አንደኛ ሳሙኤል
25 ከጊዜ በኋላም ሳሙኤል+ ሞተ፤ እስራኤላውያንም በሙሉ ሊያለቅሱለትና በራማ+ በሚገኘው ቤቱ ሊቀብሩት ተሰበሰቡ። ከዚያም ዳዊት ተነስቶ ወደ ፋራን ምድረ በዳ ወረደ።
2 በማኦን+ የሚኖር እጅግ ባለጸጋ የሆነ አንድ ሰው ነበር። ይህ ሰው የሚሠራው በቀርሜሎስ*+ ሲሆን 3,000 በጎችና 1,000 ፍየሎች ነበሩት፤ በዚያን ወቅት በቀርሜሎስ በጎቹን እየሸለተ ነበር። 3 የሰውየው ስም ናባል፣+ የሚስቱ ስም ደግሞ አቢጋኤል+ ነበር። እሷም በጣም አስተዋይና ውብ ሴት ነበረች፤ ከካሌብ+ ወገን የሆነው ባሏ ግን ኃይለኛና ምግባረ ብልሹ ሰው ነበር።+ 4 ዳዊት በምድረ በዳ ሳለ ናባል በጎቹን እየሸለተ መሆኑን ሰማ። 5 ስለዚህ ዳዊት አሥር ወጣቶችን ወደ እሱ ላከ፤ ዳዊትም ወጣቶቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ቀርሜሎስ ወጥታችሁ ናባልን ስታገኙት በስሜ ስለ ደህንነቱ ጠይቁት። 6 ከዚያም ናባልን እንዲህ በሉት፦ ‘ረጅም ዕድሜና ጤና* እመኝልሃለሁ፤ ለመላ ቤተሰብህና የአንተ ለሆነው ሁሉ ሰላም ይሁን። 7 በጎችህን እየሸለትክ እንዳለህ ሰምቻለሁ። እረኞችህም ከእኛ ጋር በነበሩበት ጊዜ ምንም ዓይነት ጉዳት አላደረስንባቸውም፤+ በቀርሜሎስ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ ምንም ነገር አልጠፋባቸውም። 8 ወጣቶችህን ጠይቅ፤ ይነግሩሃል። እንግዲህ የመጣነው በደስታ* ቀን ስለሆነ ወጣቶቼ በፊትህ ሞገስ ያግኙ። እባክህ ለአገልጋዮችህና ለልጅህ ለዳዊት የቻልከውን ያህል ስጥ።’”+
9 በመሆኑም ዳዊት የላካቸው ወጣቶች ሄደው ይህን ሁሉ በዳዊት ስም ለናባል ነገሩት። ተናግረው እንዳበቁም 10 ናባል የዳዊትን አገልጋዮች እንዲህ አላቸው፦ “ለመሆኑ ዳዊት ማን ነው? ደግሞስ የእሴይ ልጅ ማን ነው? በአሁኑ ጊዜ እንደሆነ ከጌቶቻቸው የሚኮበልሉ+ አገልጋዮች ብዙ ናቸው። 11 ታዲያ ዳቦዬን፣ ውኃዬንና ለሚሸልቱልኝ ሰዎች ያረድኩትን ሥጋ ከየት እንደመጡ እንኳ ለማላውቃቸው ሰዎች መስጠት ይኖርብኛል?”
