18 ራሱን የሚያገል ሰው ሁሉ የራስ ወዳድነት ምኞቱን ያሳድዳል፤
ጥበብንም ሁሉ ይቃወማል።
2 ሞኝ ሰው ማስተዋል አያስደስተውም፤
ይልቁንም በልቡ ያለውን ሐሳብ ይገልጣል።+
3 ክፉ ሰው ሲመጣ ንቀትም ይመጣል፤
ከውርደትም ጋር ኀፍረት ይመጣል።+
4 ከሰው አፍ የሚወጣ ቃል ጥልቅ ውኃ ነው።+
የጥበብ ምንጭ የሚንዶለዶል ጅረት ነው።
5 ለክፉ ሰው ማድላት፣
ጻድቁንም ፍትሕ መንፈግ+ መልካም አይደለም።+
6 የሞኝ ሰው ንግግር ጠብ ያስነሳል፤+
አፉም ዱላ ይጋብዛል።+
7 የሞኝ አንደበት መጥፊያው ነው፤+
ከንፈሮቹም ለሕይወቱ ወጥመድ ናቸው።
8 ስም አጥፊ የሚናገረው ቃል ጣፋጭ እንደሆነ ቁራሽ ምግብ ነው፤+
በፍጥነት ተውጦ በቀጥታ ወደ ሆድ ይገባል።+
9 በሥራው ታካች የሆነ ሰው ሁሉ፣
የአጥፊ ወንድም ነው።+
10 የይሖዋ ስም ጽኑ ግንብ ነው።+
ጻድቅ ወደዚያ በመሮጥ ጥበቃ ያገኛል።+
11 የባለጸጋ ሰው ሀብት የተመሸገ ከተማው ነው፤
በሐሳቡም ጥበቃ እንደሚያስገኝ ግንብ አድርጎ ይመለከተዋል።+
12 ሰው ለውድቀት ከመዳረጉ በፊት ልቡ ይታበያል፤+
ትሕትና ግን ክብርን ትቀድማለች።+
13 እውነታውን ከመስማቱ በፊት መልስ የሚሰጥ ሰው፣
ሞኝነት ይሆንበታል፤ ውርደትም ይከናነባል።+
14 ጠንካራ መንፈስ ያለው ሰው ሕመሙን መቋቋም ይችላል፤+
የተደቆሰን መንፈስ ግን ማን ሊቋቋም ይችላል?+
15 የአስተዋይ ሰው ልብ እውቀትን ያገኛል፤+
የጥበበኛም ጆሮ እውቀትን ለማግኘት ይጥራል።
16 ስጦታ ለሰጪው መንገዱን ይከፍትለታል፤+
በታላላቅ ሰዎችም ፊት መቅረብ ያስችለዋል።
17 ክሱን አስቀድሞ ያሰማ ትክክለኛ ይመስላል፤+
ይህም ሌላው ወገን መጥቶ እስኪመረምረው ድረስ ነው።+
18 ዕጣ መጣል ጭቅጭቅ እንዲያበቃ ያደርጋል፤+
ኃይለኛ ባላንጣዎችንም ይገላግላል።
19 የተበደለ ወንድም ከተመሸገች ከተማ ይበልጥ የማይበገር ነው፤+
እንደ ግንብ በሮች መቀርቀሪያም የጠነከረ ጠብ አለ።+
20 ሰው በአፉ ፍሬ ሆዱ ይሞላል፤+
ከንፈሩም በሚያስገኘው ምርት ይረካል።
21 አንደበት የሞትና የሕይወት ኃይል አላት፤+
ሊጠቀምባት የሚወድ ፍሬዋን ይበላል።+
22 ጥሩ ሚስት ያገኘ ጥሩ ነገር አግኝቷል፤+
የይሖዋንም ሞገስ ያገኛል።+
23 ድሃ እየተለማመጠ ይናገራል፤
ሀብታም ግን በኃይለ ቃል ይመልሳል።
24 እርስ በርስ ከመጠፋፋት ወደኋላ የማይሉ ጓደኛሞች አሉ፤+
ነገር ግን ከወንድም ይበልጥ የሚቀርብ ጓደኛ አለ።+