54 “አንቺ ያልወለድሽ መሃን ሴት፣ እልል በይ!+
አንቺ አምጠሽ የማታውቂ ሴት፣+ ደስ ይበልሽ፤ በደስታም ጩኺ፤+
የተተወችው ሴት ወንዶች ልጆች፣
ባል ካላት ሴት ወንዶች ልጆች ይልቅ በዝተዋልና”+ ይላል ይሖዋ።
2 “የድንኳንሽን ቦታ አስፊ።+
ታላቅ የሆነውን የማደሪያ ድንኳንሽን ሸራዎች ዘርጊ።
ፈጽሞ አትቆጥቢ፤ የድንኳንሽን ገመዶች አስረዝሚ፤
ካስማዎችሽንም አጠንክሪ።+
3 በቀኝም ሆነ በግራ ትስፋፊያለሽና።
ዘሮችሽ ብሔራትን ይወርሳሉ፤
ባድማ በሆኑትም ከተሞች ውስጥ ይኖራሉ።+
4 ኀፍረት ስለማይደርስብሽ+ አትፍሪ፤+
ለሐዘን ስለማትዳረጊም አትሸማቀቂ።
በልጅነትሽ ዘመን የደረሰብሽን ኀፍረት ትረሺዋለሽና፤
መበለትነትሽ ያስከተለብሽን ውርደትም ከእንግዲህ አታስታውሽም።”
5 “ታላቁ ሠሪሽ+ ባልሽ ነውና፤+
ስሙም የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ነው፤
የሚቤዥሽም+ የእስራኤል ቅዱስ ነው።
እሱም የምድር ሁሉ አምላክ ተብሎ ይጠራል።+
6 ይሖዋ የተተወችና በሐዘን የተደቆሰች ሚስት፣+
ደግሞም በልጅነቷ አግብታ፣ ከጊዜ በኋላ የተጠላች ሚስት እንደሆንሽ ቆጥሮ ጠርቶሻልና” ይላል አምላክሽ።
7 “ለአጭር ጊዜ ተውኩሽ፤
ሆኖም በታላቅ ምሕረት መልሼ እሰበስብሻለሁ።+
8 በቁጣ ጎርፍ ለጥቂት ጊዜ ፊቴን ከአንቺ ሰውሬ ነበር፤+
ሆኖም በዘላለማዊ ታማኝ ፍቅር ምሕረት አሳይሻለሁ”+ ይላል የሚቤዥሽ+ ይሖዋ።
9 “ይህ ለእኔ እንደ ኖኅ ዘመን ነው።+
የኖኅ ውኃ ምድርን ዳግመኛ አያጥለቀልቅም ብዬ እንደማልኩ ሁሉ+
አንቺንም ከእንግዲህ ላለመቆጣትም ሆነ ላለመገሠጽ እምላለሁ።+
10 ተራሮች ከቦታቸው ሊወገዱ፣
ኮረብቶችም ሊናወጡ ይችላሉ፤
ይሁንና ታማኝ ፍቅሬ ከአንቺ አይለይም፤+
የሰላም ቃል ኪዳኔም አይናጋም”+ ይላል ምሕረት የሚያሳይሽ ይሖዋ።+
11 “አንቺ የተጎሳቆልሽ፣+ በአውሎ ነፋስ የተናወጥሽና ማጽናኛ ያላገኘሽ ሴት ሆይ፣+
እነሆ ድንጋዮችሽን በኃይለኛ ማጣበቂያ እገነባለሁ፤
መሠረትሽንም በሰንፔር እሠራለሁ።+
12 መጠበቂያ ማማዎችሽን በሩቢ ድንጋዮች፣
የከተማሽንም በሮች በሚያብረቀርቁ ድንጋዮች፣
ወሰኖችሽንም ሁሉ በከበሩ ድንጋዮች እሠራለሁ።
13 ልጆችሽም ሁሉ ከይሖዋ የተማሩ ይሆናሉ፤+
የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል።+
14 በጽድቅ ጽኑ ሆነሽ ትመሠረቺያለሽ።+
ጭቆና ከአንቺ ይርቃል፤+
ምንም ነገር አትፈሪም፤ የሚያሸብርሽም ነገር አይኖርም፤
ወደ አንቺ አይቀርብምና።+
15 ማንም ጥቃት ቢሰነዝርብሽ
እኔ አዝዤው አይደለም።
ጥቃት የሚሰነዝርብሽ ሁሉ ከአንቺ የተነሳ ይወድቃል።”+
16 “እነሆ፣ የከሰል እሳቱን በወናፍ የሚያናፋውን
የእጅ ጥበብ ባለሙያ የፈጠርኩት እኔ ነኝ፤
የሚያከናውነውም ሥራ የጦር መሣሪያ ያስገኛል።
ደግሞም ጥፋት እንዲያደርስ አጥፊውን ሰው የፈጠርኩት እኔ ራሴ ነኝ።+
17 አንቺን ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ ይከሽፋል፤+
አንቺን ለመክሰስ የሚነሳን ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ።
የይሖዋ አገልጋዮች ውርሻ ይህ ነው፤
ጽድቃቸውም ከእኔ ዘንድ ነው” ይላል ይሖዋ።+