14 ጥበበኛ ሴት ቤቷን ትገነባለች፤+
ሞኝ ሴት ግን በገዛ እጇ ታፈርሰዋለች።
2 አካሄዱ ቅን የሆነ ሰው ይሖዋን ይፈራል፤
መንገዱ መሠሪ የሆነ ግን ይንቀዋል።
3 በሞኝ ሰው አፍ የትዕቢት በትር አለ፤
የጥበበኞች ከንፈር ግን ትጠብቃቸዋለች።
4 ከብት በሌለበት ግርግሙ ንጹሕ ይሆናል፤
የበሬ ጉልበት ግን ብዙ ምርት ያስገኛል።
5 ሐቀኛ ምሥክር አይዋሽም፤
ሐሰተኛ ምሥክር ግን ባወራ ቁጥር ይዋሻል።+
6 ፌዘኛ ጥበብን ይፈልጋል፤ ሆኖም አያገኛትም፤
አስተዋይ ሰው ግን እውቀትን በቀላሉ ያገኛል።+
7 ከሞኝ ሰው ራቅ፤
ከከንፈሮቹ ምንም ዓይነት እውቀት አታገኝምና።+
8 ብልህ ሰው የሚሄድበትን መንገድ በጥበብ ያስተውላል፤
ሞኞች ግን በቂልነታቸው ይታለላሉ።+
9 ሞኞች በደል ፈጽመው ያፌዛሉ፤+
ቅኖች ግን እርቅ ለመፍጠር ፈቃደኞች ናቸው።
10 ልብ የራሱን ምሬት ያውቃል፤
ደስታውንም ሌላ ሰው ሊጋራው አይችልም።
11 የክፉዎች ቤት ይወድማል፤+
የቅኖች ድንኳን ግን ይበለጽጋል።
12 ለሰው ትክክለኛ መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤+
በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ይመራል።+
13 አንድ ሰው እየሳቀ እንኳ ልቡ ሊያዝን ይችላል፤
ደስታም በሐዘን ሊቋጭ ይችላል።
14 በልቡ ጋጠወጥ የሆነ ሰው አካሄዱ የሚያስከትለውን መዘዝ ይቀበላል፤+
ጥሩ ሰው ግን የሥራውን ውጤት ያገኛል።+
15 ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል፤
ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል።+
16 ጥበበኛ ሰው ጠንቃቃ ነው፤ ከክፉም ይርቃል፤
ሞኝ ግን ደንታ ቢስ ነው፤ ደግሞም ከልክ በላይ በራሱ ይመካል።
17 ለቁጣ የሚቸኩል ሰው የሞኝነት ተግባር ይፈጽማል፤+
በጥሞና የሚያስብ ሰው አይወደድም።
18 ተላሎች ሞኝነትን ይወርሳሉ፤
ብልሆች ግን እውቀትን እንደ አክሊል ይጎናጸፋሉ።+
19 መጥፎ ሰዎች በጥሩ ሰዎች ፊት፣
ክፉዎችም በጻድቅ ደጃፍ ይሰግዳሉ።
20 ድሃ በባልንጀሮቹ ዘንድ እንኳ የተጠላ ነው፤+
የባለጸጋ ወዳጆች ግን ብዙ ናቸው።+
21 ባልንጀራውን የሚንቅ ኃጢአት ይሆንበታል፤
ለችግረኞች የሚራራ ግን ደስተኛ ነው።+
22 ተንኮል የሚሸርቡ ሰዎች መንገድ ይስቱ የለም?
መልካም ነገር ለመሥራት የሚያስቡ ሰዎች ግን ታማኝ ፍቅርንና ታማኝነትን ያተርፋሉ።+
23 በትጋት ያከናወኑት ነገር ሁሉ ጥቅም ያስገኛል፤
እንዲሁ ማውራት ግን ችግር ላይ ይጥላል።+
24 የጥበበኞች ዘውድ ሀብታቸው ነው፤
የሞኞች ቂልነት ግን ለከፋ ሞኝነት ይዳርጋል።+
25 እውነተኛ ምሥክር ሕይወትን ይታደጋል፤
አታላይ ግን ባወራ ቁጥር ይዋሻል።
26 ይሖዋን የሚፈራ ሁሉ በማንኛውም ነገር በእሱ ይታመናል፤+
ልጆቹም መጠጊያ ያገኛሉ።+
27 ይሖዋን መፍራት የሕይወት ምንጭ ነው፤
ሰውን ከሞት ወጥመድ እንዲያመልጥ ይረዳዋል።
28 የሕዝብ ብዛት የንጉሥ ግርማ ነው፤+
ተገዢዎች የሌሉት ገዢ ግን ይጠፋል።
29 ቶሎ የማይቆጣ ሰው ትልቅ ማስተዋል አለው፤+
ትዕግሥት የሌለው ሰው ግን ሞኝነቱን ይገልጣል።+
30 የሰከነ ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል፤
ቅናት ግን አጥንትን ያነቅዛል።+
31 ችግረኛን የሚያጭበረብር ፈጣሪውን ይሰድባል፤+
ለድሃ የሚራራ ሁሉ ግን አምላክን ያከብራል።+
32 ክፉ ሰው በገዛ ክፋቱ ይወድቃል፤
ጻድቅ ግን ንጹሕ አቋሙ መጠጊያ ያስገኝለታል።+
33 ጥበብ በአስተዋይ ልብ ውስጥ በጸጥታ ታርፋለች፤+
በሞኞች መካከል ግን ራሷን ትገልጣለች።
34 ጽድቅ አንድን ብሔር ከፍ ከፍ ታደርጋለች፤+
ኃጢአት ግን ሕዝብን ታዋርዳለች።
35 ንጉሥ አስተውሎ በሚሠራ አገልጋይ ደስ ይሰኛል፤+
አሳፋሪ ድርጊት በሚፈጽም አገልጋይ ላይ ግን ይቆጣል።+