የጴጥሮስ ሁለተኛው ደብዳቤ
2 ይሁን እንጂ በሕዝቡ መካከል ሐሰተኛ ነቢያት እንደነበሩ ሁሉ በእናንተም መካከል ሐሰተኛ አስተማሪዎች ይነሳሉ።+ እነዚህ ሰዎች ጥፋት የሚያስከትል ኑፋቄ በስውር ያስገባሉ፤ የዋጃቸውን+ ጌታ እንኳ ሳይቀር ክደው በራሳቸው ላይ ፈጣን ጥፋት ያመጣሉ። 2 በተጨማሪም ብዙዎች እነሱ በማንአለብኝነት የሚፈጽሙትን ድርጊት* ይፈጽማሉ፤+ በዚህም ምክንያት የእውነት መንገድ ይሰደባል።+ 3 እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች አስመሳይ ቃላት በመናገር እናንተን በስግብግብነት ይበዘብዟችኋል። ሆኖም ከብዙ ዘመን በፊት የተበየነባቸው ፍርድ+ አይዘገይም፤ ጥፋት እንደሚደርስባቸውም ጥርጥር የለውም።*+
4 ደግሞም አምላክ ኃጢአት የሠሩትን መላእክት ከመቅጣት ወደኋላ አላለም፤+ ይልቁንም በድቅድቅ ጨለማ አስሮ* በማስቀመጥ ፍርዳቸውን እንዲጠባበቁ+ ወደ እንጦሮጦስ* ጣላቸው።+ 5 እንዲሁም የጽድቅ ሰባኪ የነበረውን ኖኅን+ ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖ+ ፈሪሃ አምላክ ባልነበራቸው ሰዎች በተሞላው ዓለም ላይ የጥፋት ውኃ ባመጣ ጊዜ+ የጥንቱን ዓለም ከመቅጣት ወደኋላ አላለም።+ 6 ደግሞም ፈሪሃ አምላክ ለሌላቸው ሰዎች ለወደፊቱ ምሳሌ እንዲሆኑ+ የሰዶምና የገሞራ ከተሞችን አመድ በማድረግ ፈርዶባቸዋል።+ 7 ሆኖም ለሕግ የማይገዙ ሰዎች በማንአለብኝነት በሚፈጽሙት ድርጊት* እጅግ እየተሳቀቀ ይኖር የነበረውን ጻድቁን ሎጥን አድኖታል።+ 8 ይህ ጻድቅ ሰው ዕለት ተዕለት በመካከላቸው ሲኖር በሚያየውና በሚሰማው መረን የለቀቀ ድርጊታቸው ጻድቅ ነፍሱን* ያስጨንቅ ነበር። 9 በመሆኑም ይሖዋ፣* ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድንና+ ዓመፀኞችን ደግሞ በፍርድ ቀን ለሚደርስባቸው ጥፋት እንዴት ጠብቆ እንደሚያቆይ ያውቃል።+ 10 በተለይ ደግሞ ሰዎችን ለማርከስ+ ሲሉ ከእነሱ ጋር የፆታ ብልግና ለመፈጸም የሚመኙትንና ሥልጣን ያላቸውን የሚንቁትን*+ ለፍርድ ጠብቆ ያቆያቸዋል።
ደፋሮችና በራሳቸው የሚመሩ ከመሆናቸውም በላይ የተከበሩትን ሲሳደቡ አይፈሩም። 11 ይሁንና መላእክት፣ ከእነሱ የላቀ ብርታትና ኃይል ያላቸው ቢሆንም ለይሖዋ* ካላቸው አክብሮት የተነሳ* ሐሰተኛ አስተማሪዎቹን በመስደብ አልነቀፏቸውም።+ 12 እነዚህ ሰዎች ግን ተይዘው ለመገደል እንደተወለዱ፣ በደመ ነፍስ እንደሚንቀሳቀሱ አእምሮ የሌላቸው እንስሳት ናቸው፤ በማያውቁት ነገር እየገቡ ይሳደባሉ።+ በሚከተሉት የጥፋት ጎዳና የተነሳ ለጥፋት ይዳረጋሉ። 13 በሠሩት ክፉ ድርጊት የተነሳ በራሳቸው ላይ ክፉ ነገር በማምጣት ብድራታቸውን ይቀበላሉ።
በጠራራ ፀሐይ የሥጋ ፍላጎታቸውን ማርካትን እንደ ደስታ ይቆጥሩታል።+ እነዚህ ሰዎች እንደ ቆሻሻና እድፍ ናቸው፤ ከእናንተ ጋር በግብዣ ላይ ሲገኙ አታላይ በሆኑ ትምህርቶቻቸው ሌሎችን በማሳት እጅግ ይደሰታሉ።+ 14 አመንዝራ ዓይን+ ያላቸው በመሆኑ ኃጢአት ከመሥራት መታቀብ አይችሉም፤ ጸንተው ያልቆሙትንም* ያማልላሉ። መስገብገብ የለመደ ልብ አላቸው። የተረገሙ ልጆች ናቸው። 15 ቀናውን መንገድ ትተው በተሳሳተ ጎዳና ሄደዋል። ለጥቅም ሲል ክፉ ድርጊት መፈጸም የመረጠውን የቢዖርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከትለዋል።+ 16 በለዓም ግን ትክክለኛውን መመሪያ በመጣሱ ተወቅሷል።+ መናገር የማትችል አህያ እንደ ሰው ተናግራ የነቢዩን የእብደት አካሄድ ለመግታት ሞከረች።+
17 እነዚህ ሰዎች የደረቁ ምንጮችና በአውሎ ነፋስ የሚነዱ ደመናዎች ናቸው፤ ድቅድቅ ጨለማም ይጠብቃቸዋል።+ 18 በከንቱ ጉራ ይነዛሉ። በተሳሳተ ጎዳና ከሚመላለሱት መካከል በቅርቡ ያመለጡትን ሰዎች የሥጋ ምኞቶቻቸውን በመቀስቀስና+ ማንአለብኝነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት በመፈጸም* ያማልሏቸዋል።+ 19 እነሱ ራሳቸው የመጥፎ ሥነ ምግባር ባሪያዎች ሆነው ሳሉ ነፃ ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጧቸዋል፤+ ማንም ሰው በሌላ ሰው ከተሸነፈ የዚያ ሰው ባሪያ ይሆናልና።*+ 20 ስለ ጌታችንና አዳኛችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ባገኙት ትክክለኛ እውቀት አማካኝነት ከዓለም ርኩሰት ካመለጡ በኋላ+ ተመልሰው በዚሁ ነገር ከተጠመዱና ከተሸነፉ ከመጀመሪያው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታቸው የከፋ እንደሚሆንባቸው ምንም ጥርጥር የለውም።+ 21 የጽድቅን መንገድ በትክክል ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደኋላ ከሚሉ ቀድሞውኑ ባያውቁት ይሻላቸው ነበር።+ 22 “ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፤ የታጠበች አሳማም ተመልሳ ጭቃ ላይ ትንከባለላለች”+ የሚለው እውነተኛ ምሳሌ በእነሱ ላይ ተፈጽሟል።