ከጥገኛ ተውሳኮች ራሳችሁን ጠብቁ!
ሆንዱራስ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
ከእንቅልፍ ስትነቁ የማቅለሽለሽ ስሜት ይሰማችኋል። ቶሎ ይደክማችኋል። ሆዳችሁ በትንሹ አበጥ ብሏል። የእርግዝና ምልክት ይሆን? ምናልባት ይሆናል። ይሁንና በሞቃታማ ወይም ከፊል ሞቃታማ በሆነ የዓለም ክፍል የምትኖሩ ከሆነ ችግሩ አንድ ዓይነት የአንጀት ጥገኛ ተውሳክ ሊሆን ይችላል። የአንጀት ጥገኛ ተውሳክ የሚባሉት ምንድን ናቸው? እነዚህን የማይፈለጉ እንግዶች እያስተናገዳችሁ መሆን አለመሆናችሁን ማወቅ የምትችሉትስ እንዴት ነው?
በቀላል አነጋገር ጥገኛ ተውሳክ ማለት ሕያው በሆነ አካል ላይ ወይም ውስጥ በመሆን አንዳንድ ጥቅሞችን እያገኘ የሚኖር ዘአካል ነው። ሁለት ዓይነት የአንጀት ጥገኛ ተውሳኮች ያሉ ሲሆን እነሱም አሚባን የሚያካትቱት አሀዱ ህዋሳት (protozoans) እና ልዩ ልዩ ቅርፅ ያላቸው የሆድ ትሎች (helminths) ናቸው። በተሸካሚው ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት መጠን በዓይነታቸውና በብዛታቸው እንዲሁም በተሸካሚው እድሜና ጤንነት ላይ የተመካ ነው።
ለምሳሌ ያህል ሴቷ ዱቡልቡል ትል (roundworm) በቀን ወደ 200,000 የሚጠጉ እንቁላሎች ልትጥል ትችላለች። ይሁንና እንቁላሎቹ እንዲዳብሩ በአፈር ውስጥ መቀፍቀፍ አለባቸው። አንድ ሰው የሚኖረው የዱቡልቡል ትሎች መጠን የሚወሰነው ወደ ሰውነቱ ባስገባቸው ሕያው እንቁላሎች ወይም እጮች ብዛት ነው። ብዙ ሰዎች አይገንዘቡት እንጂ ጥቂት ዱቡልቡል ትሎች በውስጣቸው ይኖራሉ። ሆኖም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዱቡልቡል ትሎች ከባድ የሆነ የአንጀት እግደት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
የአንጀት ጥገኛ ተውሳኮች መኖራቸውን የሚያሳውቁ አንዳንድ የተለመዱ ምልክቶች የሆድ ሕመም፣ ማቅለሽለሽ፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ የሆድ እብጠት፣ ድካምና ሥር የሰደደ የምግብ አለመንሸራሸር ችግር፣ ተቅማጥ ወይም የሆድ ድርቀት ናቸው። በተጨማሪም የክብደት መቀነስ፣ በእንቅልፍ ልብ መወራጨት፣ ማሳከክ፣ ማቃሰትና ትኩሳት ጥገኛ ተውሳኮች መኖራቸውን የሚያመለክቱ ሊሆኑ ይችላሉ። እርግጥ እነዚህ ምልክቶች የበርካታ በሽታዎች ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም የተለያዩ የሰገራ ምርመራዎች በማድረግ ጥገኛ ተውሳኮች መኖር አለመኖራቸው ሊታወቅ ይችላል።
ትክክለኛ ምርመራ ማድረግ ተገቢ ነው። ለምሳሌ ያህል ድቡልቡል ትሎችና ሌላ ዓይነት ጥገኛ ተውሳኮች ከተገኙ በመጀመሪያ ማከም የሚገባው ድቡልቡል ትሎቹን ነው። ለምን? ምክንያቱም አንዳንድ መድኃኒቶች ትሎቹን ከመግደል ይልቅ ሊያስቆጧቸው ስለሚችሉ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች በመፍለስ ከባድ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ
መድኃኒት በመውሰድ ጥገኛ ተውሳኮችን ማስወገድ የሚቻል ቢሆንም አስቀድሞ በእነሱ ላለመለከፍ ጥረት ማድረጉ የተሻለ ነው። እንግዲያው ራስህን ከጥገኛ ተውሳኮች መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?
