ሕልም ሆኖ የቀረው ወረቀት አልባ ቢሮ
የዚህ ጽሑፍ የመጨረሻው ረቂቅ ተራ በሆነ ወረቀት ሲታተም 11 ገጽ ሆኗል።a ጽሑፉ በሚዘጋጅበት ወቅት ወደ 20 ለሚጠጉ ጊዜያት በተደጋጋሚ ታትሟል። በመጨረሻ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ 80 የትርጉም ቡድኖች የተላከ ሲሆን እያንዳንዱ ቡድን ደግሞ ስድስት የሚሆኑ የትርጉም ረቂቆችን ያትማል። በመሆኑም በአጠቃላይ ይህ ርዕሰ ትምህርት ማተሚያ ቤት ከመድረሱ በፊት ከ5,000 በላይ የሚሆኑ ወረቀቶችን ጨርሷል!
እነዚህ እውነታዎች የኮምፒዩተር ዘመን ሲጠባ አንዳንዶች “ወረቀት አልባ ቢሮ” መምጣቱ አይቀሬ ነው በማለት ከተነበዩት ትንቢት ጋር ፈጽሞ አይጣጣሙም። ተስፈኛው አልቪን ቶፍለር ዘ ሰርድ ዌቭ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ‘ማንኛውንም ነገር በወረቀት አትሞ ማውጣት ኋላ ቀር የሆነ አሠራርና ኮምፒዩተሮች የተሠሩበትን ዓላማ የሚጻረር ነው’ እስከ ማለት ደርሰው ነበር። ደስ የሚለው ነገር ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ማሺንስ ኮርፖሬሽን የመጀመሪያውን የግል ኮምፒዩተር በ1981 ሲያስተዋውቅ የማተሚያ መሣሪያ አብሮ ከማቅረብ ተቆጥቦ ነበር። አንዳንዶች፣ ተጠቃሚዎቹ መረጃውን እዚያው ኮምፒዩተሩ ላይ ማንበብ እንደሚያስደስታቸው አድርገው አስበው ይሆናል። በዚያም ሆነ በዚህ አንዳንዶች “ወረቀት አልባ ገነት” እንደሚመጣና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወረቀት በቤተ መዘክሮች ውስጥ የሚቀመጥ የተረሳ ነገር እንደሚሆን ገምተው ነበር።
ተስፋውና እውነታው
ይሁንና እውነታው እንደሚያሳየው ወረቀት አልባ ቢሮ ያስገኛል ተብሎ የታሰበው መሣሪያ ራሱ በወረቀት ቁልል ውስጥ ቀብሮናል። እንዲያውም አንዳንዶች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አጠቃላዩ የወረቀት ፍጆታ በእጅጉ መጨመሩን ይናገራሉ። የኢንተርናሽናል ዳታ ኮርፖሬሽን ባልደረባ የሆኑት ተንታኙ ስኮት ማክክሪዲ “ቢሮዎቻችንን በኤሌክትሮኒክስ እቃዎች መተካታችን የወረቀት ፍጆታችን እያደገ ሄዶ በዓመት ከ25 በመቶ በላይ እንዲጨምር አድርጓል” ብለዋል። የግል ኮምፒዩተሮች፣ ማተሚያዎች፣ የፋክስ መሣሪያዎች፣ ኢ-ሜይል፣ የፎቶ ኮፒ መሣሪያዎችና ኢንተርኔት ሰዎች በየቀኑ ሊመለከቱትና ሊያትሙት የሚችሉትን የመረጃ ብዛት አሳድገውታል። ካፕ ቬንቸርስ በተባለው ድርጅት አባባል መሠረት በ1998 በዓለም ዙሪያ 218 ሚልዮን ማተሚያዎች፣ 69 ሚልዮን የፋክስ መሣሪያዎች፣ 22 ሚልዮን ግብረ ብዙ መሣሪያዎች (ማተሚያ፣ ስካነርና ኮፒየር በአንድ ላይ ያላቸው)፣ 16 ሚልዮን ስካነሮችና 12 ሚልዮን የፎቶ ኮፒ መሣሪያዎች ነበሩ።
