ጥላቻዬ ወደ ፍቅር ተለወጠ
ሉትቪክ ቩርም እንደተናገረው
እስከ ዛሬ ድረስ እንደዚያ ያለ እጅግ ቀዝቃዛ የሆነ ሌሊት አጋጥሞኝ አያውቅም። ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች 52 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ደርሶ ነበር። ጊዜው የካቲት 1942 የክረምት አጋማሽ ሲሆን በወቅቱ ጦርነት እየተካሄደ ነበር። ቦታው በሌኒንግራድ አቅራቢያ ይገኝ የነበረው የሩሲያ ጦር ግንባር ነበር። ቫፈን ኤስ ኤስ (ቫፈን ሹቲስሽታፈል) ተብሎ በሚታወቀው ምርጥ የጀርመን የጦር ኃይል ውስጥ በወታደርነት አገለግል ነበር። አንድ አምሳ አለቃና እኔ ከ300 በላይ የሆኑ ጓዶችን እንድንቀብር መመሪያ ተሰጠን። ነገሩ በጣም የሚዘገንን ነበር። አብዛኞቹ በቀበሮ ጉድጓዶቻቸው ውስጥ እንዳሉ በቅዝቃዜው ምክንያት የሞቱ ነበሩ። ሆኖም መሬቱ በቅዝቃዜው የተነሣ በጣም ጠጥሮ ስለ ነበር እነርሱን ለመቅበር አልተቻለም። ከዚህ ይልቅ ክንችር ያሉትን አስክሬኖች ወና ከቀሩት ቤቶች በስተጀርባ እንደ እንጨት ከመርናቸው። እስከ ፀደይ ወራት ድረስ ሳንቀብራቸው ለመቆየት ተገድደን ነበር።
ይህ አሠቃቂ ሥራ ዘግንኖኝ ነበር ብሎ መናገር ሁኔታውን በሚገባ አይገልጸውም። ይህ ሁኔታ በጣም ስለረበሸኝ እያለቀስኩ ሳላስበው “አንተርሻፉረር (አምሳ አለቃ) ይህ ዓላማ ቢስ ግድያ የሚካሄደው ለምን እንደሆነ ልትነግረኝ ትችላለህ? ዓለም በጥላቻ የተሞላው ለምንድን ነው? የምንዋጋው ለምንድን ነው?” ብዬ ጠየቅሁት። አምሳ አለቃው ድምፁን ዝቅ አድርጎ “እኔ እንጃ ሉትቪክ። እውነቴን ነው የምልህ ዓለም በመከራና በጥላቻ የተሞላው ለምን እንደሆነ እኔም ሊገባኝ አልቻለም” አለኝ።
ከሁለት ቀናት በኋላ አንድ ጥይት አንገቴ ላይ መታኝ። በዚህም ምክንያት በድን ሆኜና ሕሊናዬን ስቼ ሞት አፋፍ ላይ ደርሼ ነበር።
ይሁን እንጂ በአእምሮዬ ውስጥ ይፈጠሩ የነበሩት የማያቋርጡ ጥያቄዎች ጥላቻና ተስፋ መቁረጥ እንዴት ወደ ፍቅርና ተስፋ ሊለወጡ እንደሚችሉ ራሴ እንድመለከት አስችለውኛል። ይህ እንዴት እንደሆነ ልግለጽላችሁ።
ከሂትለር ጋር ተገናኘሁ
በ1920 በኦስትሪያ ውስጥ ተወለድኩ። አባቴ የሉተራን እምነት ተከታይ የነበረ ሲሆን እናቴ ደግሞ ካቶሊክ ነበረች። በሉተራን የግል ትምህርት ቤት ውስጥ እማር ነበር። በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ ቄስ ቋሚ ሃይማኖታዊ ትምህርት ይሰጠኝ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝ እንደሆነ አልተማርኩም። ዘወትር እማር የነበረው “አምላክ የላከው ፉረር [መሪ]” እንደሆነ ተደርጎ ይነገርለት ስለ ነበረው አዶልፍ ሂትለርና ስለ ወደፊቱ የመላው ጀርመን ግዛት ነበር። የመማሪያ መጽሐፌ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ ማይን ካምፍ (ትግሌ) የተባለው የሂትለር መጽሐፍ ሆኖ ነበር ማለት ይቻላል። በተጨማሪም ደር ሙቶስ ደስ ትስቫንቲሲግስተን ያርሁንደርትስ (የ20ኛው መቶ ዘመን አፈ ታሪክ) የተባለውን የሮዘንበርግ መጽሐፍ አጥንቻለሁ። ሮዘንበርግ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁዳዊ ሳይሆን ነጣ ያለ ጠጉርና ሰማያዊ ዓይን የነበረው አርያን እንደሆነ ማስረጃ ለማቅረብ ሞክሯል!
