔ ወርደው ‘አንተም ሆንክ አንተን የሚከተሉ ሰዎች ሁሉ ከዚህ ሂዱልን’ በማለት ይሰግዱልኛል። ከዚያ በኋላም እወጣለሁ።” ሙሴም ይህን ተናግሮ በታላቅ ቁጣ ከፈርዖን ፊት ወጣ።
it-2 436 አን. 4
ሙሴ
በፈርዖን ፊት ለመቅረብ ድፍረት እና እምነት አስፈልጎታል። ሙሴና አሮን የተሰጣቸውን ተልእኮ መወጣት የቻሉት የይሖዋ እገዛና በእነሱ ላይ ይሠራ የነበረው የመንፈሱ እርዳታ ስላልተለያቸው ብቻ ነው። በወቅቱ የነበረው የዓለም ኃያል መንግሥት ንጉሥ የሆነውን የፈርዖንን ቤተ መንግሥት በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክር። ቤተ መንግሥቱ ግርማ ሞገስ የተላበሰ ነበር፤ አምላክ እንደሆነ የሚታመነው ትዕቢተኛው ፈርዖን በአማካሪዎቹ፣ በጦር አዛዦቹ፣ በጠባቂዎቹና በባሪያዎቹ ተከቧል። ከዚህም ሌላ የሙሴ ዋነኛ ተቃዋሚዎች የሆኑት የሃይማኖት መሪዎች ማለትም አስማተኞቹ ካህናት በዚያ አሉ። እነዚህ ሰዎች ከፈርዖን ቀጥሎ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ነበሩ። እነዚህ ሁሉ ኃያላን ሰዎች ከፈርዖን ጎን ተሰልፈው የግብፅን አማልክት ይደግፉ ነበር። ደግሞም ሙሴና አሮን ፈርዖን ፊት የቀረቡት አንዴ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ነበር፤ ፈርዖን ደግሞ ብዙ ሥራ የሚያከናውኑለትን ዕብራውያን ባሪያዎቹን ላለማጣት ቆርጦ ስለነበር ልቡ እየደነደነ ሄዶ ነበር። እንዲያውም ሙሴና አሮን የስምንተኛውን መቅሰፍት መምጣት ከተናገሩ በኋላ ከፈርዖን ፊት እንዲወጡ ተደርገዋል፤ ከዘጠነኛው መቅሰፍት በኋላ ደግሞ መሞት ካልፈለጉ በቀር ዳግመኛ የፈርዖንን ፊት ለማየት እንዳይሞክሩ ታዘው ነበር።—ዘፀ 10:11, 28
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 10:1, 2) ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ግባ፤ ምክንያቱም የእሱም ሆነ የአገልጋዮቹ ልብ እንዲደነድን እፈቅዳለሁ፤ ይህን የማደርገውም እነዚህን ተአምራዊ ምልክቶቼን በፊቱ እንዳሳይ 2 እንዲሁም ግብፅን እንዴት አድርጌ እንደቀጣሁና በመካከላቸው ተአምራዊ ምልክቶቼን እንዴት እንዳሳየሁ ለልጆችህና ለልጅ ልጆችህ እንድታውጅ ነው፤ እናንተም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ በእርግጥ ታውቃላችሁ።”
በሐሰተኛ አማልክት ላይ የተነሡ ምሥክሮች
11 እስራኤላውያን በግብፅ ውስጥ ሳሉ ይሖዋ ሙሴን ወደ ፈርዖን ላከውና “እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት ] እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በግብፃውያን ያደረግሁትን ነገር ያደረግሁባቸውንም ተአምራቴን በልጅህ በልጅ ልጅህም ጆሮች ትነግር ዘንድ፣ ይህችንም ተአምራቴን በመካከላቸው አደርግ ዘንድ የእርሱን የባሪያዎቹንም ልብ አደንድኜአለሁና ወደ ፈርዖን ግባ አለው።” (ዘጸአት 10:1, 2) ታዛዥ እስራኤላውያን የይሖዋን ድንቅ ሥራዎች ለልጆቻቸው ይናገራሉ። ልጆቻቸው በተራቸው ደግሞ ለልጆቻቸው ይናገራሉ፣ እንዲህ እንዲህ እያለም ትውልድ ለትውልድ የይሖዋን ተአምራት ይናገራል። በዚህ መንገድ የይሖዋ ተአምራቶች ሲታወሱ ይኖራሉ። ዛሬም ቢሆን ወላጆች ለልጆቻቸው የመመሥከር ግዴታ አለባቸው።—ዘዳግም 6:4–7፤ ምሳሌ 22:6
