ዳንኤል
3 ንጉሥ ናቡከደነጾር ቁመቱ 60 ክንድ፣* ወርዱ 6 ክንድ* የሆነ የወርቅ ምስል* ሠራ። ምስሉን በባቢሎን አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው። 2 ከዚያም ንጉሥ ናቡከደነጾር የአውራጃ ገዢዎቹ፣ አስተዳዳሪዎቹ፣ አገረ ገዢዎቹ፣ አማካሪዎቹ፣ የግምጃ ቤት ኃላፊዎቹ፣ ዳኞቹ፣ ሕግ አስከባሪዎቹና የየአውራጃዎቹ አስተዳዳሪዎች በሙሉ ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው ምስል የምረቃ ሥነ ሥርዓት እንዲሰበሰቡ ጥሪ አስተላለፈ።
3 በመሆኑም የአውራጃ ገዢዎቹ፣ አስተዳዳሪዎቹ፣ አገረ ገዢዎቹ፣ አማካሪዎቹ፣ የግምጃ ቤት ኃላፊዎቹ፣ ዳኞቹ፣ ሕግ አስከባሪዎቹና የየአውራጃዎቹ አስተዳዳሪዎች በሙሉ ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው ምስል የምረቃ ሥነ ሥርዓት ተሰበሰቡ። ናቡከደነጾር ባቆመውም ምስል ፊት ቆሙ። 4 አዋጅ ነጋሪው ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጣችሁ ሕዝቦች ሆይ፣ እንዲህ እንድታደርጉ ታዛችኋል፦ 5 የቀንደ መለከት፣ የእምቢልታ፣ የተለያዩ ባለ አውታር መሣሪያዎች፣ የባለ ሦስት ማዕዘን በገና፣ የባለ ከረጢት ዋሽንትና የሌሎቹን የሙዚቃ መሣሪያዎች ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ በግንባራችሁ ተደፍታችሁ ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው የወርቅ ምስል ስገዱ። 6 ተደፍቶ የማይሰግድ ማንኛውም ሰው ወዲያውኑ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ይጣላል።”+ 7 ስለዚህ ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡት ሕዝቦች በሙሉ የቀንደ መለከት፣ የእምቢልታ፣ የተለያዩ ባለ አውታር መሣሪያዎች፣ የባለ ሦስት ማዕዘን በገናና የሌሎቹን የሙዚቃ መሣሪያዎች ሁሉ ድምፅ ሲሰሙ ተደፍተው ንጉሥ ናቡከደነጾር ላቆመው የወርቅ ምስል ሰገዱ።
8 በዚህ ጊዜ አንዳንድ ከለዳውያን ወደ ፊት ቀርበው አይሁዳውያንን ከሰሱ።* 9 ንጉሥ ናቡከደነጾርን እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ሆይ፣ ለዘላለም ኑር። 10 ንጉሥ ሆይ፣ ማንኛውም ሰው የቀንደ መለከት፣ የእምቢልታ፣ የተለያዩ ባለ አውታር መሣሪያዎች፣ የባለ ሦስት ማዕዘን በገና፣ የባለ ከረጢት ዋሽንትና የሌሎቹን የሙዚቃ መሣሪያዎች ሁሉ ድምፅ ሲሰማ ተደፍቶ ለወርቁ ምስል እንዲሰግድ ትእዛዝ አስተላልፈሃል፤ 11 ተደፍቶ የማይሰግድ ሁሉ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት እንደሚጣል ተናግረሃል።+ 12 ሆኖም በባቢሎን አውራጃ አስተዳዳሪዎች አድርገህ የሾምካቸው ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የሚባሉ አይሁዳውያን አሉ።+ ንጉሥ ሆይ፣ እነዚህ ሰዎች ለአንተ አክብሮት የላቸውም። አማልክትህን አያገለግሉም እንዲሁም ላቆምከው የወርቅ ምስል ለመስገድ እንቢተኞች ሆነዋል።”
13 በዚህ ጊዜ ናቡከደነጾር እጅግ ተቆጥቶ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን እንዲያመጧቸው አዘዘ። እነሱንም በንጉሡ ፊት አቀረቧቸው። 14 ናቡከደነጾርም እንዲህ አላቸው፦ “ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ፣ አማልክቴን አለማገልገላችሁና+ ላቆምኩት የወርቅ ምስል አንሰግድም ማለታችሁ እውነት ነው? 15 አሁንም የቀንደ መለከት፣ የእምቢልታ፣ የተለያዩ ባለ አውታር መሣሪያዎች፣ የባለ ሦስት ማዕዘን በገና፣ የባለ ከረጢት ዋሽንትና የሌሎቹን የሙዚቃ መሣሪያዎች ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ ለሠራሁት ምስል ተደፍታችሁ ለመስገድ ፈቃደኞች ከሆናችሁ፣ መልካም! የማትሰግዱ ከሆነ ግን ወዲያውኑ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ትጣላላችሁ። ለመሆኑ ከእጄ ሊያስጥላችሁ የሚችል አምላክ ማን ነው?”+
