ሚልክያስ
2 “አሁንም ካህናት ሆይ፣ ይህ ትእዛዝ ለእናንተ ነው።+ 2 ለመስማት አሻፈረኝ ብትሉና ለስሜ ክብር ትሰጡ ዘንድ በልባችሁ ባታኖሩት” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣ “በእናንተ ላይ እርግማን እሰዳለሁ፤+ በረከታችሁንም ወደ እርግማን እለውጣለሁ።+ አዎ፣ በልባችሁ ስላላኖራችሁት እያንዳንዱን በረከት ወደ እርግማን ለውጫለሁ።”
3 “እነሆ፣ በእናንተ የተነሳ የዘራችሁትን ዘር አጠፋለሁ፤*+ ፈርሱንም ይኸውም በበዓሎቻችሁ ላይ የምትሠዉአቸውን እንስሳት ፈርስ ፊታችሁ ላይ እበትናለሁ፤ እናንተንም ወደዚያ* ወስደው ይጥሏችኋል። 4 ይህን ትእዛዝ የሰጠኋችሁ ከሌዊ ጋር የገባሁት ቃል ኪዳን ጸንቶ እንዲኖር መሆኑን ታውቃላችሁ”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።
5 “ከእሱ ጋር የገባሁት ቃል ኪዳን የሕይወትና የሰላም ቃል ኪዳን ነው፤ እነዚህን በረከቶች በማግኘቱ እኔን ለመፍራት* ተነሳሳ። አዎ፣ ለስሜ ታላቅ አክብሮት አሳየ። 6 የእውነት ሕግ* በአፉ ውስጥ ነበር፤+ በከንፈሮቹም ክፋት አልተገኘም። ከእኔ ጋር በሰላምና በቅንነት ሄደ፤+ ብዙዎቹንም ከስህተት ጎዳና መለሰ። 7 ካህኑ ምንጊዜም በከንፈሮቹ ላይ እውቀት ሊኖረው ይገባል፤ ሰዎችም ሕጉን* ከአፉ ሊሹ ይገባል፤+ ምክንያቱም እሱ የሠራዊት ጌታ የይሖዋ መልእክተኛ ነው።
8 “እናንተ ግን ከመንገዱ ፈቀቅ ብላችኋል። ብዙዎች ከሕጉ ጋር በተያያዘ* እንዲሰናከሉ አድርጋችኋል።+ የሌዊን ቃል ኪዳን አርክሳችኋል”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። 9 “ስለዚህ በሰዎች ሁሉ ፊት የተናቃችሁና የተዋረዳችሁ እንድትሆኑ አደርጋለሁ፤ ምክንያቱም መንገዶቼን አልጠበቃችሁም፤ ከዚህ ይልቅ ሕጉን ተግባራዊ ስታደርጉ አድልዎ ፈጽማችኋል።”+
10 “የሁላችንም አባት አንድ አይደለም?+ የፈጠረንስ አምላክ አንድ አይደለም? ታዲያ የአባቶቻችንን ቃል ኪዳን በማርከስ አንዳችን በሌላው ላይ ክህደት የምንፈጽመው ለምንድን ነው?+ 11 ይሁዳ ክህደት ፈጽሟል፤ በእስራኤልና በኢየሩሳሌምም አስጸያፊ ነገር ተፈጽሟል፤ ይሁዳ፣ ይሖዋ የሚወደውን ቅድስናውን* አርክሷልና፤+ ደግሞም የባዕድ አምላክ ሴት ልጅን አግብቷል።+ 12 ይህን የሚያደርግ ማንኛውም ሰው ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ ስጦታ አድርጎ መባ ቢያቀርብም እንኳ ይሖዋ ከያዕቆብ ድንኳኖች ያስወግደዋል።”+
13 “ሌላም የምታደርጉት ነገር አለ፤ ይህም የይሖዋ መሠዊያ በእንባ፣ በለቅሶና በሐዘን እንዲሞላ ምክንያት ሆኗል፤ በመሆኑም ስጦታ አድርጋችሁ የምታቀርቧቸውን መባዎች ከእንግዲህ አይቀበልም፤ የምታቀርቡትንም ነገር ሁሉ በሞገስ ዓይን አይመለከትም።+ 14 እናንተም ‘ይህ የሆነው ለምንድን ነው?’ ብላችኋል። ይህ የሆነው ይሖዋ በአንተ ላይ ስለመሠከረብህ ነው፤ ምክንያቱም እሷ አጋርህና የቃል ኪዳን ሚስትህ* ሆና ሳለ በወጣትነት ሚስትህ ላይ ክህደት ፈጽመሃል።+ 15 ሆኖም እንዲህ ያላደረገ አለ፤ እሱ በተወሰነ መጠን የአምላክ መንፈስ ነበረው። ፍላጎቱስ ምን ነበር? የአምላክ ዘር ነበር። በመሆኑም መንፈሳችሁን ጠብቁ፤ በወጣትነት ሚስታችሁም ላይ ክህደት አትፈጽሙ። 16 እኔ ፍቺን እጠላለሁና”*+ ይላል የእስራኤል አምላክ ይሖዋ፤ “ልብሱን በግፍ ድርጊት የሚሸፍነውንም* እጠላለሁ” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። “መንፈሳችሁን ጠብቁ፤ ክህደትም አትፈጽሙ።+
17 “ይሖዋን በቃላችሁ አታክታችሁታል።+ እናንተ ግን ‘ያታከትነው እንዴት ነው?’ ትላላችሁ። ‘ክፉ ድርጊት የሚፈጽም ሁሉ በይሖዋ ዓይን ጥሩ ነው፤ እሱ እንዲህ ባለ ሰው ደስ ይሰኛል’+ ወይም ‘የፍትሕ አምላክ የት አለ?’ በማለታችሁ ነው።”