22 ዳዊት፣ ይሖዋ ከጠላቶቹ ሁሉ እጅና ከሳኦል እጅ+ በታደገው+ ቀን የዚህን መዝሙር ቃል ለይሖዋ ዘመረ።+ 2 እንዲህም አለ፦
“ይሖዋ ቋጥኜ፣ ምሽጌና+ ታዳጊዬ ነው።+
3 አምላኬ የምሸሸግበት ዓለቴ ነው፤+
ጋሻዬ፣+ የመዳኔ ቀንድና አስተማማኝ መጠጊያዬ ነው፤+
መሸሻዬና+ አዳኜ ነው፤+ አንተ ከዓመፅ ታድነኛለህ።
4 ውዳሴ የሚገባውን ይሖዋን እጠራለሁ፤
ከጠላቶቼም እድናለሁ።
5 የሞት ማዕበል ዙሪያዬን ከቦኛል፤+
የማይረቡ ሰዎች የለቀቁት ድንገተኛ ጎርፍ አሸበረኝ።+
6 የመቃብር ገመድ ተጠመጠመብኝ፤+
የሞት ወጥመድ ተጋረጠብኝ።+
7 በጭንቅ ውስጥ ሳለሁ ይሖዋን ጠራሁት፤+
አምላኬን ደጋግሜ ጠራሁት።
እሱም በመቅደሱ ሆኖ ድምፄን ሰማ፣
እርዳታ ለማግኘት የማሰማውም ጩኸት ወደ ጆሮው ደረሰ።+
8 ምድርም ወዲያና ወዲህ ትናወጥና ትንቀጠቀጥ ጀመር፤+
የሰማያት መሠረቶች ተንቀጠቀጡ፤+
እሱ ስለተቆጣም ራዱ።+
9 ከአፍንጫው ጭስ ወጣ፤
የሚባላም እሳት ከአፉ ወጣ፤+
ፍምም ከእሱ ፈለቀ።
10 ወደ ታች ሲወርድ ሰማያት እንዲያጎነብሱ አደረገ፤+
ከእግሮቹም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበር።+
11 በኪሩብ ላይ ተቀምጦ+ እየበረረ መጣ።
በመንፈስ ክንፎችም ላይ ሆኖ ይታይ ነበር።+
12 ከዚያም ጨለማን በዙሪያው እንደ መጠለያ አደረገ፣+
ጨለማውም ጥቁር ውኃና ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረው።
13 በፊቱ ካለው ብርሃን ፍም ፈለቀ።
14 ከዚያም ይሖዋ ከሰማይ ያንጎደጉድ ጀመር፤+
ልዑሉ አምላክ ድምፁን አሰማ።+
15 ፍላጻዎቹን+ አስፈንጥሮ በታተናቸው፤
መብረቁን አብርቆ ግራ አጋባቸው።+
16 በይሖዋ ተግሣጽ፣ ከአፍንጫውም በሚወጣው ኃይለኛ እስትንፋስ+
የባሕር ወለሎች ታዩ፤+
የምድር መሠረቶችም ተገለጡ።
17 ከላይ ሆኖ እጁን ሰደደ፤
ከጥልቅ ውኃ ውስጥም አወጣኝ።+
18 ከብርቱ ጠላቴ አዳነኝ፤+
ከእኔ ይበልጥ ብርቱዎች ከሆኑት፣ ከሚጠሉኝ ሰዎች ታደገኝ።
19 ችግር ላይ በወደቅኩበት ቀን ተነሱብኝ፤+
ይሖዋ ግን ድጋፍ ሆነልኝ።
20 ደህንነት ወደሚገኝበት ስፍራ አመጣኝ፤+
በእኔ ስለተደሰተ ታደገኝ።+
21 ይሖዋ እንደ ጽድቄ ወሮታ ይከፍለኛል፤+
እንደ እጄ ንጽሕና ብድራት ይመልስልኛል።+
22 የይሖዋን መንገድ ጠብቄአለሁና፤
አምላኬን በመተው ክፉ ድርጊት አልፈጸምኩም።
23 ፍርዱ+ ሁሉ በፊቴ ነው፤
ደንቦቹን+ አልተላለፍም።
24 በፊቱ እንከን የለሽ+ ሆኜ እኖራለሁ፤
ራሴንም ከስህተት እጠብቃለሁ።+
25 ይሖዋ እንደ ጽድቄ፣+
በፊቱም እንዳለኝ ንጽሕና ብድራት ይመልስልኝ።+
26 ታማኝ ለሆነ ሰው ታማኝ ትሆናለህ፤+
እንከን የለሽ ለሆነ ኃያል ሰው እንከን የለሽ ትሆናለህ፤+
27 ከንጹሕ ሰው ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤+
