ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች...
አባባ ጥሎን የሄደው ለምንድን ነው?
“አባቴ ለምን ጥሎን እንደሄደ ምንም የማውቀው ነገር የለም። የማውቀው እናቴ የነገረችኝን ብቻ ነው።”—ጄምስa
አንድ አባት ጓዙን ጠቅልሎ ሲሄድ ብዙውን ጊዜ ቤተሰቡ ለሐዘንና ቅሬታ ይዳረጋል። “እማማና አባባ ሲለያዩ በጣም ተበሳጭቼ ነበር” በማለት በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው የ14 ዓመቱ ጄምስ ተናግሯል። አንድ አባት ምንም ቃል ሳይተነፍስ ቤቱን ጥሎ ሲሄድና በኋላም ከቤተሰቡ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሳያደርግ ሲቀር በቀጣዮቹ ዓመታት ልጆቹ ጥፋተኛ እንደሆኑና እንደተጠሉ ሊሰማቸው እንዲሁም ሊበሳጩ ይችላሉ።b
አባትህ ጥሏችሁ ከሄደ የሄደበትን ምክንያት ስታውቅ ትበሳጭ ይሆናል። ማይክል የተባለ አንድ ወጣት “አባቴ ሌላ ሴት ወድዶ ጥሎን ሄደ” በማለት ይናገራል። “አንድ ጊዜ ከእርሷ ጋር ሳየው በጣም ተናደድኩ። አባባ እንደከዳን ሆኖ ነው የተሰማኝ።” ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ የአባትየው ቤቱን ለቅቆ መሄድ ግልግል የሚሆንበት ጊዜ ይኖር ይሆናል። አባቷ የአልኮል ሱሰኛ የነበረው መሊሳ “እርሱ ቤት ቢቆይ ኖሮ ሁኔታው ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆንብን ነበር” በማለት ተናግራለች።
ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ልጆች አባታቸው ጥሏቸው የሄደበትን ምክንያት ፈጽሞ አያውቁም። ምክንያቱን አለማወቃቸው ደግሞ የእርሱ አለመኖር ይበልጥ እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል። እውነት ነው፣ ወላጆችህ ችግሮች እንዳሉባቸው ታውቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይለያያሉ የሚለው ሐሳብ ጨርሶ ወደ አእምሮህ መጥቶ ላያውቅ ይችላል። ሮበርት እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “አባባ ትቶን ሲሄድ ምን እየተከናወነ እንዳለ እንኳ በቅጡ አልገባኝም ነበር። አንድ የማውቀው ነገር ነጋ ጠባ ይጨቃጨቁ ስለነበር ጥሩ መግባባት እንደሌላቸው ብቻ ነው።”
አንዳንድ አባቶች ቤታቸውን ጥለው የሚሄዱት ለምንድን ነው? አባትህ ጥሏችሁ ቢሄድ አንተን ስለጠላህ እንደሆነ ሊሰማህ ይገባልን? ወላጆችህ የተለያዩበትን ምክንያት ለአንተ ከመንገር ወደኋላ ያሉት ለምን ሊሆን ይችላል? በግልጽ ሊያስረዱህ አይገባምን?