12 ዳዊት የላካቸው ወጣቶችም ወደመጡበት ተመልሰው በመሄድ የተባሉትን ሁሉ ነገሩት። 13 ዳዊትም ወዲያውኑ አብረውት ላሉት ሰዎች “በሉ ሁላችሁም ሰይፋችሁን ታጠቁ!”+ አላቸው። በመሆኑም ሁሉም ሰይፋቸውን ታጠቁ፤ ዳዊትም ሰይፉን ታጠቀ፤ ወደ 400 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ከዳዊት ጋር ሲወጡ 200ዎቹ ግን ጓዙን ለመጠበቅ እዚያው ቀሩ።
14 ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአገልጋዮቹ አንዱ ለናባል ሚስት ለአቢጋኤል እንዲህ አላት፦ “እነሆ፣ ዳዊት ለጌታችን መልካም ምኞቱን ለመግለጽ መልእክተኞችን ከምድረ በዳ ልኮ ነበር፤ እሱ ግን የስድብ ናዳ አወረደባቸው።+ 15 ሰዎቹ ለእኛ እጅግ ጥሩ ነበሩ። ምንም ዓይነት ጉዳት አድርሰውብን አያውቁም፤ በመስክ ከእነሱ ጋር አብረን በነበርንባቸው ጊዜያት ሁሉ አንድም ነገር ጠፍቶብን አያውቅም።+ 16 መንጋውን እየጠበቅን ከእነሱ ጋር በቆየንባቸው ጊዜያት ሁሉ ሌሊትም ሆነ ቀን በዙሪያችን እንደ መከላከያ ቅጥር ሆነውልን ነበር። 17 እንግዲህ አሁን በጌታችንና በቤቱ ሁሉ ላይ ጥፋት+ መምጣቱ ስለማይቀር ምን ማድረግ እንዳለብሽ ወስኚ፤ እሱ እንደሆነ የማይረባ*+ ሰው ስለሆነ ማንም ሊያናግረው አይችልም።”
18 ስለሆነም አቢጋኤል+ ወዲያውኑ 200 ዳቦ፣ ሁለት እንስራ የወይን ጠጅ፣ ታርደው የተሰናዱ አምስት በጎች፣ አምስት የሲህ መስፈሪያ* ቆሎ፣ 100 የዘቢብ ቂጣ እንዲሁም 200 የበለስ ጥፍጥፍ ወስዳ ሁሉንም በአህዮች ላይ ጫነች።+ 19 ከዚያም አገልጋዮቿን “ቀድማችሁኝ ሂዱ፤ እኔም እከተላችኋለሁ” አለቻቸው። ለባሏ ለናባል ግን ምንም አልነገረችውም።
20 አቢጋኤልም አህያ ላይ እንደተቀመጠች በተራራው ተከልላ እየወረደች ሳለ ዳዊትና ሰዎቹም ወደ እሷ እየወረዱ ነበር፤ እሷም አገኘቻቸው። 21 ዳዊትም እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በምድረ በዳ የዚህን ሰው ንብረት የጠበቅኩለት ለካስ እንዲያው በከንቱ ነበር። ደግሞም ከንብረቱ መካከል አንድም ነገር አልጠፋበትም፤+ እሱ ግን ደግ በሠራሁለት ክፉ መለሰልኝ።+ 22 የእሱ ከሆኑት ወንዶች* መካከል እስከ ነገ ጠዋት ድረስ አንድ ሰው እንኳ ባስቀር አምላክ በዳዊት ጠላቶች ላይ* ይህን ያድርግ፤ ከዚህ የከፋም ነገር ያምጣ።”
23 አቢጋኤልም ዳዊትን ባየችው ጊዜ፣ ከተቀመጠችበት አህያ ላይ በፍጥነት በመውረድ በዳዊት ፊት በግንባሯ ተደፍታ ሰገደች። 24 ከዚያም እግሩ ላይ ወድቃ እንዲህ አለችው፦ “ጌታዬ ሆይ፣ ጥፋቱ በእኔ ላይ ይሁን፤ እባክህ አገልጋይህ እንድታናግርህ ፍቀድላት፤ የአገልጋይህንም ቃል ስማ። 25 እባክህ ጌታዬ፣ ናባል የተባለውን ይህን የማይረባ+ ሰው ከቁብ አትቁጠረው፤ እሱ ልክ እንደ ስሙ ነውና። ስሙ ናባል* ነው፤ ደግሞም ማስተዋል የጎደለው ሰው ነው። እኔ አገልጋይህ ግን ጌታዬ የላካቸውን ወጣቶች አላየሁም። 26 እናም አሁን ጌታዬ፣ ሕያው በሆነው በይሖዋና በሕያውነትህ* እምላለሁ፣ በደም ዕዳ ተጠያቂ+ ከመሆንና በራስህ እጅ ከመበቀል* የጠበቀህ+ ይሖዋ ነው። አሁንም ጠላቶችህና ጌታዬን ሊጎዱ የሚፈልጉ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ። 27 ስለዚህ አገልጋይህ ለጌታዬ ያመጣችው ይህ ስጦታ*+ ጌታዬን ለሚከተሉት ወጣቶች+ ይሰጥ። 