በእምነታቸው ምሰሏቸው
አስተዋይነት የተንጸባረቀበት እርምጃ ወስዳለች
አቢግያን ባነጋገራት ወጣት ፊት ላይ ፍርሃት ይነበባል። ወጣቱ ብርክ ይዞታል፤ ካንዣበበው ከባድ አደጋ አንጻር የዚህን ያህል መረበሹ ምንም አያስገርምም። ይህ ወጣት አቢግያን እያነጋገራት ሳለ 400 የሚሆኑ ጦረኞች በአቢግያ ባል በናባል ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ ወንዶችን አንድም ሳያስቀሩ ለማጥፋት ቆርጠው በመነሳት ወደ ናባል ቤት እየገሰገሱ ነበር። ለምን?
ችግሩን የቆሰቆሰው ናባል ነበር። ወደ እሱ የመጡትን ሰዎች ያነጋገራቸው ጸያፍ በሆነና በሚያዋርድ መንገድ ነበር፤ ናባል እንዲህ ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በዚህ ወቅት ግን ትልቅ ስህተት ሠርቷል፤ ናባል የተሳደበው በሚገባ የሠለጠኑና ታማኝ የሆኑ ተዋጊዎች ያሉትን ተወዳጅ መሪ ነው። ከናባል ሠራተኞች፣ ምናልባትም ከእረኞቹ አንዱ ወደ አቢግያ የመጣው በዚህ ወቅት ነበር። ወጣቱ፣ አቢግያ እነሱን ለማዳን አንድ መላ እንደምትፈጥር ተስፋ አድርጎ ነበር። ይሁንና አንዲት ሴት እነዚህን ጦረኞች ለማስቆም ምን ማድረግ ትችላለች?
እስቲ በመጀመሪያ ስለዚህች አስደናቂ ሴት አንዳንድ ነገሮችን እንመልከት። ለመሆኑ አቢግያ ማን ነበረች? እንዲህ ያለ ችግር ሊፈጠር የቻለው እንዴት ነው? አቢግያ ካሳየችው እምነትስ ምን ትምህርት እናገኛለን?
“አስተዋይና ውብ”
ናባል፣ ለአቢግያ የሚመጥን ባል አልነበረም። እርግጥ ነው፣ ናባል እግሩ እስኪነቃ ቢዞር ከእሷ የተሻለች ሚስት ሊያገኝ አይችልም፤ አቢግያ ግን የገጠማት በጣም መጥፎ ሰው ነው። በእርግጥ ይህ ሰው ሀብታም ነበር። በዚህም የተነሳ ራሱን ከፍ አድርጎ ይመለከት ነበር፤ ይሁን እንጂ ሌሎች ለእሱ ምን አመለካከት ነበራቸው? ናባል ምን ያህል መጥፎ ሰው እንደነበረ ለመግለጽ የገቡት ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሌላ ለማንም አልተሰጡም ማለት ይቻላል። ስሙ ራሱ “ጅል” የሚል ፍቺ አለው። ይህ ስም ወላጆቹ ሲወለድ ያወጡለት መጠሪያ ይሆን? ወይስ ከጊዜ በኋላ የተሰጠው ቅጽል ስም? ያም ሆነ ይህ፣ ሰውየው እንደ ስሙ ነበር። ናባል “ባለጌና ምግባረ ብልሹ ሰው” ነበር። ጠበኛና ሰካራም የሆነውን ይህን ሰው ብዙዎች ይፈሩት እንዲሁም ይጠሉት ነበር።—1 ሳሙኤል 25:2, 3, 17, 21, 25
አቢግያ ግን ከባሏ ፈጽሞ የተለየች ሴት ነበረች። የስሟ ትርጉም “አባቴ ራሱን ደስተኛ አደረገ” ማለት ነው። ብዙ ጊዜ አባቶች ቆንጆ ልጅ በመውለዳቸው ይኮራሉ፤ አስተዋይ የሆነ አባት ግን ልጁ ውስጣዊ ውበት ያላት መሆኗ ይበልጥ ያስደስተዋል። አብዛኛውን ጊዜ ውጫዊ ውበት ያለው ሰው እንደ ማስተዋል፣ ጥበብ፣ ድፍረትና እምነት የመሳሰሉትን ባሕርያት ማዳበር አስፈላጊ መሆኑ አይታየውም። አቢግያ ግን እንዲህ ዓይነት ሰው አይደለችም። መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይና ውብ ነበረች” ይላል።—1 ሳሙኤል 25:3
በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች፣ አቢግያን የመሰለች ብልህ ሴት እንደ ናባል ያለውን ባለጌ ወይም የማይረባ ሰው ማግባቷ ያስገርማቸው ይሆናል። ሆኖም በጥንት ዘመን ብዙውን ጊዜ ለልጆቻቸው የትዳር ጓደኛ የሚመርጡት ወላጆች እንደነበሩ ማስታወስ ያስፈልጋል። ይህ ባይሆንም እንኳ ወላጆች በልጆቻቸው ምርጫ መስማማታቸው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነበር። የአቢግያ ወላጆች የናባልን ሀብትና ዝና በመመልከት በዚህ ጋብቻ ተስማምተው ወይም ልጃቸው ናባልን እንድታገባ ዝግጅት አድርገው ይሆን? ምናልባት ድሃ መሆናቸው እንዲህ ዓይነት ውሳኔ እንዲያደርጉ ጫና አሳድሮባቸው ይሆን? ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን፣ ናባል ሀብታም መሆኑ ጥሩ ባል እንዲሆን አላደረገውም።
ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው ለጋብቻ አክብሮት እንዲኖራቸው በቁም ነገር ያሠለጥኗቸዋል። ልጆቻቸው ለገንዘብ ብለው ትዳር እንዲመሠርቱ ወይም ኃላፊነት ለመሸከም ሳይደርሱ ገና በልጅነታቸው ለጋብቻ መጠናናት እንዲጀምሩ አይገፋፏቸውም። (1 ቆሮንቶስ 7:36) እንደነዚህ ያሉት ነገሮች ትኩረት የሚያሻቸው ቢሆኑም አቢግያ ግን በዚህ ወቅት ስለ እነዚህ ነገሮች ብታስብ ምንም ትርጉም አልነበረውም። ምክንያቱም ናባልን አንዴ አግብታዋለች፤ በመሆኑም ያለችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቋቋም የተቻላትን ሁሉ ለማድረግ ቆርጣ ነበር።
“የስድብ ናዳ አወረደባቸው”
ናባል በዚህ ወቅት የወሰደው እርምጃ የአቢግያ ሕይወት ይበልጥ አስቸጋሪ እንዲሆን የሚያደርግ ነበር። የሰደበው ታዋቂ ሰው የሆነውን ዳዊትን ነው። ዳዊት፣ ሳኦልን ተክቶ ንጉሥ እንዲሆን አምላክ የመረጠውና ነቢዩ ሳሙኤል የቀባው ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ ነበር። (1 ሳሙኤል 16:1, 2, 11-13) ንጉሥ ሳኦል በቅንዓት ተነሳስቶ ዳዊትን ሊገድለው ያሳድደው ስለነበር ዳዊት ከንጉሡ ሸሽቶ ከ600 ታማኝ ተዋጊዎቹ ጋር በምድረ በዳ እየኖረ ነበር።