ቶፍለር በ1990 ባሳተሙት ፓወርሺፍት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ዩናይትድ ስቴትስ በአንድ ዓመት ውስጥ 1.3 ትሪልዮን ሰነዶችን ማተሟን ተናግረዋል፤ ይህ ደግሞ ግራንድ ኬንየን በመባል የሚታወቀውን ከፍተኛ ጥልቀትና ስፋት ያለውን ገደላማ ሸለቆ 107 ጊዜ ሙሉ በሙሉ ለመለጠፍ የሚያስችል ነበር! የተለያዩ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ደግሞ ይህ ቁጥር በመጨመር ላይ ነው። ፎርብዝ ኤ ኤስ ኤ ፒ በተባለው መጽሔት አባባል መሠረት በ1995 ዩናይትድ ስቴትስ በዓመት ወደ አራት ትሪልዮን የሚጠጉ ሰነዶችን ታትም የነበረ ሲሆን ይህም በየቀኑ 270 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የፋይል ካቢኔት ይሞላ እንደነበር ገልጿል። አንዳንዶች በ2000 ዓመትም እንኳ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰዎች መካከል የሚኖረው የመረጃ ልውውጥ 95 በመቶ በወረቀት ላይ የተመሠረተ እንደሚሆን ይገምታሉ።
ወረቀት ጥቅም ላይ መዋሉ የሚቀጥልበት ምክንያት
የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ወረቀትን ይተካሉ የሚለው ትንበያ እውን ሊሆን ያልቻለው ለምንድን ነው? ዓለም አቀፉ የወረቀት ድርጅት እንዲህ የሚል ግምታዊ አስተያየት ሰንዝሯል:- “ሰዎች የሚፈልጉት በቅርብ ሊያገኙ የሚችሉት መረጃ ብቻ አይደለም። በእጃቸው ሊይዙት የሚችሉት መረጃ ማግኘት ይፈልጋሉ። በእጃቸው ሊነኩት፣ መሀል ላይ ወይም ጫፉን ሊያጥፉት፣ በፋክስ ሊልኩት፣ ፎቶ ኮፒ ሊያነሱት፣ ሊጠቅሱት እንዲሁም በኅዳጉ ላይ ሊጽፉበት ወይም በማቀዝቀዣዎቻቸው ላይ በኩራት ሊለጥፉት የሚችሉት ነገር ማግኘት ይፈልጋሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ወዲያውኑ፣ አለአንዳች እንከን ደስ በሚሉ ቀለማት ሊያትሙት ይፈልጋሉ።”
ወረቀት የራሱ የሆኑ ጥቅሞች እንዳሉት መገንዘብ ይገባል። ለአያያዝ የሚመችና ርካሽ ሲሆን ለረዥም ጊዜ ሊቆይ የሚችል፣ በታሪካዊ ቅርስነት ለማስቀመጥ የማያስቸግርና ተመልሶ እንደ አዲስ ሊመረት የሚችል ነገር ነው። በተጨማሪም እየገለጡ ማንበብ ቀላል ሲሆን የትኛው ገጽ ላይ እንዳለህና ስንት ገጽ እንደሚቀርህ ለመመልከት ትችላለህ። የቢሮ እቃዎችን የሚሸጥ ድርጅት ተወካይ የሆኑት ዳን ኮክስ “ሰዎች ከወረቀት ጋር ፍቅር ይዟቸዋል። በእጆቻቸው ሲይዙት ደስ ይላቸዋል” በማለት ተናግረዋል። “ሰዎች ወረቀት አልባውን ቢሮ ለማግኘት ሲጣጣሩ ተመልክተናል” ይላሉ አሪዞና በሚገኘው የአብያተ መጻሕፍት፣ ቅርሶችና ሕዝባዊ መዝገቦች ዲፓርትመንት ውስጥ የመዝገቦች መርማሪ የሆኑት ጄሪ ማልሮይ። “ይሁንና የምናያቸው በሺህ የሚቆጠሩ ኮምፒዩተሮች በሙሉ አንድ የጋራ ባሕርይ አላቸው:- ሁሉም ቢያንስ ከአንድ የማተሚያ መሣሪያ ጋር የተያያዙ ናቸው።”
ከዚህም በላይ ደግሞ ልማድ በቀላሉ አይለቅም። በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ በወረቀት ማንበብን የተማሩ ናቸው። አይጦን (mouse) አንድ ጊዜ ነካ በማድረግ ብቻ አንድን ሰነድ ወይም የኢ-ሜይል መልእክት ለማተም የሚቻል ከመሆኑም በላይ ባለቤቱ በፈለገበት ጊዜና ቦታ ሊያነብበው ይችላል። በወረቀት ላይ የታተመን ነገር አልጋ ላይ፣ ሰውነት መታጠቢያ ገንዳ ውስጥም ሆነ በባህር ዳርቻ እየተዝናኑ ማንበብ ይቻላል! አብዛኞቹን ኮምፒዩተሮች በእንዲህ ዓይነት ቦታዎች መጠቀሙ ግን አስቸጋሪ ነው።
