22 መልካም ስም ከብዙ ሀብት ይመረጣል፤+
መከበር ከብርና ከወርቅ ይሻላል።
2 ሀብታምንና ድሃን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ፦
ሁለቱንም የፈጠረው ይሖዋ ነው።+
3 ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል፤
ተሞክሮ የሌለው ግን ዝም ብሎ ይሄዳል፤ መዘዙንም ይቀበላል።
4 ትሕትናና ይሖዋን መፍራት
ሀብት፣ ክብርና ሕይወት ያስገኛል።+
5 በጠማማ ሰው መንገድ ላይ እሾህና ወጥመድ አለ፤
ለሕይወቱ ትልቅ ግምት የሚሰጥ ሁሉ ግን ከእነዚህ ይርቃል።+
6 ልጅን ሊሄድበት በሚገባው መንገድ አሠልጥነው፤+
በሚያረጅበት ጊዜም እንኳ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።+
7 ሀብታም ድሃን ይገዛል፤
ተበዳሪም የአበዳሪው ባሪያ ነው።+
8 ክፋትን የሚዘራ ሁሉ ጥፋትን ያጭዳል፤+
የቁጣውም በትር ያከትማል።+
9 ለጋስ ሰው ይባረካል፤
ምግቡን ለድሃ ያካፍላልና።+
10 ንቀት የሚያሳይን ሰው አባረው፤
ጭቅጭቅም ይቀራል፤
ጥልና ስድብ ያከትማል።
11 ንጹሕ ልብ የሚወድና ንግግሩ ለዛ ያለው ሰው፣
የንጉሥ ወዳጅ ይሆናል።+
12 የይሖዋ ዓይኖች እውቀትን ይጠብቃሉ፤
የከዳተኛን ቃል ግን ይሽራል።+
13 ሰነፍ “ውጭ አንበሳ አለ!
አደባባይ ላይ እገደላለሁ!” ይላል።+
14 የጋጠወጥ ሴት አፍ ጥልቅ ጉድጓድ ነው።+
ይሖዋ ያወገዘው ሰው እዚያ ውስጥ ይወድቃል።
15 ሞኝነት በልጅ ልብ ውስጥ ታስሯል፤+
የተግሣጽ በትር ግን ከእሱ ያርቀዋል።+
16 ሀብቱን ለመጨመር ድሃውን የሚያጭበረብር+
እንዲሁም ለባለጸጋ ስጦታ የሚሰጥ ሰው
የኋላ ኋላ ይደኸያል።
17 እውቀቴን በሙሉ ልብ እንድትቀበል+
ጆሮህን አዘንብል፤ የጥበበኞችንም ቃል አዳምጥ፤+
18 ምንጊዜም ይህ ቃል ሙሉ በሙሉ በከንፈሮችህ ላይ እንዲሆን+
ቃሉን በውስጥህ መያዝህ መልካም ነውና።+
19 በይሖዋ እንድትተማመን፣
ዛሬ እውቀት እሰጥሃለሁ።
20 ከዚህ ቀደም ምክርና
እውቀት የያዙ ሐሳቦች አልጻፍኩልህም?
21 ይህን ያደረግኩት ለላከህ ትክክለኛ ወሬ ይዘህ እንድትመለስ፣
እውነት የሆነውንና እምነት የሚጣልበትን ቃል ላስተምርህ አይደለም?
22 ድሃውን ድሃ ስለሆነ ብቻ አትዝረፈው፤+
ችግረኛውንም በከተማው በር ላይ ግፍ አትፈጽምበት፤+
23 ይሖዋ ራሱ ይሟገትላቸዋልና፤+
የሚያጭበረብሯቸውንም ሰዎች ሕይወት ያጠፋል።
24 ከግልፍተኛ ሰው ጋር አትግጠም፤
በቀላሉ ቱግ ከሚል ሰውም ጋር አትቀራረብ፤
25 አለዚያ መንገዱን ትማራለህ፤
ለራስህም ወጥመድ ይሆናል።+
26 ዋስ ለመሆን እጅ እንደሚመቱ፣
ለብድር ተያዥ እንደሚሆኑ ሰዎች አትሁን።+
27 የምትከፍለው ካጣህ
የተኛህበት አልጋ ከሥርህ ይወሰድብሃል!
28 አባቶችህ ያደረጉትን
የጥንቱን የወሰን ምልክት ከቦታው አታንቀሳቅስ።+
29 በሥራው የተካነን ሰው አይተሃል?
በነገሥታት ፊት ይቆማል፤+
ተራ በሆኑ ሰዎች ፊት አይቆምም።