አንደኛ ዜና መዋዕል
28 ዳዊት የእስራኤልን መኳንንት ሁሉ ይኸውም የነገዶቹን አለቆች፣ ንጉሡን በሚያገለግሉት ምድቦች ላይ የተሾሙትን አለቆች፣+ የሺህ አለቆቹን፣ የመቶ አለቆቹን+ እንዲሁም በንጉሡና በልጆቹ ንብረትም ሆነ መንጋ ሁሉ ላይ የተሾሙትን አለቆች+ ከቤተ መንግሥት ባለሥልጣናቱ፣ ከኃያላኑና ብቃት ካላቸው ሰዎች+ ሁሉ ጋር በኢየሩሳሌም ሰበሰባቸው። 2 ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ተነስቶ እንዲህ አለ፦
“ወንድሞቼና ወገኖቼ ሆይ፣ ስሙኝ። እኔ ለይሖዋ የቃል ኪዳን ታቦት ማረፊያና ለአምላካችን የእግር ማሳረፊያ የሚሆን ቤት ለመሥራት ከልቤ ተመኝቼ ነበር፤+ ደግሞም ይህን ቤት ለመሥራት ዝግጅት አድርጌ ነበር።+ 3 እውነተኛው አምላክ ግን ‘ብዙ ጦርነት ስላካሄድክና ደም ስላፈሰስክ ለስሜ የሚሆን ቤት አትሠራም’ አለኝ።+ 4 ይሁንና የእስራኤል አምላክ ይሖዋ በእስራኤል ላይ ለዘላለም ንጉሥ እንድሆን ከአባቴ ቤት ሁሉ መረጠኝ፤+ መሪ እንዲሆን የመረጠው ይሁዳን ነውና፤+ ከይሁዳም ቤት የአባቴን ቤት፣+ ከአባቴም ወንዶች ልጆች መካከል በመላው እስራኤል ላይ እንድነግሥ እኔን መረጠ።+ 5 ይሖዋ ከሰጠኝ ብዙ ወንዶች ልጆች+ መካከል ደግሞ በይሖዋ የንግሥና ዙፋን ላይ ተቀምጦ እስራኤልን እንዲገዛ ልጄን ሰለሞንን+ መርጦታል።+
6 “እንዲህም አለኝ፦ ‘ቤቴንና ቅጥር ግቢዎቼን የሚሠራው ልጅህ ሰለሞን ነው፤ እሱን እንደ ልጄ አድርጌ መርጬዋለሁና፤ እኔም አባቱ እሆናለሁ።+ 7 አሁን እያደረገ እንዳለው ትእዛዛቴንና ድንጋጌዎቼን+ ሳያወላውል የሚፈጽም ከሆነ ንግሥናውን ለዘላለም አጸናለሁ።’+ 8 በመሆኑም የይሖዋ ጉባኤ በሆነው በእስራኤል ሁሉ ፊት፣ አምላካችን እየሰማ ይህን እነግራችኋለሁ፦ መልካሚቱን ምድር እንድትወርሱና+ ከእናንተ በኋላ ለሚመጡት ልጆቻችሁ ቋሚ ርስት አድርጋችሁ እንድታወርሱ የአምላካችሁን የይሖዋን ትእዛዛት በሙሉ በጥብቅ ተከተሉ፤ ደግሞም ፈልጉ።
9 “አንተም ልጄ ሰለሞን ሆይ፣ የአባትህን አምላክ እወቅ፤ በሙሉ ልብና*+ በደስተኛ* ነፍስ* አገልግለው፤ ይሖዋ ልብን ሁሉ ይመረምራልና፤+ ሐሳብንና ውስጣዊ ዝንባሌን ሁሉ ይረዳል።+ ብትፈልገው ይገኝልሃል፤+ ከተውከው ግን ለዘላለም ይተውሃል።+ 10 አሁንም ለመቅደስ የሚሆን ቤት እንድትሠራ ይሖዋ እንደመረጠህ ልብ በል። እንግዲህ ደፋር ሁን፤ ሥራህንም ጀምር።”
