61 የሉዓላዊው ጌታ የይሖዋ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤+
ምክንያቱም ይሖዋ የዋህ ለሆኑ ሰዎች ምሥራች እንድናገር ቀብቶኛል።+
ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣
ለተማረኩት ነፃነትን እንዳውጅ
እንዲሁም ‘የእስረኞች ዓይን ይከፈታል’ ብዬ እንድናገር ልኮኛል፤+
2 ይሖዋ በጎ ፈቃድ የሚያሳይበትን ዓመት፣
አምላካችን የሚበቀልበትንም ቀን እንዳውጅ፣+
የሚያለቅሱትንም ሁሉ እንዳጽናና ልኮኛል፤+
3 በጽዮን የተነሳ ላዘኑት
በአመድ ፋንታ የራስ መሸፈኛ፣
በሐዘን ፋንታ የደስታ ዘይት፣
በተደቆሰም መንፈስ ፋንታ የውዳሴ ልብስ እንድሰጥ ልኮኛል።
እነሱም ይሖዋ ራሱን ክብር ለማጎናጸፍ
የተከላቸው ትላልቅ የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ።+
4 የጥንቶቹን ፍርስራሾች መልሰው ይገነባሉ፤
በቀድሞዎቹ ጊዜያት ባድማ የሆኑትን ቦታዎች ይሠራሉ፤+
የወደሙትን ከተሞች፣
ከትውልድ እስከ ትውልድም ፈራርሰው የቆዩትን ቦታዎች መልሰው ይገነባሉ።+
5 “እንግዳ ሰዎች መጥተው መንጎቻችሁን ይጠብቃሉ፤
የባዕድ አገር ሰዎችም+ ገበሬዎቻችሁና የወይን አትክልት ሠራተኞቻችሁ ይሆናሉ።+
6 እናንተም የይሖዋ ካህናት ተብላችሁ ትጠራላችሁ፤+
የአምላካችን አገልጋዮች ብለው ይጠሯችኋል።
የብሔራትን ሀብት ትበላላችሁ፤+
በእነሱም ክብር ትኮራላችሁ።
7 በኀፍረት ፋንታ እጥፍ ድርሻ ይኖራችኋል፤
በውርደትም ፋንታ በሚያገኙት ድርሻ በደስታ እልል ይላሉ።
አዎ፣ በምድራቸው እጥፍ ድርሻ ይወርሳሉ።+
የዘላለም ሐሴት የእነሱ ይሆናል።+
8 እኔ ይሖዋ ፍትሕን እወዳለሁና፤+
ዝርፊያንና ክፋትን እጠላለሁ።+
ደሞዛቸውን በታማኝነት እሰጣቸዋለሁ፤
ከእነሱም ጋር ዘላለማዊ ቃል ኪዳን አደርጋለሁ።+
9 ዘሮቻቸው በብሔራት፣
ልጆቻቸውም በሕዝቦች መካከል የታወቁ ይሆናሉ።+
የሚያዩአቸው ሁሉ
ይሖዋ የባረካቸው ዘሮች እንደሆኑ ይገነዘባሉ።”+
10 እኔ በይሖዋ እጅግ ደስ ይለኛል።
ሁለንተናዬ በአምላኬ ሐሴት ያደርጋል።+
የመዳንን መጎናጸፊያ አልብሶኛልና፤+
የካህን ዓይነት ጥምጥም+ እንደሚያደርግ ሙሽራ፣
በጌጣጌጧም ራሷን እንዳስዋበች ሙሽሪት
የጽድቅ ቀሚስ አልብሶኛል።
11 ምድር ቡቃያዋን እንደምታበቅል፣
የአትክልት ቦታም በላዩ ላይ የተዘሩትን ዘሮች እንደሚያበቅል
ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋም
በብሔራት ሁሉ ፊት ጽድቅንና+ ውዳሴን ያበቅላል።+