የይሖዋ ‘ዓይኖች’ ሁሉንም ይመረምራሉ
‘የይሖዋ ዐይኖች የሰው ልጆችን ይመረምራሉ።’—መዝ. 11:4
1. መቅረብ የምንፈልገው ምን ዓይነት ባሕርያት ያሏቸውን ሰዎች ነው?
ስለ አንተ ከልባቸው ስለሚያስቡ ሰዎች ምን ይሰማሃል? እንዲህ ያሉ ሰዎች ሐሳብ እንዲያካፍሉህ ስትጠይቃቸው ሐቁን ይነግሩሃል። ችግር ሲያጋጥምህ አንተን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው። ምክር በሚያሻህ ወቅት ደግሞ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ምክራቸውን ይለግሱሃል። (መዝ. 141:5፤ ገላ. 6:1) እንዲህ ካሉ ሰዎች ጋር ለመቀራረብ አትነሳሳም? ይሖዋና ልጁ እንዲህ ዓይነት ወዳጆች ናቸው። እንዲያውም ከማንኛውም ሰው ይበልጥ ስለ አንተ ያስባሉ፤ አሳቢነት የሚያሳዩህ ደግሞ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማግኘት እንድትችል አንተን ለመርዳት ስለሚፈልጉ እንጂ በራስ ወዳድነት ተነሳስተው አይደለም።—1 ጢሞ. 6:19፤ ራእይ 3:19
2. ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ምን ያህል ያስባል?
2 መዝሙራዊው ዳዊት ይሖዋ ስለ እኛ ምን ያህል እንደሚያስብ ሲገልጽ “[የይሖዋ ዐይኖች] ሰዎችን ይመለከታሉ፤ ቅንድቦቹም የሰው ልጆችን ይመረምራሉ” ብሏል። (መዝ. 11:4) ይህ ጥቅስ እንደሚያሳየው አምላክ እኛን እንዲሁ በማየት ብቻ ሳይወሰን በጥልቅ ይመረምረናል። ዳዊት “ልቤን መረመርኸው፣ በሌሊት ጠጋ ብለህ ፈተንኸኝ፣ . . . አንዳች አላገኘህብኝም” በማለትም ጽፏል። (መዝ. 17:3) ከዚህ በግልጽ ለመመልከት እንደምንችለው ዳዊት፣ ይሖዋ ከልብ እንደሚያስብለት ያውቅ ነበር። ዳዊት ወደ ኃጢአት የሚገፋፉ ሐሳቦችን ካላስወገደ ወይም ተንኰለኛ ልብ እንዳይኖረው ካልተጠነቀቀ ይሖዋን እንደሚያሳዝነው እንዲሁም የእሱን ሞገስ እንደሚያጣ ተገንዝቦ ነበር። ይሖዋ ለዳዊት እውን የሆነለትን ያህል ለአንተም እውን ሆኖልሃል?
ይሖዋ ልብን ይመለከታል
3. ይሖዋ ፍጹማን አለመሆናችንን እንደሚረዳ ያሳየው እንዴት ነው?
3 ይሖዋ በዋነኛነት ትኩረት የሚያደርገው በውስጣዊ ማንነታችን ማለትም በልባችን ውስጥ ባለው ነገር ላይ ነው። (መዝ. 19:14፤ 26:2) አፍቃሪ አምላክ ስለሆነ ጥቃቅን በሆኑ ጉድለቶቻችን ላይ አያተኩርም። ለምሳሌ ያህል፣ የአብርሃም ሚስት ሣራ ለአንድ መልአክ እውነት ያልሆነ መልስ በሰጠችው ጊዜ ሣራ ይህን ያደረገችው ስለፈራችና ስላፈረች መሆኑን መልአኩ ተገንዝቦ ነበር፤ በመሆኑም ለዘብ ያለ እርማት በመስጠት አልፏታል። (ዘፍ. 18:12-15) ከእምነት አባቶች አንዱ የሆነው ኢዮብ “ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ” አድርጎ ቢናገርም ይሖዋ እሱን ከመባረክ ወደኋላ አላለም፤ ምክንያቱም ሰይጣን በኢዮብ ላይ ከባድ መከራ እንዳደረሰበት ይሖዋ ያውቅ ነበር። (ኢዮብ 32:2፤ 42:12) በተመሳሳይም በሰራፕታ ትኖር የነበረችው መበለት ነቢዩ ኤልያስን በድፍረት በመናገሯ ይሖዋ አላዘነባትም። ይህቺ ሴት አንድ ልጇን በሞት በማጣቷ በጥልቅ እንዳዘነች አምላክ ተገንዝቦ ነበር።—1 ነገ. 17:8-24
4, 5. ይሖዋ ለአቢሜሌክ አሳቢነትና ደግነት ያሳየው እንዴት ነው?
