21 የንጉሥ ልብ በይሖዋ እጅ እንዳለ ጅረት ነው።+
እሱ ደስ ወዳሰኘው አቅጣጫ ሁሉ ይመራዋል።+
2 ሰው መንገዱ ሁሉ ትክክል መስሎ ይታየዋል፤+
ይሖዋ ግን ልብን ይመረምራል።+
3 መሥዋዕት ከማቅረብ ይልቅ
ትክክልና ፍትሐዊ የሆነ ነገር ማድረግ ይሖዋን ይበልጥ ደስ ያሰኘዋል።+
4 ትዕቢተኛ ዓይንና እብሪተኛ ልብ
የክፉዎች መብራት ናቸው፤ ደግሞም ኃጢአት ናቸው።+
5 የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል፤+
ችኩሎች ሁሉ ግን ለድህነት ይዳረጋሉ።+
6 በሐሰተኛ ምላስ የሚገኝ ውድ ሀብት
ወዲያው እንደሚጠፋ ጉም ነው፤ ገዳይ ወጥመድም ነው።+
7 ክፉዎች ፍትሕን ማስፈን ስለማይፈልጉ
የሚፈጽሙት ግፍ ጠራርጎ ይወስዳቸዋል።+
8 የበደለኛ ሰው መንገድ ጠማማ ነው፤
የንጹሕ ሰው ሥራ ግን ቀና ነው።+
9 ከጨቅጫቃ ሚስት ጋር በአንድ ቤት ከመኖር
በጣሪያ ማዕዘን ላይ መኖር ይሻላል።+
10 ክፉ ሰው መጥፎ ነገር ይመኛል፤+
ለባልንጀራው ሞገስ አያሳይም።+
11 ፌዘኛ ሲቀጣ ተሞክሮ የሌለው ሰው ይበልጥ ጥበበኛ ይሆናል፤
ጥበበኛ ሰው ጥልቅ ማስተዋል ሲያገኝም እውቀት ይቀስማል።+
12 ጻድቅ የሆነው አምላክ፣ የክፉውን ቤት ልብ ብሎ ይመለከታል፤
ክፉዎችንም ይጠፉ ዘንድ ይገለብጣቸዋል።+
13 ችግረኛው የሚያሰማውን ጩኸት ላለመስማት ጆሮውን የሚደፍን ሁሉ፣
እሱ ራሱ ይጮኻል፤ መልስም አያገኝም።+
14 በድብቅ የተሰጠ ስጦታ ቁጣን ያበርዳል፤+
በስውር የተሰጠ ጉቦም ኃይለኛ ቁጣ እንዲከስም ያደርጋል።
15 ጻድቅ ፍትሐዊ ነገር ማድረግ ያስደስተዋል፤+
ክፉ ድርጊት ለሚፈጽሙ ግን አስከፊ ነገር ነው።
16 ከማስተዋል መንገድ ወጥቶ የሚባዝን ሰው፣
በሞት ከተረቱት ጋር ያርፋል።+
17 ፈንጠዝያ የሚወድ ሰው ይደኸያል፤+
የወይን ጠጅና ዘይት የሚወድ ባለጸጋ አይሆንም።
18 ክፉ ሰው ለጻድቅ ቤዛ ነው፤
ከዳተኛ የሆነ ሰውም በቅን ሰው ፋንታ ይወሰዳል።+
19 ጨቅጫቃና ቁጡ ከሆነች ሚስት ጋር ከመኖር
በምድረ በዳ መኖር ይሻላል።+
20 ውድ ሀብትና ምርጥ ዘይት በጥበበኛ ሰው ቤት ይገኛል፤+
ሞኝ ሰው ግን ያለውን ያባክናል።+
21 ጽድቅንና ታማኝ ፍቅርን የሚከታተል ሰው ሁሉ
ሕይወትን፣ ጽድቅንና ክብርን ያገኛል።+
22 ጥበበኛ ሰው የኃያላን ሰዎች ከተማ ላይ ይወጣል፤
የሚታመኑበትንም ብርታት ያዳክማል።+
23 አፉንና ምላሱን የሚጠብቅ፣
ራሱን ከችግር ይጠብቃል።+
24 በእብሪት የመሰለውን የሚያደርግ ሰው
እብሪተኛና ጉረኛ ይባላል።+
25 ሰነፍ ሰው ምኞቱ ይገድለዋል፤
እጆቹ መሥራት አይፈልጉምና።+
26 ቀኑን ሙሉ በስግብግብነት ሲመኝ ይውላል፤
ጻድቅ ግን ምንም ሳይሰስት ይሰጣል።+
27 የክፉ ሰው መሥዋዕት አስጸያፊ ነው።+
በክፉ ዓላማ ተነሳስቶ ሲያቀርብማ ምንኛ የከፋ ይሆናል!
28 ውሸታም ምሥክር ይጠፋል፤+
በጥሞና የሚያዳምጥ ሰው ግን የምሥክርነት ቃሉ ተቀባይነት ያገኛል።
29 ክፉ ሰው ኀፍረት የሚባል ነገር አያውቅም፤+
የቅን ሰው አካሄድ ግን አስተማማኝ ነው።+
30 ይሖዋን የሚጻረር ጥበብ፣ ማስተዋልም ሆነ ምክር ከንቱ ነው።+
31 ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፤+
መዳን ግን ከይሖዋ ዘንድ ነው።+