ናባል የሚኖረው በማዖን ሲሆን ሥራውን የሚያከናውነው ግን በአቅራቢያው በሚገኘው በቀርሜሎስ ነበር፤ በዚህ አካባቢ መሬትም የነበረው ይመስላል።a በከፍታ ቦታ ላይ የሚገኙት እነዚህ ከተሞች የግጦሽ መሬት ስለነበራቸው ለበግ እርባታ አመቺ ነበሩ፤ ናባል ደግሞ 3,000 በጎች ነበሩት። በእነዚህ ከተሞች ዙሪያ የነበረው አካባቢ ግን ያልለማ መሬት ነበር። በስተ ደቡብ ሰፊ የሆነው የፋራን ምድረ በዳ ይገኛል። በስተ ምሥራቅ ደግሞ እስከ ጨው ባሕር ድረስ ያለው አካባቢ ገደላ ገደልና ዋሻ የበዛበት ጠፍ መሬት ነው። ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ለኑሮ አስቸጋሪ በሆነው በዚህ አካባቢ በነበሩበት ወቅት የሚበሉት ለማግኘት ማደን የነበረባቸው ከመሆኑም በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንዳሳለፉ ምንም ጥርጥር የለውም። እነዚህ ሰዎች ባለጸጋ የሆነውን የናባልን በጎች ከሚጠብቁት እረኞች ጋር በተደጋጋሚ የመገናኘት አጋጣሚ ነበራቸው።
ታታሪ ሠራተኞች የነበሩት የዳዊት ወታደሮች ከእረኞቹ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ምን ይመስላል? የዳዊት ወታደሮች በፈለጉት ጊዜ ከናባል መንጋ በጎችን መዝረፍ ይችሉ ነበር፤ እነሱ ግን እንዲህ አላደረጉም። ከዚህ በተቃራኒ እንደ አጥር በመሆን የናባልን መንጎችና እረኞች ከጥቃት ጠብቀዋቸዋል። (1 ሳሙኤል 25:15, 16) በጎችም ሆነ የሚጠብቋቸው እረኞች ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው። በዚያ ዘመን አውሬዎች በአካባቢው በብዛት ይገኙ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ቦታው ለእስራኤል ደቡባዊ ድንበር ቅርብ በመሆኑ ከባዕድ አገር የሚመጡ ወንበዴዎችና ዘራፊዎች ብዙ ጊዜ ጥቃት ይሰነዝሩ ነበር።b
ዳዊት በምድረ በዳ በነበረበት ወቅት አብረውት የሚኖሩትን ብዙ ሰዎች መመገብ ከባድ ኃላፊነት እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም። ይህም በመሆኑ አንድ ቀን ዳዊት፣ ናባል ምግብ እንዲሰጠው ለመጠየቅ አሥር መልእክተኞችን ላከ። ዳዊት ይህን ጥያቄ ያቀረበው ጥሩ ጊዜ መርጦ ነበር። በወቅቱ ናባል በጎቹን እየሸለተ ሲሆን በዚህ የደስታ ጊዜ ድግስ መደገስና ለሌሎች በልግስና መስጠት የተለመደ ነበር። ዳዊት ጥያቄውን ያቀረበው በትሕትና እና በአክብሮት ነበር። ከዚህም ሌላ መልእክቱን ሲልክ ‘ልጅህ ዳዊት’ በማለት የተናገረ ሲሆን ይህም በዕድሜ ለሚበልጠው ለናባል አክብሮት እንደነበረው የሚያሳይ ሳይሆን አይቀርም። ታዲያ ናባል፣ ዳዊት ላቀረበለት ጥያቄ ምን ምላሽ ሰጠ?—1 ሳሙኤል 25:5-8