አዶልፍ ሂትለር በእርግጥም በአምላክ የተላከ ሰው ነው የሚል እምነት አደረብኝ። በ1933 የሂትለር ወጣቶች ንቅናቄ አባል ለመሆን በመቻሌ ኩራት ተሰማኝ። ከእርሱ ጋር በግል መገናኘት የምችልበት አጋጣሚ በማግኘቴ ምን ያህል እንደተደሰትኩ ልትገምቱ ትችላላችሁ። ሂትለር ባልተለመደ አስተያየት ዓይኖቹን ዓይኔ ላይ ሰክቶ እንዴት እንደተመለከተኝ እስከ ዛሬ ድረስ በደንብ ይታወሰኛል። ይህ ሁኔታ በእኔ ላይ ከፍተኛ ለውጥ በማምጣቱ ምክንያት ወደ ቤት ስመለስ እናቴን እንዲህ አልኳት:- “ከእንግዲህ ወዲህ የአንቺ አይደለሁም። ሕይወቴን ለመሪዬ ለአዶልፍ ሂትለር ሰጥቻለሁ። አንድ ሰው ሊገድለው ሲል ካየሁ እርሱን ለማዳን ሕይወቴን እሠዋለሁ።” እናቴ እያለቀሰች አጥብቃ ያቀፈችኝ ለምን እንደሆነ የገባኝ ከብዙ ዓመታት በኋላ ነበር።
የናዚ ፓርቲ መጀመሪያ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ
በ1934 ብሔራዊ ሶሻሊስቶች በኦስትሪያ መንግሥት ላይ ዓመፁ። በዚህ ግጭት ወቅት የኦስትሪያንና የጀርመንን ውህደት ይቃወሙ የነበሩት ቻንስለር ኤግልበርት ዶልፉስ በናዚዎች ተገደሉ። የዓመፁ መሪዎች ተይዘው ለፍርድ ከቀረቡ በኋላ የሞት ቅጣት ተበየነባቸው። ከዚያ በኋላ የኦስትሪያ መንግሥት ወታደራዊ ሕግ አወጣ፤ እኔም የጀርመን ብሔራዊ ሶሻሊስት ሠራተኞች ፓርቲ የሆነው የናዚ ፓርቲ ሕቡዕ ንቅናቄ ንቁ ተሳታፊ ሆንኩ።
ከዚያም በ1938 ጀርመን ኦስትሪያን በኃይል ያዘች። የናዚ ፓርቲ ሕጋዊ ሆነ። በዚያው ዓመት ከጥቂት ጊዜ በኋላ በኑረምበርግ በሚገኘው በትሴፔሊን ሜዶው አደባባይ በተደረገው የራይክ ፓርቲ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ሂትለር ከጋበዛቸው ታማኝ የፓርቲ አባላት መካከል ነበርኩ። እዚህ ቦታ ሂትለር እየጨመረ የሄደውን ኃይሉን ሲያሳይ ተመልክቻለሁ። አድማጮቹን የሚያፈዙ ጉራ የተሞላባቸው ንግግሮቹ በዓለም ዙሪያ ያሉ አይሁዶችንና በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው የሚጠሩ ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ጨምሮ በመላው የናዚ ፓርቲ ተቃዋሚዎች ላይ ያለውን ጥላቻ የገለጸባቸው ነበሩ። “እነዚህ የታላቋ ጀርመን ጠላቶች፣ እነዚህ የዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር ጫጩቶች ከጀርመን ይደመሰሳሉ” በማለት በጉራ የተናገራቸውን ቃላት በደንብ አስታውሳለሁ። የይሖዋ ምሥክሮችን ፈጽሞ አግኝቻቸው ስለማላውቅ ሂትለር እንደዚህ የጠላቸው እነዚህ አደገኛ ሰዎች እነማን ይሆኑ ብዬ አሰብኩ።
በቡከንቫልድ የማጎሪያ ካምፕ የነበረኝ ሥራ
በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ ወዲያው በፈቃደኝነት ቫፈን ኤስ ኤስ የተባለው ምርጥ የጀርመን የጦር ኃይል አባል ሆንኩ። መሪያችን በአምላክ የተላከ እስከ ሆነ ድረስ በዚህ ጦርነት የምከፍላቸው መሥዋዕቶች በሙሉ ተገቢ ናቸው ብዬ አምን ነበር። ሆኖም በ1940 የጦር ጓዳችን በሉክሰምበርግና በቤልጅየም አቋርጦ ወደ ፈረንሳይ በተንቀሳቀሰበት ወቅት የአንድ መልከ መልካም ፈረንሳዊ ወጣት ወታደር አስክሬን ወድቆ ለመጀመሪያ ጊዜ ስመለከት ተረበሽኩ። አምላክ ከጎናችን በመሰለፉ ምክንያት እኛ ጀርመናውያን እንደምናሸንፍ የተረጋገጠ ሆኖ ሳለ ፈረንሳውያን ወጣቶች ለምን ሕይወታቸውን በጦርነት እንደሚሠዉ ሊገባኝ አልቻለም።
ፈረንሳይ ውስጥ ቆሰልኩና ወደ ጀርመን ተመልሼ ሆስፒታል ገባሁ። ከዳንኩ በኋላ በቫይማር አቅራቢያ ወደሚገኘው የቡከንቫልድ የእስረኞች ማጎሪያ ካምፕ ተዛውሬ በካምፑ የውጪ ክፍል መሥራት ጀመርኩ። ከቶተንኮፕፈርቤንደ (የሞት አለቆች) ከሆኑት የኤስ ኤስ የካምፕ ጠባቂዎች ወይም ከእስረኞቹ ጋር እንዳንቀላቀል ከአለቆቻችን ጥብቅ መመሪያ ተሰጥቶን ነበር። በተለይም ትልቅ የመግቢያ በር ባለው ረጅም ግንብ ወደ ታጠረው የእስረኞች መኖሪያ ክልል እንዳንገባ ተከልክለን ነበር። እዚህ ቦታ መግባት የሚችሉት ልዩ የይለፍ ወረቀት ያላቸው የኤስ ኤስ ጠባቂዎች ብቻ ነበሩ።
በየቀኑ በካምፑ ውስጥ አንድ የኤስ ኤስ ጠባቂና ሌላ ካፖ ተብሎ የሚጠራ ኃላፊነት የተሰጠው እስረኛ እየመሯቸው እስረኞቹ ወደ ሥራ ቦታቸው በሰልፍ ሲሄዱ እንመለከት ነበር። በእስር ቤት ልብሳቸው ላይ የኮከብ ምልክት ያለባቸው አይሁዳውያን፣ ቀይ ትራያንግል ምልክት ያለባቸው የፖለቲካ እስረኞች፣ ጥቁር ምልክት ያለባቸው ወንጀለኞችና ወይን ጠጅ ቀለም ያለው ትራያንግል ምልክት ያለባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ።
በምሥክሮቹ ፊት ላይ ይታይ የነበረው ብሩህ ሁኔታ ስሜቴን ማረከው። መጥፎ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ይኖሩ እንደነበር አውቃለሁ፤ ሆኖም ያለቀውን ሰውነታቸውን የሚሸፍን ግርማ ሞገስ ነበራቸው። ስለ እነርሱ ምንም የማውቀው ነገር ስላልነበር የበላይ አዛዦቻችንን የይሖዋ ምሥክሮች ወደ እስረኞች ማጎሪያ ካምፕ የገቡበትን ምክንያት ጠየቅኋቸው። የሰጡኝ መልስ ከኮሚኒስቶች ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላቸው የጁዊሽ አሜሪካን ኑፋቄ ናቸው የሚል ነበር። ይሁን እንጂ እንከን የሌለው ጠባያቸው፣ ለመሠረታዊ ሥርዓቶች ያላቸው የጸና አቋምና የሥነ ምግባር ንጽሕናቸው ስለ እነርሱ የማወቅ ጉጉት አሳደረብኝ።
“እንደ መሲሕ” አድርጌ እመለከተው የነበረው ሰው ፍጻሜ
በ1945 እተማመንበት የነበረው ሥርዓት ድምጥማጡ ጠፋ። ቀሳውስት አምላክ የላከው ፉረር እንደሆነ አድርገው ያወደሱት “አምላኬ” አዶልፍ ሂትለር ሐሰተኛ መሲሕ መሆኑ ተረጋገጠ። አልሞት የነበረው ታውዘንድጃሪጅ ራይክ (የሺህ ዓመት አገዛዝ) ከ12 ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ፈጽሞ ተደመሰሰ። በተጨማሪም በሚልዮን በሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ላይ የደረሰው እልቂት ከሚያስከትልበት ኃላፊነት ለመሸሽ ራሱን የገደለ ፈሪ ነበር። ከዚያ በኋላ የመጀመሪያዎቹ የአቶሚክ ቦምቦች በጃፓን ላይ እንደተጣሉ ስሰማ ልቀውስ ምንም ያህል አልቀረኝም ነበር።
