የሐዋርያት ሥራ
24 ከአምስት ቀን በኋላ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ+ ከተወሰኑ ሽማግሌዎችና ጠርጡለስ ከሚባል ጠበቃ ጋር ወደ ቂሳርያ ወረደ፤ እነሱም በጳውሎስ ላይ ያላቸውን ክስ ለአገረ ገዢው አቀረቡ።+ 2 በተጠራም ጊዜ ጠርጡለስ እንዲህ ሲል ይከሰው ጀመር፦
“ክቡር ፊሊክስ ሆይ፣ በአንተ አማካኝነት ብዙ ሰላም አግኝተናል፤ አስተዋይነትህም ለዚህ ሕዝብ መሻሻል አስገኝቷል፤ 3 በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም ቦታ ለእነዚህ ነገሮች ሁሉ ታላቅ ምስጋና እናቀርባለን። 4 ይሁንና አሁን ጊዜህን እንዳልወስድብህ በአጭሩ የምንነግርህን ጉዳይ መልካም ፈቃድህ ሆኖ እንድትሰማን እለምንሃለሁ። 5 ይህ ሰው መቅሰፍት* ሆኖብናል፤+ በዓለም ባሉት አይሁዳውያን ሁሉ መካከል ዓመፅ ያነሳሳል፤+ ከዚህም ሌላ የናዝሬታውያን ኑፋቄ ቀንደኛ መሪ ነው።+ 6 በዚህ ላይ ደግሞ ቤተ መቅደሱን ለማርከስ ሲሞክር ስላገኘነው ያዝነው።+ 7 *—— 8 አንተ ራስህ ስትመረምረው በእሱ ላይ ያቀረብነው ክስ ትክክል መሆኑን ማረጋገጥ ትችላለህ።”
9 አይሁዳውያኑም የተባለው ነገር ሁሉ እውነት መሆኑን በመግለጽ በክሱ ተባበሩ። 10 አገረ ገዢውም እንዲናገር በጭንቅላቱ ምልክት በሰጠው ጊዜ ጳውሎስ እንዲህ ሲል መለሰ፦
“ለብዙ ዓመታት ለዚህ ሕዝብ ፈራጅ ሆነህ ስታገለግል መቆየትህን አውቃለሁ፤ በመሆኑም ስለ ራሴ የመከላከያ መልስ የማቀርበው በደስታ ነው።+ 11 ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ከ12 ቀን እንደማይበልጥ አንተው ራስህ ማረጋገጥ ትችላለህ፤+ 12 እንዲሁም በቤተ መቅደሱ ከማንም ጋር ስከራከርም ሆነ በምኩራቦች ወይም በከተማው ውስጥ ሕዝቡን ለዓመፅ ሳነሳሳ አላገኙኝም። 13 በተጨማሪም አሁን ላቀረቡብኝ ክስ ሁሉ ምንም ማስረጃ ሊያቀርቡልህ አይችሉም። 14 ይሁን እንጂ በሕጉና በነቢያት የተጻፉትን ነገሮች ሁሉ+ ስለማምን እነሱ ኑፋቄ ብለው የሚጠሩትን የሕይወት መንገድ እንደምከተልና በዚህም መንገድ ለአባቶቼ አምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንደማቀርብ አልክድም።+ 15 ደግሞም እነዚህ ሰዎች ራሳቸው ተስፋ እንደሚያደርጉት ጻድቃንም ሆኑ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች+ ከሞት እንደሚነሱ+ በአምላክ ተስፋ አለኝ። 16 በዚህ የተነሳ በአምላክም ሆነ በሰው ፊት ንጹሕ* ሕሊና ይዤ ለመኖር ሁልጊዜ ጥረት አደርጋለሁ።+ 17 ከብዙ ዓመታት በኋላም ለወገኖቼ ምጽዋት ለመስጠትና+ ለአምላክ መባ ለማቅረብ መጣሁ። 18 በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያገኙኝ የመንጻት ሥርዓት ፈጽሜ+ ይህንኑ ሳደርግ እንጂ ከብዙ ሕዝብ ጋር ሆኜ ሁከት ሳነሳሳ አልነበረም። ሆኖም ከእስያ አውራጃ የመጡ አንዳንድ አይሁዳውያን ነበሩ፤ 19 እነሱ እኔን የሚከሱበት ነገር ካላቸው እዚህ ፊትህ ተገኝተው ሊከሱኝ ይገባ ነበር።+ 20 ወይም እዚህ ያሉት ሰዎች በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት በቀረብኩበት ጊዜ ያገኙብኝ ጥፋት ካለ እነሱ ራሳቸው ይናገሩ፤ 21 በመካከላቸው ቆሜ በነበረበት ጊዜ ድምፄን ከፍ አድርጌ ‘ዛሬ በፊታችሁ ለፍርድ የቀረብኩት በሙታን ትንሣኤ በማመኔ ነው!’ ብዬ ከመናገር በቀር ያደረግኩት ነገር የለም።”+
22 ይሁን እንጂ ፊሊክስ ስለ ጌታ መንገድ+ በሚገባ ያውቅ ስለነበረ “የሠራዊቱ ሻለቃ ሉስዮስ ሲመጣ ለጉዳያችሁ ውሳኔ እሰጣለሁ” በማለት ያቀረቡትን ክስ ለሌላ ጊዜ አስተላለፈው። 23 ከዚያም ጳውሎስ በቁጥጥር ሥር እንዲቆይ፣ ይሁንና መጠነኛ ነፃነት እንዲሰጠው መኮንኑን አዘዘው፤ ደግሞም ወዳጆቹ የሚያስፈልገውን ነገር ለማድረግ ሲመጡ እንዲፈቅድላቸው መመሪያ ሰጠው።
24 ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ፊሊክስ አይሁዳዊት ከሆነችው ሚስቱ ከድሩሲላ ጋር መጣ፤ ጳውሎስንም አስጠርቶ በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ማመን ሲናገር አዳመጠው።+ 25 ጳውሎስ ስለ ጽድቅ፣ ራስን ስለ መግዛትና ስለሚመጣው ፍርድ+ ሲናገር ግን ፊሊክስ ፈርቶ “ለአሁኑ ይበቃል፤ አጋጣሚ ሳገኝ ግን እንደገና አስጠራሃለሁ” አለው። 26 በዚሁ አጋጣሚ ጳውሎስ ጉቦ ይሰጠኛል ብሎ ተስፋ ያደርግ ስለነበር ብዙ ጊዜ እያስጠራ ያነጋግረው ነበር። 27 ይሁንና ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ፊሊክስ በጶርቅዮስ ፊስጦስ ተተካ፤ በዚህ ጊዜ ፊሊክስ በአይሁዳውያን ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፍ ስለፈለገ+ ጳውሎስን እንደታሰረ ተወው።