ናባል የዳዊትን መልእክት ሲሰማ በቁጣ ደነፋ! በመግቢያው ላይ የጠቀስነው ወጣት በወቅቱ የተፈጠረውን ሁኔታ ለአቢግያ ሲነገራት፣ ናባል በመልእክተኞቹ ላይ ‘የስድብ ናዳ እንዳወረደባቸው’ ገልጾ ነበር። ገብጋባ የሆነው ናባል እንጀራውን፣ ውኃውንና ያረደውን ፍሪዳ መስጠት እንደማይፈልግ በቁጣ ገለጸ። ዳዊትን እንደማይረባ ሰው አድርጎ ያቃለለው ከመሆኑም ሌላ ከጌቶቻቸው ከኮበለሉ አገልጋዮች እንደ አንዱ ቆጥሮታል። ናባል የነበረው አመለካከት ዳዊትን ይጠላው ከነበረው ከሳኦል የተለየ አልነበረም ለማለት ይቻላል። ሁለቱም ቢሆኑ ይሖዋ ለዳዊት ያለው ዓይነት አመለካከት አልነበራቸውም። አምላክ፣ ዳዊትን የሚወደው ከመሆኑም በላይ እንደ አንድ ዓመፀኛ ባሪያ ሳይሆን የእስራኤል የወደፊት ንጉሥ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተው ነበር።—1 ሳሙኤል 25:10, 11, 14
የዳዊት መልእክተኞች ወደ እሱ ተመልሰው የናባልን ምላሽ ሲነግሩት ዳዊት በጣም ተናደደ። “በሉ ሁላችሁም ሰይፋችሁን ታጠቁ” የሚል ትእዛዝ አስተላለፈ። ከዚያም እሱ ራሱ መሣሪያውን በመታጠቅ 400 ሰዎችን አሰልፎ በናባል ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ጉዞ ጀመረ። ዳዊት የናባል ከሆነው ሁሉ አንድ ወንድ እንኳ በሕይወት ላለማስቀረት ምሎ ነበር። (1 ሳሙኤል 25:12, 13, 21, 22) ዳዊት ለመቆጣት የሚያበቃ ምክንያት የነበረው ቢሆንም ቁጣውን የገለጸበት መንገድ ግን የተሳሳተ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ቁጣ የአምላክ ጽድቅ እንዲፈጸም አያደርግም” ይላል። (ያዕቆብ 1:20) ታዲያ አቢግያ ቤተሰቧን ማዳን የምትችለው እንዴት ነው?
‘ስለ በጎ ሐሳብሽ የተባረክሽ ሁኚ’
ቀደም ሲል እንደተመለከትነው አቢግያ የተፈጠረውን ከባድ ችግር ለማስተካከል የመጀመሪያውን እርምጃ ወስዳለች ማለት ይቻላል። ከባሏ ከናባል በተለየ መልኩ አቢግያ፣ ወጣቱ የሚነግራትን ለማዳመጥ ፈቃደኛ ነበረች። ወጣቱ አገልጋይ ስለ ናባል ሲናገር “እርሱ እንደ ሆነ . . . ባለጌ [“ምናምንቴ፣” የ1954 ትርጉም] ሰው ስለሆነ፣ ደፍሮ የሚነግረው አንድም ሰው የለም” ብሎ ነበር።c (1 ሳሙኤል 25:17) የሚያሳዝነው፣ ናባል ራሱን ከፍ አድርጎ ስለሚመለከት ሌሎች የሚሉትን አይሰማም ነበር። በዛሬው ጊዜም ብዙዎች እንዲህ ዓይነት የእብሪተኝነት ዝንባሌ ይታይባቸዋል። ወጣቱ አገልጋይ፣ አቢግያ ከዚህ የተለየ አመለካከት ያላት ሴት እንደሆነች ያውቅ ነበር፤ የተፈጠረውን ችግር ለእሷ የነገራትም ለዚህ ሳይሆን አይቀርም።