4 ይሖዋ ልብን ስለሚመረምር በእሱ ለማያምኑ ሰዎችም እንኳ አሳቢነት አሳይቷል። ለምሳሌ፣ ጌራራ የተባለችው የፍልስጥኤም ከተማ ንጉሥ ከሆነው ከአቢሜሌክ ጋር በተያያዘ ያደረገውን እንመልከት። አቢሜሌክ፣ ሣራ የአብርሃም ሚስት መሆኗን ስላላወቀ ሊያገባት በማሰብ ወስዷት ነበር። ሆኖም አቢሜሌክ ምንም ነገር ከማድረጉ በፊት ይሖዋ በሕልም ተገልጦለት እንዲህ አለው፦ “አንተ ይህን ያደረግኸው በቅን ልቦና መሆኑን ዐውቄአለሁ፤ በእኔም ላይ ኀጢአት እንዳትሠራ የጠበቅሁህና እንዳትነካትም ያደረግሁት ለዚሁ ነው። አሁንም ሚስቱን ለሰውዬው መልስለት፤ ነቢይ ነውና ይጸልይልሃል፤ አንተም ትድናለህ።”—ዘፍ. 20:1-7
5 ይሖዋ፣ የሐሰት አማልክት የሚያመልከውን አቢሜሌክን ሊቀጣው ይችል እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ አምላክ፣ ይህ ሰው ድርጊቱን የፈጸመው በቅንነት እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም ይህንን ከግምት በማስገባት ንጉሡ ምሕረት የሚያገኝበትንና ‘መዳን’ የሚችልበትን መንገድ በደግነት ነግሮታል። አንተስ ለማምለክ የምትፈልገው እንዲህ ያለውን አምላክ አይደለም?
6. ኢየሱስ አባቱን የኮረጀው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
6 ኢየሱስም፣ በደቀ መዛሙርቱ መልካም ጎን ላይ በማተኮር እንዲሁም ስሕተት በሚሠሩበት ጊዜ ይቅር በማለት አባቱን ፍጹም በሆነ መንገድ ኮርጇል። (ማር. 10:35-45፤ 14:66-72፤ ሉቃስ 22:31, 32፤ ዮሐ. 15:15) የኢየሱስ አመለካከት በዮሐንስ 3:17 ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው ራሱ ከተናገረው ከሚከተለው ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነበር፦ “እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ለመፍረድ ሳይሆን፣ ዓለምን በእርሱ ለማዳን ነው።” በእርግጥም ይሖዋና ኢየሱስ ለእኛ ያላቸው ፍቅር ጥልቅ ከመሆኑም በላይ ምንጊዜም አይለወጥም። ሕይወት እንድናገኝ ያላቸው ፍላጎት እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንዳላቸው ያሳያል። (ኢዮብ 14:15) ይሖዋ ለእኛ እንዲህ ዓይነት ፍቅር እንዳለው መገንዘባችን፣ ለምን እንደሚመረምረንና እንዴት እንደሚመለከተን እንዲሁም ባየው ነገር ላይ ተመሥርቶ እርምጃ የሚወስደው እንዴት እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል።—1 ዮሐንስ 4:8, 19ን አንብብ።
ይሖዋ የሚመረምረን በፍቅር ተነሳስቶ ነው
7. ይሖዋ እኛን የሚመረምርበት ዓላማ ምንድን ነው?
