የዮሐንስ የመጀመሪያው ደብዳቤ
5 ኢየሱስ በእርግጥ ክርስቶስ እንደሆነ የሚያምን ሁሉ ከአምላክ ተወልዷል፤+ አባቱን የሚወድ ሁሉ ደግሞ ከእሱ የተወለደውንም ይወዳል። 2 አምላክን ስንወድና ትእዛዛቱን ስንፈጽም የአምላክን ልጆች+ እንደምንወድ በዚህ እናውቃለን። 3 አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤+ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባድ አይደሉም፤+ 4 ምክንያቱም ከአምላክ የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል።+ ዓለምን ድል እንድናደርግ ያስቻለን እምነታችን ነው።+
5 ዓለምን ሊያሸንፍ የሚችል ማን ነው?+ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ የሚያምን ሰው አይደለም?+ 6 በውኃና በደም አማካኝነት የመጣው፣ እሱ ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ የመጣውም ከውኃ ጋር ብቻ ሳይሆን+ ከውኃና ከደም ጋር ነው።+ ምሥክርነት የሚሰጠውም መንፈስ ነው፤+ ምክንያቱም መንፈስ እውነት ነው። 7 ምሥክርነት የሚሰጡ ሦስት ነገሮች አሉ፦ 8 እነሱም መንፈሱ፣+ ውኃውና+ ደሙ+ ናቸው፤ እነዚህ ሦስቱ ደግሞ ይስማማሉ።
9 ሰዎች የሚሰጡትን ምሥክርነት ከተቀበልን አምላክ የሚሰጠው ምሥክርነት ደግሞ ከዚያ የላቀ ነው። ምክንያቱም አምላክ የሰጠው ምሥክርነት ስለ ልጁ የሰጠው የምሥክርነት ቃል ነው። 10 በአምላክ ልጅ የሚያምን የምሥክርነቱ ቃል በልቡ አለው። በአምላክ የማያምን ግን አምላክ ስለ ልጁ የሰጠውን ምሥክርነት ስላላመነ እሱን ውሸታም አድርጎታል።+ 11 ምሥክርነቱም ይህ ነው፤ አምላክ የዘላለም ሕይወት ሰጠን፤+ ይህም ሕይወት የተገኘው በልጁ ነው።+ 12 ልጁ ያለው ይህ ሕይወት አለው፤ የአምላክ ልጅ የሌለው ይህ ሕይወት የለውም።+
13 እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ በአምላክ ልጅ ስም የምታምኑት+ እናንተ የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ እንድታውቁ ነው።+ 14 በእሱ ላይ ያለን ትምክህት* ይህ ነው፤+ የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል።+ 15 የምንጠይቀውንም ነገር ሁሉ እንደሚሰማን ስለምናውቅ የምንጠይቀውን ነገር እንደምናገኝ እርግጠኞች ነን።+
16 ማንም ሰው ወንድሙ ለሞት የማያበቃ ኃጢአት ሲሠራ ቢያየው ስለ እሱ ይለምናል፤ አምላክም ሕይወት ይሰጠዋል።+ ይህ የሚሆነው ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት ላልሠሩ ሰዎች ነው። ይሁን እንጂ ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት አለ።+ እንዲህ ዓይነት ኃጢአት ለሠራ ግለሰብ ማንም ሰው ይጸልይ አልልም። 17 ጽድቅ ያልሆነ ነገር ሁሉ ኃጢአት ነው፤+ ይሁንና ለሞት የማያበቃ ኃጢአት አለ።
18 ከአምላክ የተወለደ ሁሉ በኃጢአት ጎዳና እንደማይመላለስ እናውቃለን፤ ይልቁንም ከአምላክ የተወለደው* ይጠብቀዋል፤ ክፉውም* ምንም ሊያደርገው አይችልም።+ 19 እኛ ከአምላክ ወገን መሆናችንን እናውቃለን፤ መላው ዓለም ግን በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው።+ 20 ይሁንና የአምላክ ልጅ እንደመጣ እናውቃለን፤+ እሱም ስለ እውነተኛው አምላክ እውቀት ማግኘት እንድንችል ማስተዋል* ሰጥቶናል። እኛም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ከእሱ ጋር አንድነት አለን።+ አዎ፣ እሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።+ 21 ልጆቼ ሆይ፣ ከጣዖቶች ራቁ።+