የሐዋርያት ሥራ
5 ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው ከሚስቱ ከሰጲራ ጋር መሬት ሸጠ። 2 ይሁንና ከገንዘቡ የተወሰነውን ደብቆ አስቀረ፤ ሚስቱም ይህን ታውቅ ነበር፤ የቀረውንም አምጥቶ ለሐዋርያት አስረከበ።+ 3 ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለ፦ “ሐናንያ፣ ሰይጣን መንፈስ ቅዱስን እንድትዋሽና+ ከመሬቱ ሽያጭ የተወሰነውን ደብቀህ እንድታስቀር ያደፋፈረህ ለምንድን ነው? 4 ሳትሸጠው በፊት ያንተው አልነበረም? ከሸጥከውስ በኋላ ገንዘቡን የፈለግከውን ልታደርግበት ትችል አልነበረም? እንዲህ ያለ ድርጊት ለመፈጸም በልብህ ለምን አሰብክ? የዋሸኸው ሰውን ሳይሆን አምላክን ነው።” 5 ሐናንያ ይህን ቃል ሲሰማ ወደቀና ሞተ። ይህን የሰሙ ሁሉ እጅግ ፈሩ። 6 ወጣት ወንዶችም ተነስተው በጨርቅ ከጠቀለሉት በኋላ ተሸክመው አውጥተው ቀበሩት።
7 ይህ ከሆነ ከሦስት ሰዓት ገደማ በኋላ ደግሞ የተፈጸመውን ነገር ያላወቀችው ሚስቱ መጣች። 8 ጴጥሮስም “እስቲ ንገሪኝ፣ መሬቱን የሸጣችሁት በዚህ ዋጋ ነው?” አላት። እሷም “አዎ፣ በዚሁ ዋጋ ነው” አለች። 9 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ሁለታችሁ የይሖዋን* መንፈስ ለመፈተን የተስማማችሁት ለምንድን ነው? እነሆ፣ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግር ደጃፍ ላይ ነው፤ እነሱም ተሸክመው ያወጡሻል” አላት። 10 ወዲያውም እግሩ ሥር ወድቃ ሞተች። ወጣቶቹ ሲገቡም ሞታ አገኟት፤ ተሸክመው አውጥተውም ከባሏ አጠገብ ቀበሯት። 11 በመሆኑም መላው ጉባኤ እንዲሁም ይህን የሰሙ ሰዎች ሁሉ በከፍተኛ ፍርሃት ተዋጡ።
12 በተጨማሪም ሐዋርያት በሕዝቡ መካከል ብዙ ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች መፈጸማቸውን ቀጥለው ነበር፤+ ሁሉም አንድ ላይ ሆነው መጠለያ ባለው “የሰለሞን መተላለፊያ”+ ይሰበሰቡ ነበር። 13 እርግጥ ከሌሎቹ መካከል ከእነሱ ጋር ሊቀላቀል የደፈረ አንድም ሰው አልነበረም፤ ሆኖም ሕዝቡ ያሞግሳቸው ነበር። 14 ከዚህም በላይ በጌታ ያመኑ እጅግ በርካታ ወንዶችና ሴቶች በየጊዜው በእነሱ ላይ ይጨመሩ ነበር።+ 15 ደግሞም ጴጥሮስ በዚያ ሲያልፍ በአንዳንዶቹ ላይ ቢያንስ ጥላው ቢያርፍባቸው በማለት ሕመምተኞችን አውራ ጎዳናዎች ላይ አውጥተው በትናንሽ አልጋዎችና በምንጣፎች ላይ ያስተኟቸው ነበር።+ 16 በተጨማሪም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ከሚገኙ ከተሞች ብዙ ሰዎች ሕመምተኞችንና በርኩሳን መናፍስት የሚሠቃዩ ሰዎችን ተሸክመው መምጣታቸውን ቀጠሉ፤ የመጡትም ሁሉ ይፈወሱ ነበር።
17 ይሁንና ሊቀ ካህናቱና አብረውት የነበሩት የሰዱቃውያን ሃይማኖታዊ ቡድን አባላት ሁሉ በቅናት ተሞልተው ተነሱ። 18 ሐዋርያትንም ይዘው እስር ቤት ከተቷቸው።+ 19 ይሁን እንጂ ሌሊት የይሖዋ* መልአክ የእስር ቤቱን በሮች ከፍቶ+ አወጣቸውና እንዲህ አላቸው፦ 20 “ሂዱና በቤተ መቅደሱ ቆማችሁ ስለዚህ ሕይወት የሚገልጸውን ቃል ሁሉ ለሕዝቡ መናገራችሁን ቀጥሉ።” 21 እነሱም በተነገራቸው መሠረት ንጋት ላይ ወደ ቤተ መቅደሱ ገብተው ያስተምሩ ጀመር።
