ዘፍጥረት
24 አብርሃምም አረጀ፤ ዕድሜውም ገፋ፤ ይሖዋም አብርሃምን በሁሉ ነገር ባረከው።+ 2 አብርሃም ንብረቱን በሙሉ የሚያስተዳድርለትንና በቤቱ ውስጥ ካሉት አገልጋዮች ሁሉ አንጋፋ የሆነውን አገልጋዩን+ እንዲህ አለው፦ “እባክህ እጅህን ከጭኔ ሥር አድርግ፤ 3 በመካከላቸው ከምኖረው ከከነአናውያን ሴቶች ልጆች ለልጄ ሚስት እንዳታመጣለት የሰማይና የምድር አምላክ በሆነው በይሖዋ አስምልሃለሁ።+ 4 ከዚህ ይልቅ ወደ አገሬና ወደ ዘመዶቼ+ ሄደህ ለልጄ ለይስሐቅ ሚስት አምጣለት።”
5 ይሁንና አገልጋዩ “ሴቲቱ ከእኔ ጋር ወደዚህ ምድር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆንስ? ልጅህን አንተ ወደመጣህበት አገር+ መመለስ ይኖርብኛል?” አለው። 6 በዚህ ጊዜ አብርሃም እንዲህ አለው፦ “ልጄን ወደዚያ እንዳትወስደው ተጠንቀቅ።+ 7 ከአባቴ ቤትና ከዘመዶቼ አገር ያወጣኝ+ እንዲሁም ‘ይህን ምድር+ ለዘርህ+ እሰጣለሁ’ ብሎ የነገረኝና የማለልኝ+ የሰማይ አምላክ ይሖዋ መልአኩን ከፊትህ ይልካል፤+ አንተም ከዚያ አገር+ ለልጄ ሚስት ታመጣለታለህ። 8 ሆኖም ሴቲቱ ከአንተ ጋር ለመምጣት ፈቃደኛ ሳትሆን ብትቀር ከዚህ መሐላ ነፃ ትሆናለህ። ልጄን ግን በምንም ዓይነት ወደዚያ እንዳትወስደው።” 9 ከዚያም አገልጋዩ እጁን ከጌታው ከአብርሃም ጭን ሥር አደረገ፤ ስለዚህ ጉዳይም ማለለት።+
10 በመሆኑም አገልጋዩ ከጌታው ግመሎች መካከል አሥሩን ወሰደ፤ ከጌታውም ንብረት ምርጥ ምርጡን ሁሉ ይዞ ተነሳ። ከዚያም ወደ ሜሶጶጣሚያ፣ ወደ ናኮር ከተማ ጉዞ ጀመረ። 11 ከከተማዋ ውጭ ባለ አንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብም ግመሎቹን አንበረከከ። ጊዜውም ወደ ማምሻው አካባቢ ነበር፤ ይህ ጊዜ ደግሞ ሴቶች ውኃ ለመቅዳት የሚወጡበት ነው። 12 ከዚያም እንዲህ አለ፦ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ ይሖዋ፣ እባክህ በዚህ ዕለት ጉዳዬን አሳካልኝ፤ ለጌታዬ ለአብርሃምም ታማኝ ፍቅርህን አሳየው። 13 ይኸው እኔ እዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማዋ ሴቶች ልጆች ውኃ ለመቅዳት እየመጡ ነው። 14 እንግዲህ ‘እባክሽ፣ ውኃ እንድጠጣ እንስራሽን አውርጂልኝ’ ስላት ‘እንካ ጠጣ፤ ግመሎችህንም አጠጣልሃለሁ’ የምትለኝ ወጣት ለአገልጋይህ ለይስሐቅ የመረጥካት ትሁን፤ እንዲህ ካደረግክልኝ ለጌታዬ ታማኝ ፍቅር እንዳሳየኸው አውቃለሁ።”
