የማርቆስ ወንጌል
6 ከዚያ ተነስቶ ወደ ትውልድ አገሩ መጣ፤+ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። 2 እሱም በሰንበት ቀን በምኩራብ ማስተማር ጀመረ፤ የሰሙትም አብዛኞቹ ሰዎች በመገረም እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች የተማረው ከየት ነው?+ ይህን ጥበብ ያገኘውስ እንዴት ነው? ደግሞስ እንዲህ ያሉ ተአምራትን ማከናወን የቻለው እንዴት ነው?+ 3 ይህ አናጺው+ የማርያም ልጅ+ እንዲሁም የያዕቆብ፣+ የዮሴፍ፣ የይሁዳና የስምዖን ወንድም+ አይደለም? እህቶቹስ የሚኖሩት ከእኛው ጋር አይደለም?” ከዚህም የተነሳ ተሰናከሉበት። 4 ኢየሱስ ግን “ነቢይ በገዛ አገሩ፣ በዘመዶቹ ዘንድና በገዛ ቤቱ ካልሆነ በስተቀር በሌላ ቦታ ሁሉ ይከበራል” አላቸው።+ 5 ስለሆነም ጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን በመጫን ከመፈወስ በቀር በዚያ ሌላ ተአምር መፈጸም አልቻለም። 6 እንዲያውም ባለማመናቸው እጅግ ተደነቀ። ከዚህ በኋላ በዙሪያው ባሉት መንደሮች እየተዘዋወረ አስተማረ።+
7 አሥራ ሁለቱን ከጠራ በኋላ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤+ ርኩሳን መናፍስትን እንዲያዝዙም ሥልጣን ሰጣቸው።+ 8 ደግሞም ከበትር በስተቀር ለጉዟቸው ዳቦም ሆነ የምግብ ከረጢት እንዲሁም በመቀነታቸው ገንዘብ* እንዳይዙ አዘዛቸው፤+ 9 በተጨማሪም ሁለት ልብስ* እንዳይዙ፣ ጫማ ግን እንዲያደርጉ ነገራቸው። 10 አክሎም እንዲህ አላቸው፦ “ወደ አንድ ቤት ስትገቡ አካባቢውን ለቃችሁ እስክትሄዱ ድረስ እዚያው ቆዩ።+ 11 ነገር ግን የሚቀበላችሁ ወይም የሚሰማችሁ ካጣችሁ ከዚያ ቦታ ስትወጡ ምሥክር እንዲሆንባቸው የእግራችሁን አቧራ አራግፉ።”*+ 12 እነሱም ከዚያ ወጥተው ሰዎች ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰበኩ፤+ 13 ብዙ አጋንንትም አስወጡ፤+ እንዲሁም ብዙ ሕመምተኞችን ዘይት እየቀቡ ፈወሱ።
14 የኢየሱስ ስም በሰፊው ታውቆ ስለነበር ንጉሥ ሄሮድስ ይህን ሰማ፤ ሰዎችም “አጥማቂው ዮሐንስ ከሞት ተነስቷል፤ እንዲህ ያሉ ተአምራት መፈጸም የቻለውም ለዚህ ነው” ይሉ ነበር።+ 15 ሌሎች ግን “ኤልያስ ነው” ይሉ ነበር። ሌሎች ደግሞ “እንደቀድሞዎቹ ነቢያት ያለ ነቢይ ነው” ይሉ ነበር።+ 16 ሄሮድስ ግን ይህን በሰማ ጊዜ “እኔ ራሱን የቆረጥኩት ዮሐንስ ከሞት ተነስቷል” አለ። 17 ሄሮድስ የወንድሙ የፊልጶስ ሚስት በሆነችው በሄሮድያዳ ምክንያት ሰዎች ልኮ ዮሐንስን በማስያዝ በሰንሰለት አስሮ ወህኒ አስገብቶት ነበር፤ ይህም የሆነው ሄሮድስ እሷን አግብቶ ስለነበር ነው።+ 18 ዮሐንስ ሄሮድስን “የወንድምህን ሚስት እንድታገባ ሕግ አይፈቅድልህም” ይለው ነበር።+ 19 በመሆኑም ሄሮድያዳ በእሱ ላይ ቂም ይዛ ልትገድለው ትፈልግ ነበር፤ ሆኖም ይህን ማድረግ አልቻለችም። 20 ሄሮድስ፣ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው+ መሆኑን ስለሚያውቅ ይፈራውና ጉዳት እንዳያገኘው ይጠብቀው ነበር። ዮሐንስ የሚናገረውን ሲሰማ ምን እንደሚያደርገው ግራ ይገባው የነበረ ቢሆንም በደስታ ያዳምጠው ነበር።
