‘ጥበብ ጥላ ከለላ ነው’
ምሳሌ 16:16 “ከወርቅ ይልቅ ጥበብን ማግኘት፣ ከብርም ማስተዋልን መምረጥ ምንኛ ይበልጣል!” በማለት ይናገራል። ጥበብ ይህን ያህል ጠቃሚ የሆነችው ለምንድን ነው? ምክንያቱም “ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ጥበብም ጥላ ከለላ ነው፤ የዕውቀት ብልጫዋ ግን፣ ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት መጠበቋ ነው።” (መክብብ 7:12) ይሁንና ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት የምትጠብቀው እንዴት ነው?
አምላካዊ ጥበብ ማግኘታችን ማለትም የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ትክክለኛ እውቀት መቅሰማችንና ከዚህ እውቀት ጋር የሚስማማ ተግባር ማከናወናችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ባለው መንገድ እንድንመላለስ ይረዳናል። (ምሳሌ 2:10-12) የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን “የቅኖች ጐዳና ከክፋት የራቀ ነው፤ መንገዱንም የሚጠብቅ ሕይወቱን ይጠብቃል” ብሏል። (ምሳሌ 16:17) አዎን፣ ጥበብ ባለቤቷን ከመጥፎ መንገድ የምትጠብቀው ከመሆኑም በላይ ሕይወቱን ታድነዋለች! በምሳሌ 16:16-33 ላይ እጥር ምጥን ብለው የተቀመጡት ጥበብ አዘል ምክሮች አምላካዊ ጥበብ በባሕርያችን፣ በንግግራችንና በድርጊታችን ላይ ሊያሳድር የሚችለውን በጎ ተጽዕኖ ያሳያሉ።a
‘የተዋረደ መንፈስ’ ይኑራችሁ
በሰው የተመሰለችው ጥበብ “እኔም ትዕቢትንና እብሪትን . . . እጠላለሁ” በማለት እንደተናገረች ተደርጎ ተገልጿል። (ምሳሌ 8:13) እብሪትና ጥበብ ፍጹም ተቃራኒ ናቸው። በመሆኑም በጥበብ መመላለስ እንዲሁም የትዕቢትና የእብሪት ባሕርይ እንዳናዳብር መጠንቀቅ ያስፈልገናል። በተለይ ደግሞ በአንዳንድ የሕይወታችን ዘርፎች ተሳክቶልን አሊያም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ አግኝተን ከሆነ እንዲህ ያለ ባሕርይ እንዳይታይብን መጠንቀቅ ይኖርብናል።
ምሳሌ 16:18 “ትዕቢት ጥፋትን፣ የእብሪት መንፈስም ውድቀትን ትቀድማለች” በማለት ያስጠነቅቃል። ራሱን ሰይጣን ዲያብሎስ ባደረገው የአምላክ ፍጹም መንፈሳዊ ልጅ ላይ የደረሰውን ውድቀት ተመልከት። በእሱ ላይ የደረሰው ጥፋት በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ ተወዳዳሪ የለውም። (ዘፍጥረት 3:1-5፤ ራእይ 12:9) ሰይጣን ለውድቀት ከመዳረጉ በፊት የእብሪት መንፈስ አላሳየም? መጽሐፍ ቅዱስ አንድ አዲስ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ሆኖ መሾም የማይኖርበት ለምን እንደሆነ ሲገልጽ “በትዕቢት ተነፍቶ ዲያብሎስ በወደቀበት ፍርድ እንዳይወድቅ” ማለቱ ሰይጣን እንዲህ ያለ መንፈስ እንዳሳየ ይጠቁማል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1, 2, 6) ሌሎች የኩራት መንፈስ እንዲያድርባቸው ከማድረግ መቆጠባችን ብሎም ይህ መንፈስ በውስጣችን እንዳያድግ ራሳችንን መጠበቃችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!