በሕይወቴ ውስጥ የተፈጸሙ አስደናቂ ለውጦች
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ አገሪቷን የተቆጣጠሩት የዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎች ክፍል የሆነው የአሜሪካ የጦር ሠራዊት ሲ አይ ሲ (ካውንተርኢንተለጀንስ ኮርፕስ) ስለ እኔ ጥቆማ ደረሰው። ናዚና የቫፈን ኤስ ኤስ አባል በመሆኔ ምክንያት ታሰርኩ። አፍቃሪ እጮኛዬ የነበረችው ትሩዲ ስለ ጉዳዩ ለአንድ ዶክተር ነገረችውና ዶክተሩ በአከርካሪዬ ላይ የደረሰብኝ ጉዳት ባስከተለብኝ የጤንነት ችግር ምክንያት ከእስር ቤት መውጣት እንዳለብኝ ለሲ አይ ሲ ኃላፊዎች ገለጸላቸው። ከዚህ በኋላ በጦር ወንጀለኛነት ከቀረቡብኝ ክሶች ሁሉ ነፃ እስክሆን ድረስ አንድ ጠባቂ ታዝዞልኝ የቁም እስረኛ እንድሆን ተደረገ።
ጦርነቱ ባስከተለብኝ የአካል ጉዳት ምክንያት ለጤና ምርመራ በኦስትሪያ አልፕስ ወደሚገኘው የማገገሚያ ሆስፒታል ተላክሁ። ከዚያም በፀደይ ወራት አንድ ቀን ጠዋት ልብ የሚሰርቀውን የተፈጥሮ ውበት እየተመለከትኩ፣ ፀሐይ እየሞቅኩና የወፎችን ጣፋጭ ዝማሬ እያዳመጥኩ “አምላክ በእርግጥ ካለህ የሚያስጨንቁኝን በርካታ ጥያቄዎች መመለስ ይኖርብሃል” በማለት አጭር ጸሎት በልቤ አቀረብኩ።
ወደ ቤቴ ከተመለስኩ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ቤቴ መጣች። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ሰጠችኝ። ዘወትር እሑድ ጠዋት እየመጣች ብታነጋግረኝም በዚያን ጊዜ የምትነግረኝን በቁም ነገር አልተመለከትኩትም፤ ያበረከተችልኝን ጽሑፍም አላነበብኩም። ሆኖም አንድ ቀን ከሥራ ወደ ቤት ስመለስ አእምሮዬ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተረብሾ ነበር። ባለቤቴ አእምሮዬን ዘና ለማድረግ ምሥክሮቹ የሰጡኝን ሰላም— ዘላቂ ሊሆን ይችላልን? የተባለውን የይሖዋ ምሥክሮች ቡክሌት እንዳነብ ሐሳብ አቀረበችልኝ።
ቡክሌቱን ማንበብ ከጀመርኩ በኋላ እስክጨርሰው ድረስ ንባቤን ማቋረጥ አልቻልኩም። ባለቤቴን እንዲህ አልኳት:- “ይህ ቡክሌት የታተመው በ1942 ነው። በዚያን ወቅት አንድ ሰው ሂትለርና ሞሶሎኒ በጦርነቱ ይሸነፋሉ፤ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር በተባበሩት መንግሥታት መልክ እንደገና ይቋቋማል በማለት በአደባባይ ቢናገር ኖሮ ሰዎች ይህ ሰው አእምሮው ተቃውሷል ብለው ያስቡ ነበር። ሆኖም ይህ ቡክሌት ይፈጸማሉ ብሎ የተናገራቸው ነገሮች በትክክል ተፈጽመዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይኖር ይሆን? እነዚህን ጥቅሶች አውጥቼ ሐሳቡን ባመሳክር ጥሩ ነበር።”