አቢግያ የሆነውን ነገር ስትሰማ በጉዳዩ ላይ ካሰበችበት በኋላ ፈጣን እርምጃ ወሰደች። መጽሐፍ ቅዱስ “አቢግያም ጊዜ አላጠፋችም” በማለት ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ‘መፍጠንን’ የሚያመለክተው ግስ በዚህ ዘገባ ላይ ብቻ ከአቢግያ ጋር በተያያዘ አራት ጊዜ ተሠርቶበታል። አቢግያ ለዳዊትና አብረውት ላሉት ሰዎች እንጀራ፣ የወይን ጠጅ፣ በጎች፣ የተጠበሰ እሸት፣ ዘቢብ፣ ጥፍጥፍ የበለስ ፍሬና ሌሎች በርካታ ስጦታዎችን አዘጋጀች። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አቢግያ በቤቷ ያለውን ንብረት በሚገባ ታውቅ እንዲሁም ኃላፊነቷን ጥሩ አድርጋ ትወጣ ነበር፤ በእርግጥም በምሳሌ መጽሐፍ ላይ ከተጠቀሰችው ጠባየ መልካም ወይም ባለሙያ ሚስት ጋር ትመሳሰላለች። (ምሳሌ 31:10-31) አቢግያ ያዘጋጀችውን ምግብ አገልጋዮቿ ይዘው ቀድመው እንዲሄዱ ካደረገች በኋላ እሷም ተከተለቻቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “ለባሏ ለናባል ግን አልነገረችውም” ይላል።—1 ሳሙኤል 25:18, 19
አቢግያ እንዲህ ማድረጓ የባሏን የራስነት ሥልጣን እንደማታከብር የሚያሳይ ነው? በፍጹም። ናባል፣ ይሖዋ በቀባው ሰው ላይ ክፉ ድርጊት የፈጸመ ሲሆን ይህም ምንም ያላጠፉ በርካታ የናባል ቤተሰብ አባላት እንዲገደሉ ሊያደርግ ይችላል። አቢግያ እርምጃ ሳትወስድ ብትቀር ኖሮ ከባሏ ጋር ተባባሪ እንደሆነች የሚያስቆጥርባት አይሆንም ነበር? ያም ሆነ ይህ ለአምላክ የምታሳየው ተገዢነት ለባሏ ሥልጣን ከምታሳየው ተገዢነት መቅደም ነበረበት።
ብዙም ሳይቆይ አቢግያ፣ ዳዊትንና አብረውት የነበሩትን ሰዎች አገኘቻቸው። በዚህ ጊዜም ወዲያው ከአህያዋ በመውረድ በዳዊት ፊት በግምባሯ ተደፍታ እጅ ነሣች። (1 ሳሙኤል 25:20, 23) ከዚያም ዳዊት ለባሏም ሆነ ለቤተሰቧ ምሕረት እንዲያደርግላቸው ከልቧ አጥብቃ ለመነችው። ዳዊት ልመናዋን እንዲሰማ ያደረገው ምን ነበር?
ለተፈጠረው ችግር ኃላፊነቱን ራሷ በመውሰድ ዳዊት ይቅርታ እንዲያደርግላት ጠየቀችው። አቢግያ ባሏ እንደ ስሙ ጅል መሆኑን አምና ተቀብላለች፤ ምናልባትም ይህ አነጋገሯ እሱን መቅጣት የዳዊትን ክብር ዝቅ የሚያደርግ እንደሆነ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። ከዚህም በላይ ዳዊት የይሖዋ ወኪል መሆኑን እንደምታምንና የሚዋጋውም ‘የይሖዋን ጦርነት’ እንደሆነ ገልጻለች። አምላክ፣ ዳዊትን ‘በእስራኤል ላይ እንደሚያነግሠው’ መናገሯም ይሖዋ ዳዊትን ለማንገሥ የገባውን ቃል እንደምታውቅ የሚጠቁም ነው። በተጨማሪም ዳዊት የደም ዕዳ እንዲኖርበት ወይም በኋላ ላይ ‘የሚያዝንበት ምክንያት’ እንዲኖር ሊያደርግ የሚችል ምንም ዓይነት እርምጃ እንዳይወስድ ለምናዋለች፤ ይህን ስትል የሕሊና ጸጸት የሚያስከትልበት ነገር እንዳያደርግ መጠየቋ ነበር። (1 ሳሙኤል 25:24-31) በእርግጥም አቢግያ የተናገረችው ሐሳብ ደግነት የተንጸባረቀበት እንዲሁም ልብ የሚነካ ነበር!