28 ጌታዬ እየተዋጋ ያለው የይሖዋን ጦርነት+ ስለሆነ ይሖዋ የጌታዬን ቤት ለዘለቄታው ያጸናለታል፤+ ስለሆነም እባክህ የአገልጋይህን መተላለፍ ይቅር በል፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህ።+ 29 ማንም ሰው አንተን ለማሳደድ ቢነሳና ሕይወትህን* ለማጥፋት ቢፈልግ የጌታዬ ሕይወት* በአምላክህ በይሖዋ ዘንድ በደንብ በታሰረ የሕይወት ከረጢት ውስጥ ትቀመጣለች፤ የጠላቶችህን ሕይወት* ግን ከወንጭፍ እንደሚወረወር ድንጋይ ይወነጭፈዋል። 30 ይሖዋ ቃል የገባለትን መልካም ነገር ሁሉ ለጌታዬ በሚፈጽምለትና በእስራኤል ላይ መሪ አድርጎ በሚሾመው+ ጊዜ 31 ጌታዬ ያለምክንያት ደም በማፍሰሱና እጁን ለበቀል በማንሳቱ* ልቡን የሚቆጨው ወይም የሚጸጽተው* ነገር አይኖርም።+ ይሖዋ ለጌታዬ መልካም ነገር በሚያደርግለት ጊዜ አገልጋይህን አስባት።”
32 በዚህ ጊዜ ዳዊት አቢጋኤልን እንዲህ አላት፦ “ዛሬ እኔን እንድታገኚኝ የላከሽ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ይወደስ! 33 ማስተዋልሽም የተባረከ ይሁን! በዚህ ዕለት በራሴ ላይ የደም ዕዳ እንዳላመጣና+ በገዛ እጄ እንዳልበቀል* ስለጠበቅሽኝ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ። 34 በአንቺ ላይ ጉዳት ከማድረስ በጠበቀኝ+ ሕያው በሆነው በእስራኤል አምላክ በይሖዋ እምላለሁ፣ እኔን ለማግኘት ፈጥነሽ ባትመጪ ኖሮ+ እስከ ነገ ጠዋት ድረስ የናባል የሆነ አንድም ወንድ* ባልተረፈ ነበር።”+ 35 ከዚያም ዳዊት ያመጣችለትን ነገር ከእጇ ተቀብሎ “ወደ ቤትሽ በሰላም ሂጂ። ይኸው ቃልሽን ሰምቻለሁ፤ የጠየቅሽኝንም እፈጽምልሻለሁ” አላት።
36 በኋላም አቢጋኤል በቤቱ እንደ ንጉሥ ግብዣ ያለ ታላቅ ግብዣ አዘጋጅቶ ወደነበረው ወደ ናባል ተመለሰች፤ ናባልም ልቡ በሐሴት ተሞልቶ በጣም ሰክሮ ነበር። እሷም እስኪነጋ ድረስ ምንም ነገር አልነገረችውም። 37 ጠዋት ላይ ናባል ስካሩ ሲበርድለት ሚስቱ የሆነውን ሁሉ ነገረችው። ልቡም እንደ ሞተ ሰው ልብ ሆነ፤ ሰውነቱም እንደ ድንጋይ በድን ሆነ። 38 ከአሥር ቀን ገደማ በኋላም ይሖዋ ናባልን ስለቀሰፈው ሞተ።
39 ዳዊት፣ ናባል መሞቱን ሲሰማ እንዲህ አለ፦ “ከናባል የደረሰብኝን ነቀፋ+ የተሟገተልኝና+ አገልጋዩን መጥፎ ድርጊት ከመፈጸም የጠበቀው+ ይሖዋ ይወደስ፤ ይሖዋ የናባልን ክፋት በራሱ ላይ መለሰው!” ከዚያም ዳዊት አቢጋኤል ሚስት እንድትሆነው ጥያቄ ለማቅረብ መልእክት ላከ። 40 በመሆኑም የዳዊት አገልጋዮች በቀርሜሎስ ወዳለችው ወደ አቢጋኤል መጥተው “ዳዊት ሊያገባሽ ስለፈለገ ወደ አንቺ ልኮናል” አሏት። 41 እሷም ወዲያውኑ ተነሳች፤ በግንባሯም ተደፍታ በመስገድ “ባሪያህ እንደ አገልጋይ በመሆን የጌታዬን አገልጋዮች እግር ለማጠብ+ ዝግጁ ነች” አለች። 42 ከዚያም አቢጋኤል+ ፈጥና ተነሳች፤ አምስት ሴት አገልጋዮቿንም በማስከተል በአህያ ላይ ተቀምጣ ጉዞ ጀመረች፤ ከዳዊት መልእክተኞችም ጋር አብራ ሄደች፤ የዳዊትም ሚስት ሆነች።
43 በተጨማሪም ዳዊት ከኢይዝራኤል+ አኪኖዓምን+ አግብቶ ነበር፤ ሁለቱም ሴቶች ሚስቶቹ ሆኑ።+
44 ሳኦል ግን የዳዊት ሚስት የነበረችውን ልጁን ሜልኮልን+ የጋሊም ሰው ለሆነው ለላይሽ ልጅ ለፓልጢ+ ድሯት ነበር።