ሕዝበ ክርስትና በከነዓናውያን መንገድ እየሄደች ነው
ከነዓናውያን የነበራቸው ሃይማኖት ምንዝርን፣ ዝሙትን፣ ግብረ ሰዶምን እና ልጆችን መግደል ያካተተ ነበር። በዚህም ምክንያት ምድሪቱ ተፋቻቸው። እስራኤላውያንም ተመሳሳይ መንገድ በመከተል ይህንን ጸያፍ ነገር ከይሖዋ አምልኮ ጋር በመቀላቀላቸው ምድሪቱ ተፋቻቸው። ዛሬም ቢሆን ክርስቲያን ነን የሚሉ ነገር ግን የጥንቱን የጾታ ብልግና ተከትለው የሚሄዱ ሰዎችና ሃይማኖቶች አሉ። ምንዝርና ዝሙት የተለመደ የዕለት ተዕለት ተግባር ሆኗል። የግብረ ሰዶም ድርጊትና በማሕፀን ያሉ ሕፃናትን ሕይወት ማጥፋት በፍጥነት እያደጉና እየተስፋፉ መጥተዋል። በከነዓን በመቶዎች የሚቆጠሩ የማይፈለጉ ሕጻናት ለመሥዋዕት ይቀርቡ ነበር፤ ዛሬ ደግሞ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሕፃናት እንደ ቁሻሻ እየተጠረጉ ነው። ይህም አኃዝ በዓመት 55 ሚልዮን ይደርሳል።—ከዘጸአት 21:22, 23 ጋር አወዳድር።
ዛሬ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ጊዜ ያለፈበት ወይም ኋላ ቀር ሆነው ላለመታየት “ሁሉም ያስኬዳል” የሚለውን ዘመናዊ ፈሊጥ እየተከተሉ ነው። ለተሰበሰቡት አዳማጮቹ ኮንዶም ለማደል ሲል ስብከቱን ቆም እንዳደረገው የዩኒታሪያን ዩኒቨርሳል ቄስ አንዳንዶቹም “በጥንቃቄ” የጾታ ኃጢአት የሚፈጽሙበትን ሁኔታ ሳይቀር ያመቻቹላቸዋል።
የኤጲስቆጶሳውያን እምነት ተከታይ የሆነ አንድ የጋዜጣ አምድ አዘጋጅ ሲናገር “በ1980ዎቹ ውስጥ የነበረችው የኤጲስቆጶሳውያን ቤተ ክርስቲያን የጌጥ ማከማቻ ሱቅ ሆና ነበር። ወቅታዊ መስሎ በሚታየው በማንኛውም ዓይነት ማሕበራዊ ዘርፍ ሁሉን አዘጋጅታ ለሕዝብ በማቅረብ ረገድ ልንመካባት የምንችል ናት። በአንዳንድ ዓመታት ወረቱ ፖለቲካ ነበር። በዚህ ዓመት ደግሞ ጾታ ሆኗል” ብሏል። በመሰጠት ላይ ያለውን አዲስ የጾታ ሥርዓተ ትምህርት በተመለከተም “ክርስቲያኖች በተመሳሳይ ጾታና . . . ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚደረገውን የጾታ ግንኙነት ደስታ ለመካፈል እምቢ የሚሉበት ጊዜ አልፏል” የሚለውን ትምህርት ጠቅሷል። በኒው ዮርክ የሚገኙ አንድ የኤጲስቈጶሳውያን ጳጳስ “ክፉውንና ደጉን በመለየት የተፈጸመ ግብረ ሰዶም ከሆነ አንድ ቀን እንደ አምላክ ፈቃድ ተደርጎ የሚታይበት ጊዜ ይመጣል” ብለዋል።
በየሳምንቱ ከሚወጣው ዩናይትድ ሜቶዲስት ሪፖርተር ከተባለው ሃይማኖታዊ ጋዜጣ ጋር አብረው የሚሠሩት ሮይ ሆዋርድ ቤክ ኦን ቲን አይስ በተባለው መጽሐፋቸው “በሥነ ምግባር ብልግና የሚወድቁት የቴሌቪዥን ወንጌላውያን፣ ከፍተኛ ቦታ ላይ ያሉ ሰባኪዎች፣ ጳጳሳት፣ በጣም የታወቁና በስብከታቸው የተደነቁ መሪዎች፣ ጎላ ብለው የሚታዩ መሪዎች፣ የተከበሩ የትናንሽ አብያተ ክርስቲያናት ፓስተሮች፣ ካህናት፣ የጰንጠቆስጤ እምነት አባሎች፣ ሊበራሎች፣ ወግ አጥባቂዎች ሌሎቹም ተጨምረው ቤተ ክርስቲያን የኅብረተሰቡን ማሕበራዊ ሁኔታ በመለወጥ ረገድ ባላት ሚና ላይ ያተኮረ እንዴት ያለ ሐተታ ቀርቧል!” በማለት ጽፈዋል።—ገጽ 214
የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን
የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ፓርላማ ማለትም አጠቃላይ ሲኖዶሱ “ምንዝር፣ ዝሙት እና የግብረ ሰዶም ድርጊቶች ኃጢያት መሆናቸውን” ለማረጋገጥ ድምፅ የሚሰጥ ጉባኤ በኅዳር 1987 ተካሄዶ ነበር። የግብረ ሰዶማውያን ክርስቲያን ሴቶችና ወንዶች እንቅስቃሴ ዋና ጸሐፊ “ይህ ነገር ውሳኔ አግኝቶ ቢጸድቅ ቤተ ክርስቲያኗን ያፈራርሳታል፤ ይህንንም የከንተር ቤሪው ሊቀ ጳጳስ ያውቃሉ። በአጠቃላይ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚያክሉት የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች እንደሆኑ እናምናለን” በማለት ተናግረዋል።
ፊሊፕ ኬኔዲ የተባሉ ሪፖርተር ጥቅምት 29, 1987 ዴይሊ ኤክስፕሬስ በተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ ላይ “ማርጋሬት ታቸር የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለሕዝቡ በቂ የሥነ ምግባር መመሪያ ለመስጠት ባለመቻላቸው የሰነዘሩት ወቀሳ በአሥር ዓመቱ ውስጥ ከታዩት ሁሉ ይበልጣል ተብሎ የተነገረለትን የቄሶች ሽኩቻ ይበልጥ ያጋልጠዋል። ምክንያቱም ጳጳሳቱ በጠቅላላና በተለይም በካንተርቤሪ የሚገኙት ሊቃነ ጳጳሳት የወላዋዮችና የቀባዣሪዎች ክምችት መሆናቸውን የተረዱት ጠቅላይ ሚንስትሯ ብቻ አለመሆናቸው ነው።”
በኅዳር 11, 1987 ጉባኤው ሲካሄድ ጉዳዩ አልዋጥ ያለ ትልቅ ክኒን ሆኖባቸው ነበር። ከዚያም ብዙዎቹ በተስማሙበት ደካማ የማሻሻያ ሐሳብ አወራረዱት። በመሆኑም እንደተባለለት “የአሥርተ ዓመቱ ታላቅ የቀሳውስት ሽኩቻ” ሳይሆን ቀረ። ሁኔታው ሁሉ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆኖ ተጠናቀቀ። ለታይታ የተቀመጡት ቄሶች ራሳቸውን ቀበሩ፣ ከተጠያቂነት ለማምለጥ ተሽሎከለኩ፣ ለማስመሰል ሞከሩ፣ ከአቋማቸውም አፈገፈጉ።
የጠቅላይ ሲኖዶሱ ውሳኔ እንዲህ የሚል ነበር:- እንደ ደንቡ የጾታ ግንኙነት መፈጸም ያለበት ቋሚ በሆነ ጋብቻ ከተሳሰሩ ብቻ ነው፤ ምንዝርና ዝሙት ይህን ሥርዓት የሚጻረሩ ኃጢአቶች ናቸው፤ ግብረ ሰዶማዊ የጾታ ግንኙነት ግን ይህንን ሥርዓት አይፈጽምም፤ ክርስቲያኖች ሁሉ የጾታ ሥነ ምግባርን ጨምሮ በሁሉም የሥነ ምግባር ዘርፍ ምሳሌ መሆን አለባቸው። ግብረ ሰዶም ከምንዝርና ከዝሙት ይልቅ ቀለል ብሎ ታይቷል፤ ምንዝርና ዝሙት ግን ከሥርዓቱ ተጻራሪ እንደሆኑ ተደርገው ሲገለጹ ግብረ ሰዶም የፈጸመ ግን እንዲያው ሥርዓቱን እንዳላሟላ ብቻ ተደርጎ ታይቷል። አመንዝሮቹ አይወገዱም። ዝሙት የሚፈጽሙትም ከሥራቸው አይባረሩም። ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ቀሳውስትና ገበዛትም ነጻ ሆነዋል።
ሲኖዶሱ ያሰማው መለከት ትርጉም የለሽ ነበር፤ በደብር አለቃው በቶኒ ሃይተን የቀረበው የመጀመሪያ ጥያቄም ተድበስብሶ ቀረ። (1 ቆሮንቶስ 14:8) ይሁንና በጉባኤው ለተላለፈው ደካማ ውሳኔ ድጋፍ መስጠቱ እንግዳ ነገር ሲሆን በውጤቱም “በጣም በጣም ተደስቶ” ነበር። ቀደም ሲል “ቤተ ክርስቲያን ቤትዋን ሥርዓት ካላስያዘች አምላክ እራሱ ይፈርድባታል” ሲል ከሰጠው ማስፈራርያ ጋር ሲነጻጸር አሁን የሰጠው ምላሽ ግራ የሚያጋባ ነው።