(ዘፀአት 11:7) ሆኖም ይሖዋ በግብፃውያንና በእስራኤላውያን መካከል ልዩነት ማድረግ እንደሚችል እንድታውቁ በእስራኤላውያን ላይ፣ በሰዎቹም ሆነ በእንስሶቻቸው ላይ ውሻ እንኳ አይጮኽም።’
it-1 783 አን. 5
ዘፀአት
ይሖዋ ኃይሉን አስደናቂ በሆነ መንገድ በማሳየት ስሙን ከፍ ከፍ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ እስራኤላውያንን ነፃ አወጣቸው። ከጥፋት ተርፈው በቀይ ባሕር ምሥራቃዊ ዳርቻ ከደረሱ በኋላ ሙሴና እስራኤላውያን መዝሙር ዘመሩ፤ የሙሴ እህት የሆነችው ነቢይቱ ሚርያም ደግሞ አታሞ አንስታ ከወንዶቹ ጋር እየተቀባበለች ዘመረች፤ ሴቶቹም ሁሉ አታሞ እየመቱና እየጨፈሩ ተከተሏት። (ዘፀ 15:1, 20, 21) ጠላቶቻቸው ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን ላይ ሊደርሱባቸው አይችሉም። እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡበት ወቅት ሰውም ሆነ እንስሳ ጉዳት እንዲያደርስባቸው አልተፈቀደም፤ ውሻ እንኳ አልጮኸባቸውም ወይም ምላሱን አላሾለባቸውም። (ዘፀ 11:7) የዘፀአት ዘገባ ፈርዖን ከሠራዊቱ ጋር ወደ ባሕሩ ገብቶ እንደጠፋ ባይናገርም መዝሙር 136:15 ይሖዋ “ፈርዖንንና ሠራዊቱን ቀይ ባሕር ውስጥ” እንደወረወረ ይናገራል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፀአት 10:1-15) ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ግባ፤ ምክንያቱም የእሱም ሆነ የአገልጋዮቹ ልብ እንዲደነድን እፈቅዳለሁ፤ ይህን የማደርገውም እነዚህን ተአምራዊ ምልክቶቼን በፊቱ እንዳሳይ 2 እንዲሁም ግብፅን እንዴት አድርጌ እንደቀጣሁና በመካከላቸው ተአምራዊ ምልክቶቼን እንዴት እንዳሳየሁ ለልጆችህና ለልጅ ልጆችህ እንድታውጅ ነው፤ እናንተም እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ በእርግጥ ታውቃላችሁ።” 3 በመሆኑም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ገብተው እንዲህ አሉት፦ “የዕብራውያን አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘ለመሆኑ ለእኔ ለመገዛት ፈቃደኛ የማትሆነው እስከ መቼ ነው? እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 4 አሁንም ሕዝቤን ለመልቀቅ ፈቃደኛ የማትሆን ከሆነ ግን በነገው ዕለት በግዛትህ ላይ አንበጦችን አመጣለሁ። 