16 ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ለንጉሡ መልሰው እንዲህ አሉ፦ “ናቡከደነጾር ሆይ፣ በዚህ ጉዳይ ለአንተ መልስ መስጠት አያስፈልገንም። 17 ወደ እሳቱ የምንጣል ከሆነ የምናገለግለው አምላካችን ከሚንበለበለው የእቶን እሳት ሊያስጥለን ይችላል፤ ንጉሥ ሆይ፣ ከእጅህም ያስጥለናል።+ 18 ሆኖም እሱ ባያስጥለንም እንኳ ንጉሥ ሆይ፣ የአንተን አማልክት እንደማናገለግልና ላቆምከው የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ እወቅ።”+
19 በዚህ ጊዜ ናቡከደነጾር በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ እጅግ ተቆጣ፤ የፊቱም ገጽታ ተለወጠባቸው፤* የእቶኑም እሳት ከወትሮው ይበልጥ ሰባት እጥፍ እንዲነድ አዘዘ። 20 ከዚያም በሠራዊቱ መካከል ያሉ ኃያላን ሰዎች ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስረው ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት እንዲጥሏቸው አዘዘ።
21 በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ልብሳቸውን እንደለበሱ ማለትም መጎናጸፊያቸውን፣ ከውስጥም ሆነ ከላይ ያደረጉትን ልብስና ጥምጥማቸውን በሙሉ እንደለበሱ ታስረው ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ተጣሉ። 22 የንጉሡ ትእዛዝ እጅግ ጥብቅ ስለነበረና የእቶኑ እሳት በኃይል ስለተቀጣጠለ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን የወሰዷቸው ሰዎች በእሳቱ ወላፈን ተቃጥለው ሞቱ። 23 ይሁንና ሦስቱ ሰዎች ይኸውም ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ እንደታሰሩ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ወደቁ።
24 ከዚያም ንጉሥ ናቡከደነጾር በድንጋጤ ከተቀመጠበት ዘሎ ተነሳ፤ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱንም “አስረን እሳት ውስጥ የጣልናቸው ሦስት ሰዎች አልነበሩም እንዴ?” ሲል ጠየቃቸው፤ እነሱም “አዎ፣ ንጉሥ ሆይ” ብለው መለሱ። 25 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፣ ያልታሰሩ አራት ሰዎች በእሳቱ መካከል ሲመላለሱ አያለሁ፤ ጉዳትም አልደረሰባቸውም፤ አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል።”
26 ናቡከደነጾር የሚንበለበል እሳት ወዳለበት እቶን በር ቀርቦ “እናንተ የልዑል አምላክ አገልጋዮች፣+ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ወጥታችሁ ወደዚህ ኑ!” አለ። ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎም ከእሳቱ ውስጥ ወጡ። 27 በዚያ ተሰብስበው የነበሩት የአውራጃ ገዢዎቹ፣ አስተዳዳሪዎቹ፣ አገረ ገዢዎቹና የንጉሡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣+ እሳቱ ሰውነታቸውን እንዳልጎዳው፣*+ ከራሳቸው ፀጉር አንዲቷ እንኳ እንዳልተቃጠለች፣ መጎናጸፊያቸው መልኩ እንዳልተለወጠና የእሳቱ ሽታ በላያቸው እንዳልነበረ ተመለከቱ።
28 ከዚያም ናቡከደነጾር እንዲህ አለ፦ “መልአኩን ልኮ አገልጋዮቹን የታደገው የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ የተመሰገነ ይሁን።+ እነሱ በእሱ በመታመን የንጉሡን ትእዛዝ ለመቀበል ፈቃደኞች አልሆኑም፤ የራሳቸውን አምላክ ትተው ሌላ አምላክ ከማገልገል ወይም ከማምለክ ይልቅ ሞትን መርጠዋል።*+ 29 ስለዚህ በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ አምላክ ላይ ማንኛውንም መጥፎ ነገር የሚናገር ከየትኛውም ብሔርና ቋንቋ የሆነ ሕዝብ ሁሉ እንዲቆራረጥ፣ ቤቱም የሕዝብ መጸዳጃ* እንዲሆን አዝዣለሁ፤ እንደ እሱ ማዳን የሚችል ሌላ አምላክ የለምና።”+
30 ከዚያም ንጉሡ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ በባቢሎን አውራጃ ውስጥ የደረጃ እድገት እንዲያገኙ አደረገ።+