ባለቤቴ ከጣሪያው ሥር ወዳለው ደርብ ወጣችና ሉተር የተረጎመው አንድ የቆየ መጽሐፍ ቅዱስ አገኘች። በቡክሌቱ ውስጥ የተጠቀሱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እያወጣሁ መረመርኩ። ብዙም ሳይቆይ ቀደም ሲል ፈጽሞ ሰምቻቸው የማላውቃቸውን ብዙ ነገሮች ተማርኩ። መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መሲሐዊ መንግሥት የሚተዳደር አዲስ ዓለም እዚህ ምድር ላይ እንደሚቋቋም የሚሰጠውን ተስፋ ማወቅ ቻልኩ። አስደሳችና አስተማማኝ ጊዜ እንደሚመጣ የሚገልጸው ይህ እውነተኛ ተስፋ ብዙውን ጊዜ በልጅነቴ ወቅት እደግመው በነበረው “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” በሚለው በኢየሱስ የናሙና ጸሎት ላይ ተገልጿል። ከዚህ በላይ በጣም ያስገረመኝ ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው የሰማይና የምድር ፈጣሪ ይሖዋ የተባለ የግል ስም እንዳለው ማወቄ ነበር።— ማቴዎስ 6:9, 10፤ መዝሙር 83:18 አዓት
ብዙም ሳይቆይ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባ ላይ በተገኘሁበት ወቅት ሴት ልጃቸውና አማቻቸው በእምነታቸው ምክንያት በጀርመን የእስረኞች ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ከተገደሉባቸው አንዲት አረጋዊት ሴት ጋር ተገናኘሁ። በጣም አፈርኩ። ከዚህ በፊት ከናዚዎች ጋር እሠራ ስለ ነበር እርሳቸውና ቤተሰባቸው የደረሰባቸውን ነገር እንደማውቅና ለዚህ ሁኔታ በኃላፊነት ከሚጠየቁ ሰዎች ጋር ከነበረኝ ግንኙነት አንፃር ሲታይ በጥላቻ ፊቴ ላይ ሊተፉብኝ ይችሉ እንደነበር ገለጽኩላቸው።
ጥላቻ ከማሳየት ይልቅ ፊታቸው በእንባ ሲታጠብ ስመለከት ገረመኝ። ሞቅ ባለ ስሜት አቀፉኝና “ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው ይሖዋ የተቃዋሚ ቡድኖች አባላት የሆኑ ግለሰቦች ወደ ቅዱስ ድርጅቱ እንዲመጡ መፍቀዱ ምንኛ የሚያስደስት ነው!” አሉ።
እነዚህ ሰዎች በሄድኩበት ሁሉ እመለከተው የነበረውን ጥላቻ ሳይሆን ራስ ወዳድነት የሌለበት አምላካዊ ፍቅር ማለትም እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር ሲያሳዩ ተመልክቻለሁ። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” በማለት የተናገረውን እንዳነበብኩ አስታወስኩ። (ዮሐንስ 13:35) እፈልገው የነበረውም ይህንኑ ነው። አሁን ደግሞ ማልቀሱ የእኔ ተራ ሆነ። እኔም ታላቁን አምላክ ይሖዋን በማድነቅ እንደ ሕፃን ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ።
ገና ብዙ የምማረው ነገር ነበር
