ዘኁልቁ
16 ከዚያም የሌዊ+ ልጅ፣ የቀአት+ ልጅ፣ የይጽሃር+ ልጅ ቆሬ+ ከሮቤል ልጆች አንዱ ከሆነው ከኤልያብ+ ልጆች ከዳታንና ከአቤሮን እንዲሁም ከሮቤል+ ልጆች አንዱ ከሆነው ከፐሌት ልጅ ከኦን ጋር በመሆን ተነሳ። 2 እነሱም ከማኅበረሰቡ አለቆች ይኸውም ከጉባኤው መካከል ከተመረጡት ታዋቂ የሆኑ 250 እስራኤላውያን ወንዶች ጋር በማበር በሙሴ ላይ ተነሱ። 3 እነሱም ሙሴንና አሮንን ለመቃወም+ ተሰብስበው መጡ፤ እንዲህም አሏቸው፦ “ምነው፣ አላበዛችሁትም እንዴ! መላው ማኅበረሰብ እኮ ቅዱስ ነው፤+ ሁሉም ቅዱስ ናቸው፤ ይሖዋም በመካከላቸው ነው።+ ታዲያ በይሖዋ ጉባኤ ላይ ራሳችሁን ከፍ ከፍ የምታደርጉት ለምንድን ነው?”
4 ሙሴ ይህን ሲሰማ ወዲያውኑ በግንባሩ ተደፋ። 5 ከዚያም ቆሬንና ግብረ አበሮቹን ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ “ጠዋት ላይ ይሖዋ የእሱ የሆነውን፣+ ቅዱስ የሆነውንና ወደ እሱ መቅረብ የሚችለውን+ ሰው ያሳውቃል፤ እሱ የመረጠውም+ ሰው ወደ እሱ ይቀርባል። 6 ስለዚህ እንዲህ አድርጉ፦ ቆሬ፣ አንተም ሆንክ ግብረ አበሮችህ+ በሙሉ የዕጣን ማጨሻዎች+ ውሰዱ፤ 7 ከዚያም በነገው ዕለት እሳት ካደረጋችሁባቸው በኋላ በይሖዋ ፊት ዕጣን ጨምሩባቸው፤ ይሖዋ የሚመርጠውም ሰው፣+ እሱ ቅዱስ ይሆናል። እናንተ የሌዊ ልጆች፣+ በጣም አብዝታችሁታል!”
8 ከዚያም ሙሴ ቆሬን እንዲህ አለው፦ “እናንተ የሌዊ ልጆች፣ እባካችሁ አዳምጡ። 9 የእስራኤል አምላክ እናንተን ከእስራኤል ማኅበረሰብ+ መለየቱ እንዲሁም በይሖዋ የማደሪያ ድንኳን የሚከናወነውን አገልግሎት ትፈጽሙና በማኅበረሰቡ ፊት ቆማችሁ እነሱን ታገለግሉ ዘንድ ወደ እሱ እንድትቀርቡ መፍቀዱ እንደ ቀላል ነገር የሚታይ ነው?+ 10 ደግሞስ አንተንና የሌዊ ልጆች የሆኑትን ወንድሞችህን በሙሉ ወደ እሱ እንድትቀርቡ ማድረጉ ቀላል ነገር ነው? ታዲያ የክህነት አገልግሎቱንም ለመጠቅለል መሞከር ይገባችኋል?+ 11 ስለዚህ አንተም ሆንክ አብረውህ የተሰበሰቡት ግብረ አበሮችህ በሙሉ ይሖዋን እየተቃወማችሁ ነው። በአሮን ላይ የምታጉረመርሙት እሱ ምን ስለሆነ ነው?”+
12 ከዚያም ሙሴ የኤልያብን ልጆች ዳታንንና አቤሮንን+ አስጠራቸው፤ እነሱ ግን እንዲህ አሉ፦ “አንመጣም! 13 በምድረ በዳ ልትገድለን ወተትና ማር ከምታፈሰው ምድር ያወጣኸን አይበቃህም?+ አሁን ደግሞ በእኛ ላይ ፈላጭ ቆራጭ* ልትሆን ያምርሃል? 14 ደግሞም ወተትና ማር ወደምታፈስ ምድር+ አላስገባኸንም፤ ወይም እርሻና የወይን የአትክልት ቦታዎችን ርስት አድርገህ አልሰጠኸንም። ታዲያ የእነዚያን ሰዎች ዓይን ልታወጣ ነው? እኛ እንደሆነ አንመጣም!”