ከሁሉ የተሻለው መከላከያ ንጽሕና ነው። ዓይነ ምድር በምንም ዓይነት ለአየር በተጋለጠ ሁኔታ መተው የለበትም። መጸዳጃ ቤቶች ከውኃ ምንጮች ጨርሶ የራቁ መሆን አለባቸው። የሰው ሰገራ ለማዳበሪያነት ማገልገል የለበትም። የግል ንጽሕናን መጠበቅም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ልጆች ቆሻሻ ነገር እንዳይበሉ መከላከል ያስፈልጋል። አንድ ልጅ ጥገኛ ተውሳክ እንዳለበት ከታወቀ የቤተሰቡ አባላት በሙሉ የጤና ምርመራ ቢያደርጉ የተሻለ ነው።
ምግብ ስትገዙና ስታዘጋጁም ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ። ንጽሕናው የተጠበቀ መሆኑ በሚነገርለት ቦታ የተመረቱ ምርቶችን ለመግዛት ሞክሩ። የምንበላው ሥጋ በደንብ መብሰል አለበት። ጥሬ ሥጋ በፍጹም አትብሉ። ሳይበስሉ የሚበሉ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች አስቀድመው በደንብ መታጠብ አለባቸው። ሆኖም ያጠባችሁበት ውኃ ሊበከል ስለሚችል በድጋሚ እንዳትጠቀሙበት ተጠንቀቁ።
ለመጠጥ የሚሆን ውኃ እስኪፍለቀለቅ ድረስ መፍላት አለበት። ውኃው ከቀዘቀዘ በኋላ የወጣውን ኦክሲጅን ለመተካት ሲባል ውኃውን ማናፈስ ይቻላል። በብዙ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ የውኃ ማጣሪያዎች ሁሉንም ጥገኛ ተውሳኮች የማስወገድ ብቃት የላቸውም። ለገበያ የሚቀርበው በጠርሙስ የታሸገ ውኃ የሚኖረው ጥራት የሚመረትበት ፋብሪካ በሚከተለው የንጽሕና ደረጃ የተመካ ነው።
በጉዞ ወቅት ወይም ከቤታችን ውጭ በምንመገብበት ጊዜ ተጨማሪ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። በጠርሙስና በካርቶን የታሸጉ መጠጦች በረዶ ሳይጨመርባቸው ከተወሰዱ አብዛኛውን ጊዜ ለጤና አስጊ አይደሉም። አንዳንድ ጥገኛ ተውሳኮች ከፍተኛ ቅዝቃዜን ለመቋቋም ይችላሉ፤ የበረዶው ንጽሕና የተመካው በተሠራበት ውኃ ጥራት መጠን ነው። መንገድ ላይ ከሚሸጡ ሰዎች ምግብ ገዝታችሁ ስትበሉ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋችሁ ይሆናል። አናናስ ወይም ሐብሐብ ተቆርጦ ስታዩ ለመብላት ትጓጉ ይሆናል፤ አብዛኛውን ጊዜ ግን ወዲያው ተቆርጦ የቀረበ እንዲመስል ሲባል ውኃ ይርከፈከፍበታል፤ የሚርከፈከፍበት ውኃ ደግሞ የተበከለ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ጥንቃቄ አድርጉ እንጂ በጉዟችሁ እስከማትደሰቱ ድረስ በፍርሃት አትዋጡ። ተገቢ የሆነ ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ ራሳችሁን ከጥገኛ ተውሳኮች ለመጠበቅ ብዙ ለማድረግ ትችላላችሁ።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሁሉ የተሻለው መከላከያ ንጽሕና ነው
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የበረዶ ንጽሕና የተመካው በተሠራበት ውኃ ጥራት መጠን ነው
[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ሁለቱ የጥገኛ ተውሳክ ዓይነቶች አሚባዎችና ትሎች ናቸው
[ምንጭ]
DPDx, the CDC Parasitology Website