5 አንበጦቹም ምድሪቱን ይሸፍናሉ፤ መሬቱንም ማየት አይቻልም። እነሱም ከበረዶው ያመለጠውንና የቀረላችሁን ነገር ሁሉ ሙልጭ አድርገው ይበሉታል፤ በመስክ ላይ እየበቀሉ ያሉትን ዛፎቻችሁን በሙሉ ይበሏቸዋል። 6 አንበጦቹ አባቶችህና አያቶችህ በዚህች ምድር ላይ መኖር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ አይተውት በማያውቁት ሁኔታ ቤቶችህን፣ የአገልጋዮችህን ቤቶች ሁሉና የግብፅን ቤቶች ሁሉ ይሞላሉ።’” እሱም ይህን ከተናገረ በኋላ ፊቱን አዙሮ ከፈርዖን ፊት ወጥቶ ሄደ። 7 ከዚያም የፈርዖን አገልጋዮች ፈርዖንን እንዲህ አሉት፦ “ይህ ሰው ወጥመድ የሚሆንብን እስከ መቼ ነው? አምላካቸውን ይሖዋን እንዲያገለግሉ ሰዎቹን ልቀቃቸው። ግብፅ እየጠፋች እንደሆነ እስካሁን አልተገነዘብክም?” 8 በመሆኑም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ተመልሰው እንዲመጡ ተደረገ፤ እሱም “ሂዱ፤ አምላካችሁን ይሖዋን አገልግሉ። ይሁንና የሚሄዱት እነማን ናቸው?” አላቸው። 9 በዚህ ጊዜ ሙሴ “ለይሖዋ የምናከብረው በዓል ስላለን ወጣቶቻችንን፣ አዛውንቶቻችንን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንን እንዲሁም በጎቻችንንና ከብቶቻችንን ይዘን እንሄዳለን” አለ። 10 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተንና ልጆቻችሁን ከለቀኩማ በእርግጥም ይሖዋ ከእናንተ ጋር ነው! መቼም የሆነ ተንኮል እንዳሰባችሁ ግልጽ ነው። 11 ይሄማ አይሆንም! ወንዶቹ ብቻ ሄደው ይሖዋን ያገልግሉ፤ ምክንያቱም የጠየቃችሁት ይህንኑ ነው።” ከዚያም ከፈርዖን ፊት እንዲወጡ ተደረገ። 12 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንበጦች መጥተው የግብፅን ምድር እንዲወሩና ከበረዶ የተረፈውን በምድሩ ላይ ያለውን ማንኛውንም ተክል ጠራርገው እንዲበሉ በግብፅ ምድር ላይ እጅህን ዘርጋ።” 13 ሙሴም ወዲያው በግብፅ ምድር ላይ በትሩን ሰነዘረ፤ ይሖዋም በዚያን ዕለት ቀኑንና ሌሊቱን ሙሉ በምድሩ ላይ የምሥራቅ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ። ሲነጋም የምሥራቁ ነፋስ አንበጦችን አመጣ። 14 አንበጦቹም በመላው የግብፅ ምድር ላይ መውጣትና በግብፅ ግዛት ሁሉ ላይ መስፈር ጀመሩ። ሁኔታው እጅግ አስከፊ ነበር፤ ከዚህ በፊት ያን ያህል ብዛት ያለው አንበጣ ታይቶ አያውቅም፤ ዳግመኛም ያን ያህል ብዛት ያለው አንበጣ ፈጽሞ አይከሰትም። 15 አንበጦቹም መላውን ምድር ሸፈኑት፤ ምድሪቱም በእነሱ የተነሳ ጨለመች፤ እነሱም ከበረዶው የተረፈውን በምድሩ ላይ ያለውን ተክል ሁሉ እንዲሁም በዛፎች ላይ ያለውን ፍሬ ሁሉ ጠራርገው በሉት፤ በመላው የግብፅ ምድር በዛፎችም ሆነ በመስክ ባሉ ተክሎች ላይ አንድም ለምለም ቅጠል አልተረፈም።
ከሐምሌ 27–ነሐሴ 2
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 12
“ፋሲካ ለክርስቲያኖች ምን ትርጉም አለው?”