ከጊዜ በኋላ ሕይወቴን ለይሖዋ አምላክ ወሰንኩና በ1948 ተጠመቅሁ። ሆኖም ገና ብዙ ነገር መማር እንደሚያስፈልገኝ ተገንዝቤ ነበር። ለምሳሌ ያህል የናዚ ፍልስፍና በአስተሳሰቤ ላይ ኃይለኛ ተጽዕኖ አሳድሮብኝ ስለ ነበር የይሖዋ ድርጅት አንዳንድ ጊዜ መጥፎ ስም ያተረፈውን ኤስ ኤስን የሚነቅፉ ጽሑፎች ለምን እንደምታወጣ አይገባኝም ነበር። በግለሰብ ደረጃ እኛ ጥፋተኞች አይደለንም እያልኩ እከራከር ነበር። እኛ ተራ ወታደሮች ነበርን፤ በተጨማሪም አብዛኞቻችን በእስረኞች ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የሚፈጸመውን ነገር ፈጽሞ አናውቅም ነበር።
ከዚያ አንድ ቀን ችግሬን የተረዳና ራሱ ለብዙ ዓመታት በእስረኞች ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ መከራ የደረሰበት አንድ የተወደደ ወንድም አቀፍ አድርጎ እንዲህ አለኝ:- “ወንድም ሉትቪክ በጥሞና አዳምጠኝ። ይህን ነጥብ ለመረዳት ከተቸገርክና በጣም የሚረብሽህ ከሆነ ከአእምሮህ አውጣው። ከዚያም ችግርህን ለይሖዋ በጸሎት ግለጽለት። እመነኝ፣ እንደዚህ ካደረግህ ይሖዋ አንድ ቀን ይህንና ሌሎች ግራ የሚያጋቡህን ጉዳዮች እንድታስተውል ይረዳሃል።” የሰጠኝን ጥሩ ምክር ተቀበልኩ። ከበርካታ ዓመታት በኋላ የተፈጸመው ሁኔታ ልክ እሱ እንዳለው ነበር። ኤስ ኤስም ሆነ መላው የብሔራዊ ሶሻሊዝም ሥርዓት የጠቅላላው የሰይጣን ዲያብሎስ ሥርዓት አንዱ ክፍል እንደነበረ አስተዋልኩ።— 2 ቆሮንቶስ 4:4
በኑረምበርግ ወደሚገኘው የዜፔሊን ሜዶው አደባባይ መመለስ
በ1955 ወደ ኑረምበርግ ተመልሼ ትሪዮምፊረንድስ ኮዬኒግራይክ (ድል አድራጊው መንግሥት) በተባለው የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ መገኘቴ በሕይወቴ ውስጥ ምን ዓይነት ጉልህ ስፍራ እንደነበረው ልትገምቱ ትችላላችሁ! አዎን፣ ይህ ትልቅ ስብሰባ የተካሄደው ሂትለር የይሖዋ ምሥክሮችን ከጀርመን እንደሚያጠፋቸው በጉራ በዛተበት ቦታ ነበር። እዚህ ቦታ ላይ ከ107,000 በላይ የሆኑ ከመላው ዓለም የመጡ የይሖዋ ምሥክሮችና ወዳጆቻቸው አንድ ሳምንት ሙሉ ለአምልኮ ተሰብስበዋል። ግፊያ አልነበረም፤ በቁጣ የሚደነፉ ሰዎች አልነበሩም። በእውነትም በሰላም ተስማምቶ የሚኖር ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ ነው።
የቫፈን ኤስ ኤስ አባላት የነበሩና በአሁኑ ጊዜ ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች የሆኑ አንዳንድ የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቼን በዚህ ትልቅ ስብሰባ ላይ ሳገኝ የተሰማኝን ስሜት መግለጽ ያስቸግረኛል። በእርግጥም በዚህ መልክ እንደገና አንድ ላይ መገናኘታችን በጣም የሚያስደስት ነበር!
የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ መጠባበቅ