15 ስለዚህ ሙሴ እጅግ ተቆጣ፤ ይሖዋንም እንዲህ አለው፦ “የእህል መባቸውን አትመልከት። ከእነዚህ ሰዎች አንድ አህያ እንኳ አልወሰድኩም፤ አንዳቸውንም ቢሆን አልበደልኩም።”+
16 ከዚያም ሙሴ ቆሬን እንዲህ አለው፦ “አንተና ግብረ አበሮችህ በሙሉ ነገ በይሖዋ ፊት ቅረቡ፤ አንተም ሆንክ እነሱ እንዲሁም አሮን መቅረብ ይኖርባችኋል። 17 እያንዳንዱ ሰው የየራሱን የዕጣን ማጨሻ ይያዝ፤ በላዩም ላይ ዕጣን ያድርግበት፤ አንተንና አሮንን ጨምሮ እያንዳንዱ ሰው በይሖዋ ፊት የዕጣን ማጨሻውን ያቀርባል፤ ይህም በአጠቃላይ 250 የዕጣን ማጨሻዎች ማለት ነው፤ እያንዳንዱም የየራሱን የዕጣን ማጨሻ ይዞ ይቀርባል።” 18 ስለዚህ እያንዳንዳቸው የዕጣን ማጨሻቸውን ይዘው መጡ፤ በላዩም ላይ እሳትና ዕጣን አደረጉበት፤ ከዚያም ከሙሴና ከአሮን ጋር በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ቆሙ። 19 ቆሬ፣ ግብረ አበሮቹ+ በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ሙሴንና አሮንን በመቃወም እንዲሰበሰቡ ባደረገ ጊዜ የይሖዋ ክብር ለመላው ማኅበረሰብ ተገለጠ።+
20 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 21 “በአንዴ ጠራርጌ እንዳጠፋቸው ራሳችሁን ከዚህ ቡድን ለዩ።”+ 22 እነሱም በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፍተው እንዲህ አሉ፦ “አምላክ ሆይ፣ አንተ የሰው ሁሉ መንፈስ* አምላክ ነህ፤+ ታዲያ አንድ ሰው በሠራው ኃጢአት የተነሳ በመላው ማኅበረሰብ ላይ ትቆጣለህ?”+
23 ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 24 “ለማኅበረሰቡ ‘ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን+ ድንኳኖች አካባቢ ራቁ!’ ብለህ ንገራቸው።”
25 ሙሴም ተነስቶ ወደ ዳታንና አቤሮን ሄደ፤ የእስራኤል ሽማግሌዎችም+ አብረውት ሄዱ። 26 ከዚያም ማኅበረሰቡን እንዲህ አላቸው፦ “በኃጢአታቸው ተጠራርጋችሁ እንዳትጠፉ እባካችሁ፣ ከእነዚህ ክፉ ሰዎች ድንኳኖች ራቁ፤ የእነሱ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትንኩ።” 27 እነሱም ወዲያውኑ ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳኖች፣ ከዙሪያቸውም ሁሉ ራቁ፤ ዳታንና አቤሮንም ወጥተው ከሚስቶቻቸው፣ ከልጆቻቸውና ከሕፃኖቻቸው ጋር በድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆሙ።
28 ሙሴም እንዲህ አለ፦ “እነዚህን ነገሮች ሁሉ የማደርገው ከልቤ አመንጭቼ ሳይሆን* ይሖዋ ልኮኝ መሆኑን በዚህ ታውቃላችሁ፦ 29 እነዚህ ሰዎች እንደ ማንኛውም ሰው አሟሟት የሚሞቱ ከሆነና የሚደርስባቸውም ቅጣት በሌሎች ሰዎች ሁሉ ላይ የሚደርስ ዓይነት ከሆነ እኔን ይሖዋ አላከኝም ማለት ነው።+ 30 ሆኖም ይሖዋ በእነሱ ላይ እንግዳ የሆነ ነገር ቢያደርግና መሬት አፏን ከፍታ እነሱንም ሆነ የእነሱ የሆነውን ነገር ሁሉ ብትውጥ፣ በሕይወት እንዳሉም ወደ መቃብር* ቢወርዱ፣ እነዚህ ሰዎች ይሖዋን እንደናቁ በእርግጥ ታውቃላችሁ።”