7 ይሖዋ፣ ኃጢአት ስንሠራ ለመቅጣት ሲል ከሰማይ ሆኖ የሚመለከተን ፖሊስ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ምንኛ ስሕተት ነው! የሰው ልጆችን የሚከሰው እንዲሁም ራስ ወዳድ እንደሆኑ አድርጎ የሚከራከረው ሰይጣን ነው። (ራእይ 12:10) ሰይጣን በውስጣችን ምንም መጥፎ ዝንባሌ ሳይኖር እንኳ መጥፎ ዝንባሌ እንዳለን አድርጎ ይከሰናል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4, 5) መዝሙራዊው አምላክን በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአትን ብትቈጣጠር፣ ጌታ ሆይ፤ ማን ሊቆም ይችላል?” (መዝ. 130:3) የዚህ ጥያቄ መልስ ‘ማንም ሊቆም አይችልም’ የሚል ነው! (መክ. 7:20) ይሖዋ፣ ኃጢአትን ከመቆጣጠር ይልቅ የሚወዳቸውን ልጆቹን ከአደጋ ለመጠበቅ እንደሚፈልግ አሳቢ ወላጅ በምሕረትና በደግነት ይመለከተናል። ይሖዋ ራሳችንን የሚጎዳ እርምጃ እንዳንወስድ ሊጠብቀን ስለሚፈልግ ፍጽምና የጎደለንና ድክመቶች ያሉብን መሆናችንን በተደጋጋሚ ያስታውሰናል።—መዝ. 103:10-14፤ ማቴ. 26:41
8. ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚያስተምራቸውና የሚያርማቸው እንዴት ነው?
8 አምላክ በቅዱሳን መጻሕፍት እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያዘጋጀው መንፈሳዊ ምግብ አማካኝነት የሚሰጠን መመሪያና እርማት ለእኛ ፍቅር እንዳለው ያሳያል። (ማቴ. 24:45 የ1954 ትርጉም፤ ዕብ. 12:5, 6) ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤና “ስጦታ” በሆኑት ወንዶች አማካኝነት ተጨማሪ እርዳታ ይሰጠናል። (ኤፌ. 4:8) ከዚህም በላይ ለሚሰጠን አባታዊ ሥልጠና ምን ምላሽ እንደምንሰጥ ለማወቅ ይመለከተናል፤ እንዲሁም ተጨማሪ እርዳታ ያደርግልናል። መዝሙር 32:8 “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ” ይላል። እንግዲያው ምንጊዜም ይሖዋን ማዳመጣችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ይሖዋ አፍቃሪ አስተማሪያችንና አባታችን እንደሆነ በመገንዘብ ሁልጊዜ ራሳችንን በፊቱ ዝቅ ማድረግ ይኖርብናል።—ማቴዎስ 18:4ን አንብብ።
9. የትኞቹን ዝንባሌዎች ማስወገድ ይኖርብናል? ለምንስ?
9 በሌላ በኩል ደግሞ በትዕቢት፣ እምነት በማጣት ወይም ‘ኃጢአት ባለው የማታለል ኃይል’ ልባችን እንዳይደነድን ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። (ዕብ. 3:13 NW፤ ያዕ. 4:6) አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ያሉት ዝንባሌዎች የሚጀምሩት አንድ ሰው ጤናማ ባልሆኑ ሐሳቦች ወይም ምኞቶች ላይ ሲያተኩር ነው። እንዲህ ያለው ሰው ውሎ አድሮ ተገቢ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮችን እንኳ ለመቀበል ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል። ከዚህ የከፋው ደግሞ ግለሰቡ በመጥፎ ዝንባሌው ወይም አካሄዱ ሊገፋበትና ራሱን የአምላክ ጠላት ሊያደርግ የሚችል መሆኑ ነው፤ ይህ በጣም የሚያስፈራ ነው! (ምሳሌ 1:22-31) የአዳምና የሔዋን የበኩር ልጅ የነበረውን የቃየንን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት።
ይሖዋ ሁሉንም ነገር በመመልከት እርምጃ ይወስዳል
10. ይሖዋ የቃየንን መሥዋዕት ያልተቀበለው ለምን ነበር? ቃየንስ ምን አደረገ?
10 ቃየንና አቤል መሥዋዕት ባቀረቡበት ወቅት ይሖዋ የተመለከተው ያቀረቡትን መሥዋዕት ብቻ ሳይሆን የልባቸውን ዝንባሌም ጭምር ነበር። በዚህም ምክንያት አምላክ በእምነት የቀረበውን የአቤልን መሥዋዕት ቢቀበልም ቃየን ግን እምነት ይጎድለው ስለነበር ያቀረበውን መሥዋዕት ተቀባይነት አልነበረውም። (ዘፍ. 4:4, 5፤ ዕብ. 11:4) ቃየን ከዚህ ሁኔታ ትምህርት በማግኘት አስተሳሰቡን ከማስተካከል ይልቅ በወንድሙ ላይ በጣም ተቆጣ።—ዘፍ. 4:6
11. ቃየን ተንኰለኛ ልብ እንደነበረው የሚጠቁመው ምንድን ነው? እኛስ ከቃየን ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?