15 እሱም ገና ንግግሩን ሳይጨርስ የባቱኤል+ ልጅ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ተሸክማ ብቅ አለች፤ ባቱኤል የአብርሃም ወንድም የናኮር+ ሚስት ሚልካ+ የወለደችው ነው። 16 ወጣቷም በጣም ቆንጆና ከወንድ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጽማ የማታውቅ ድንግል ነበረች። እሷም ወደ ምንጩ ወርዳ በእንስራዋ ውኃ ሞልታ ተመለሰች። 17 አገልጋዩም ወዲያውኑ ወደ እሷ ሮጦ በመሄድ “እባክሽ ከእንስራሽ ውኃ ልጎንጭ” አላት። 18 እሷም መልሳ “ጌታዬ ጠጣ” አለችው። ከዚያም ፈጠን ብላ እንስራዋን ወደ እጇ በማውረድ የሚጠጣው ውኃ ሰጠችው። 19 ለእሱ ሰጥታው ከጠጣ በኋላ “ግመሎችህም ጠጥተው እስኪጠግቡ ድረስ ውኃ እቀዳላቸዋለሁ” አለችው። 20 በእንስራዋ ውስጥ የነበረውን ውኃም በፍጥነት ገንዳ ውስጥ ገለበጠች፤ ከዚያም በሩጫ እየተመላለሰች ከጉድጓዱ ውኃ ትቀዳ ጀመር፤ ለግመሎቹም ሁሉ ቀዳች። 21 ይህ ሁሉ ሲሆን ሰውየው ይሖዋ ጉዞውን አሳክቶለት እንደሆነና እንዳልሆነ በማሰብ ዝም ብሎ በመገረም ይመለከታት ነበር።
22 ግመሎቹም ጠጥተው ሲጨርሱ ሰውየው ግማሽ ሰቅል* የሚመዝን የወርቅ የአፍንጫ ቀለበት እንዲሁም አሥር ሰቅል* የሚመዝኑ ሁለት የወርቅ አምባሮች አውጥቶ ሰጣት፤ 23 እንዲህም አላት፦ “እስቲ ንገሪኝ፣ ለመሆኑ የማን ልጅ ነሽ? በአባትሽ ቤት የምናድርበት ቦታ ይኖር ይሆን?” 24 እሷም መልሳ “ሚልካ ለናኮር+ የወለደችለት የባቱኤል ልጅ ነኝ”+ አለችው። 25 አክላም “ገለባና ብዙ ገፈራ እንዲሁም ለማደሪያ የሚሆን ስፍራ አለን” አለችው። 26 በዚህ ጊዜ ሰውየው በይሖዋ ፊት ተደፍቶ ሰገደ፤ 27 እንዲህም አለ፦ “ለጌታዬ ታማኝ ፍቅሩንና ታማኝነቱን ያልነፈገው የጌታዬ የአብርሃም አምላክ ይወደስ። ይሖዋ ወደ ጌታዬ ወንድሞች ቤት መራኝ።”
28 ወጣቷም የሆነውን ሁሉ ለእናቷ ቤተሰቦች ለመንገር እየሮጠች ሄደች። 29 ርብቃ፣ ላባ+ የሚባል ወንድም ነበራት። ላባም ከከተማዋ ውጭ በምንጩ አጠገብ ወዳለው ሰው እየሮጠ ሄደ። 30 የአፍንጫ ቀለበቱንና አምባሮቹን በእህቱ እጆች ላይ ሲመለከት እንዲሁም እህቱ ርብቃ “ሰውየው እንዲህ እንዲህ አለኝ” ብላ ስትናገር ሲሰማ በምንጩ አጠገብ ከግመሎቹ ጋር ቆሞ የነበረውን ሰው ለማግኘት ወደ እሱ ሄደ። 31 እሱም ሰውየውን እንዳገኘው “አንተ ይሖዋ የባረከህ ሰው፣ ና እንጂ። ውጭ የቆምከው ለምንድን ነው? ቤቱን አዘጋጅቻለሁ፤ ለግመሎቹም ማደሪያ አለ” አለው። 32 ስለዚህ ሰውየው ወደ ቤት ገባ፤ እሱም* የግመሎቹን ጭነት አራገፈለት፤ ለግመሎቹም ገለባና ገፈራ ሰጣቸው። እንዲሁም ሰውየውና አብረውት የነበሩት ሰዎች እግራቸውን የሚታጠቡበት ውኃ አቀረበላቸው። 33 ሆኖም ሰውየው የሚበላ ነገር ሲቀርብለት “የመጣሁበትን ጉዳይ ሳልናገር እህል አልቀምስም” አለ። በመሆኑም ላባ “እሺ፣ ተናገር!” አለው።
