ዘፍጥረት
45 በዚህ ጊዜ ዮሴፍ አጠገቡ በነበሩት አገልጋዮቹ ፊት ስሜቱን መቆጣጠር አልቻለም።+ በመሆኑም “ሁሉንም ሰው አስወጡልኝ!” በማለት ጮኸ። ዮሴፍ ራሱን ለወንድሞቹ በገለጠበት+ ወቅት ከእሱ ጋር ማንም ሰው አልነበረም።
2 ከዚያም ጮክ ብሎ ማልቀስ ጀመረ፤ ግብፃውያንም ሰሙት፤ በፈርዖንም ቤት ተሰማ። 3 በመጨረሻም ዮሴፍ ወንድሞቹን “እኔ ዮሴፍ ነኝ። አባቴ እስካሁን በሕይወት አለ?” አላቸው። ወንድሞቹ ግን በሁኔታው በጣም ስለደነገጡ ምንም ሊመልሱለት አልቻሉም። 4 ስለሆነም ዮሴፍ ወንድሞቹን “እባካችሁ ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው። እነሱም ወደ እሱ ቀረቡ።
ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “እኔ ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ።+ 5 አሁን ግን እኔን ወደዚህ በመሸጣችሁ አትዘኑ፤ እርስ በርሳችሁም አትወቃቀሱ፤ ምክንያቱም አምላክ ከእናንተ አስቀድሞ የላከኝ ሕይወት ለማዳን ሲል ነው።+ 6 ረሃቡ በምድር ላይ ከጀመረ ይህ ሁለተኛ ዓመቱ ነው፤+ ምንም የማይታረስባቸውና አዝመራ የማይሰበሰብባቸው አምስት ዓመታት ገና ይቀራሉ። 7 አምላክ ግን በምድር ላይ ዘራችሁን ሊያስቀርና+ በታላቅ ማዳን ሕይወታችሁን ሊታደግ ከእናንተ አስቀድሞ ላከኝ። 8 ስለዚህ ለፈርዖን ዋና አማካሪ፣* በቤቱም ሁሉ ላይ ጌታ እንዲሁም በመላው የግብፅ ምድር ላይ ገዢ ሊያደርገኝ+ ወደዚህ የላከኝ እውነተኛው አምላክ እንጂ እናንተ አይደላችሁም።
9 “ቶሎ ብላችሁ ወደ አባቴ ሂዱና እንዲህ በሉት፦ ‘ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ በመላው ግብፅ ላይ ጌታ አድርጎኛል።+ ሳትዘገይ ወደ እኔ ና።+ 10 ወንዶች ልጆችህን፣ የልጅ ልጆችህን፣ መንጎችህን፣ ከብቶችህንና ያለህን ነገር በሙሉ ይዘህ በመምጣት በአቅራቢያዬ በጎሸን ምድር ትኖራለህ።+ 11 ረሃቡ ገና ለአምስት ዓመታት ስለሚቀጥል እኔ የሚያስፈልግህን ምግብ እሰጥሃለሁ።+ አለዚያ አንተም ሆንክ ቤትህ እንዲሁም የአንተ የሆነው ሁሉ ችግር ላይ ትወድቃላችሁ።”’ 12 እንግዲህ አሁን እያናገርኳችሁ ያለሁት እኔው ራሴ መሆኔን እናንተም ሆናችሁ ወንድሜ ቢንያም በገዛ ዓይናችሁ አይታችኋል።+ 13 በመሆኑም በግብፅ ስላለኝ ክብር ሁሉ እንዲሁም ስላያችሁት ስለ ማንኛውም ነገር ለአባቴ ንገሩት። አሁንም በፍጥነት ሄዳችሁ አባቴን ወደዚህ ይዛችሁት ኑ።”
14 ከዚያም በወንድሙ በቢንያም አንገት ላይ ተጠምጥሞ አለቀሰ፤ ቢንያምም አንገቱን አቅፎት አለቀሰ።+ 15 የቀሩትን ወንድሞቹንም አንድ በአንድ እየሳመ አለቀሰ፤ ከዚህ በኋላም ወንድሞቹ ከእሱ ጋር ማውራት ጀመሩ።
16 “የዮሴፍ ወንድሞች መጥተዋል!” የሚለው ወሬ በፈርዖን ቤት ተሰማ። ፈርዖንና አገልጋዮቹም ደስ አላቸው። 17 ስለዚህ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “ወንድሞችህን እንዲህ በላቸው፦ ‘እንዲህ አድርጉ፦ የጋማ ከብቶቻችሁን ጫኑና ወደ ከነአን ምድር ሂዱ። 18 የግብፅን ምድር መልካም ነገሮች እንድሰጣችሁ አባታችሁንና ቤተሰባችሁን ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ ከዚያም ለም* ከሆነው የምድሪቱ ክፍል ትበላላችሁ።’+ 19 አንተንም እንዲህ ብለህ እንድትነግራቸው አዝዤሃለሁ፦+ ‘እንዲህ አድርጉ፦ ልጆቻችሁንና ሚስቶቻችሁን የምታጓጉዙባቸውን ሠረገሎች ከግብፅ ምድር ውሰዱ፤+ አባታችሁንም በአንዱ ሠረገላ ላይ ጭናችሁ ወደዚህ ኑ።+ 20 ስለ ንብረታችሁ+ ምንም አትጨነቁ፤ ምክንያቱም በግብፅ ምድር ያለ ምርጥ ነገር ሁሉ የእናንተው ነው።’”
21 የእስራኤልም ወንዶች ልጆች እንደተባሉት አደረጉ፤ ዮሴፍ በፈርዖን ትእዛዝ መሠረት ሠረገሎችን ሰጣቸው፤ ለጉዟቸው የሚሆን ስንቅም አስያዛቸው። 22 ለእያንዳንዳቸው ቅያሪ ልብስ ሰጣቸው፤ ለቢንያም ግን 300 የብር ሰቅልና አምስት ቅያሪ ልብስ ሰጠው።+ 23 ለአባቱም የግብፅን ምድር መልካም ነገሮች የጫኑ አሥር አህዮችን እንዲሁም ለጉዞ ስንቅ እንዲሆነው እህል፣ ዳቦና ሌሎች ምግቦችን የጫኑ አሥር እንስት አህዮችን ላከ። 24 በዚህ መንገድ ወንድሞቹን ሸኛቸው፤ እነሱም ጉዞ ሲጀምሩ “ደግሞ በመንገድ ላይ እርስ በርስ እንዳትጣሉ” አላቸው።+
25 እነሱም ከግብፅ ወጥተው ሄዱ፤ በከነአን ምድር ወዳለው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብም መጡ። 26 ከዚያም “ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ ደግሞም በመላው የግብፅ ምድር ላይ ገዢ ሆኗል!”+ ሲሉ ነገሩት። እሱ ግን ክው ብሎ ቀረ፤ ሊያምናቸውም አልቻለም።+ 27 ዮሴፍ የነገራቸውን ነገር በሙሉ ሲነግሩትና ዮሴፍ እሱን ለመውሰድ የላካቸውን ሠረገሎች ሲያይ የአባታቸው የያዕቆብ መንፈስ ታደሰ። 28 እስራኤልም “በቃ አምኛችኋለሁ! ልጄ ዮሴፍ በሕይወት አለ! እንግዲህ ከመሞቴ በፊት ሄጄ ዓይኑን ማየት አለብኝ!” አላቸው።+