ሁለተኛ ሳሙኤል
7 ንጉሡ በራሱ ቤት* መኖር በጀመረና+ ይሖዋም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ እረፍት በሰጠው ጊዜ 2 ነቢዩ ናታንን+ “የእውነተኛው አምላክ ታቦት በድንኳን ውስጥ+ ተቀምጦ ሳለ ይኸው እኔ ከአርዘ ሊባኖስ በተሠራ+ ቤት ውስጥ እየኖርኩ ነው” አለው። 3 ናታንም ንጉሡን “ይሖዋ ከአንተ ጋር ስለሆነ ሄደህ በልብህ ያለውን ነገር ሁሉ አድርግ” አለው።+
4 በዚያው ሌሊት የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ናታን መጣ፦ 5 “ሂድና አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “አንተ የምኖርበትን ቤት መሥራት ይኖርብሃል?+ 6 እስራኤላውያንን ከግብፅ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳንና በማደሪያ ድንኳን እጓዝ ነበር እንጂ በቤት ውስጥ አልኖርኩም።+ 7 ከእስራኤላውያን* ሁሉ ጋር በተጓዝኩበት ጊዜ በሙሉ ሕዝቤን እስራኤልን እረኛ ሆነው እንዲጠብቁ ከሾምኳቸው የነገድ መሪዎች መካከል ‘በአርዘ ሊባኖስ ቤት ያልሠራህልኝ ለምንድን ነው?’ ያልኩት ማን አለ?”’ 8 አሁንም አገልጋዬን ዳዊትን እንዲህ በለው፦ ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪ እንድትሆን+ መንጋ ከምትጠብቅበት ስፍራ+ ወሰድኩህ። 9 እኔም በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤+ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋለሁ፤+ ስምህንም በምድር ላይ እንዳሉ ታላላቅ ሰዎች ስም ገናና አደርገዋለሁ።+ 10 ለሕዝቤ ለእስራኤል ቦታ እሰጣቸዋለሁ፤ ተረጋግተው እንዲቀመጡም አደርጋለሁ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ከእንግዲህም የሚረብሻቸው አይኖርም፤ ክፉዎች እንደቀድሞው ዳግመኛ አይጨቁኗቸውም፤+ 11 በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሳፍንትን ከሾምኩበት+ ጊዜ አንስቶ ሲያደርጉ እንደነበሩት አያደርጉባቸውም። እኔም ከጠላቶችህ ሁሉ እረፍት እሰጥሃለሁ።+
“‘“በተጨማሪም ይሖዋ ቤት* እንደሚሠራልህ ይሖዋ ራሱ ነግሮሃል።+ 12 የሕይወት ዘመንህ አብቅቶ+ ከአባቶችህ ጋር በምታንቀላፋበት ጊዜ ከአንተ በኋላ ከአብራክህ የሚወጣውን ዘርህን አስነሳለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለሁ።+ 13 ለስሜ የሚሆን ቤት የሚሠራልኝ እሱ ነው፤+ እኔም የመንግሥቱን ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ።+ 14 አባት እሆነዋለሁ፤ እሱም ልጄ ይሆናል።+ ጥፋት በሚያጠፋበት ጊዜም በሰዎች በትር፣ በሰው* ልጆች አለንጋ እቀጣዋለሁ።+ 15 ከፊትህ ካስወገድኩት ከሳኦል ላይ ታማኝ ፍቅሬን እንደወሰድኩ+ ከእሱ ላይ አይወሰድም። 16 ቤትህና መንግሥትህ ለዘላለም በፊትህ ጸንቶ ይኖራል፤ ዙፋንህም ለዘላለም የጸና ይሆናል።”’”+
17 ናታንም ይህን ቃል ሁሉና ይህን ራእይ በሙሉ ለዳዊት ነገረው።+
18 በዚህ ጊዜ ንጉሥ ዳዊት ገብቶ በይሖዋ ፊት ተቀመጠ፤ እንዲህም አለ፦ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ኧረ ለመሆኑ እኔ ማን ነኝ? እስከዚህ ድረስ ያደረስከኝስ ቤቴ ምን ስለሆነ ነው?+ 19 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ይህ ሳያንስ ስለ አገልጋይህ ቤት ገና ወደፊት የሚሆነውንም ነገር ተናገርክ፤ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ይህ ለሰው ዘር ሁሉ የተሰጠ መመሪያ* ነው። 20 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ታዲያ አገልጋይህ ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? አንተ በሚገባ ታውቀኝ የለ?+ 21 ለቃልህ ስትል፣ ከልብህ ጋር በሚስማማ ሁኔታ* እነዚህን ሁሉ ታላላቅ ነገሮች ፈጽመሃል፤ እንዲሁም ለአገልጋይህ ገልጠህለታል።+ 22 ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ በእርግጥም ታላቅ+ የሆንከው ለዚህ ነው። እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤+ ከአንተ በቀር አምላክ የለም፤+ በጆሯችን የሰማነው ነገር ሁሉ ይህን ያረጋግጣል። 23 በምድር ላይ እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ ሌላ ብሔር ማን አለ?+ አምላክ ሄዶ ለእነሱ ሲል ታላላቅና አስፈሪ ነገሮችን+ በመፈጸም እንዲሁም ስሙን በማስጠራት+ ሕዝቡ አድርጎ ዋጃቸው።+ ከግብፅ ለዋጀኸው ሕዝብ ስትል ብሔራትንና አማልክታቸውን አባረርክ። 24 ሕዝብህን እስራኤልን እስከ ወዲያኛው የራስህ ሕዝብ አድርገህ አጸናኸው፤+ ይሖዋ ሆይ፣ አንተም አምላኩ ሆንክ።+
25 “አሁንም ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ አገልጋይህንና ቤቱን በተመለከተ የገባኸውን ቃል እስከ ወዲያኛው ፈጽም፤ ቃል እንደገባኸውም አድርግ።+ 26 ሰዎች ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በእስራኤል ላይ አምላክ ነው’ እንዲሉ ስምህ ለዘላለም ከፍ ከፍ ይበል፤+ የአገልጋይህም የዳዊት ቤት በፊትህ የጸና ይሁን።+ 27 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ‘ለአንተ ቤት* እሠራልሃለሁ’+ በማለት ለአገልጋይህ ራእይ ገልጠህለታል። አገልጋይህ ይህን ጸሎት ወደ አንተ ለማቅረብ ድፍረት* ያገኘው በዚህ ምክንያት ነው። 28 አሁንም ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ እውነተኛው አምላክ አንተ ነህ፤ ቃልህ እውነት ነው፤+ ለአገልጋይህም እነዚህን መልካም ነገሮች ለማድረግ ቃል ገብተህለታል። 29 በመሆኑም የአገልጋይህን ቤት እባክህ ባርክ፤ በፊትህም ለዘላለም የጸና ይሁን፤+ ምክንያቱም ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ራስህ ቃል ገብተሃል፤ በአንተም በረከት የአገልጋይህ ቤት ለዘላለም የተባረከ ይሁን።”+