12 ተግሣጽን የሚወድ እውቀትን ይወዳል፤+
ወቀሳን የሚጠላ ግን የማመዛዘን ችሎታ ይጎድለዋል።+
2 ጥሩ ሰው የይሖዋን ሞገስ ያገኛል፤
ክፋት የሚያሴርን ሰው ግን እሱ ይፈርድበታል።+
3 በክፋት ጸንቶ መቆም የሚችል ሰው የለም፤+
ጻድቅ ግን ፈጽሞ አይነቀልም።
4 ጥሩ ሚስት ለባሏ ዘውድ ናት፤+
አሳፋሪ ሚስት ግን አጥንቱ ውስጥ እንዳለ ንቅዘት ናት።+
5 የጻድቃን ሐሳብ ፍትሐዊ ነው፤
የክፉዎች ምክር ግን አሳሳች ነው።
6 የክፉዎች ቃል ገዳይ ወጥመድ ነው፤+
የቅኖች አፍ ግን ይታደጋቸዋል።+
7 ክፉዎች ሲገለበጡ ደብዛቸው ይጠፋል፤
የጻድቃን ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል።+
8 ሰው አስተዋይ በሆነ አንደበቱ ይመሰገናል፤+
ልቡ ጠማማ የሆነ ግን ይናቃል።+
9 የሚበላው ሳይኖረው ራሱን ከፍ ከፍ ከሚያደርግ ሰው ይልቅ
አገልጋይ ኖሮት ራሱን ዝቅ አድርጎ የሚኖር ሰው ይሻላል።+
10 ጻድቅ የቤት እንስሳቱን ይንከባከባል፤+
ክፉዎች ግን ርኅራኄያቸው እንኳ ጭካኔ ነው።
11 መሬቱን የሚያርስ ሰው የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል፤+
ከንቱ ነገሮችን የሚያሳድድ ግን ማስተዋል ይጎድለዋል።
12 ክፉ ሰው፣ ሌሎች መጥፎ ሰዎች ባጠመዱት ነገር ይቀናል፤
የጻድቃን ሥር ግን ፍሬ ያፈራል።
13 መጥፎ ሰው በክፉ ንግግሩ ይጠመዳል፤+
ጻድቅ ግን ከመከራ ያመልጣል።
14 ሰው ከአፉ ፍሬ መልካም ነገር ይጠግባል፤+
የእጁ ሥራም ብድራት ይከፍለዋል።
15 የሞኝ መንገድ በራሱ ዓይን ትክክል ነው፤+
ጥበበኛ ግን ምክር ይቀበላል።+
16 ሞኝ ሰው ቁጣውን ወዲያውኑ ይገልጻል፤+
ብልህ ሰው ግን ስድብን ችላ ብሎ ያልፋል።
17 ታማኝ ምሥክር እውነቱን ይናገራል፤
ውሸታም ምሥክር ግን ያታልላል።
18 ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤
የጥበበኞች ምላስ ግን ፈውስ ነው።+
19 እውነት የሚናገሩ ከንፈሮች ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ፤+
ሐሰተኛ ምላስ ግን የሚቆየው ለቅጽበት ብቻ ነው።+
20 ተንኮል በሚሸርቡ ሰዎች ልብ ውስጥ ማታለያ አለ፤
ሰላምን የሚያራምዱ ግን ደስተኞች ናቸው።+
21 ጻድቅ ምንም ዓይነት ጉዳት አያገኘውም፤+
የክፉዎች ሕይወት ግን በመከራ የተሞላ ይሆናል።+
22 ይሖዋ ውሸታም ከንፈሮችን ይጸየፋል፤+
በታማኝነት የሚመላለሱ ግን ደስ ያሰኙታል።
23 ብልህ ሰው እውቀቱን ይሰውራል፤
የሞኝ ልብ ግን ሞኝነቱን ይዘከዝካል።+
24 የትጉ ሰዎች እጅ ገዢ ትሆናለች፤+
ሥራ ፈት እጆች ግን ለባርነት ይዳረጋሉ።+
25 በሰው ልብ ውስጥ ያለ ጭንቀት ልቡ እንዲዝል ያደርገዋል፤+
መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።+
26 ጻድቅ የግጦሽ መሬቱን በሚገባ ይቃኛል፤
የክፉዎች መንገድ ግን እንዲባዝኑ ያደርጋቸዋል።
27 ሰነፍ ሰው አደኑን አሳድዶ አይዝም፤+
ትጋት ግን የሰው ውድ ሀብት ነው።
28 የጽድቅ ጎዳና ወደ ሕይወት ይመራል፤+
በጎዳናው ላይ ሞት የለም።