(ዘፀአት 12:5-7) የምትመርጡት በግ እንከን የሌለበት፣ ተባዕትና አንድ ዓመት የሞላው መሆን ይኖርበታል። ከበግ ጠቦቶች ወይም ከፍየሎች መካከል መምረጥ ትችላላችሁ። 6 እስከዚህ ወር 14ኛ ቀን ድረስ እየተንከባከባችሁ አቆዩት፤ መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ጉባኤም አመሻሹ ላይ ይረደው። 7 ከደሙም ወስደው በጉን በሚበሉበት ቤት በር በሁለቱ መቃኖችና በጉበኑ ላይ ይርጩት።
‘ደስታህ ፍጹም ይሆናል’
4 ኢየሱስ ኒሳን 14, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሞተ። በእስራኤል፣ ኒሳን 14 የማለፍ በዓል የሚከበርበት አስደሳች ዕለት ነበር። በየዓመቱ፣ በዚህ ቀን ቤተሰቦች አንድ ላይ ሆነው ንጹሕ የሆነን አንድ ጠቦት ጨምሮ የተለያዩ ምግቦችን ይመገቡ ነበር። ይህም ኒሳን 14, 1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት አንድ መልአክ የግብጻውያንን በኩር በገደለበትና የእስራኤላውያን በኩሮች ደግሞ በዳኑበት ጊዜ የጠቦቱ ደም የነበረውን ሚና ለማስታወስ ያስችላቸዋል። (ዘፀአት 12:1-14) ሐዋርያው ጳውሎስ “የፋሲካ በጋችን የሆነው ክርስቶስ ተሠውቶአል” በማለት የማለፍ በግ ለኢየሱስ ጥላ ሆኖ ማገልገሉን ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 5:7) የፈሰሰው የኢየሱስ ደም እንደ ማለፍ በግ ደም ለብዙ ሰዎች መዳን አስገኝቷል።—ዮሐንስ 3:16, 36
(ዘፀአት 12:12, 13) ምክንያቱም በዚህ ሌሊት በግብፅ ምድር አልፋለሁ፤ ከሰው አንስቶ እስከ እንስሳ ድረስ በግብፅ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ እመታለሁ፤ በግብፅ አማልክት ሁሉ ላይም የፍርድ እርምጃ እወስዳለሁ። እኔ ይሖዋ ነኝ። 13 ደሙም እናንተ ያላችሁበትን ቤት የሚጠቁም ምልክት ሆኖ ያገለግላል፤ እኔም ደሙን ሳይ እናንተን አልፌ እሄዳለሁ፤ የግብፅን ምድር በምመታበት ጊዜ መቅሰፍቱ መጥቶ እናንተን አያጠፋም።
it-2 583 አን. 6
ፋሲካ
የፋሲካ በዓል አንዳንድ ገጽታዎች በኢየሱስ ላይ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ከእነዚህ ገጽታዎች መካከል አንዱ በግብፅ በነበሩት ቤቶች ላይ የተቀባው ደም፣ የበኩር ልጆች በአጥፊው መልአክ ከመጥፋት እንዲድኑ ያደርግ የነበረ መሆኑ ነው። ጳውሎስ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የበኩራት ጉባኤ እንደሆኑ (ዕብ 12:23)፣ ክርስቶስ ደግሞ በደሙ አማካኝነት እንዳዳናቸው ገልጿል። (1ተሰ 1:10፤ ኤፌ 1:7) ከፋሲካው በግ አጥንቶች መካከል አንዱም አይሰበርም ነበር። ከኢየሱስ አጥንቶች መካከልም አንዳቸውም ቢሆኑ እንደማይሰበሩ በትንቢት ተነግሯል፤ ይህም በሞተበት ወቅት ፍጻሜውን አግኝቷል። (መዝ 34:20፤ ዮሐ 19:36) በመሆኑም አይሁዳውያን በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሲያከብሩት የቆዩት የፋሲካ በዓል ወደፊት ለሚመጡት ነገሮች ጥላ ከሆኑና “የአምላክ በግ” በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ፍጻሜያቸውን ካገኙ የሕጉ ገጽታዎች መካከል አንዱ ነው።—ዕብ 10:1፤ ዮሐ 1:29