31 እሱም ይህን ተናግሮ እንደጨረሰ፣ የቆሙባት ምድር ተሰነጠቀች።+ 32 ምድሪቱም አፏን ከፍታ እነሱን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ የቆሬ የሆነውን ማንኛውንም ሰውና+ ንብረታቸውን ሁሉ ዋጠች። 33 በዚህ መንገድ እነሱም ሆኑ የእነሱ የሆኑት ሁሉ በሕይወት እንዳሉ ወደ መቃብር* ወረዱ፤ ምድርም ተከደነችባቸው፤ ስለዚህ ከጉባኤው መካከል ጠፉ።+ 34 በዙሪያቸው የነበሩት እስራኤላውያን በሙሉ ጩኸታቸውን ሲሰሙ “ኧረ ምድሪቱ እኛንም እንዳትውጠን!” በማለት መሸሽ ጀመሩ። 35 ከዚያም ከይሖዋ ዘንድ እሳት መጥቶ+ ዕጣን ሲያጥኑ የነበሩትን 250 ሰዎች በላ።+
36 በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 37 “የዕጣን ማጨሻዎቹ+ ቅዱስ ስለሆኑ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ከእሳቱ ውስጥ እንዲያወጣቸው ንገረው። በተጨማሪም እሳቱን ራቅ አድርጎ እንዲበትነው ንገረው። 38 ኃጢአት በመሥራታቸው የተነሳ ሕይወታቸውን የከፈሉት* ሰዎች ይዘዋቸው የነበሩት የዕጣን ማጨሻዎች ቅዱስ ስለሆኑ ለመሠዊያው መለበጫ+ እንዲያገለግሉ በስሱ ይጠፍጠፉ፤ ምክንያቱም በይሖዋ ፊት ስላቀረቧቸው ቅዱስ ሆነዋል። ለእስራኤላውያንም ምልክት ሆነው ያገልግሉ።”+ 39 ስለሆነም ካህኑ አልዓዛር በእሳት የተቃጠሉት ሰዎች ያቀረቧቸውን የመዳብ የዕጣን ማጨሻዎች ወሰደ፤ ከዚያም መሠዊያውን ለመለበጥ በስሱ ጠፈጠፋቸው፤ 40 ይህን ያደረገውም ይሖዋ በሙሴ በኩል ለእሱ በነገረው መሠረት ነው። ይህም የአሮን ዘር ያልሆነ ማንኛውም ያልተፈቀደለት ሰው* በይሖዋ ፊት ዕጣን ለማጨስ እንዳይቀርብ+ እንዲሁም ማንም ሰው እንደ ቆሬና እንደ ግብረ አበሮቹ እንዳይሆን ለእስራኤላውያን ማሳሰቢያ እንዲሆን ነው።+
41 በማግስቱም መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ “እናንተ ሰዎች የይሖዋን ሕዝብ ገድላችኋል” በማለት በሙሴና በአሮን ላይ ያጉረመርም ጀመር።+ 42 የእስራኤልም ማኅበረሰብ ሙሴንና አሮንን በመቃወም በተሰበሰበ ጊዜ ወደ መገናኛ ድንኳኑ ዞር ብሎ ሲመለከት፣ የመገናኛ ድንኳኑን ደመና ሸፍኖት አየ፤ የይሖዋም ክብር ተገለጠ።+
43 ሙሴና አሮንም ወደ መገናኛ ድንኳኑ ፊት መጡ፤+ 44 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 45 “በአንዴ እንዳጠፋቸው+ ራሳችሁን ከዚህ ማኅበረሰብ ለዩ።” እነሱም በዚህ ጊዜ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፉ።+ 46 ከዚያም ሙሴ አሮንን እንዲህ አለው፦ “የዕጣን ማጨሻ ውሰድና ከመሠዊያው ላይ እሳት አድርግበት፤+ በላዩም ላይ ዕጣን ጨምርበት፤ ፈጥነህም ወደ ማኅበረሰቡ በመሄድ አስተሰርይላቸው፤+ ምክንያቱም ይሖዋ ተቆጥቷል። መቅሰፍቱ ጀምሯል!” 47 አሮን ልክ ሙሴ እንዳለው ወዲያውኑ የዕጣን ማጨሻውን ይዞ ወደ ጉባኤው መካከል እየሮጠ ገባ፤ መቅሰፍቱ በሕዝቡ መካከል ጀምሮ ነበር። በመሆኑም ዕጣኑን በዕጣን ማጨሻው ላይ በማድረግ ለሕዝቡ ማስተሰረይ ጀመረ። 48 እሱም በሞቱትና በሕይወት ባሉት መካከል ቆመ፤ መቅሰፍቱም ቀስ በቀስ ቆመ። 49 በቆሬ ምክንያት የሞቱትን ሳይጨምር በመቅሰፍቱ የሞቱት ሰዎች ብዛት 14,700 ነበር። 50 በመጨረሻም አሮን በመገናኛ ድንኳኑ መግቢያ ላይ ወደነበረው ወደ ሙሴ ሲመለስ መቅሰፍቱ ቆሞ ነበር።