በሲኖዶሱ ጉባኤ ወቅት ሃይተን ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ቄሶችን የሚያጋልጥ ስሜት ቀስቃሽ የሆነ ማስረጃ አቅርቦ ነበር። አንዱ ሕጻናትን በማባለግ ተወንጅሎ ወደ ሌላ ደብር እንዲዛወር ብቻ ተደረገ። ሌላው ቄስ ደግሞ በሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች ውስጥ በሚፈጽመው ብልግና የሞላበት ድርጊት ተወንጅሎ ወደ ሌላ አገረ ስብከት ተዛወረ፤ እዚያም ቢሆን በተመመሳሳይ ጉዳይ ቢከሰስም ከኃላፊነት ቦታው ግን አልወረደም። ሃይተን ሪፖርት እንዳደረገው በለንደን የሚገኙ ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ የአንግሊካን ቄሶች የቤተ ክርስቲያኑን የመጻሕፍት መሸጫ “የግብረ ሰዶም ድርጊትን፣ የወንድ ጋለሞታዎችን ጥቅምና የተለያዩ ዓይነት የግብረ ሰዶም ድርጊቶችን ያበረታታሉ ብለው የሚያምኑባቸው መጽሔቶች ይሸጡበታል።” በዚያ ከሚሸጡት መጻሕፍት መካከል አንዱ “አንዲት የአምስት ዓመት ልጅ ከአባቷና ከእርሱ የወንድ ፍቅረኛ ጋር በአልጋ ላይ ተኝታ ያሳያል።”
የሃይተን ማስረጃዎች በሙሉ ችላ ከተባሉ እንዴት “በጣም፣ በጣም ደስ” ሊለው ቻለ? ምክንያቱም የአንግሊካን ቤተ ክህነት አባላት በቀላሉ የሚደሰቱ ረጋ ያሉ ነፍሳት ስለሆኑ ነው። አንድ የዜና ዘጋቢ “ከእነዚህ አሳፋሪ ድርጊቶች ማንኛቸውም ቢሆኑ እንደ ነጎድጓድ ያለ አስፈሪ ተቃውሞ አላጋጠማቸውም፤ ከዚያ ይልቅ ግን አንግሊካኖች የገጠማቸው እንደ ካፊያ ዝናብ የለሰለሰ ተቃውሞ ነበር” ብለዋል።
ግብረ ሰዶም ፈጻሚ የሆኑት ቀሳውስት እንደተደሰቱ ግልጽ ነው። “ሲኖዶሱ በግልጽ ለግብረ ሰዶም ፈጻሚ ወንዶችና ሴቶች በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ቦታ ሰጥቷቸዋል” ብለዋል። ከዚህም በላይ የካንተርቤሪው ሊቀ ጳጳስ ሩንሴ “ሥርዓታማና ኃላፊነቱን የሚወጣ ግብረ ሰዶማዊን ቤተ ክርስቲያን ማውገዝ አይገባትም ሲሉ ተከራክረዋል።” እንዲሁም “በተፈጥሮው ግብረ ሰዶማዊ የሆነ ሰው ምንም የማይጎድለው ሰብዓዊ ፍጡር መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ” ብለዋል።
የካንተርቤሪው ሊቀ ጳጳስ “በተፈጥሮው ግብረ ሰዶማዊ የሆነ” ብለዋል። ግብረ ሰዶማዊ እንዲሆኑ የወሰነባቸው ተፈጥሯቸው ነውን? አንዳንዶች “ግብረ ሰዶማዊ መሆን የሥነ ምግባር ምርጫ ሳይኖረው አስቀድሞ የተወሰነ መሠረታዊ የሥነ ልቦና ባሕርይ ነው” ብለው ይከራከራሉ። በለንደን የሚታተመው ዘታይምስ ጋዜጣ በመንፈስ አነሣሽነት ግብረ ሰዶምን አውግዞ የጻፈውን ሐዋርያው ጳውሎስን “ይህ አጉል ዓይናፋርነት ነው” በማለት ተቃውሞታል
የታወቁት መምህር ሰር ኢማኑኤል ጃኮቦቪትስ “ግብረ ሰዶም ተፈጥሯዊ ሆኖ” መታየቱ አጠያያቂ ነው ካሉ በኋላ “በተፈጥሮ የተወሰነ ነው በሚል መሠረት መከራከሩ ጠቅላላውን የሥነ ምግባር ሥርዓት ወደ ውድቀት የሚመራ አንሸራታች ድጥ ነው . . . በየትኛውም ኅብረተሰብ ውስጥ ቢሆን ተፈጥሯዊ ዝንባሌ ነው ማለቱ ብቻውን በቂ ምክንያት ሆኖ ከተጠያቂነት ነፃ ያደርጋል ብለን መቀበል አንችልም። ተፈጥሮን ልንቆጣጠረው፣ የበላይ እንጂ የእርሱ ሰለባ ልንሆን አይገባም።”