ሌላው ምክንያት ደግሞ ከጥቂት ጊዜ በፊት በሥራው የተካኑ አታሚዎች ብቻ ያወጧቸው የነበሩ ሰነዶችን በኮምፒዩተር አማካኝነት ማንኛውም ሰው ለማተም መቻሉ ነው። ሙሉ ቀለም ያላቸው ቅጂዎች፣ ረቂቆች፣ ሪፖርቶች፣ በሥዕል የተደገፉ ጽሑፎች፣ ቻርቶች፣ ሰንጠረዦች፣ የግብዣ ካርዶችና ፖስት ካርዶች ያለ ብዙ ድካም በቀላሉ ማተም ይቻላል። ይህ ደግሞ ሙከራ ማድረግን ይጋብዛል። ስለዚህ አንድ የኮምፒዩተር ተጠቃሚ አንድ ሰነድ ካተመ በኋላ ምናልባት የፊደላቱን ቅርጽና አቀማመጥ ለውጦ እንደገና ለማተም ይፈልግ ይሆናል። አሁንም ተጨማሪ ማስተካከያዎች ያደርግ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ መገመት እንደምትችለው የኅትመቱ ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋል!
የኢንተርኔት አገልግሎትም ቢሆን ሰዎች ሥፍር ቁጥር የሌለው መረጃ እንዲደርሳቸው በማድረጉ ለዚህ ሁኔታ አስተዋጽኦ አድርጓል።b የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ደግሞ ፈልገው ያገኟቸውን ነገሮች አብዛኛውን ጊዜ በወረቀት ስለሚያትሙ ከፍተኛ የሆነ የወረቀት ፍጆታ ማስከተሉ የማይቀር ነው።
በቸልታ የማይታለፈው ሐቅ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመጉረፍ ላይ ያለውን የኮምፒዩተር ሶፍትዌርና ቁሳቁስ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የሚያሳዩ መመሪያዎችን የያዙ መጻሕፍት በብዛት የሚያስፈልጉ መሆናቸው ነው። የኮምፒዩተር ተጠቃሚዎች መበራከታቸው ደግሞ እነዚህን የመሳሰሉ መመሪያ መጻሕፍትና ስለ ኮምፒዩተር የሚናገሩ መጽሔቶች እንዲበራከቱ ምክንያት ሆኗል።
በተጨማሪም በኮምፒዩተር መሳያ (monitor) ላይ በተለይም በድሮዎቹ የኮምፒዩተር መሳያዎች ላይ ለማንበብ መሞከር የራሱ ችግሮች እንዳሉት መገንዘብ ይገባል። አንዳንድ ተጠቃሚዎች አሁንም ቢሆን በዓይናቸው ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን በማማረር ይናገራሉ። በዚያም ሆነ በዚህ የቪዲዮ መሳያ እቃዎች ጥራት ኖሯቸው ግሩም የሆነ እይታን ለመፍጠር እንዲችሉ አሁን ካሉበት ደረጃ በአሥር እጥፍ መሻሻል እንደሚያስፈልጋቸው ይገመታል።
ከዚህም በተጨማሪ አንዳንዶች ከኮምፒዩተር መሳያ ይልቅ በወረቀት ላይ የተጻፈ ነገር ወሳኝነት ያለውና ላቅ ያለ ግምት የሚሰጠው እንዲሁም ፍጥነትና ኃይል ያለው ሆኖ ይሰማቸው ይሆናል። የታተመ ሰነድ የአንድን ሰው ሥራና የጥረቱን ውጤት ተጨባጭ በሆነ መንገድ የሚያሳይ ተደርጎ ይወሰዳል። በወረቀት ላይ የሰፈረ ሰነድ በአንድ የሥራ ኃላፊ ወይም ደንበኛ እጅ በሚገባበት ጊዜ እንኳን ሳይቀር ከኤሌክትሮኒክ መልእክት የበለጠ ትኩረትና አፋጣኝ ምላሽ ሊያገኝ ይችላል።