34 እሱም እንዲህ አለ፦ “እኔ የአብርሃም አገልጋይ ነኝ።+ 35 ይሖዋ ጌታዬን እጅግ ባርኮታል፤ በጎች፣ ከብቶች፣ ብር፣ ወርቅ፣ ወንድና ሴት አገልጋዮች እንዲሁም ግመሎችና አህዮች በመስጠት በጣም አበልጽጎታል።+ 36 በተጨማሪም የጌታዬ ሚስት ሣራ በስተርጅናዋ ለጌታዬ ወንድ ልጅ ወልዳለታለች፤+ ጌታዬም ያለውን ሁሉ ለእሱ ይሰጠዋል።+ 37 በመሆኑም ጌታዬ እንዲህ በማለት አስማለኝ፦ ‘በአገራቸው ከምኖረው ከከነአናውያን ሴቶች ልጆች መካከል ለልጄ ሚስት እንዳታመጣለት።+ 38 ፈጽሞ እንዲህ እንዳታደርግ፤ ከዚህ ይልቅ ወደ አባቴ ቤትና ወደ ቤተሰቦቼ+ ሄደህ ለልጄ ሚስት አምጣለት።’+ 39 እኔ ግን ጌታዬን ‘ሴቲቱ ከእኔ ጋር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆንስ?’ አልኩት።+ 40 እሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘አካሄዴን በፊቱ ያደረግኩት+ ይሖዋ መልአኩን ከአንተ ጋር ይልካል፤+ ጉዞህን ያሳካልሃል፤ አንተም ከቤተሰቦቼና ከአባቴ ቤት+ ለልጄ ሚስት ታመጣለታለህ። 41 ወደ ቤተሰቦቼ ከሄድክና እነሱም ልጅቷን ለመስጠት ፈቃደኛ ካልሆኑ ከማልክልኝ መሐላ ነፃ ትሆናለህ። እንዲህ ካደረግክ ከመሐላህ ነፃ ትሆናለህ።’+
42 “እኔም ዛሬ ምንጩ አጠገብ ስደርስ እንዲህ አልኩ፦ ‘የጌታዬ የአብርሃም አምላክ ይሖዋ፣ ጉዞዬን የምታሳካልኝ ከሆነ 43 ይኸው እዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ ቆሜአለሁ። አንዲት ወጣት ሴት+ ውኃ ለመቅዳት ስትመጣ “እባክሽ፣ ከእንስራሽ ትንሽ ውኃ አጠጪኝ” እላታለሁ፤ 44 እሷም “አንተም ጠጣ፤ ለግመሎችህም እቀዳላቸዋለሁ” ካለችኝ ይህች ሴት ይሖዋ ለጌታዬ ልጅ የመረጣት ትሁን።’+
45 “እኔም ገና በልቤ ተናግሬ ሳልጨርስ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ተሸክማ ብቅ አለች፤ እሷም ወደ ምንጩ ወርዳ ውኃ ቀዳች። ከዚያም እኔ ‘እባክሽ፣ ውኃ አጠጪኝ’ አልኳት።+ 46 እሷም ፈጠን ብላ እንስራዋን ከትከሻዋ በማውረድ ‘ጠጣ፤+ ግመሎችህንም አጠጣልሃለሁ’ አለችኝ። እኔም ጠጣሁ፤ ግመሎቹንም አጠጣች። 47 ከዚያም ‘ለመሆኑ የማን ልጅ ነሽ?’ ስል ጠየቅኳት፤ እሷም ‘ሚልካ ለናኮር የወለደችለት የባቱኤል ልጅ ነኝ’ አለችኝ። ስለዚህ ቀለበቱን በአፍንጫዋ ላይ፣ አምባሮቹን ደግሞ በእጆቿ ላይ አደረግኩላት።+ 48 እኔም በይሖዋ ፊት ተደፍቼ ሰገድኩ፤ የጌታዬን ወንድም ሴት ልጅ ለጌታዬ ልጅ እንድወስድለት በትክክለኛው መንገድ የመራኝን የጌታዬን የአብርሃምን አምላክ ይሖዋን አወደስኩ።+ 49 እንግዲህ አሁን ለጌታዬ ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት ማሳየት የምትፈልጉ ከሆነ ንገሩኝ፤ ካልሆነ ግን ማድረግ ያለብኝን ነገር እንድወስን* ቁርጡን አሳውቁኝ።”+