11 ይሖዋ የቃየን አካሄድ አደገኛ መሆኑን ስለተመለከተ ቃየን መልካም ቢያደርግ ተቀባይነት እንደሚያገኝ በመግለጽ በአሳቢነት አነጋገረው። የሚያሳዝነው ግን ቃየን የፈጣሪውን ምክር ችላ በማለት ወንድሙን ገደለው። አምላክ “ወንድምህ አቤል የት ነው?” በማለት ሲጠይቀው ቃየን የሰጠው አክብሮት የጎደለው ምላሽም ክፉ ልብ እንዳለው የሚጠቁም ነው። ቃየን የሰጠው መልስ “አላውቅም፤ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” የሚል ነበር። (ዘፍ. 4:7-9) የሰው ልብ እንዴት ተንኰለኛ ነው! አንድ ሰው አምላክ በቀጥታ የሰጠውን ምክር እንኳ አቅልሎ እንዲመለከት ሊያደርገው ይችላል። (ኤርምያስ 17:9) እኛም እንደዚህ ካሉት ታሪኮች ትምህርት በማግኘት የተሳሳቱ አስተሳሰቦችንና ምኞቶችን ልንቆጣጠራቸው የማንችልበት ደረጃ ላይ ከመድረሳቸው በፊት እናስወግዳቸው። (ያዕቆብ 1:14, 15ን አንብብ።) ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ሲሰጠን አመስጋኞች እንሁን፤ እንዲሁም የይሖዋ ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አድርገን እንመልከተው።
ከይሖዋ የተሰወረ ኃጢአት የለም
12. ይሖዋ በኃጢአተኞች ላይ ምን እርምጃ ይወስዳል?
12 አንዳንዶች፣ መጥፎ ነገር ሲሠሩ ማንም ሰው ካላያቸው ከቅጣት የሚያመልጡ ይመስላቸዋል። (መዝ. 19:12) እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ስውር ኃጢአት የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም “ስለ ራሳችን መልስ መስጠት በሚገባን በእርሱ ፊት ሁሉም ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው።” (ዕብ. 4:13) ይሖዋ ውስጣዊ ዝንባሌያችንን የሚመረምር ዳኛ ሲሆን ኃጢአት በፈጸሙ ሰዎች ላይ የሚወስደው እርምጃም ፍጹም ፍትሕ የሚንጸባረቅበት ነው። ይሖዋ ‘ርኅሩኅና ቸር’ እንዲሁም “ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ” አምላክ ነው። ያም ቢሆን ግን ‘ሆን ብለው ኃጢአት መሥራትን ልማድ ያደረጉ’ ወይም የክፋት ዝንባሌ ያላቸው ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችን “ሳይቀጣ ዝም ብሎ አይተውም።” (ዘፀ. 34:6, 7፤ ዕብ. 10:26 NW) ይሖዋ በአካን እንዲሁም በሐናንያና በሰጲራ ላይ የወሰደው እርምጃ ይህ እውነት መሆኑን ያሳያል።
13. አካን የነበረው የተሳሳተ ዝንባሌ መጥፎ ድርጊት እንዲፈጽም ያደረገው እንዴት ነው?
13 አካን፣ አምላክ የሰጠውን ግልጽ መመሪያ በመጣስ ከኢያሪኮ ከተማ ከተገኘው ምርኮ ላይ የተወሰኑ ዕቃዎችን ወስዶ ድንኳኑ ውስጥ ደበቃቸው፤ ይህን ሲያደርግ ቤተሰቡም ተባብረውት ሊሆን ይችላል። አካን ኃጢአቱ ሲጋለጥ “እግዚአብሔርን በድያለሁ” ብሎ መናገሩ የፈጸመው ድርጊት ምን ያህል ከባድ መሆኑን እንደተገነዘበ ያሳያል። (ኢያሱ 7:20) እንደ ቃየን ሁሉ አካንም ክፉ ልብ ነበረው። የአካን ዋነኛ ድክመት ስግብግብነት ሲሆን ይህም ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት እንዲፈጽም አድርጎታል። ከኢያሪኮ የተገኘው ምርኮ ለይሖዋ መሰጠት ስለነበረበት አካን የሰረቀው ከአምላክ ነው ማለት ይቻላል። እንዲህ ማድረጉ የራሱንም ሆነ የቤተሰቡን ሕይወት አሳጥቶታል።—ኢያሱ 7:25
14, 15. ሐናንያና ሰጲራ የአምላክን ሞገስ እንዲያጡ ያደረጋቸው ምንድን ነው? እኛስ ከእነሱ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?
