የሉቃስ ወንጌል
17 ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “ሰዎችን የሚያሰናክሉ ነገሮች መከሰታቸው የማይቀር ነው። ሆኖም ለመሰናክሉ ምክንያት ለሚሆነው ለዚያ ሰው ወዮለት! 2 ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ከሚያሰናክል የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል።+ 3 ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው፤+ ከተጸጸተም ይቅር በለው።+ 4 በቀን ሰባት ጊዜ ቢበድልህ እንኳ ‘ተጸጽቻለሁ’ እያለ ሰባት ጊዜ ወደ አንተ ከመጣ ይቅር ልትለው ይገባል።”+
5 በዚህ ጊዜ ሐዋርያቱ ጌታን “እምነት ጨምርልን” አሉት።+ 6 ጌታም እንዲህ አለ፦ “የሰናፍጭ ዘር የሚያህል እምነት ካላችሁ ይህን የሾላ ዛፍ ‘ከዚህ ተነቅለህ ባሕሩ ውስጥ ተተከል!’ ብትሉት ይታዘዛችኋል።+
7 “ከእናንተ መካከል አራሽ ወይም እረኛ የሆነ ባሪያ ያለው ሰው ቢኖር፣ ባሪያው ከእርሻ ሲመለስ ‘ቶሎ ናና ወደ ማዕድ ቅረብ’ ይለዋል? 8 ከዚህ ይልቅ ‘ራቴን አዘጋጅልኝ፤ በልቼና ጠጥቼ እስክጨርስም ድረስ አሸርጠህ አገልግለኝ፤ ከዚያ በኋላ መብላትና መጠጣት ትችላለህ’ አይለውም? 9 ባሪያው የተሰጠውን ሥራ በማከናወኑ ጌታው የሚያመሰግነው ይመስላችኋል? 10 በተመሳሳይ እናንተም የተሰጣችሁን ሥራ ሁሉ ባከናወናችሁ ጊዜ ‘ምንም የማንጠቅም ባሪያዎች ነን። ያደረግነው ልናደርገው የሚገባንን ነገር ነው’ በሉ።”+
11 ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄደ ሳለ በሰማርያና በገሊላ መካከል አለፈ። 12 ወደ አንድ መንደር እየገባም ሳለ የሥጋ ደዌ የያዛቸው አሥር ሰዎች አዩት፤ እነሱም በርቀት ቆሙ።+ 13 ድምፃቸውንም ከፍ በማድረግ “ኢየሱስ፣ መምህር፣ ምሕረት አድርግልን!” አሉ። 14 እሱም ባያቸው ጊዜ “ሄዳችሁ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” አላቸው።+ ከዚያም እየሄዱ ሳሉ ነጹ።+ 15 ከእነሱ አንዱ እንደተፈወሰ ባየ ጊዜ አምላክን በታላቅ ድምፅ እያመሰገነ ተመለሰ። 16 ኢየሱስ እግር ላይ ተደፍቶም አመሰገነው። ሰውየውም ሳምራዊ+ ነበር። 17 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ “የነጹት አሥሩም አይደሉም እንዴ? ታዲያ ዘጠኙ የት አሉ? 18 ከዚህ ከባዕድ አገር ሰው በስተቀር አምላክን ለማመስገን የተመለሰ ሌላ አንድም ሰው የለም?” 19 ከዚያም ሰውየውን “ተነስና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል” አለው።+
20 ፈሪሳውያን የአምላክ መንግሥት መቼ እንደሚመጣ ሲጠይቁት+ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “የአምላክ መንግሥት በግልጽ በሚታይ ሁኔታ አይመጣም፤ 21 ሰዎችም ‘እነሆ እዚህ ነው!’ ወይም ‘እዚያ ነው!’ አይሉም። እነሆ፣ የአምላክ መንግሥት በመካከላችሁ ነውና።”+
22 ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ለማየት የምትመኙበት ጊዜ ይመጣል፤ ግን አታዩትም። 23 ሰዎችም ‘እዚያ ነው!’ ወይም ‘እዚህ ነው!’ ይሏችኋል። ነገር ግን አትሂዱ ወይም አትከተሏቸው።+ 24 ምክንያቱም መብረቅ ከአንዱ የሰማይ ክፍል እስከ ሌላኛው የሰማይ ክፍል እንደሚያበራ ሁሉ የሰው ልጅ+ በሚገለጥበትም ቀን እንዲሁ ይሆናል።+ 25 በመጀመሪያ ግን ብዙ መከራ መቀበሉና በዚህ ትውልድ ተቀባይነት ማጣቱ የግድ ነው።+ 26 በተጨማሪም በኖኅ ዘመን+ እንደተከሰተው ሁሉ በሰው ልጅ ዘመንም እንዲሁ ይሆናል፦+ 27 ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበትና+ የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም እስካጠፋበት ቀን+ ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ወንዶች ያገቡ፣ ሴቶችም ይዳሩ ነበር። 28 በተመሳሳይም በሎጥ ዘመን እንደተከሰተው ሁሉ እንዲሁ ይሆናል፦+ ሰዎች ይበሉ፣ ይጠጡ፣ ይገዙ፣ ይሸጡ፣ ይተክሉና ቤቶችን ይገነቡ ነበር። 29 ሆኖም ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ከሰማይ እሳትና ድኝ ዘንቦ ሁሉንም አጠፋቸው።+ 30 የሰው ልጅ በሚገለጥበትም ቀን+ እንዲሁ ይሆናል።
31 “በዚያን ቀን በጣሪያ* ላይ ያለ ሰው በቤቱ ውስጥ ያለውን ዕቃ ለመውሰድ አይውረድ፤ እርሻም ላይ ያለ ሰው በኋላው ያለውን ነገር ለመውሰድ አይመለስ። 32 የሎጥን ሚስት አስታውሱ።+ 33 ሕይወቱን* ጠብቆ ለማቆየት የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፤ ሕይወቱን የሚያጣት ሁሉ ግን በሕይወት ጠብቆ ያቆያታል።+ 34 እላችኋለሁ፣ በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ላይ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላኛው ግን ይተዋል።+ 35 ሁለት ሴቶች በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፤ ሌላኛዋ ግን ትተዋለች።” 36 *—— 37 እነሱም መልሰው “ጌታ ሆይ፣ የት?” አሉት። እሱም “በድን ባለበት ንስሮች ይሰበሰባሉ” አላቸው።+