ምሳሌ 16:19 “በተዋረደ መንፈስ ከተጨቈኑት ጋር መሆን፣ ከትዕቢተኞች [“ራሳቸውን ከፍ ከፍ ከሚያደርጉ፣” NW] ጋር ብዝበዛን ከመካፈል ይሻላል” በማለት ይናገራል። የጥንቷ ባቢሎን ንጉሥ በነበረው በናቡከደነፆር ላይ የደረሰው ሁኔታ የዚህን ምክር ትክክለኝነት ያረጋግጣል። ናቡከደነፆር በኩራት ተነሳስቶ በዱራ ሜዳ ላይ አንድ ግዙፍ ምስል አሠርቶ ነበር። ምስሉ እሱን የሚወክል ሳይሆን አይቀርም። ይህ ሐውልት 27 ሜትር የሚደርስ ቁመት ስለነበረው ምናልባትም የቆመው በትልቅ መሠረት ላይ ይሆናል። (ዳንኤል 3:1) አስደናቂ የሆነው ይህ ግዙፍ ሐውልት የናቡከደነፆር ግዛት መለያ ምልክት ነበር። ናቡከደነፆር ያሠራውን ምስል፣ ሐውልቶችን፣ ጉልላቶችንና ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎችን የመሳሰሉ በጣም ረጃጅምና ግዙፍ ነገሮች ሰዎችን ያስደምሙ ይሆናል፤ አምላክ ግን በእነዚህ ነገሮች አይደነቅም። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] በከፍታ ስፍራ ቢሆንም፣ ዝቅ ያለውን ይመለከተዋል፤ ትዕቢተኛውን ከሩቅ ያውቀዋል” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 138:6) እንዲያውም “በሰዎች ዘንድ የከበረ፣ በእግዚአብሔር ፊት የረከሰ ነው።” (ሉቃስ 16:15) በመሆኑም ‘ከትዕቢት’ ይልቅ ‘የትሕትናን ነገር ማሰባችን’ የተሻለ ይሆናል።—ሮሜ 12:16 የ1954 ትርጉም
‘ማስተዋል በታከለበትና አሳማኝ በሆነ መንገድ’ ተናገሩ
ጥበብን ማግኘት በአነጋገራችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? ጠቢቡ ንጉሥ እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “አንድን ነገር ጠለቅ ብሎ የሚያስተውል መልካም ነገርን ያገኛል፤ በይሖዋ የሚታመንም ደስተኛ ነው። ልቡ ጥበበኛ የሆነ አስተዋይ ይባላል፤ ከንፈሩ ጣፋጭ የሆነም የማሳመን ችሎታ አለው። ጥልቅ ማስተዋል ለባለቤቱ የሕይወት ምንጭ ነው፤ የሞኞች ቅጣት ራሱ ሞኝነታቸው ነው። የጥበበኛ ሰው ልብ፣ አንደበቱ ጥልቅ ማስተዋል እንዲያንጸባርቅ ያደርጋል፤ ለከንፈሩም የማሳመን ቸሎታ ይጨምርለታል።”—ምሳሌ 16:20-23 NW
ጥበብ ማስተዋል በታከለበትና አሳማኝ በሆነ መንገድ መናገር እንድንችል ይረዳናል። ለምን? ምክንያቱም ልቡ ጥበበኛ የሆነ ሰው በአንድ ጉዳይ ላይ “መልካም ነገርን” ለማግኘት የሚሞክር ከመሆኑም በላይ ‘በይሖዋ ይታመናል።’ የሌሎችን መልካም ጎን ለማየት ጥረት ስናደርግ ስለ እነሱ የምንናገረው ነገር ይበልጥ አዎንታዊ እየሆነ ይሄዳል። ቃላቶቻችን ደግነት የጎደላቸውና ቁጣ የሚንጸባረቅባቸው ከመሆን ይልቅ ጣፋጭና አሳማኝ ይሆናሉ። ሌሎች ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ ጠለቅ ብለን ማስተዋላችን፣ እየደረሰባቸው ያለውን ችግርና ይህንንም እንዴት እየተቋቋሙት እንዳሉ እንድንገነዘብ ይረዳናል።
ጥበብ የተንጸባረቀበት አነጋገር ከስብከትና ደቀ መዛሙርት ከማድረግ ሥራችን ጋር በተያያዘም በጣም አስፈላጊ ነው። የአምላክን ቃል ለሌሎች ስናስተምር ዓላማችን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ ማስተላለፍ ብቻ አይደለም። ግባችን የሰዎቹን ልብ መንካት ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ አሳማኝ በሆነ መንገድ መናገር ያስፈልጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ የሥራ ባልደረባው ለነበረው ጢሞቴዎስ ‘እንዲያምን በተደረገው’ ነገር እንዲጸና ነግሮት ነበር።—2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15 NW