ራሴን ወስኜ ከተጠመቅሁ ጀምሮ በኦስትሪያ ውስጥ ቀደም ሲል የናዚ ፓርቲ አባላት የነበሩ ብዙ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ችያለሁ። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹም ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። በ1956 ከኦስትሪያ ወጥቼ በአሁኑ ወቅት በአውስትራሊያ ውስጥ እየኖርኩ ነው። አውስትራሊያ ውስጥ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመሥራት መብት አግኝቻለሁ። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዕድሜዬ እየገፋ መሄዱና ያጋጠመኝ የጤና ችግር በአገልግሎቴ የማደርገውን እንቅስቃሴ ውስን አድርጎታል።
አቋማቸውን ባለማላላት ከክፉው የናዚ ሥርዓት ጋር ለመስማማት ፈቃደኞች ባለመሆናቸውና ንጹሕ አቋማቸውን በመጠበቃቸው ምክንያት በእስረኞች ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የተገደሉ አንዳንድ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ከሞት ሲነሡ መቀበል የምችልበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ።
በአሁኑ ጊዜ በጣም ጎጂ የሆነው የጥላቻ ባሕርይ ቃል በቃል ወደ ፍቅርና ተስፋ ሲለወጥ መመልከት ችያለሁ። ወደፊት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ሰብዓዊ ፍጽምና በማግኘት ከበሽታና ከሞት ነፃ ሆኜ የምኖርበት ጊዜ እንደሚመጣ የጸና እምነት አለኝ። ይህ እኔ ብቻ ሳልሆን ይሖዋ ለሾመውና በአሁኑ ጊዜ በመግዛት ላይ ለሚገኘው ለንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሳቸውን በትሕትና የሚያስገዙ ሰዎች ሁሉ የሚያገኙት ተስፋ ነው። በእኔ በኩል ሐዋርያው ጳውሎስ “በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ሞላ ተስፋው አያሳፍርም” በማለት የተናገራቸው ቃላት በእምነት ማስተጋባት እችላለሁ።— ሮሜ 5:5 የ1980 ትርጉም
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኤስ ኤስ የደንብ ልብሴን ለብሼ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቀደም ሲል ሂትለር የናዚ ፓርቲ ስብሰባዎችን ያደርግበት በነበረው በኑረምበርግ በ1955 የተካሄደው “ድል አድራጊው መንግሥት” የተባለው የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ
[ምንጭ]
U.S. National Archives photo
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአውስትራሊያ ቦርሳዬን ይዤ ወደ አገልግሎት ስወጣ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ምንጭ]
UPI/Bettmann