21 ይሁንና ሄሮድስ በልደት ቀኑ+ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱን፣ የጦር አዛዦቹንና በገሊላ ያሉ ታላላቅ ሰዎችን ራት በጋበዘ ጊዜ ሄሮድያዳ ምቹ አጋጣሚ ተፈጠረላት።+ 22 የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ በመጨፈር ሄሮድስንና ከእሱ ጋር እየበሉ የነበሩትን አስደሰተቻቸው። ንጉሡም ልጅቷን “የፈለግሽውን ሁሉ ጠይቂኝ፣ እሰጥሻለሁ” አላት። 23 ደግሞም “እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ” ሲል ማለላት። 24 እሷም ወደ እናቷ ሄዳ “ምን ብጠይቀው ይሻላል?” አለቻት። እናቷም “የአጥማቂው ዮሐንስን ራስ ጠይቂው” አለቻት። 25 ወዲያውም ወደ ንጉሡ ፈጥና በመግባት “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አሁኑኑ በሳህን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” ስትል ጠየቀችው።+ 26 ንጉሡ በዚህ እጅግ ቢያዝንም ስለገባው መሐላና ስለ እንግዶቹ ሲል እንቢ ሊላት አልፈለገም። 27 ከዚያም ንጉሡ ጠባቂውን ወዲያው ልኮ የዮሐንስን ራስ እንዲያመጣ አዘዘው። ጠባቂውም ሄዶ ወህኒ ቤት ውስጥ ራሱን ቆረጠው፤ 28 ራሱንም በሳህን ይዞ መጣ። ከዚያም ለልጅቷ ሰጣት፤ ልጅቷም ለእናቷ ሰጠቻት። 29 ደቀ መዛሙርቱም ይህን በሰሙ ጊዜ መጥተው አስከሬኑን በመውሰድ በመቃብር አኖሩት።
30 ሐዋርያቱ በኢየሱስ ዙሪያ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ነገር ሁሉ ነገሩት።+ 31 እሱም “ለብቻችን ወደ አንድ ገለል ያለ ስፍራ እንሂድና በዚያ ትንሽ አረፍ በሉ” አላቸው።+ ብዙዎች ይመጡና ይሄዱ ስለነበር ምግብ ለመብላት እንኳ ፋታ አላገኙም። 32 ስለዚህ ብቻቸውን ለመሆን በጀልባ ተሳፍረው ገለል ወዳለ ስፍራ ሄዱ።+ 33 ይሁንና ሰዎች ሲሄዱ አዩአቸው፤ ብዙዎችም መሄዳቸውን አወቁ፤ ስለሆነም ከከተሞች ሁሉ አንድ ላይ በእግር በመሮጥ ቀድመዋቸው ደረሱ። 34 ኢየሱስም ከጀልባዋ ሲወርድ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተመለከተ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች+ ስለነበሩም በጣም አዘነላቸው።+ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር።+
