106 ያህን አወድሱ!
ይሖዋ ጥሩ+ ስለሆነ ምስጋና አቅርቡለት፤
ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።+
2 የይሖዋን ታላላቅ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ሊያስታውቅ የሚችለው ማን ነው?
ወይስ የሚያስመሰግኑ ተግባሮቹን ሁሉ ሊያውጅ የሚችለው ማን ነው?+
3 ፍትሐዊ ድርጊት የሚፈጽሙ፣
ምንጊዜም ትክክል የሆነውን የሚያደርጉ+ ደስተኞች ናቸው።
4 ይሖዋ ሆይ፣ ለሕዝብህ ሞገስ በምታሳይበት ጊዜ እኔንም አስታውሰኝ።+
ተንከባከበኝ፤ ደግሞም አድነኝ፤
5 ይህም ለተመረጡ አገልጋዮችህ+ የምታሳየውን ጥሩነት እንድቀምስ፣
ከሕዝብህ ጋር ሐሴት እንዳደርግ፣
ከርስትህም ጋር አንተን በኩራት እንዳወድስ ነው።
6 እኛም እንደ አባቶቻችን ኃጢአት ሠርተናል፤+
በድለናል፤ ክፉ ነገርም አድርገናል።+
7 አባቶቻችን በግብፅ በነበሩበት ጊዜ፣ ድንቅ ሥራዎችህን በአድናቆት አልተመለከቱም።
የታማኝ ፍቅርህን ብዛት አላስታወሱም፤
ከዚህ ይልቅ በባሕሩ አጠገብ ይኸውም ቀይ ባሕር አጠገብ ዓመፁ።+
8 ይሁንና ኃያልነቱ እንዲታወቅ ሲል፣+
ለስሙ ብሎ አዳናቸው።+
9 ቀይ ባሕርን ገሠጸ፤ ባሕሩም ደረቀ፤
በበረሃ የሚሄዱ ያህል በጥልቅ ውኃው መካከል መራቸው፤+
10 ከባላጋራዎቻቸው እጅ አዳናቸው፤+
ከጠላቶቻቸውም እጅ ታደጋቸው።+
11 ውኃው ጠላቶቻቸውን ዋጠ፤
ከእነሱ አንድ ሰው እንኳ አልዳነም።+
12 በዚያን ጊዜ በገባው ቃል አመኑ፤+
የውዳሴ መዝሙር ይዘምሩለት ጀመር።+
13 ይሁን እንጂ ያደረገውን ነገር ወዲያውኑ ረሱ፤+
እሱ የሚሰጣቸውን ምክር በትዕግሥት አልጠበቁም።
14 በምድረ በዳ በራስ ወዳድነት ምኞት ተሸነፉ፤+
በበረሃ አምላክን ተፈታተኑት።+
15 እሱም የለመኑትን ሰጣቸው፤
ነገር ግን በሚያመነምን በሽታ መታቸው።+
16 በሰፈር ውስጥ በሙሴ፣
ደግሞም የይሖዋ ቅዱስ አገልጋይ+ በሆነው በአሮን ቀኑ።+
17 በዚህ ጊዜ ምድር ተከፍታ ዳታንን ዋጠች፤
ከአቤሮንም ጋር ያበሩትን ሰለቀጠች።+
18 እሳትም በማኅበራቸው መካከል ነደደች፤
ነበልባልም ክፉዎችን በላች።+
19 በኮሬብ ጥጃ ሠሩ፤
ከብረት ለተሠራም ሐውልት ሰገዱ፤+
20 ሣር በሚበላ ኮርማ ምስል
ክብሬን ለወጡ።+
21 በግብፅ ታላላቅ ነገሮች ያደረገውን፣+
አዳኛቸው የሆነውን አምላክ ረሱ፤+
22 በካም ምድር አስደናቂ ሥራዎች፣+
በቀይ ባሕር የሚያስፈሩ ነገሮች ያከናወነውን+ አምላክ ዘነጉ።
23 እንዲጠፉ ሊያዝዝ ምንም አልቀረውም ነበር፤
ሆኖም እሱ የመረጠው አገልጋዩ ሙሴ፣
አጥፊ ቁጣውን እንዲመልስ አምላክን ተማጸነ።+
24 ከዚያም የተወደደችውን ምድር ናቁ፤+
በገባው ቃል ላይ እምነት አልነበራቸውም።+