14 ሐናንያና ሚስቱ ሰጲራ በኢየሩሳሌም የሚገኘው የጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ነበሩ። በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የጰንጠቆስጤ በዓልን ለማክበር ራቅ ካሉ አካባቢዎች ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው በዚያ የቆዩ ሰዎች ነበሩ። እነዚህ አዳዲስ አማኞች የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች ለማሟላት ገንዘብ ይሰበሰብ ነበር። ክርስቲያኖች ለዚህ ዓላማ የሚውል ገንዘብ በፈቃደኝነት መዋጮ ያደርጉ ነበር። ሐናንያ መሬቱን ሸጠና ከገንዘቡ የተወሰነውን ለራሱ በማስቀረት የተረፈውን መዋጮ አደረገ። ሆኖም ሐናንያ ከመሬቱ ሽያጭ ያገኘውን ገንዘብ በሙሉ እንደሰጠ አድርጎ ተናገረ፤ ሚስቱም እንዲህ ብሎ መናገሩን በሚገባ ታውቅ ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት ይህን ያደረጉት በጉባኤው ውስጥ ለየት ያለ አክብሮት እንዲሰጣቸው ፈልገው እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ የተናገሩት ነገር ውሸት ነበር። ይሖዋ፣ እነዚህ ባልና ሚስት የፈጸሙትን የማታለል ድርጊት ተአምራዊ በሆነ መንገድ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ገለጠለት፤ ጴጥሮስ ሐናንያን ለምን እንዲህ እንዳደረገ ሲጠይቀው ሐናንያ ወድቆ ሞተ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሰጲራም ሞተች።—ሥራ 5:1-11
15 ሐናንያና ሰጲራ እንዲህ ያለውን ድርጊት የፈጸሙት ተሳስተው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ውሸት የተናገሩት ሆን ብለው ሐዋርያቱን ለማታለል አስበው ነው። ከሁሉ የከፋው ደግሞ ‘የዋሹት መንፈስ ቅዱስንና አምላክን’ መሆኑ ነው። ይሖዋ ጉባኤውን ከግብዞች ከማጽዳት ወደኋላ እንደማይል በእነዚህ ባልና ሚስት ላይ ከወሰደው እርምጃ በግልጽ ማየት ይቻላል። በእርግጥም “በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ እጅግ የሚያስፈራ ነው”!—ዕብ. 10:31
ምንጊዜም ንጹሕ አቋማችሁን ጠብቃችሁ ለመኖር ጥረት አድርጉ
16. (ሀ) ሰይጣን የአምላክን ሕዝቦች አቋም ለማበላሸት የሚጥረው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ለ) አንተ በምትኖርበት አካባቢ ዲያብሎስ የሰዎችን አስተሳሰብ ለማበላሸት በየትኞቹ ዘዴዎች ይጠቀማል?
16 ሰይጣን አቋማችንን ለማበላሸት እንዲሁም የይሖዋን ሞገስ እንድናጣ ለማድረግ የተቻለውን ሁሉ ይጥራል። (ራእይ 12:12, 17) በጾታ ብልግና ያበደውና በዓመፅ የተሞላው ይህ ዓለም የዲያብሎስን የክፋት ዓላማ በግልጽ ያንጸባርቃል። በዛሬው ጊዜ የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን በኮምፒውተር እንዲሁም በሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች አማካኝነት በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። ሁላችንም በሰይጣን ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ ልንጠነቀቅ ይገባል። እንደ መዝሙራዊው ዳዊት ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል፤ ዳዊት “እንከን የማይገኝባትን መንገድ አጥብቄ እይዛለሁ፤ . . . በቤቴ ውስጥ፣ በንጹሕ ልብ እመላለሳለሁ” ብሏል።—መዝ. 101:2
17. (ሀ) ይሖዋ የተሰወሩ ኃጢአቶችን እሱ በመረጠው ጊዜ የሚያጋልጠው ለምንድን ነው? (ለ) ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?