ሊቀ ካህናቱና ከእሱ ጋር የነበሩት በመጡ ጊዜም የሳንሄድሪንን ሸንጎና መላውን የእስራኤል ልጆች ሽማግሌዎች ጉባኤ በአንድነት ሰበሰቡ፤ ሐዋርያቱንም ወደ እነሱ እንዲያመጧቸው ሰዎችን ወደ እስር ቤቱ ላኩ። 22 የቤተ መቅደሱ ጠባቂዎች እዚያ በደረሱ ጊዜ ግን እስር ቤቱ ውስጥ አላገኟቸውም። ስለዚህ ተመልሰው መጥተው ነገሯቸው፤ 23 እንዲህም አሏቸው፦ “እስር ቤቱ በሚገባ ተቆልፎ ጠባቂዎቹም በሮቹ ላይ ቆመው አገኘናቸው፤ በሮቹን ስንከፍት ግን ውስጥ ማንንም አላገኘንም።” 24 የቤተ መቅደሱ ሹምና የካህናት አለቆቹም ይህን ሲሰሙ ‘የዚህ ነገር መጨረሻ ምን ይሆን?’ በማለት በነገሩ ግራ ተጋቡ። 25 በዚህ ጊዜ አንድ ሰው መጥቶ “እስር ቤት ያስገባችኋቸው ሰዎች በቤተ መቅደሱ ቆመው ሕዝቡን እያስተማሩ ነው” ብሎ ነገራቸው። 26 ከዚያም የቤተ መቅደሱ ሹም ከጠባቂዎቹ ጋር ሄዶ አመጣቸው፤ ሆኖም ሕዝቡ በድንጋይ እንዳይወግራቸው ስለፈሩ ያመጧቸው በኃይል አስገድደው አልነበረም።+
27 አምጥተውም በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት አቆሟቸው። ከዚያም ሊቀ ካህናቱ ይጠይቃቸው ጀመር፤ 28 እንዲህም አለ፦ “በዚህ ስም ማስተማራችሁን እንድታቆሙ በጥብቅ አዘናችሁ ነበር፤+ እናንተ ግን ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋታል፤ የዚህንም ሰው ደም በእኛ ላይ ለማምጣት ቆርጣችሁ ተነስታችኋል።”+ 29 ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያትም እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል።+ 30 እናንተ በእንጨት* ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሳው።+ 31 እስራኤል ንስሐ እንዲገባና የኃጢአት ይቅርታ እንዲያገኝ+ አምላክ እሱን “ዋና ወኪል”+ እና “አዳኝ”+ አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው።+ 32 ለዚህም ጉዳይ እኛ ምሥክሮች ነን፤+ እንዲሁም አምላክ እሱን እንደ ገዢያቸው አድርገው ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምሥክር ነው።”+
33 እነሱም ይህን ሲሰሙ እጅግ ተቆጡ፤ ሊገድሏቸውም ፈለጉ። 34 ሆኖም በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የተከበረ፣ የሕግ አስተማሪ የሆነ ገማልያል+ የሚባል አንድ ፈሪሳዊ በሳንሄድሪኑ ሸንጎ መካከል ተነስቶ ሰዎቹን ለጊዜው ወደ ውጭ እንዲያስወጧቸው አዘዘ። 35 ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ በእነዚህ ሰዎች ላይ ልታደርጉ ያሰባችሁትን ነገር በተመለከተ ልትጠነቀቁ ይገባል። 36 ለምሳሌ ያህል፣ ከዚህ ቀደም ቴዎዳስ ራሱን እንደ ታላቅ ሰው በመቁጠር ተነስቶ ነበር፤ ወደ 400 የሚጠጉ ሰዎችም ከእሱ ጋር ተባብረው ነበር። ነገር ግን እሱም ተገደለ፤ ተከታዮቹም ሁሉ ተበታትነው እንዳልነበሩ ሆኑ። 37 ከእሱ በኋላ ደግሞ የሕዝብ ቆጠራ በተካሄደበት ወቅት የገሊላው ይሁዳ ተነስቶ ተከታዮች አፍርቶ ነበር። ይሁንና እሱም ጠፋ፤ ተከታዮቹም ሁሉ ተበታተኑ። 38 ስለዚህ አሁን የምላችሁ፣ እነዚህን ሰዎች አትንኳቸው፤ ተዉአቸው። ይህ ውጥን ወይም ይህ ሥራ ከሰው ከሆነ ይጠፋል፤ 39 ከአምላክ ከሆነ ግን ልታጠፏቸው አትችሉም።+ እንዲያውም ከአምላክ ጋር ስትጣሉ ትገኙ ይሆናል።”+ 40 እነሱም ምክሩን ተቀበሉ፤ ሐዋርያትንም ጠርተው ገረፏቸው፤*+ ከዚያም በኢየሱስ ስም መናገራቸውን እንዲያቆሙ አዘው ለቀቋቸው።
41 እነሱም ስለ ስሙ ውርደት ለመቀበል ብቁ ሆነው በመቆጠራቸው ደስ እያላቸው+ ከሳንሄድሪን ሸንጎ ወጡ። 42 ከዚያም በየቀኑ በቤተ መቅደስም ሆነ ከቤት ወደ ቤት+ እየሄዱ ስለ ክርስቶስ ይኸውም ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን ምሥራች ያለማሰለስ ማስተማራቸውንና ማወጃቸውን ቀጠሉ።+