25 በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሆነው ማጉረምረማቸውን ቀጠሉ፤+
የይሖዋን ድምፅ አልሰሙም።+
26 በመሆኑም በምድረ በዳ ሊጥላቸው፣
ስለ እነሱ እጁን አንስቶ ማለ፤+
27 ዘራቸውን በብሔራት መካከል እንደሚጥል፣
በየአገሩ እንደሚበትናቸውም ማለ።+
28 ከዚያም በፌጎር የነበረውን ባአል አመለኩ፤+
ለሙታን የቀረቡትን መሥዋዕቶችም በሉ።
29 በሥራቸው አምላክን አስቆጡት፤+
በመካከላቸውም መቅሰፍት ተነሳ።+
30 ሆኖም ፊንሃስ ተነስቶ እርምጃ በወሰደ ጊዜ፣
መቅሰፍቱ ተገታ።+
31 ይህም በትውልዶች ሁሉ፣ ለዘላለም
ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።+
32 በመሪባ ውኃ አጠገብ አምላክን አስቆጡት፤
በእነሱም የተነሳ ሙሴ ችግር ላይ ወደቀ።+
33 መንፈሱን አስመረሩት፤
እሱም በከንፈሮቹ በችኮላ ተናገረ።+
34 ይሖዋ ባዘዛቸው መሠረት፣+
ሕዝቦቹን ከማጥፋት ወደኋላ አሉ።+
35 ይልቁንም በዚያ ከነበሩት ብሔራት ጋር ተቀላቀሉ፤+
የእነሱንም መንገድ ተከተሉ።+
36 ጣዖቶቻቸውን አመለኩ፤+
እነሱም ወጥመድ ሆኑባቸው።+
37 ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን
ለአጋንንት መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር።+
38 ንጹሕ ደም፣
ይኸውም ለከነአን ጣዖቶች የሠዉአቸውን+
የገዛ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ደም አፈሰሱ፤+
ምድሪቱም በደም ተበከለች።
39 በሥራቸው ረከሱ፤
በድርጊታቸውም መንፈሳዊ ምንዝር ፈጸሙ።+
40 በመሆኑም የይሖዋ ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤
ርስቱንም ተጸየፈ።
41 በተደጋጋሚ ጊዜያት በብሔራት እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤+
ይህም የሚጠሏቸው ሰዎች እንዲገዟቸው ነው።+
42 ጠላቶቻቸው ጨቆኗቸው፤
ለእነሱም ሥልጣን ተገዢ ሆኑ።
43 ብዙ ጊዜ ታደጋቸው፤+
እነሱ ግን ያምፁና ለመታዘዝ አሻፈረኝ ይሉ ነበር፤+
ከሠሩት ጥፋት የተነሳም ተዋረዱ።+
44 እሱ ግን ጭንቀታቸውን ይመለከት፣+
እርዳታ ለማግኘት የሚያሰሙትንም ጩኸት ይሰማ ነበር።+
45 ለእነሱ ሲል ቃል ኪዳኑን ያስታውስ ነበር፤
ታላቅ በሆነው ታማኝ ፍቅሩ ተገፋፍቶ ያዝንላቸው ነበር።+
46 የማረኳቸው ሰዎች ሁሉ
በሐዘኔታ እንዲይዟቸው ያደርግ ነበር።+
47 ይሖዋ አምላካችን ሆይ፣ አድነን፤+
ደግሞም ለቅዱስ ስምህ ምስጋና እንድናቀርብ፣
አንተንም በማወደስ ሐሴት እንድናደርግ፣+
ከብሔራት ሰብስበን።+
48 የእስራኤል አምላክ ይሖዋ
ከዘላለም እስከ ዘላለም ይወደስ፤+
ሕዝቦችም ሁሉ “አሜን!” ይበሉ።
ያህን አወድሱ!