35 ሰዓቱ እየገፋ በመሄዱ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፦ “ይህ ቦታ ራቅ ያለ ነው፤ ሰዓቱ ደግሞ ገፍቷል።+ 36 በአካባቢው ወዳሉት ገጠሮችና መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ አሰናብታቸው።”+ 37 እሱም መልሶ “እናንተ የሚበሉት ነገር ስጧቸው” አላቸው። እነሱም “ሄደን በ200 ዲናር* ዳቦ ገዝተን እንዲበሉ እንስጣቸው?” አሉት።+ 38 እሱም “ስንት ዳቦ አላችሁ? እስቲ ሄዳችሁ እዩ!” አላቸው። ሄደው ካዩ በኋላ “አምስት ዳቦና ሁለት ዓሣ” አሉት።+ 39 ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ በቡድን በቡድን ሆኖ በለመለመው መስክ ላይ እንዲቀመጥ አዘዘ።+ 40 በመሆኑም ሕዝቡ መቶ መቶና ሃምሳ ሃምሳ እየሆነ በቡድን ተቀመጠ። 41 እሱም አምስቱን ዳቦና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ ቀና በማለት ባረከ።+ ከዚያም ዳቦውን ቆርሶ ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ ሁለቱን ዓሣም ለሁሉም አከፋፈለ። 42 ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ 43 ከዚያም ቁርስራሹን ሰበሰቡ፤ ቁርስራሹም ዓሣውን ሳይጨምር 12 ቅርጫት ሙሉ ሆነ።+ 44 ዳቦውን የበሉትም 5,000 ወንዶች ነበሩ።
45 ወዲያውም፣ እሱ ሕዝቡን እያሰናበተ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ጀልባ ተሳፍረው በቤተሳይዳ አቅጣጫ ወዳለው የባሕር ዳርቻ ቀድመውት እንዲሻገሩ አደረገ።+ 46 ከተሰናበታቸው በኋላ ግን ለመጸለይ ወደ አንድ ተራራ ወጣ።+ 47 በመሸም ጊዜ ጀልባዋ በባሕሩ መካከል ነበረች፤ እሱ ግን ብቻውን የብስ ላይ ነበር።+ 48 ነፋሱ ከፊት ለፊታቸው ይነፍስ ስለነበር ለመቅዘፍ ሲታገሉ ባያቸው ጊዜ በአራተኛው ክፍለ ሌሊት* ገደማ በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ እነሱ መጣ፤ ይሁንና አልፏቸው ሊሄድ ነበር።* 49 እነሱም በባሕሩ ላይ ሲራመድ ባዩት ጊዜ “ምትሃት ነው!” ብለው ስላሰቡ በኃይል ጮኹ። 50 ሁሉም እሱን ባዩት ጊዜ ተረበሹ። ሆኖም ወዲያውኑ አነጋገራቸው፤ ደግሞም “አይዟችሁ! እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው።+ 51 ከዚያም ጀልባዋ ላይ ወጥቶ አብሯቸው ሆነ፤ ነፋሱም ቆመ። በዚህ ጊዜ በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት ተዋጡ፤ 52 ይህም የሆነው የዳቦውን ተአምር ትርጉም ባለማስተዋላቸው ነው፤ ልባቸው አሁንም መረዳት ተስኖት ነበር።
53 ወደ የብስ በተሻገሩ ጊዜ ጌንሴሬጥ ደረሱ፤ በአቅራቢያውም ጀልባዋን አቆሙ።+ 54 ሆኖም ከጀልባዋ እንደወረዱ ሰዎች አወቁት። 55 ወደ አካባቢው ሁሉ በመሮጥ ሕመምተኞችን በቃሬዛ እየተሸከሙ እሱ ይገኝበታል ወደተባለው ቦታ ያመጡ ጀመር። 56 በገባበት መንደር ወይም ከተማ ወይም ገጠር ሁሉ ሕመምተኞቹን በገበያ ስፍራ* ያስቀምጡ ነበር፤ የልብሱንም ዘርፍ እንኳ ለመንካት ይማጸኑት ነበር።+ የነኩትም ሁሉ ተፈወሱ።