ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ
6 ስለዚህ ስለ ክርስቶስ ከተማርነው መሠረታዊ ትምህርት አልፈን ስለሄድን+ ወደ ጉልምስና ለመድረስ እንጣጣር፤+ መሠረትን ደግመን አንመሥርት፤ ይኸውም ከሞቱ ሥራዎች ንስሐ ስለ መግባት፣ በአምላክ ስለ ማመን፣ 2 እንዲሁም ስለ ጥምቀቶች፣ እጆችን ስለ መጫን፣+ ስለ ሙታን ትንሣኤና+ ስለ ዘላለማዊ ፍርድ የሚገልጹ ትምህርቶችን ደግመን አንማር። 3 አምላክ ከፈቀደ ይህን እናደርጋለን።
4 ቀደም ሲል ብርሃን በርቶላቸው የነበሩትን፣+ ሰማያዊውን ነፃ ስጦታ የቀመሱትን፣ መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉትን፣ 5 መልካም የሆነውን የአምላክ ቃልና በሚመጣው ሥርዓት* የሚገኙትን በረከቶች* የቀመሱትን፣ 6 በኋላ ግን ከእምነት ጎዳና የራቁትን+ እንደገና ወደ ንስሐ መመለስ አይቻልም፤ ምክንያቱም የአምላክን ልጅ ለራሳቸው እንደገና በእንጨት ላይ ይቸነክሩታል፤ እንዲሁም በአደባባይ ያዋርዱታል።+ 7 በየጊዜው በላዩ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የሚጠጣና ለአራሾቹ መብል የሚሆን አትክልት የሚያፈራ መሬት ከአምላክ በረከትን ያገኛልና። 8 እሾህና አሜኬላ የሚያበቅል ከሆነ ግን የተተወና ለመረገም የተቃረበ ይሆናል፤ በመጨረሻም በእሳት ይቃጠላል።
9 ይሁን እንጂ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ምንም እንኳ እንደዚህ ብለን ብንናገርም እናንተ በተሻለ ሁኔታ ላይ ይኸውም ወደ መዳን በሚያደርስ ሁኔታ ላይ እንደምትገኙ እርግጠኞች ነን። 10 አምላክ ቅዱሳንን በማገልገልም* ሆነ ወደፊትም ማገልገላችሁን በመቀጠል የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር+ በመርሳት ፍትሕ አያዛባም። 11 ይሁንና ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ የሆነውን ተስፋ+ እስከ መጨረሻው መያዝ እንድትችሉ+ እያንዳንዳችሁ ያንኑ ትጋት እንድታሳዩ እንመኛለን፤ 12 ይህም አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች በእምነትና በትዕግሥት የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ነው።+
13 አምላክ ለአብርሃም ቃል በገባለት ጊዜ ሊምልበት የሚችል ከእሱ የሚበልጥ ሌላ ማንም ስለሌለ በራሱ ስም ማለ፤+ 14 እንዲህም አለ፦ “በእርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም በእርግጥ አበዛዋለሁ።”+ 15 በመሆኑም አብርሃም በትዕግሥት ከጠበቀ በኋላ ይህን የተስፋ ቃል አገኘ። 16 ሰዎች ከእነሱ በሚበልጥ ይምላሉ፤ መሐላቸውም እንደ ሕጋዊ ዋስትና ስለሆነ ማንኛውም ሙግት በመሐላው ይቋጫል።+ 17 በተመሳሳይም አምላክ ዓላማው ፈጽሞ የማይለወጥ መሆኑን ለተስፋው ቃል ወራሾች+ ይበልጥ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ለማሳየት በወሰነ ጊዜ የተስፋውን ቃል በመሐላ አረጋገጠ። 18 ይህን ያደረገው መጠጊያ ለማግኘት ወደ እሱ የሸሸን እኛ፣ አምላክ ሊዋሽ በማይችልባቸው፣+ ፈጽሞ በማይለወጡት በእነዚህ ሁለት ነገሮች አማካኝነት በፊታችን ያለውን ተስፋ አጥብቀን እንድንይዝ የሚረዳንን ከፍተኛ ማበረታቻ እንድናገኝ ነው። 19 እኛ ለነፍሳችን* እንደ መልሕቅ አስተማማኝና ጽኑ የሆነ ይህ ተስፋ አለን፤+ ተስፋውም መጋረጃውን አልፎ ወደ ውስጥ ይገባል፤+ 20 ከመልከጼዴቅ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ለዘላለም ሊቀ ካህናት+ የሆነው ኢየሱስ+ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ስለ እኛ ወደዚያ ገብቷል።