16 ሰው የልቡን ሐሳብ ያዘጋጃል፤
የሚሰጠው መልስ ግን ከይሖዋ ዘንድ ነው።+
2 ሰው መንገዱ ሁሉ ትክክል መስሎ ይታየዋል፤+
ይሖዋ ግን ውስጣዊ ዓላማን ይመረምራል።+
3 የምታደርገውን ሁሉ ለይሖዋ አደራ ስጥ፤+
ዕቅድህም ሁሉ ይሳካል።
4 ይሖዋ ማንኛውንም ነገር ያዘጋጀው ለራሱ ዓላማ ነው፤
ክፉውም ሰው እንኳ በመዓት ቀን እንዲጠፋ ያደርጋል።+
5 ይሖዋ ኩሩ ልብ ያለውን ሁሉ ይጸየፋል።+
እንዲህ ያለው ሰው ሳይቀጣ እንደማይቀር እርግጠኛ ሁን።
6 በታማኝ ፍቅርና በታማኝነት በደል ይሰረያል፤+
ሰውም ይሖዋን በመፍራት ከክፋት ይርቃል።+
7 ይሖዋ በሰው አካሄድ ደስ በሚሰኝበት ጊዜ
ጠላቶቹ እንኳ ሳይቀሩ ከሰውየው ጋር ሰላም እንዲኖራቸው ያደርጋል።+
8 አግባብ ባልሆነ መንገድ ከሚገኝ ብዙ ገቢ ይልቅ
በጽድቅ የሚገኝ ጥቂት ነገር ይሻላል።+
9 ሰው በልቡ መንገዱን ያቅዳል፤
ይሖዋ ግን አካሄዱን ይመራለታል።+
10 የንጉሥ ከንፈር በመንፈስ ተመርቶ ውሳኔ መስጠት ይገባዋል፤+
ፍትሕን ፈጽሞ ማዛባት የለበትም።+
11 ትክክለኛ መለኪያና ሚዛን ከይሖዋ ናቸው፤
በከረጢት ውስጥ ያሉት መለኪያዎች ሁሉ የእሱ ሥራ ናቸው።+
12 ክፉ ድርጊት በነገሥታት ዘንድ አስጸያፊ ነው፤+
ዙፋን የሚጸናው በጽድቅ ነውና።+
13 ነገሥታት የጽድቅ ንግግር ደስ ያሰኛቸዋል።
ሐቁን የሚናገር ሰው ይወዳሉ።+
14 የንጉሥ ቁጣ እንደ ሞት መልእክተኛ ነው፤+
ጥበበኛ ሰው ግን ቁጣውን ያበርደዋል።+
15 የንጉሥ ፊት ሲፈካ ሰው በደስታ ይኖራል፤
ሞገሱም ዝናብ እንዳዘለ የበልግ ደመና ነው።+
16 ጥበብን ማግኘት ወርቅ ከማግኘት ምንኛ የተሻለ ነው!+
ማስተዋልን ማግኘትም ብር ከማግኘት ይመረጣል።+
17 ቅኖች ከክፋት ጎዳና ይርቃሉ።
መንገዱን የሚጠብቅ ሁሉ በሕይወት ይኖራል።+
18 ኩራት ጥፋትን፣
የትዕቢት መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል።+
19 የትዕቢተኞችን ምርኮ ከመካፈል ይልቅ
ከየዋሆች ጋር የትሕትና መንፈስ ማሳየት ይሻላል።+
20 አንድን ነገር ጠለቅ ብሎ የሚያስተውል ሰው ስኬታማ ይሆናል፤
በይሖዋ የሚታመንም ደስተኛ ነው።
21 ልቡ ጥበበኛ የሆነ ሰው አስተዋይ ይባላል፤+
በደግነት የሚናገርም የማሳመን ችሎታ አለው።+
22 ጥልቅ ማስተዋል ለባለቤቱ የሕይወት ምንጭ ነው፤
ሞኞች ግን በገዛ ሞኝነታቸው ይቀጣሉ።
23 የጥበበኛ ሰው ልብ፣ አንደበቱ ጥልቅ ማስተዋል እንዲኖረው ያደርጋል፤+
ለንግግሩም የማሳመን ችሎታ ይጨምርለታል።
24 ደስ የሚያሰኝ ቃል እንደ ማር እንጀራ ነው፤
ለነፍስ ጣፋጭ፣ ለአጥንትም ፈውስ ነው።+
25 ለሰው ትክክለኛ መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤
በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ይመራል።+
26 ሠራተኛን የምግብ ፍላጎቱ ተግቶ እንዲሠራ ያደርገዋል፤
ረሃቡ እንዲህ እንዲያደርግ ያስገድደዋልና።+
27 የማይረባ ሰው ክፋትን ይምሳል፤+
ንግግሩ እንደሚለበልብ እሳት ነው።+
28 ነገረኛ ሰው ጭቅጭቅ ያስነሳል፤+
ስም አጥፊም የልብ ጓደኛሞችን ይለያያል።+
29 ዓመፀኛ ሰው ባልንጀራውን ክፉ ነገር እንዲሠራ ያግባባዋል፤
ወደተሳሳተ መንገድም ይመራዋል።
30 በዓይኑ እየጠቀሰ ተንኮል ይሸርባል።
ከንፈሮቹን ነክሶ ሸር ይሠራል።
31 ሽበት በጽድቅ መንገድ ሲገኝ+
የውበት ዘውድ ነው።+
32 ቶሎ የማይቆጣ ሰው+ ከኃያል ሰው፣
ስሜቱን የሚቆጣጠርም ከተማን ድል ከሚያደርግ ሰው ይሻላል።+
33 ዕጣ ጭን ላይ ይጣላል፤+
ውሳኔውን በሙሉ የሚያስተላልፈው ግን ይሖዋ ነው።+