የካንተርቤሪው ሊቀ ጳጳስ የኢየሱስን ቃላት በማቃለልና በመቀየር “በዚህ የኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ መቅደስ ብዙ መኖሪያዎች አሉ፤ ሁሉም ከብርጭቆ የተሰሩ ናቸው” በማለት ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቦታ እንዲኖራቸው እስከ ማድረግ ደርሰዋል። (ከዮሐንስ 14:2 ጋር አወዳድር።) ይህን ሲሉም ‘በማንም ላይ በግብረ ሰዶም ፈጻሚዎቹም ላይ እንኳ ቢሆን ድንጋይ አትወርውሩ ምክንያቱም እነርሱም በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መኖሪያ አላቸውና’ ማለታቸው ነበር።
የቼስተሩ ጳጳስ ሚካኤል ቦውን “የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ለግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች ‘ፍቅርና አዛኝነት መግለጽ፣ በጥንቃቄ መያዝና ስሜታቸውን መረዳት’ ይገባል በማለት አሻሽላ ያወጣችውን መሠረተ ትምህርት የአዲስ ኪዳን ግሪክኛ ጽሑፍ ይደግፈዋል፤” ግብረ ሰዶም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚወገዘው “ከመንገድ እንደወጣ ተደርጎ ብቻ ነው” ብለው ተከራክረዋል። ቅዱሳን ጽሑፎች ግን ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች ከዚህ አቋማቸው ካልተለወጡ መንግሥቲቱን አይወርሱም፤ እንዲያውም “ሞት ይገባቸዋል” ይላሉ።—ሮሜ 1:27, 32፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9–11
ዘ ታይምስ የተባለውን ጋዜጣ እንደገና ለመጥቀስ ያህል ሲኖዶሱ “የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን በምንም ባታምንም ሁሉንም ትቀበላለች የሚለውን በጣም የተለመደ ክስ ወላዋይነቷን ይኸውም የተሻሻለና አዲስ ፋሽን ሆኖ የመጣውን ሁሉ ወንጌል ይመስል የምትውጥ መሆኗን” አረጋግጧል። ሊቨርፑል ዴይሊ ፖስት የተባለው ጋዜጣ “የተድበሰበሰው የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ” በሚል ርዕስ “የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ትክክል ወይም ስህተት ነው ብለው የሚያምኑበትን ግልጽ በሆነ መንገድ መናገር እያቃታቸው የሄደ ይመስላል” ብሏል። ዘ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት “የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የግብረ ሰዶም ድርጊትን ትቃወማለች፤ ግን ያን ያህል አይደለም” በማለት ገልጾታል።
