ሁለተኛ መጽሐፍ
(መዝሙር 42-72)
ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ። የቆሬ ልጆች ማስኪል።+
42 ርኤም ጅረቶችን እንደምትናፍቅ፣
አምላክ ሆይ፣ አንተን እናፍቃለሁ።
2 አምላክን፣ ሕያው አምላክን ተጠማሁ።+
ወደ አምላክ የምሄደውና በፊቱ የምቀርበው መቼ ይሆን?+
3 እንባዬ ቀን ከሌት ምግብ ሆነኝ፤
ሰዎች ቀኑን ሙሉ “አምላክህ የት አለ?” እያሉ ይሳለቁብኛል።+
4 እነዚህን ነገሮች አስታውሳለሁ፤ ነፍሴንም አፈሳለሁ፤
በአንድ ወቅት ከብዙ ሰዎች ጋር እጓዝ ነበር፤
በእልልታና በምስጋና ድምፅ፣
በዓል በሚያከብር ሕዝብ ድምፅ፣
ከፊታቸው ሆኜ ወደ አምላክ ቤት በኩራት እሄድ ነበር።+
5 ተስፋ የምቆርጠው ለምንድን ነው?+
ውስጤ የሚረበሸው ለምንድን ነው?
አምላክን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤+
እሱን እንደ ታላቅ አዳኜ አድርጌ ገና አወድሰዋለሁና።+
6 አምላኬ ሆይ፣ ተስፋ ቆርጫለሁ።+
ከዮርዳኖስ ምድርና ከሄርሞን አናት፣
ከሚዛር ተራራ
የማስብህ ለዚህ ነው።+
7 በፏፏቴህ ድምፅ አማካኝነት
ጥልቁ ውኃ፣ ጥልቁን ውኃ ይጣራል።
ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ ዋጠኝ።+
8 ይሖዋ በቀን ታማኝ ፍቅሩን ያሳየኛል፤
እኔ ደግሞ በሌሊት ስለ እሱ እዘምራለሁ፤ ሕይወት ለሰጠኝ አምላክ ጸሎት አቀርባለሁ።+
9 ዓለቴ የሆነውን አምላክ እንዲህ እለዋለሁ፦
“ለምን ረሳኸኝ?+
ጠላት ከሚያደርስብኝ ግፍ የተነሳ በሐዘን ተውጬ ለምን እሄዳለሁ?”+
10 ለእኔ ካላቸው ጥላቻ የተነሳ ሊገድሉኝ የሚሹ ጠላቶቼ ይሳለቁብኛል፤
ቀኑን ሙሉ “አምላክህ የት አለ?” እያሉ ይሳለቁብኛል።+
11 ተስፋ የምቆርጠው ለምንድን ነው?
ውስጤ የሚረበሸው ለምንድን ነው?
አምላክን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤+
እሱን እንደ ታላቅ አዳኜና አምላኬ አድርጌ ገና አወድሰዋለሁና።+