(ዘፀአት 12:24-27) “እናንተም ይህን ነገር ለእናንተና ለልጆቻችሁ ዘላቂ ሥርዓት አድርጋችሁ አክብሩት። 25 ልክ ይሖዋ በተናገረው መሠረትም ወደሚሰጣችሁ ምድር በምትገቡበት ጊዜ ይህን በዓል አክብሩ። 26 ልጆቻችሁ ‘ይህን በዓል የምታከብሩት ለምንድን ነው?’ ብለው ሲጠይቋችሁ 27 እንዲህ በሏቸው፦ ‘ግብፃውያንን በመቅሰፍት በመታበት ጊዜ በግብፅ ያሉትን የእስራኤላውያንን ቤቶች አልፎ በመሄድ ቤቶቻችንን ላተረፈልን ለይሖዋ የሚቀርብ የፋሲካ መሥዋዕት ነው።’” ከዚያም ሕዝቡ ተደፍቶ ሰገደ።
‘ይህ ለመታሰቢያ ይሁናችሁ’
13 አባቶች ለልጆቻቸው የበዓሉን ትርጉም ስለሚያስረዱ መጪዎቹ ትውልዶች አስፈላጊ ትምህርቶች እያገኙ ይሄዳሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ አገልጋዮቹን የመጠበቅ ችሎታ እንዳለው ይማራሉ። እስራኤላውያን ልጆች ስለ ይሖዋ ማወቅ አስቸጋሪ እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። ይሖዋ፣ ለሕዝቦቹ የሚያስብና እነሱን ለመታደግ እርምጃ የሚወስድ እውን እና ሕያው የሆነ አምላክ ነው። ይሖዋ “ግብፃውያንን በቀሠፈ ጊዜ” ለእስራኤላውያን በኩራት ጥበቃ በማድረግ እንዲህ ዓይነት አምላክ መሆኑን አሳይቷል። በዚህ ወቅት የእስራኤል በኩራት በሕይወት እንዲተርፉ አድርጓል።
14 ክርስቲያን ወላጆች፣ የአይሁዳውያን ፋሲካ ያለውን ትርጉም በየዓመቱ ለልጆቻቸው እንዲያስተምሩ አይጠበቅባቸውም። ይሁን እንጂ ወላጆች፣ ከበዓሉ የሚገኘውን ትምህርት ይኸውም አምላክ ሕዝቦቹን እንደሚጠብቅ ለልጆቻችሁ ታስተምሯቸዋላችሁ? ይሖዋ እውን እንደሆነና አሁንም ቢሆን ለሕዝቦቹ ጥበቃ እንደሚያደርግ ያላችሁን ጠንካራ እምነት ልጆቻችሁ በግልጽ ማየት ይችላሉ? (መዝ. 27:11፤ ኢሳ. 12:2) ለልጆቻችሁ ይህን ስታስተምሩ እናንተ ብቻ በመናገር ልጆቹ እንዲሰለቹ ከማድረግ ይልቅ ውይይቱ አስደሳች እንዲሆን ትጥራላችሁ? ከፋሲካ በዓል የሚገኙ ትምህርቶችን በመጠቀም ቤተሰባችሁ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ ለመርዳት ጥረት አድርጉ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 12:12) ምክንያቱም በዚህ ሌሊት በግብፅ ምድር አልፋለሁ፤ ከሰው አንስቶ እስከ እንስሳ ድረስ በግብፅ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ እመታለሁ፤ በግብፅ አማልክት ሁሉ ላይም የፍርድ እርምጃ እወስዳለሁ። እኔ ይሖዋ ነኝ።
it-2 582 አን. 2
ፋሲካ
በግብፅ ላይ የደረሱት አሥሩ መቅሰፍቶች፣ በተለይም የበኩር ልጆች የሞቱበት አሥረኛው መቅሰፍት በግብፅ አማልክት ላይ የተላለፈ ፍርድ ነበር። (ዘፀ 12:12) ተባዕት በግ፣ ራ ለተባለው አምላክ ቅዱስ ነበር፤ በመሆኑም የፋሲካ በግ ደም በበር ላይ መረጨቱ በግብፃውያን ዘንድ አምላክን እንደመሳደብ ይቆጠር ነበር። ኮርማም ቅዱስ ተደርጎ ይታይ ነበር፤ ከዚህ አንጻር የኮርማ በኩሮች መገደላቸው ኦሳይረስ ለተባለው አምላክ ትልቅ ውድቀት ነበር። ፈርዖን ራሱም ቢሆን የራ ልጅ እንደሆነ ተደርጎ ስለሚቆጠር እንደ ቅዱስ ይታይ ነበር። በመሆኑም የፈርዖን የበኩር ልጅ መሞቱ ራም ሆነ ፈርዖን አቅመ ቢስ እንደሆኑ ያሳያል።