በዊልያም ኧርነስት ቫይን የተዘጋጀው አን ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ “ማሳመን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ምክንያታዊና ተቀባይነት ያለው ማስረጃ በማቅረብ አመለካከትን እንዲለውጡ ማድረግ” የሚል ትርጉም እንዳለው ገልጿል። የአድማጫችንን አእምሮ ለመለወጥ የሚያስችሉ አሳማኝ ማስረጃዎችን ለማቅረብ የግለሰቡን አስተሳሰብ፣ ፍላጎት፣ ችግርና ቀደም ሲል የነበረበትን ሁኔታ ጠለቅ ብሎ ማስተዋል ያስፈልጋል። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን ጥልቅ ማስተዋል ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ . . . ይሁን” በማለት መልሱን ሰጥቷል። (ያዕቆብ 1:19) አድማጫችንን ጥያቄዎች በመጠየቅና የሚናገረውን ትኩረት ሰጥተን በማዳመጥ የሚያሳስበውን ነገር ማወቅ እንችላለን።
ሐዋርያው ጳውሎስ ከፍተኛ የማሳመን ችሎታ ነበረው። (የሐዋርያት ሥራ 18:4) ከተቃዋሚዎቹ አንዱ የነበረው ብር አንጥረኛው ድሜጥሮስ እንኳ ስለ እሱ ሲናገር “በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን፣ በመላው የእስያ አውራጃ የሚገኘውን በርካታ ሕዝብ እያሳመነ [አስቷል]” ብሎ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 19:26) ጳውሎስ በስብከት ሥራው ውጤታማ የሆነው ባለው ችሎታ ምክንያት እንደሆነ ተናግሯል? በፍጹም። የተሰጠው የስብከት ሥራ ‘በአምላክ መንፈስ ኃይል የተደገፈ’ እንደሆነ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 2:4, 5 የ1980 ትርጉም) እኛም ብንሆን የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ አለን። በይሖዋ ስለምንታመን በአገልግሎት በምንካፈልበት ወቅት ማስተዋል በታከለበትና አሳማኝ በሆነ መንገድ ለመናገር ጥረት እስካደረግን ድረስ የእሱ እርዳታ እንደማይለየን እርግጠኞች ነን።
“ልቡ ጥበበኛ የሆነ” ሰው “ብልህ” ወይም “አስተዋይ” መባሉ ምንም አያስደንቅም! (ምሳሌ 16:21 አን አሜሪካን ትራንስሌሽን) አዎን፣ ጥልቅ ማስተዋል፣ ለሚያገኙት ሰዎች “የሕይወት ምንጭ” ነው። ይሁንና ስለ ሞኞችስ ምን ለማለት ይቻላል? እነሱ “ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ።” (ምሳሌ 1:7) እነዚህ ሰዎች የይሖዋን ተግሣጽ ባለመቀበላቸው ምን ይደርስባቸዋል? ከላይ እንደተመለከትነው ሰሎሞን “የሞኞች ቅጣት ራሱ ሞኝነታቸው ነው” ብሏል። (ምሳሌ 16:22 NW) ሞኞች ተጨማሪ ተግሣጽ የሚቀበሉ ሲሆን ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ ከበድ ያለ ቅጣት ያስከትልባቸዋል። ከዚህም በላይ ሞኞች በራሳቸው ላይ ችግር፣ ሃፍረትና በሽታ ሊያመጡ አልፎ ተርፎም ያለ ዕድሜያቸው በሞት ሊቀጩ ይችላሉ።
የእስራኤሉ ንጉሥ፣ ጥበብ በአነጋገራችን ላይ ስለሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ ተጨማሪ ነጥብ ሲጠቅስ “ደስ የሚያሰኝ ቃል የማር ወለላ ነው፤ ለነፍስ ጣፋጭ፣ ለዐጥንትም ፈውስ ነው” ብሏል። (ምሳሌ 16:24) ማር ጣፋጭና ለተራበ ሰው ቶሎ ብርታት የሚሰጥ እንደሆነ ሁሉ ደስ የሚያሰኙ ቃላትም የሚያበረታቱና የሚያነቃቁ ናቸው። በተጨማሪም ማር ለጤና ጠቃሚ ሲሆን የመድኃኒትነት ባሕርይም ስላለው ለአንድ ሰው በጣም አስፈላጊ ነው። በተመሳሳይ ደስ የሚያሰኙ ቃላትም መንፈሳዊ ጤንነት ይጨምራሉ።—ምሳሌ 24:13, 14
‘ቀና መስሎ ከሚታይ መንገድ’ ተጠበቁ
ሰሎሞን “ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤ በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ይመራል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 16:25) ይህ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው የተሳሳተ አስተሳሰብንና ከመለኮታዊው ሕግ ጋር የሚጋጭ አካሄድ መከተልን አስመልክቶ ነው። አንድ መንገድ ከሰዎች አመለካከት አንጻር ሲታይ ትክክል ሊመስል ይችላል፤ ይሁንና ይህ መንገድ በአምላክ ቃል ውስጥ ከሰፈሩት የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ ይሆናል። ከዚህም በላይ ሰይጣን፣ አንድ ሰው ትክክለኛ እንደሆነ ያመነበትን ሆኖም ወደ ሞት የሚመራውን መንገድ እንዲከተል በመገፋፋት እንዲህ ዓይነቱን ማታለያ ያስፋፋ ይሆናል።