በመጨረሻ ደግሞ ብዙ ሰዎች ያስቀመጡትን መረጃ የማጣት ስጋት አለባቸው። ስጋታቸው ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ እውነት ሆኖ ይገኛል። በጊዜያችን ውስብስብ የሆኑ የመረጃ ማከማቺያ ቅንባሮዎች ቢኖሩም የኤሌክትሪክ ኃይል መዋዠቅ፣ የዲስክ መበላሸት ወይም የተሳሳተ ቁልፍ መንካት የሰዓታት ሥራን መና ሊያስቀር ይችላል። በመሆኑም ብዙ ሰዎች ወረቀትን ይበልጥ አስተማማኝ ሆኖ አግኝተውታል። እንዲያውም አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከ200 እስከ 300 ዓመታት የመቆየት ችሎታ ካለው ከአሲድ ነፃ የሆነ ወረቀት ጋር ሲወዳደሩ የኤሌክትሮኒክ መዝገቦች የሚቆዩት ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው። እርግጥ የኤሌክትሮኒክ መረጃ ተፈላጊነት እየቀነሰ የሚመጣው ቀስ በቀስ ነው። ይሁንና ቴክኖሎጂ በፍጥነት በማደግ ላይ ነው። ጊዜ ያለፈባቸው ሃርድዌሮችና ሶፍትዌሮች እየተተዉ በመሆናቸው በድሮ ኮምፒዩተሮች ላይ የተዘገቡ መረጃዎችን ማንበብ ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል።
ወረቀት አልባ ቢሮ ይመጣል የሚለው ሕልም እውን መሆን አለመሆኑ ወደፊት የምናየው ነገር ይሆናል። እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን የወረቀት ተፈላጊነት እየቀነሰ ይሄዳል የሚሉት ዘገባዎች በእጅጉ ተጋነዋል ለማለት ይቻላል።
ዛፎችን ጨፍጭፈን እንጨርሳቸው ይሆን?
ከአንድ ዛፍ ምን ያህል ወረቀት ማግኘት ይቻላል? ይህን የሚወስኑ በርካታ ነገሮች አሉ። የዛፉ መጠንና ዓይነት እንዲሁም የሚመረተው ወረቀት ዓይነትና ክብደት ወሳኝ ከሆኑት ነገሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ይሁንና አንድ ለገበያ የሚቀርብ መጠን ያለው ለወረቀት የሚሆን ዛፍ ወደ 12,000 የሚጠጋ ለመጻፊያ ወይም ለሕትመት የሚሆን መደበኛ ወረቀት ይወጣዋል። ያም ሆኖ ግን በአሁኑ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውለው ከፍተኛ መጠን ያለው ወረቀት ጫካዎች መለመላቸውን እንዳይቀሩና ጠፍ መሬት እንዳይሆኑ የሚያሰጋ ነው። ታዲያ ይህ ምህዳራዊ ቀውስ ውስጥ ይከተን ይሆን?
የወረቀት አምራቾች ይህ ሁኔታ ስጋት የሚያሳድር አይደለም ይላሉ። ከፍተኛ መጠን ያለው ወረቀት፣ በአንዳንድ አገሮች እንዲያውም እስከ 50 በመቶ የሚጠጋ መጠን ያለው ወረቀት ከእንጨት ኢንዱስትሪ ከሚገኘውና ለሌላ ለምንም ጥቅም ከማይውለው ሰጋቱራ የሚሠራ መሆኑን ይናገራሉ። ሰጋቱራ በሚበሰብስበት ጊዜ ሚቴን የሚባለውን ጋዝ የሚያፈልቅ ሲሆን ይህ ደግሞ ከምድር የሙቀት መጠን መጨመር ጋር የተያያዘ ነው። በመሆኑም የወረቀት ምርት ይህ ሰጋቱራ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደርጋል። ይሁንና የአካባቢ ጉዳይ ተሟጋቾች የወረቀት ኢንዱስትሪ ብክለት ይፈጥራል እንዲሁም ደኖችን አላግባብ ይጨፈጭፋል የሚል ወቀሳ ይሰነዝራሉ። ወረቀትን ለማምረት ጥቅም ላይ የሚውሉት ነዳጆች ራሳቸው የአካባቢ ሙቀት እንዲጨምር የሚያደርጉ ጋዞችን ያፈልቃሉ በማለት ይከራከራሉ! በተጨማሪም ቆሻሻ ወረቀት በሚጣልበት ጊዜ የአካባቢ ሙቀት እንዲጨምር የሚያደርጉ ተጨማሪ ጋዞች እንደሚፈልቁ ይናገራሉ።