11 ከዚያም ዳዊት የበረንዳውን፣+ የመቅደሱን ክፍሎች፣ የግምጃ ቤቶቹን፣ ሰገነት ላይ ያሉትን ክፍሎች፣ የውስጠኛዎቹን ክፍሎችና የስርየት መክደኛው+ የሚቀመጥበትን ክፍል* ንድፍ+ ለልጁ ለሰለሞን ሰጠው። 12 ዳዊት በመንፈስ የተገለጠለትን የይሖዋን ቤት ቅጥር ግቢዎች፣+ በዙሪያው ያሉትን የመመገቢያ ክፍሎች ሁሉ፣ የእውነተኛውን አምላክ ቤት ግምጃ ቤቶችና የተቀደሱት ነገሮች*+ የሚቀመጡባቸውን ግምጃ ቤቶች ንድፍ ሁሉ ለሰለሞን ሰጠው፤ 13 እንዲሁም የካህናቱንና+ የሌዋውያኑን ምድብ፣ በይሖዋ ቤት አገልግሎት የሚከናወነውን ሥራ ሁሉና በይሖዋ ቤት ለሚከናወነው አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች ሁሉ በተመለከተ መመሪያ ሰጠው፤ 14 በተጨማሪም የወርቁን ይኸውም ለተለያዩ አገልግሎቶች ለሚውሉት ዕቃዎች ሁሉ የሚያስፈልገውን ወርቅ መጠን፣ የብር ዕቃዎቹን ሁሉ መጠንና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉትን ዕቃዎች ሁሉ መጠን አሳወቀው፤ 15 ደግሞም እንደየመቅረዙ አገልግሎት ዓይነት፣ ለወርቅ መቅረዞቹና+ ለወርቅ መብራቶቻቸው ይኸውም ለተለያዩ ዓይነት መቅረዞችና መብራቶቻቸው የሚያስፈልገውን ወርቅ መጠን እንዲሁም ለብር መቅረዞቹ ማለትም ለእያንዳንዱ መቅረዝና ለመብራቶቹ የሚያስፈልገውን ብር መጠን ገለጸለት፤ 16 በተጨማሪም የሚነባበረው ዳቦ*+ ለሚቀመጥበት ለእያንዳንዱ ጠረጴዛ የሚያስፈልገውን ወርቅ መጠንና ለብር ጠረጴዛዎቹ የሚያስፈልገውን ብር መጠን አሳወቀው፤ 17 ከንጹሕ ወርቅ ለሚሠሩት ሹካዎች፣ ጎድጓዳ ሳህኖችና ማንቆርቆሪያዎች እንዲሁም ለእያንዳንዱ ትንሽ የወርቅ ጎድጓዳ ሳህን+ የሚያስፈልገውን ወርቅ መጠንና ለእያንዳንዱ ትንሽ የብር ጎድጓዳ ሳህን የሚያስፈልገውን ብር መጠን ገለጸለት። 18 ደግሞም ለዕጣኑ መሠዊያ+ የሚያስፈልገውን እንዲሁም ለሠረገላው ምስል+ ይኸውም ክንፋቸውን ለሚዘረጉትና የይሖዋን የቃል ኪዳን ታቦት ለሚሸፍኑት የወርቅ ኪሩቦች+ የሚያስፈልገውን የጠራ ወርቅ መጠን አሳወቀው። 19 ዳዊትም “የይሖዋ እጅ በእኔ ላይ ነበረ፤ የግንባታ ንድፉንም+ ዝርዝር በሙሉ በጽሑፍ እንዳሰፍር ማስተዋል ሰጠኝ” አለ።+
20 ከዚያም ዳዊት ልጁን ሰለሞንን እንዲህ አለው፦ “ደፋርና ብርቱ ሁን፤ ሥራህንም ጀምር። አትፍራ ወይም አትሸበር፤ አምላኬ፣ ይሖዋ አምላክ ከአንተ ጋር ነውና።+ በይሖዋ ቤት ለሚከናወነው አገልግሎት አስፈላጊ የሆነው ሥራ በሙሉ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከአንተ ጋር ይሆናል እንጂ አይጥልህም ወይም አይተውህም።+ 21 እነሆ፣ በእውነተኛው አምላክ ቤት ለሚከናወነው አገልግሎት ሁሉ የሚያስፈልጉት የካህናትና+ የሌዋውያን+ ምድቦች ተዘጋጅተዋል። ማንኛውንም ዓይነት አገልግሎት ለማከናወን ፈቃደኛ የሆኑና የተካኑ ሠራተኞች አሉልህ፤+ መኳንንቱና+ ሕዝቡም ሁሉ መመሪያህን በሙሉ ይፈጽማሉ።”