የዳዊት ምላሽ ምን ነበር? አቢግያ ያመጣችለትን ስጦታ ከተቀበለ በኋላ እንዲህ አላት፦ “ዛሬ እንድታገኚኝ ወደ እኔ የላከሽ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። ደም እንዳላፈስ . . . ዛሬ ስለ ጠበቅሽኝ ስለ በጎ ሐሳብሽ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ።” አቢግያ እሱን ለማግኘት ፈጥና በመምጣት ድፍረት የተሞላበት እርምጃ በመውሰዷ ዳዊት ያመሰገናት ከመሆኑም ሌላ ደም ከማፍሰስ እንዲቆጠብ እንዳደረገችውም ገልጿል። “በሰላም ወደ ቤትሽ ሂጂ” ካላት በኋላ “ቃልሽን ሰምቻለሁ” በማለት በትሕትና ተናግሯል።—1 ሳሙኤል 25:32-35
“እነሆ፤ እኔ ገረድህ”
አቢግያ ከዳዊት ጋር ከተለያየች በኋላ ስለዚህ አጋጣሚ ማሰቧ አይቀርም፤ ታማኝ ብሎም ደግ ሰው በሆነው በዳዊት እና ጠበኛ በሆነው ባለቤቷ መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነትም እንደምታስተውል የታወቀ ነው። ይሁንና በዚህ ጉዳይ ላይ ማውጠንጠኗን አልቀጠለችም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘አቢግያ ወደ ናባል እንደተመለሰች’ ይናገራል። በዚህ ጊዜ የሚስትነት ኃላፊነቷን በሚገባ ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቁርጥ ውሳኔ አድርጋ ነበር። ለዳዊትና አብረውት ለነበሩት ሰዎች ስለሰጠችው ስጦታ ለናባል መንገር ነበረባት። ምክንያቱም ይህንን የማወቅ መብት አለው። ከዚህም በላይ በቤተሰቡ ላይ አንዣብቦ የነበረውን አደጋ እንዴት እንዳስቀረችው ልትነግረው ይገባል፤ ጉዳዩን ከሌላ ሰው ከሚሰማና የከፋ ውርደት ከሚደርስበት ከእሷ መስማቱ የተሻለ ነው። ይሁን እንጂ ስለዚህ ጉዳይ አሁን ልትነግረው አትችልም። ናባል ልክ እንደ ነገሥታት ድል ያለ ድግስ ደግሶ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ጥንብዝ ብሎ ሰክሮ ነበር።—1 ሳሙኤል 25:36
በዚህ ጊዜም አቢግያ፣ ባሏ ስካሩ እስኪበርድለት ጠብቃ በማግስቱ በማናገር ድፍረትና ማስተዋል አሳይታለች። ናባል በነጋታው ስካሩ የበረደለትና የምትነግረውን ለመረዳት የሚችል ቢሆንም በቁጣ ሊገነፍል ስለሚችል በዚህ ወቅት እሱን ማናገሩ ለአቢግያ ይበልጥ አደገኛ ነበር። ያም ቢሆን አቢግያ የተከናወነውን ነገር አንድም ሳታስቀር ነገረችው። በዚህ ጊዜ በንዴት ጦፎ ጉዳት ሊያደርስባት እንደሚችል ጠብቃ ሊሆን ይችላል። እሱ ግን በተቀመጠበት ደርቆ ቀረ።—1 ሳሙኤል 25:37
ናባል ምን ሆኖ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ልቡ ቀጥ አለ፤ ሰውነቱም እንደ ድንጋይ በድን ሆነ” ይላል። ምናልባት የደም መርጋት ችግር አጋጥሞት ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ከአሥር ቀናት በኋላ ሕይወቱ አለፈ፤ የሞቱ መንስኤ ከበሽታው ጋር የተያያዘ ብቻ ላይሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ናባልን ቀሠፈው፤ እርሱም ሞተ” ይላል። (1 ሳሙኤል 25:38) አምላክ እንዲህ ያለ ትክክለኛ የሆነ የፍርድ እርምጃ በመውሰዱ አቢግያ በትዳሯ ይገጥማት ከነበረው መከራ ተገላገለች። ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ተአምራዊ በሆነ መንገድ የቅጣት እርምጃ ባይወስድም ይህ ዘገባ በቤት ውስጥ የሚፈጸም ማንኛውም ጭቆና ወይም በደል ከእሱ እይታ እንደማይሰወር ያስተምረናል። ይሖዋ፣ እሱ በወሰነው ጊዜ ፍትሕ እንዲፈጸም ያደርጋል።
