29 ብዙ ጊዜ ተወቅሶ አንገቱን ያደነደነ ሰው፣+
ሊፈወስ በማይችል ሁኔታ በድንገት ይሰበራል።+
2 ጻድቃን ሲበዙ ሕዝብ ሐሴት ያደርጋል፤
ክፉ ሰው ሲገዛ ግን ሕዝብ ይቃትታል።+
3 ጥበብን የሚወድ ሰው አባቱን ደስ ያሰኛል፤+
ከዝሙት አዳሪዎች ጋር የሚወዳጅ ግን ሀብቱን ያባክናል።+
4 ንጉሥ ፍትሕ በማስፈን አገርን ያረጋጋል፤+
ጉቦ የሚፈልግ ሰው ግን ያወድማታል።
5 ባልንጀራውን የሚሸነግል ሰው፣
ለእግሩ ወጥመድ ይዘረጋበታል።+
6 መጥፎ ሰው በደሉ ወጥመድ ይሆንበታል፤+
ጻድቅ ግን እልል ይላል፤ ሐሴትም ያደርጋል።+
7 ጻድቅ ለድሆች መብት ይቆረቆራል፤+
ክፉ ሰው ግን ለእንዲህ ዓይነት ጉዳይ ደንታ የለውም።+
8 ጉራ የሚነዙ ሰዎች ከተማን ያቃጥላሉ፤+
ጥበበኞች ግን ቁጣን ያበርዳሉ።+
9 ጥበበኛ ሰው ከሞኝ ጋር ቢሟገት፣
ሁከትና ፌዝ ይነግሣል፤ ደስታ ግን አይኖርም።+
10 ደም የተጠሙ ሰዎች ንጹሕ የሆነን ሰው ሁሉ ይጠላሉ፤+
ቅን የሆነውን ሰው ሕይወት ለማጥፋት ይሻሉ።
11 ሞኝ ስሜቱን ሁሉ እንዳሻው ይገልጻል፤+
ጥበበኛ ግን ስሜቱን ይቆጣጠራል።+
12 ገዢ የሐሰት ወሬ የሚሰማ ከሆነ፣
አገልጋዮቹ ሁሉ ክፉዎች ይሆናሉ።+
13 ድሃንና ጨቋኝን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ፦
ይሖዋ ለሁለቱም የዓይን ብርሃን ይሰጣል።
14 ንጉሥ ለድሆች በትክክል ሲፈርድ፣+
ዙፋኑ ምንጊዜም ጸንቶ ይኖራል።+
15 በትርና ወቀሳ ጥበብ ያስገኛሉ፤+
መረን የተለቀቀ ልጅ ግን እናቱን ያሳፍራል።
16 ክፉዎች ሲበዙ ክፋት ይበዛል፤
ጻድቃን ግን የእነሱን ውድቀት ያያሉ።+
17 ልጅህን ገሥጸው፤ ሰላም ይሰጥሃል፤
ደግሞም እጅግ ደስ ያሰኝሃል።+
18 ራእይ ከሌለ ሕዝብ እንዳሻው ይሆናል፤+
ሕግን የሚጠብቁ ግን ደስተኞች ናቸው።+
19 አገልጋይ በቃል ብቻ ለመታረም ፈቃደኛ አይሆንም፤
የሚነገረውን ነገር ቢረዳውም እንኳ እሺ ብሎ አይታዘዝምና።+
20 ለመናገር የሚቸኩል ሰው አይተህ ታውቃለህ?+
ከእሱ ይልቅ ሞኝ የተሻለ ተስፋ አለው።+
21 አገልጋይ ከልጅነቱ ጀምሮ ከተሞላቀቀ፣
የኋላ ኋላ ምስጋና ቢስ ይሆናል።
22 በቀላሉ የሚቆጣ ሰው ጠብ ያስነሳል፤+
ግልፍተኛ የሆነም ብዙ በደል ይፈጽማል።+
23 ሰውን ትዕቢቱ ያዋርደዋል፤+
ትሑት መንፈስ ያለው ግን ክብር ይጎናጸፋል።+
24 የሌባ ግብረ አበር ራሱን ይጠላል።
እንዲመሠክር የቀረበለትን ጥሪ ቢሰማም ምንም አይናገርም።+
25 ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው፤+
በይሖዋ የሚታመን ግን ጥበቃ ያገኛል።+
26 ብዙዎች ከገዢ ጋር ተገናኝተው መነጋገር ይሻሉ፤
ሰው ግን ፍትሕ የሚያገኘው ከይሖዋ ነው።+
27 ጻድቅ ፍትሐዊ ያልሆነን ሰው ይጸየፋል፤+
ክፉ ሰው ግን በቀና መንገድ የሚሄደውን ይጸየፋል።+