(ዘፀአት 12:14-16) “‘ይህ ቀን ለእናንተ መታሰቢያ ይሆናል፤ እናንተም በመጪዎቹ ትውልዶቻችሁ ሁሉ የይሖዋ በዓል አድርጋችሁ አክብሩት። ይህን ዘላቂ ደንብ አድርጋችሁ አክብሩት። 15 ለሰባት ቀን ቂጣ ትበላላችሁ። አዎ፣ በመጀመሪያው ቀን ከቤታችሁ እርሾ አስወግዱ፤ ምክንያቱም ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ እስከ ሰባተኛው ቀን ድረስ እርሾ የገባበትን ነገር የሚበላ ማንኛውም ሰው ከእስራኤል መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረጋል። 16 በመጀመሪያው ቀን ቅዱስ ጉባኤ አድርጉ፤ በሰባተኛውም ቀን ሌላ ቅዱስ ጉባኤ አድርጉ። በእነዚህ ቀናት ምንም ዓይነት ሥራ መሠራት የለበትም። እያንዳንዱ ሰው የሚበላውን ነገር ከማዘጋጀት ውጭ ሌላ ምንም ነገር አትሥሩ።
it-1 504 አን. 1
ጉባኤ
የሁሉም “ቅዱስ ጉባኤዎች” አንዱ ለየት ያለ ገጽታ በእነዚህ ጉባኤዎች ወቅት ሰዎች የጉልበት ሥራ ማከናወን ያልነበረባቸው መሆኑ ነው። ለምሳሌ የቂጣ በዓል በሚከበርበት ወቅት በመጀመሪያውና በሰባተኛው ቀን “ቅዱስ ጉባኤ” ይደረግ ነበር፤ ይሖዋ ይህን ወቅት አስመልክቶ ሲናገር “በእነዚህ ቀናት ምንም ዓይነት ሥራ መሠራት የለበትም። እያንዳንዱ ሰው የሚበላውን ነገር ከማዘጋጀት ውጭ ሌላ ምንም ነገር አትሥሩ” ብሏል። (ዘፀ 12:15, 16) ሆኖም ካህናቱ ‘በቅዱስ ጉባኤዎች’ ወቅት ለይሖዋ መሥዋዕቶች ያቀርቡ ነበር (ዘሌ 23:37, 38)፤ ይህን ማድረጋቸው የዕለት ተዕለት ሥራ እንዳይሠራ የሚያዝዘውን ሕግ እንደመጣስ ተደርጎ እንደማይቆጠር ግልጽ ነው። እነዚህ ዝግጅቶች ሰዎች ሥራ ፈተው እንዲውሉ ለማድረግ ታስበው የተዘጋጁ አልነበሩም፤ ከዚህ ይልቅ ታላቅ መንፈሳዊ ጥቅም የሚያስገኙ ዝግጅቶች ነበሩ። በሳምንታዊው የሰንበት ቀን ሕዝቡ ለአምልኮና ለትምህርት አንድ ላይ ይሰበሰቡ ነበር። ከዚያም የአምላክ ቃል ሲነበብና ሲብራራ ያዳምጣሉ፤ ከጊዜ በኋላም በምኩራቦች ውስጥ እንዲህ ይደረግ ነበር። (ሥራ 15:21) በመሆኑም በሰንበት ቀንም ሆነ በሌሎቹ “ቅዱስ ጉባኤዎች” ወቅት ሕዝቡ የጉልበት ሥራ ባይሠሩም በጸሎት እንዲሁም ስለ ፈጣሪና ስለ ዓላማዎቹ በማሰላሰል ተጠምደው ይውሉ ነበር።—ስብሰባ የሚለውን ተመልከት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
(ዘፀአት 12:1-20) ይሖዋም ሙሴንና አሮንን በግብፅ ምድር እንዲህ አላቸው፦ 2 “ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሆንላችኋል። ከዓመቱም ወሮች የመጀመሪያው ይሆንላችኋል። 3 ለመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ እንዲህ ብላችሁ ንገሩ፦ ‘ይህ ወር በገባ በአሥረኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው ለአባቱ ቤት አንድ በግ ይኸውም ለአንድ ቤት አንድ በግ ይውሰድ። 4 ሆኖም ቤተሰቡ ለአንድ በግ የሚያንስ ከሆነ እነሱና የእነሱ የቅርብ ጎረቤቶች በጉን በየቤታቸው ባሉት ሰዎች ቁጥር ልክ ይከፋፈሉት። በምታሰሉበት ጊዜም እያንዳንዱ ሰው ከበጉ ምን ያህል እንደሚበላ ወስኑ። 