ያም ሆኖ ግን ዎርልድ ቢዝነስ ካውንስል ፎር ሰስቴይኔብል ዴቬሎፕመንት ባደረገው ጥናት የምድር የተፈጥሮ ሀብት ሳይሟጠጥ ተፈላጊ መጠን ያለው ወረቀት ማምረት ይቻላል የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል። አንደኛው ምክንያት ዛፎች የሚተኩ መሆናቸውና ወረቀት ደግሞ ተመልሶ ሊመረት የሚችል መሆኑ ነው። ይሁንና “በእያንዳንዱ የወረቀት ዑደት ደረጃ ይኸውም በኢንዱስትሪ የደን ልማት አመራር፣ በተፈጨ እንጨትና በወረቀት የማምረት ሥራ፣ በወረቀት አጠቃቀም፣ በመልሶ ማምረት (recycling)፣ በኃይል ማዳንና በመጨረሻ የማስወገድ ሂደት ላይ ተጨማሪ ለውጦች ማድረግ እንደሚያስፈልግ” ጥናቱ አሳይቷል። ለአካባቢ ጉዳት የማያስከትልና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ለወረቀት የሚሆን የተፈጨ እንጨት ለማምረት በሚደረገው ጥረት የወረቀት ኢንዱስትሪ ከስንዴ ገለባ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሚያድጉ ዛፎች፣ ከበቆሎና ሄምፕ ከተባለው ተክል አማራጮችን በመፈለግ ላይ ነው። እነዚህ እርምጃዎች እስከ ምን ድረስ ተግባራዊና ውጤታማ እንደሚሆኑ ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ተጨማሪ ማብራሪያዎችንና የሥዕል መግለጫዎችን ጨምሮ ማለት ነው።
b በሐምሌ 22, 1997 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “ኢንተርኔት—የሚያስፈልግህ ነገር ነውን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በቢሮ ውስጥ የወረቀት ብክነትን መቀነስ የሚቻልበት መንገድ
✔ በተቻለ መጠን ጥቂት ነገሮችን ብቻ ማተም። ሰነዶችን በመሳያው ላይ ማረምና ማስተካከል። የምታትማቸውን ነገሮችና የወረቀት ረቂቆችን ቁጥር መቀነስ።
✔ በርከት ያለ መጠን ያላቸውን ጽሑፎች ስታትም ጽሑፉ ለማንበብ በማያስቸግር መጠን ደቀቅ ያለ እንዲሆን አድርግ።
✔ የማተሚያ መሣሪያህ በተከፈተ ቁጥር ወይም በሚያትምበት ጊዜ ሁሉ ለሙከራ ወረቀት የሚወስድ ከሆነ ይህን ማድረጉን እንዲያቆም አድርግ።
✔ ቆሻሻ ወረቀቶችን እንደገና ተጠቀምባቸው።
✔ በአንድ በኩል ብቻ የታተመበትን ወረቀት እንደገና እንዲመረት ከማድረግህ በፊት ረቂቆችን ለማተም ወይም ለሌላ አገልግሎት እንዲውል ለይተህ አስቀምጠው።
✔ በሚቻልበት ጊዜ ሁሉ በሁለቱም የወረቀቱ ገጾች ማተም ወይም ቅጂዎችን ማዘጋጀት።
✔ በአንድ ቢሮ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ ሊያዩት የሚገባ ሰነድ በሚኖርበት ጊዜ ለእያንዳንዱ ሰው ቅጂ ከማዘጋጀት ይልቅ አንዱን ቅጂ ብቻ እየተቀባበሉ እንዲመለከቱት ማድረግ።
✔ በወረቀት መጠቀምን ለማስቀረት የፋክስ መልእክቶችን በቀጥታ ከኮምፒዩተር ላይ መላክ። ፋክስ ለመላክ የግድ በወረቀት መጠቀም ካስፈለገ ደግሞ ለሽፋን የሚሆን ወረቀት ባለመጠቀም የወረቀት ፍጆታን መቀነስ።
✔ የኢ-ሜይል መልእክቶችን አስፈላጊ በማይሆንበት ጊዜ ሁሉ ከማተም መታቀብ።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንዶች ወረቀት አልባ ቢሮ ያስገኛል ተብሎ የተገመተው መሣሪያ ራሱ በወረቀት ቁልል ውስጥ ቀብሮናል በማለት ይከራከራሉ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንድ ጊዜ ከኮምፒዩተር መሳያ ይልቅ በታተመ ወረቀት ላይ ማንበብ ይቀልላል