17 ይሖዋ ቀደም ባሉት ዘመናት አልፎ አልፎ እንዳደረገው በዛሬው ጊዜ ከባድ ኃጢአቶችን ወይም የማታለል ድርጊቶችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ አያጋልጥም። ያም ቢሆን ሁሉንም ነገር የሚያይ ሲሆን እሱ በመረጠው ጊዜና መንገድ የተሰወሩ ነገሮችን ገሃድ ያወጣል። ጳውሎስ “የአንዳንድ ሰዎች ኀጢአት ግልጽ ነው፤ ከእነርሱም ቀድሞ ፍርድ ቦታ ይደርሳል፤ ሌሎችን ግን ኀጢአታቸው ይከተላቸዋል” ብሏል። (1 ጢሞ. 5:24) ይሖዋ የኃጢአት ድርጊቶችን እንዲያጋልጥ የሚያነሳሳው ዋነኛ ምክንያት ፍቅር ነው። የክርስቲያን ጉባኤን የሚወደው ሲሆን ንጽሕናውንም ለመጠበቅ ይፈልጋል። ከዚህም በላይ ኃጢአት ቢሠሩም ከልባቸው ንስሐ ለገቡ ሰዎች ምሕረት ያሳያል። (ምሳሌ 28:13) እንግዲያው አምላክን በፍጹም ልባችን ለመታዘዝና አቋማችንን ከሚያበላሽ ከማንኛውም ተጽዕኖ ለመራቅ ጥረት እናድርግ።
ይሖዋን በፍጹም ልባችሁ ለማገልገል ጥረት አድርጉ
18. ንጉሥ ዳዊት፣ ልጁ ስለ አምላክ ምን ዓይነት ስሜት እንዲያድርበት ፈልጎ ነበር?
18 ንጉሥ ዳዊት ለልጁ ለሰሎሞን እንዲህ ብሎት ነበር፦ “እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ስለሚመረምርና ሐሳብን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ የአባትህን አምላክ ዕወቅ፤ በፍጹም ልብና በበጎ ፈቃድ አገልግለው።” (1 ዜና 28:9) ዳዊት፣ ልጁ ሰሎሞን በአምላክ በማመኑ ብቻ ረክቶ ከመኖር ይልቅ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ምን ያህል እንደሚያስብላቸው እንዲገነዘብ ፈልጎ ነበር። አንተስ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ በጥልቅ የሚያስብ አምላክ በመሆኑ አመስጋኝ ነህ?
19, 20. በመዝሙር 19:7-11 መሠረት ዳዊት ወደ አምላክ እንዲቀርብ የረዳው ምንድን ነው? እኛስ እሱን መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?
19 ይሖዋ፣ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ወደ እሱ እንደሚሳቡ እንዲሁም ማራኪ ስለሆኑት ባሕርያቱ የሚያገኙት እውቀት ወደ እሱ እንደቀረቡ እንዲሰማቸው እንደሚያደርግ ያውቃል። በመሆኑም ይሖዋ ስለ እሱና ድንቅ ስለሆኑት ባሕርያቱ እንድናውቅ ይፈልጋል። ይህንን እውቀት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ቃሉን በማጥናትና በሕይወታችን ውስጥ የሚሰጠንን በረከቶች በመመልከት ነው።—ምሳሌ 10:22፤ ዮሐ. 14:9
20 አንተስ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ ቃል መሆኑን በመገንዘብ በየዕለቱ ታነበዋለህ? ያነበብከውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ እንድትችል እንዲረዳህ ወደ አምላክ ትጸልያለህ? በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሕይወትን መምራት ያለውን ጠቀሜታስ ትገነዘባለህ? (መዝሙር 19:7-11ን አንብብ።) መልስህ ‘አዎን’ ከሆነ በይሖዋ ላይ ያለህ እምነት እየተጠናከረ እንዲሁም ለእሱ ያለህ ፍቅር እያደገ ይሄዳል። እሱም በምላሹ እጅህን ይዞ የሚሄድ ያህል ወደ አንተ የበለጠ ይቀርባል። (ኢሳ. 42:6፤ ያዕ. 4:8) አዎን፣ ወደ ሕይወት በሚወስደው ጠባብ መንገድ ላይ ስትጓዝ ይሖዋ ለአንተ በረከቱን በማፍሰስና መንፈሳዊ ጥበቃ በማድረግ ፍቅሩን ያሳይሃል።—መዝ. 91:1, 2፤ ማቴ. 7:13, 14
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ይሖዋ የሚመረምረን ለምንድን ነው?
• አንዳንድ ግለሰቦች የአምላክ ጠላቶች እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምንድን ነው?
• ይሖዋ እውን እንደሆነልን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
• አምላክን በፍጹም ልብ ማገልገል የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ፣ አሳቢ እንደሆነ ወላጅ የሚመለከተን እንዴት ነው?
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሐናንያ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋን በፍጹም ልብ ማገልገላችንን እንድንቀጥል የሚረዳን ምንድን ነው?