ዴይሊ ፖስት “ሲኖዶሱ ስለ ግብረ ሰዶም ያሳለፈው ውሳኔ ቁጣ አስነሣ” በሚል ርዕስ የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ የፓርላማ አባል የሆኑ የብዙ ሰዎችን አስተያየት አስፍሯል። አንድ የፓርላማ አባል የሲኖዶሱን ውሳኔ “አሳፋሪና የፍርሃት ውሳኔ” ነው ብለውታል። ሌላው አባል ደግሞ “ግብረ ሰዶም በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ካህናት መካከልና በራሷ በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተደላድሎ በሁለት እግሩ ለመቆም ችሏል ብዬ እፈራለሁ” ብለዋል። ሦስተኛው አባል ደግሞ “ይህንን ውሳኔ አሳፋሪና የተድበሰበሰ ነው ብለው ይቀለኛል፤ ይህ ልጆችን አደጋ ላይ የሚጥል ነው። ጓደኛ ማግኘት ያልቻሉ የግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች ፊታቸውን ወደ ልጆች ያዞራሉ፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ልጆች ለዚህ የተጋለጡ ይሆናሉ። . . . ነገሩን ግልጽ ለማድረግ ቤተ ክርስቲያኗ ራሷ በውስጧ እያደገ የመጣውን ክፋት ማስወገድ አልቻለችም።”
የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ግብረ ሰዶም በጣም ትልቅ ኃጢአት ነው ስለምትል በድርጊቱ አለመስማማቷ ግልጽ ነው። በተግባር ሲታይ ግን ቤተ ክርስቲያኗ ወንጀለኛ የሆኑ ቄሶች የፈጸሙትን ድርጊት በመሸፋፈን ከለላ የሚሆን ድርጊት በመፈጸም በዚያው ብልሹ የጾታ ድርጊታቸው እንዲቀጥሉ ሁኔታዎችን ታመቻቻለች። ፓፓ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ “ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ይገኛሉ” ብለው እነሱን ደስ በሚያሰኙ ቃላት ተናግረዋል።
የካቲት 27, 1987 የወጣ ዘ ናሽናል ካቶሊክ ሪፖርተር የተባለ አንድ ነፃ የካቶሊክ ጋዜጣ በአሜሪካ ካቶሊክ ቤተ ክህነት ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች እንደሆኑ ግብረ ሰዶም ፈጻሚ የሆኑ ቄሶች ተናግረዋል ብሏል። ይህ አኀዝ እንደተለወጠ ይነገራል። አንድ የስነ ልቦና ተመራማሪ ከ1,500 ሰዎች ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ መሠረት በማድረግ በአሜሪካ ውስጥ ከሚገኙት 57, 000 የካቶሊክ ቀሳውስት መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች ናቸው ብለው ሲናገሩ በሌላ መልኩ ግን በጣም በቅርብ ጊዜ የወጡ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት “ሌሎች የሕክምና ባለሙያዎች ዛሬ ትክክለኛ ቁጥሩ ወደ 40 በመቶ እንደሚጠጋ ገምተዋል።”
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ኤጲስቆጶሳውያን:- “ክርስቲያኖች በተመሳሳይ ጾታ መካከል በሚደረገው የጾታ ግንኙነት ለመካፈል እምቢ የሚሉበት ጊዜ አልፏል”
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚያክሉት የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስት ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች እንደሆኑ እናምናለን”
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ሕፃናትን በጾታ ለሚያስነውሩ ቀሳውስት” የሚደረግ ሽፋን