ጠማማ ለሆነ ሰው ግን ብልህ መሆንህን ታሳያለህ።+
28 ትሑት የሆኑትን ታድናለህና፤+
ዓይኖችህ ግን በትዕቢተኞች ላይ ናቸው፤ አንተም ታዋርዳቸዋለህ።+
29 ይሖዋ ሆይ፣ አንተ መብራቴ ነህና፤+
ጨለማዬን ብርሃን የሚያደርገው ይሖዋ ነው።+
30 በአንተ እርዳታ ወራሪውን ቡድን መጋፈጥ እችላለሁ፤
በአምላክ ኃይል ቅጥር መውጣት እችላለሁ።+
31 የእውነተኛው አምላክ መንገድ ፍጹም ነው፤+
የይሖዋ ቃል የነጠረ ነው።+
እሱ መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ ጋሻቸው ነው።+
32 ደግሞስ ከይሖዋ ሌላ አምላክ ማን ነው?+
ከአምላካችንስ በቀር ዓለት ማን ነው?+
33 እውነተኛው አምላክ ጠንካራ ምሽጌ ነው፤+
መንገዴንም ፍጹም ያደርግልኛል።+
34 እግሮቼን እንደ ዋልያ እግሮች ያደርጋል፤
በከፍታ ቦታዎች ላይ ያቆመኛል።+
35 እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናል፤
ክንዶቼ የመዳብ ደጋን ማጠፍ ይችላሉ።
36 የመዳን ጋሻህን ትሰጠኛለህ፤
ትሕትናህም ታላቅ ያደርገኛል።+
37 ለእርምጃዬ መንገዱን ታሰፋልኛለህ፤
እግሮቼ አያዳልጣቸውም።+
38 ጠላቶቼን አሳድጄ አጠፋቸዋለሁ፤
ተጠራርገው እስኪጠፉ ድረስ ወደ ኋላ አልመለስም።
39 እንዳያንሰራሩም ጠራርጌ አጠፋቸዋለሁ፣ አደቃቸዋለሁ፤+
እግሬ ሥር ይወድቃሉ።
40 ለውጊያው ብርታት ታስታጥቀኛለህ፤+
ጠላቶቼ ሥሬ እንዲወድቁ ታደርጋለህ።+
41 ጠላቶቼ ከእኔ እንዲሸሹ ታደርጋለህ፤+
እኔም የሚጠሉኝን አጠፋለሁ።+
42 እርዳታ ለማግኘት ይጮኻሉ፤ ሆኖም የሚያድናቸው የለም፤
ወደ ይሖዋም ይጮኻሉ፤ እሱ ግን አይመልስላቸውም።+
43 በምድር ላይ እንዳለ አቧራ አደቃቸዋለሁ፤
በመንገድ ላይ እንዳለ ጭቃ እረግጣቸዋለሁ፤ አደቃቸዋለሁ።
44 ስህተት ከሚለቃቅሙት ሕዝቦቼ ታድነኛለህ።+
የብሔራት መሪ እንድሆን ትጠብቀኛለህ፤+
የማላውቀው ሕዝብ ያገለግለኛል።+
45 ባዕዳንም ተሸማቀው ወደ ፊቴ ይቀርባሉ፤+
ስለ እኔ የሚሰሙትም እንዲታዘዙኝ ያደርጋቸዋል።
46 የባዕድ አገር ሰዎች ወኔ ይከዳቸዋል፤
ከምሽጎቻቸው እየተንቀጠቀጡ ይወጣሉ።
47 ይሖዋ ሕያው ነው! ዓለቴ ይወደስ!+
የመዳኔ ዓለት የሆነው አምላክ ከፍ ከፍ ይበል።+
48 እውነተኛው አምላክ ይበቀልልኛል፤+
ሕዝቦችንም ከበታቼ ያስገዛልኛል፤+
49 እሱ ከጠላቶቼ ያድነኛል።
ከሚያጠቁኝ ሰዎች በላይ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፤+
ከዓመፀኛ ሰው ታድነኛለህ።+
50 ይሖዋ ሆይ፣ በብሔራት መካከል የማመሰግንህ ለዚህ ነው፤+
ለስምህም እንዲህ ብዬ የውዳሴ መዝሙር እዘምራለሁ፦+
51 ለንጉሡ ታላላቅ የማዳን ሥራዎችን ያከናውናል፤+
ለቀባውም ታማኝ ፍቅር ያሳያል፤
ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም ይህን ያደርጋል።”+