5 የምትመርጡት በግ እንከን የሌለበት፣ ተባዕትና አንድ ዓመት የሞላው መሆን ይኖርበታል። ከበግ ጠቦቶች ወይም ከፍየሎች መካከል መምረጥ ትችላላችሁ። 6 እስከዚህ ወር 14ኛ ቀን ድረስ እየተንከባከባችሁ አቆዩት፤ መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ጉባኤም አመሻሹ ላይ ይረደው። 7 ከደሙም ወስደው በጉን በሚበሉበት ቤት በር በሁለቱ መቃኖችና በጉበኑ ላይ ይርጩት። 8 “‘ሥጋውንም በዚያው ሌሊት ይብሉት። ሥጋውን በእሳት ጠብሰው ከቂጣና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት። 9 የትኛውንም የሥጋውን ብልት ጥሬውን ወይም ቅቅሉን አትብሉ፤ ነገር ግን ጭንቅላቱን ከእግሩና ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት ጥበሱት። 10 እስከ ጠዋት ድረስ ምንም አታስተርፉ፤ ሳይበላ ያደረ ካለ ግን በእሳት አቃጥሉት። 11 የምትበሉትም ወገባችሁን ታጥቃችሁ፣ ጫማችሁን አድርጋችሁና በትራችሁን በእጃችሁ ይዛችሁ መሆን አለበት፤ በጥድፊያም ብሉት። ይህ የይሖዋ ፋሲካ ነው። 12 ምክንያቱም በዚህ ሌሊት በግብፅ ምድር አልፋለሁ፤ ከሰው አንስቶ እስከ እንስሳ ድረስ በግብፅ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ እመታለሁ፤ በግብፅ አማልክት ሁሉ ላይም የፍርድ እርምጃ እወስዳለሁ። እኔ ይሖዋ ነኝ። 13 ደሙም እናንተ ያላችሁበትን ቤት የሚጠቁም ምልክት ሆኖ ያገለግላል፤ እኔም ደሙን ሳይ እናንተን አልፌ እሄዳለሁ፤ የግብፅን ምድር በምመታበት ጊዜ መቅሰፍቱ መጥቶ እናንተን አያጠፋም። 14 “‘ይህ ቀን ለእናንተ መታሰቢያ ይሆናል፤ እናንተም በመጪዎቹ ትውልዶቻችሁ ሁሉ የይሖዋ በዓል አድርጋችሁ አክብሩት። ይህን ዘላቂ ደንብ አድርጋችሁ አክብሩት። 15 ለሰባት ቀን ቂጣ ትበላላችሁ። አዎ፣ በመጀመሪያው ቀን ከቤታችሁ እርሾ አስወግዱ፤ ምክንያቱም ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ እስከ ሰባተኛው ቀን ድረስ እርሾ የገባበትን ነገር የሚበላ ማንኛውም ሰው ከእስራኤል መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረጋል። 16 በመጀመሪያው ቀን ቅዱስ ጉባኤ አድርጉ፤ በሰባተኛውም ቀን ሌላ ቅዱስ ጉባኤ አድርጉ። በእነዚህ ቀናት ምንም ዓይነት ሥራ መሠራት የለበትም። እያንዳንዱ ሰው የሚበላውን ነገር ከማዘጋጀት ውጭ ሌላ ምንም ነገር አትሥሩ። 17 “‘የቂጣን በዓል አክብሩ፤ ምክንያቱም በዚህ ቀን ሠራዊታችሁን ከግብፅ ምድር አወጣለሁ። እናንተም ይህን ዕለት በመጪዎቹ ትውልዶቻችሁ ሁሉ ዘላቂ ደንብ አድርጋችሁ አክብሩት። 18 በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም ከ14ኛው ቀን ምሽት አንስቶ እስከ ወሩ 21ኛ ቀን ምሽት ድረስ ቂጣ ትበላላችሁ። 19 ለሰባት ቀናት እርሾ የሚባል ነገር በቤታችሁ ውስጥ አይገኝ፤ ምክንያቱም እርሾ ያለበትን ነገር የሚበላ ማንኛውም ሰው የባዕድ አገር ሰውም ሆነ የአገሩ ተወላጅ፣ ያ ሰው ከእስራኤል ማኅበረሰብ መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ ይደረጋል። 20 እርሾ ያለበት ምንም ነገር አትብሉ። በቤታችሁ ሁሉ ቂጣ ብሉ።’”