50 ከዚያም ላባና ባቱኤል እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “ይህ ነገር ከይሖዋ የመጣ ነው። እኛ እሺም ሆነ እንቢ ልንልህ አንችልም።* 51 ርብቃ ይቻትልህ። ይዘሃት ሂድ፤ ልክ ይሖዋ እንደተናገረውም ለጌታህ ልጅ ሚስት ትሁን።” 52 የአብርሃም አገልጋይም ያሉትን ሲሰማ ወዲያውኑ በይሖዋ ፊት መሬት ላይ ተደፍቶ ሰገደ። 53 ከዚያም አገልጋዩ የብርና የወርቅ ጌጣጌጦችን እንዲሁም ልብሶችን እያወጣ ለርብቃ ይሰጣት ጀመር፤ ለወንድሟና ለእናቷም ውድ የሆኑ ዕቃዎችን ሰጣቸው። 54 ከዚህ በኋላ እሱና ከእሱ ጋር ያሉት ሰዎች በሉ፣ ጠጡም፤ እዚያም አደሩ።
እሱም ጠዋት ሲነሳ “በሉ እንግዲህ ወደ ጌታዬ እንድንሄድ አሰናብቱን” አላቸው። 55 በዚህ ጊዜ ወንድሟና እናቷ “ልጅቷ ከእኛ ጋር ቢያንስ ለአሥር ቀን ትቆይ። ከዚያ በኋላ መሄድ ትችላለች” አሉት። 56 እሱ ግን “ይሖዋ ጉዞዬን እንዳሳካልኝ እያያችሁ አታዘግዩኝ። ወደ ጌታዬ እንድሄድ አሰናብቱኝ” አላቸው። 57 እነሱም “ልጅቷን እንጥራና እንጠይቃት” አሉት። 58 ርብቃን ጠርተውም “ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽ?” አሏት። እሷም “አዎ፣ እሄዳለሁ” አለች።
59 ስለዚህ እህታቸውን ርብቃንና+ ሞግዚቷን*+ እንዲሁም የአብርሃምን አገልጋይና አብረውት የነበሩትን ሰዎች አሰናበቷቸው። 60 ርብቃንም “እህታችን ሆይ፣ ሺዎች ጊዜ አሥር ሺህ ሁኚ፤* ዘርሽም የጠላቶቹን በር* ይውረስ”+ ብለው መረቋት። 61 ከዚያም ርብቃና ሴት አገልጋዮቿ ተነሱ፤ በግመሎች ላይ ተቀምጠው ሰውየውን ተከተሉት። አገልጋዩም ርብቃን ይዞ ጉዞውን ቀጠለ።
62 ይስሐቅም በኔጌብ+ ምድር ይኖር ስለነበር ከብኤርላሃይሮዒ+ አቅጣጫ መጣ። 63 ይስሐቅም አመሻሹ ላይ ለማሰላሰል+ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር። ቀና ብሎ ሲመለከትም ግመሎች ሲመጡ አየ! 64 ርብቃም ቀና ብላ ስትመለከት ይስሐቅን አየችው፤ ከዚያም ከግመሉ ላይ በፍጥነት ወረደች። 65 አገልጋዩንም “ከእኛ ጋር ለመገናኘት ሜዳውን አቋርጦ የሚመጣው ያ ሰው ማን ነው?” ስትል ጠየቀችው። አገልጋዩም “ጌታዬ ነው” አላት። በመሆኑም ዓይነ ርግቧን ወስዳ ራሷን ሸፈነች። 66 አገልጋዩም ያደረገውን ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። 67 ከዚያም ይስሐቅ ርብቃን ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን ይዟት ገባ።+ በዚህ መንገድ ሚስቱ አድርጎ ወሰዳት፤ እሱም ወደዳት፤+ ከእናቱም ሞት ተጽናና።+