አቢግያ መጥፎ ከነበረው ትዳሯ ከመገላገሏም ባሻገር ሌላ በረከት አግኝታለች። ዳዊት ናባል መሞቱን ሲሰማ መልእክተኞችን በመላክ የጋብቻ ጥያቄ አቀረበላት። እሷም “እነሆ፤ እኔ ገረድህ አንተን ለማገልገል፣ የጌታዬንም አገልጋዮች እግር ለማጠብ ዝግጁ ነኝ” በማለት መለሰችለት። ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው አቢግያ የዳዊት ሚስት ልሆን ነው ብላ አልተኩራራችም፤ እንዲያውም አገልጋዮቹን ለማገልገል ፈቃደኛ መሆኗን ገልጻለች! በዚህ ጊዜም ወደ ዳዊት ለመሄድ ፈጥና እንደተነሳች ዘገባው ይገልጻል።—1 ሳሙኤል 25:39-42
አቢግያ ዳዊትን ካገባች በኋላ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላታል ማለት አይደለም፤ በትዳሯ ውስጥ አንዳንድ ችግሮች አጋጥመዋት ይሆናል። ዳዊት አኪናሆም የምትባል ሚስትም ነበረችው፤ ከአንድ በላይ ማግባት በራሱ በዚያ ዘመን ለነበሩ ታማኝ ሴቶች ችግር እንደሚያስከትልባቸው አይካድም።d ከዚህም ሌላ ዳዊት ንጉሥ ሆኖ መግዛት ገና ስላልጀመረ ይህ እስኪሆን ድረስ አንዳንድ እንቅፋቶችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች መፈጠራቸው የማይቀር ነበር። ያም ቢሆን አቢግያ ዳዊትን በሕይወቱ ሁሉ በመደገፍ አጋር ሆናለታለች፤ እንዲሁም ከጊዜ በኋላ ወንድ ልጅ ወልዳለታለች። በዚህ ጊዜ ሁሉ ባሏ፣ የሚያደንቃትና ከጥቃት የሚከላከልላት ሰው መሆኑን መመልከት ችላ ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት ማርከው ከወሰዷት ሰዎች እጅ አስጥሏታል! (1 ሳሙኤል 30:1-19) በእርግጥም ዳዊት የይሖዋን ምሳሌ እንደሚከተል አሳይቷል፤ ይሖዋ እንደ አቢግያ ያሉ አስተዋይ፣ ደፋርና ታማኝ የሆኑ ሴቶችን የሚወዳቸው ከመሆኑም በላይ ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a እዚህ ላይ የተጠቀሰው ቀርሜሎስ፣ በስተ ሰሜን የሚገኘውና ታዋቂ የሆነው የቀርሜሎስ ተራራ ሳይሆን በስተ ደቡብ ባለው ምድረ በዳ ጫፍ ላይ የሚገኝ ከተማ ነው።
b ዳዊት በአካባቢው የነበሩትን ባለርስቶችና መንጎቻቸውን ከጥቃት መጠበቅን ይሖዋ አምላክን እንደማገልገል አድርጎ ሳይቆጥረው አልቀረም። በዚያ ዘመን የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ ዝርያዎች በዚያ አካባቢ እንዲኖሩ የይሖዋ ዓላማ ነበር። በመሆኑም ይህንን አካባቢ ከባዕድ አገር ከመጡ ወራሪዎችና ዘራፊዎች ጥቃት መጠበቅ ለይሖዋ የሚቀርብ ቅዱስ አገልግሎት እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር።
c ወጣቱ አገልጋይ ናባልን ለመግለጽ የተጠቀመበት ሐረግ ቃል በቃል ሲተረጎም “የክፋት (የከንቱነት) ልጅ” የሚል ፍቺ አለው። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ዓረፍተ ነገር ሲተረጉሙ ናባልን “የማንንም ምክር የማይሰማ” ሰው እንደሆነ አድርገው የገለጹት ከመሆኑም ሌላ “ለእሱ መናገር ምንም ዋጋ የለውም” የሚል መግለጫ ይዘዋል።
d በገጽ 30 ላይ የሚገኘውን “አምላክ ከአንድ በላይ ማግባትን ይደግፋል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባሏ በተለየ መልኩ አቢግያ ጥሩ አድማጭ ነበረች
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አቢግያ ዳዊትን ያነጋገረችው ትሕትና፣ ድፍረትና አስተዋይነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ነበር