ጥበበኛና አስተዋይ ልብ እንዲኖረን ከማድረግ እንዲሁም በአምላክ ቃል እውቀት የሠለጠነ ሕሊና ከማግኘት የተሻለ ራስን ከማታለል መጠበቅ የምንችልበት መንገድ የለም። ከሥነ ምግባር፣ ከአምልኮ ወይም ከሌሎች ነገሮች ጋር በተያያዘ ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ራሳችንን ከማታለል የምንጠበቅበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ አምላክ መልካምንና ክፉን አስመልክቶ ባወጣው መሥፈርት መመራት ነው።
“ሠራተኛን የዕለት ጕርስ ፍላጎቱ ታታሪ ያደርገዋል”
ጠቢቡ ንጉሥ ቀጥሎ “ሠራተኛን የዕለት ጕርስ ፍላጎቱ ታታሪ ያደርገዋል፤ ራቡም ይገፋፋዋል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 16:26) እዚህ ላይ ሰሎሞን አንድ ሠራተኛ ለመመገብ ያለው ፍላጎት ‘ታታሪ እንዲሆን ይገፋፋዋል’ እያለ ነው። ለምግብ ያለን ተፈጥሯዊ ፍላጎት ውጤታማ ሠራተኞች እንድንሆን ሊገፋፋን ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ፍላጎት ጠቃሚ ነው። ይሁን እንጂ ተገቢ የሆነው ፍላጎት ከመጠን አልፎ ስግብግብነት ደረጃ ላይ ቢደርስ ውጤቱ ምን ይሆናል? ይህ ሁኔታ ምግብ ለማብሰል የተቀጣጠለ እሳት ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ሰደድ እሳት ቢያስነሳ ከሚፈጠረው ውጤት ጋር ተመሳሳይ ነው። ስግብግብነት ከቁጥጥር ውጪ የሆነ አጥፊ ባሕርይ ነው። ጥበበኛ ሰው ሊከተል የሚችለውን አደጋ ስለሚገነዘብ ተገቢ በሆኑ ፍላጎቶቹ ላይ እንኳ ሳይቀር ቁጥጥር ያደርጋል።
‘መልካም ባልሆነው’ መንገድ አትሂዱ
እንደሚያቃጥል እሳት ሁሉ ከአፋችን የሚወጡት ቃላትም አጥፊ ሊሆኑ ይችላሉ። ሰሎሞን የሰዎችን ስህተት መፈላለግና ይህንኑም ማስፋፋት ያለውን ጎጂ ውጤት አስመልክቶ ሲናገር “ወራዳ ሰው ክፋትን ያውጠነጥናል፤ ንግግሩም እንደሚለበልብ እሳት ነው። ጠማማ ሰው ጠብን ይዘራል፤ ሐሜተኛም የቅርብ ወዳጆችን ይለያያል” ብሏል።—ምሳሌ 16:27, 28
የባልንጀራውን ስም ለማጥፋት የሚሞክር ሰው “ወራዳ” ነው። በመሆኑም ሁላችንም የሌሎችን መልካም ጎን ለማየት ብሎም ሌሎች እነሱን እንዲያከብሯቸው የሚያስችሏቸውን ነገሮች ለመናገር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ሐሜት የሚያሰራጩ ሰዎችን ማዳመጥን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? የእነዚህ ሰዎች ንግግር መሠረተ ቢስ ጥርጣሬ በማስነሳት ጓደኛሞችን ሊለያይና በጉባኤ ውስጥ መከፋፈልን ሊፈጥር ይችላል። ጥበብ ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ጆሯችንን እንዳንሰጥ ይገፋፋናል።
ሰሎሞን፣ ማታለል ያለው ኃይል አንድን ሰው የተሳሳተ ጎዳና እንዲከተል እንደሚያደርገው ሲያስጠነቅቅ እንዲህ ብሏል:- “ክፉ [“ዓመጸኛ፣” NW] ሰው ባልንጀራውን ያባብለዋል፤ መልካም ወዳልሆነውም መንገድ ይመራዋል። በዐይኑ የሚጠቅስ ሰው ጠማማነትን ያውጠነጥናል፤ በከንፈሩ የሚያሽሟጥጥም ወደ ክፋት ያዘነብላል።”—ምሳሌ 16:29, 30
ዓመጽ እውነተኛ አምላኪዎችን የማታለል ኃይል ሊኖረው ይችላል? በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ‘ጠማማነትን በማውጠንጠን’ ተታልለዋል። እነዚህ ሰዎች የዓመጽ ድርጊቶችን ያስፋፋሉ አሊያም እነሱ ራሳቸው ዓመጸኛ ይሆናሉ። በእንዲህ ዓይነቱ የዓመጽ ድርጊት በቀጥታ ከመካፈል መራቅ ከባድ ላይሆንብን ይችላል። ይሁን እንጂ በረቀቀ ዘዴ በቀረበ የዓመጽ ድርጊት መማረክን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተታልለው የዓመጽ ድርጊቶች ጎልተው የሚታዩባቸውን መዝናኛዎች አሊያም ስፖርቶች አይመለከቱም? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል” በማለት ግልጽ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል። (ምሳሌ 13:20) በእርግጥም አምላካዊ ጥበብ ጥበቃ ይሆናል!
ጠቢብና አስተዋይ ከሆኑ ሰዎች ጋር ካልሆነ በስተቀር ጓደኝነት መሥርቶ እንዲሁም ‘መልካም ባልሆነ መንገድ ሄዶ ስለማያውቅ’ ሰውስ ምን ማለት ይቻላል? ሕይወቱን በጽድቅ መንገድ ላይ የመራ ሰው በአምላክ ዘንድ ውብ ተደርጎ የሚታይ ከመሆኑም በላይ አክብሮት ይገባዋል። ምሳሌ 16:31 “ሽበት የክብር ዘውድ ነው፤ የሚገኘውም በጽድቅ ሕይወት ነው” ይላል።
በሌላ በኩል ግን ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ቁጣ ምንም ዓይነት ውበት የለውም። የአዳምና የሔዋን የበኵር ልጅ የነበረው ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ‘ክፉኛ ስለተናደደ ገድሎታል።’ (ዘፍጥረት 4:1, 2, 5, 8) መቆጣታችን ተገቢ የሚሆንባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ቁጣችን ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን። ምሳሌ 16:32 “ታጋሽ ሰው ከጦረኛ፣ ስሜቱን የሚገዛም ከተማን በጕልበቱ ከሚይዝ ይበልጣል” በማለት በግልጽ ይናገራል። ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ቁጣ የጥንካሬም ሆነ የጨዋነት ምልክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንድን ሰው ‘መልካም ወዳልሆነ’ ጎዳና ሊመራው የሚችል ድክመት ነው።
‘ውሳኔ በሙሉ ከይሖዋ ዘንድ ነው’
የእስራኤሉ ንጉሥ “ዕጣ በጕያ ውስጥ ይጣላል፤ ውሳኔው በሙሉ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” በማለት ተናገረ። (ምሳሌ 16:33) በጥንት እስራኤል ይሖዋ ፈቃዱ ምን እንደሆነ ለማሳወቅ በዕጣ የተጠቀመባቸው ጊዜያት ነበሩ። በዚያን ጊዜ ዕጣዎች የሚዘጋጁት ከጠጠር፣ ከቁርጥራጭ እንጨት ወይም ከድንጋይ ነበር። በመጀመሪያ አንድን ጉዳይ በሚመለከት የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ በጸሎት ይጠየቃል። ከዚያም ዕጣዎቹ በአንድ በታጠፈ ልብስ ውስጥ ይጨመሩና አንድ ሰው ዕጣውን እንዲያወጣ ይደረጋል። የሚወጣው ዕጣ የአምላክ ፈቃድ እንደሆነ ተደርጎ ስለሚታይ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል።
በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ፈቃዱ ምን እንደሆነ ለሕዝቦቹ ለማሳወቅ በዕጣ አይጠቀምም። ፈቃዱን በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮልናል። አምላካዊ ጥበብን ለማግኘት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ወሳኝ ነው። በመሆኑም በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትን ቅዱሳን መጻሕፍት ሳናነብ አንድም ቀን እንዲያልፈን መፍቀድ አይኖርብንም።—መዝሙር 1:1, 2፤ ማቴዎስ 4:4
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በምሳሌ 16:1-15 ላይ የቀረበውን ማብራሪያ ለማግኘት የግንቦት 15, 2007 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 17-20ን ተመልከት።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥበብ ከወርቅ በእጅጉ ይበልጣል የምንለው ለምንድን ነው?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአገልግሎት ስትካፈል የተሻለ የማሳመን ችሎታ እንዲኖርህ የሚያስችልህ ምንድን ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ወራዳ ሰው ክፋትን ያውጠነጥናል”
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ቁጣ አንድን ሰው ‘መልካም ወዳልሆነ’ መንገድ ይመራዋል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዓመጽ የማታለል ኃይል አለው