ዝም የሚሉበት ምክንያት
አንድ አባት ቤቱን ጥሎ እንዲሄድ የሚያደርጉት ምክንያቶች ጨርሶ አያስደስቱም። ብዙውን ጊዜ ምክንያት የሚሆነው ነገር ምንዝር ሲሆን በአብዛኛው ደግሞ ቤተሰቡ ስለዚህ መጥፎ ድርጊት ምንም የሚያውቀው ነገር አይኖርም። አንዲት ሚስት እንዲህ ያለው መጥፎ ድርጊት መፈጸሙን ስታውቅ ባሏን ለመፍታት ትወስን ይሆናል። እንዲያውም የፍቺ ፋይል ከመከፈቱ በፊትም ሹልክ ብሎ እንዲወጣ ትነግረው ይሆናል። ይሁን እንጂ ልጆቹ አባታቸው ጥሏቸው የሄደው ለምን እንደሆነ ፈጽሞ ላያውቁ ይችላሉ።
ስለዚህ እናትህ ሁኔታውን ግልጥልጥ አድርጋ ከመናገር ወደኋላ የምትልበትን ምክንያት ለመረዳት ሞክር። አንደኛ ነገር የአባትህን መጥፎ ድርጊት ገልጾ መናገሩ የስሜት ሥቃይ ከማስከተል ውጪ ምንም የሚፈይደው ነገር አይኖርም ብላ አስባ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም አንዲት ሚስት ባሏ ታማኝነቱን እንዳጎደለ ማወቋ ምን ያህል ሊጎዳት እንደሚችል አስብ። (ሚልክያስ 2:13, 14) ስለዚህ ለወላጆችህ መለያየት መንስኤው ምንዝር ከነበረ እናትህ ስለ ሁኔታው ከአንተ ጋር መወያየቱ ቢከብዳት አትደነቅ።
ስለ አባትህስ ምን ለማለት ይቻላል? ለእናትህ ታማኝ ሳይሆን ቀርቶ ከነበረ ስለ ጉዳዩ እንደማይነግርህ የታወቀ ነው። አንዳንድ ወንዶች በፈጸሙት መጥፎ ተግባር ምክንያት ከባድ የጥፋተኝነት ስሜት ስለሚሰማቸው የልጆቻቸውን ፊት እንኳ ማየት ይከብዳቸዋል! ይሁን እንጂ ብዙ አባቶች አሳፋሪ ድርጊት ቢፈጽሙም ልጆቻቸውን መውደዳቸውን ይቀጥላሉ። ከልጆቻቸው ጋር የነበራቸውንም ግንኙነት እንደገና ለማደስ ይጥራሉ።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አባትየው ቤቱን ጥሎ እንዲሄድ የሚያደርገው ሚስትየው የፈጸመችው መጥፎ ድርጊት ቢሆንም ከልጆቹ ጋር የነበረውን የተቀራረበ ዝምድና ጠብቆ ለማቆየት የተቻለውን ያህል ይጥራል። ይሁን እንጂ ለትዳር መፍረስ ምክንያት የሚሆነው ምንዝር ብቻ አይደለም። በትዳር ውስጥ የሚነሱት ሌሎች አለመግባባቶች ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርሱም ለትዳር መፍረስ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ።c (ምሳሌ 18:24 NW ) እንዲህ ያለው ጉዳይ ብዙውን ጊዜ በባልና ሚስቱ መካከል ብቻ ያለ በመሆኑ የተጣሉበትን ምክንያት በተመለከተ ምንም የምታውቀው ነገር ላይኖር ይችላል።
መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 25:9 ላይ እንዲህ ይላል:- “ክርክርህን ከባልንጀራህ ጋር ተከራከር፤ የሌላ ሰው ምሥጢር ግን አትግለጥ።” አንዳንድ ጊዜ በትዳር ውስጥ ለሚፈጠሩ አለመግባባቶች ምክንያት የሚሆኑት ነገሮች በግልጽ የሚነገሩ አይደሉም። ብታምንም ባታምንም እንዲህ ያሉትን ነገሮች ጭራሽ ባትሰማቸው ይሻልሃል። በተጨማሪም ብዙውን ጊዜ ‘ምስጢርን መግለጥ’ የተበላሸውን ሁኔታ ይበልጥ ሊያባብሰው ይችላል። አንደኛውን ወገን ወደ መደገፍ እንድታዘነብል ሊያደርግህ ይችላል። ይህም በቤተሰብህ መካከል የተፈጠረውን ክፍተት ይበልጥ ያሰፋዋል። ስለዚህ ወላጆችህ ያልተግባቡባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች አለመናገራቸው የኋላ ኋላ ጥቅሙ ለአንተ ነው።
ማስተዋል በመጠቀም ቅሬታን ማስወገድ
ያም ሆኖ ግን አባትህ ቤቱን ጥሎ መሄዱ ሳያንስ ለምን ሄደ ለሚለው ጥያቄ መልስ አለማግኘትህ በጉዳዩ ላለመበሳጨት ወይም ቅሬታ እንዳያድርብህ የምታደርገውን ትግል ያከብድብሃል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 19:11 ላይ እንዲህ ይላል:- “ሰውን ጠቢብ አእምሮው ከቍጣ ያዘገየዋል [ሁልጊዜ ቁጣውን ያስወግድለታል ማለት አይደለም]።” ማስተዋል ለማግኘት ደግሞ የግድ ዝርዝር ጉዳዩን ማወቅ አያስፈልግህም።
ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆቻችን ፍጹማን አለመሆናቸውን እንድንገነዘብ ይረዳናል። “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” ይላል። (ሮሜ 3:23) ይህንን መራራ ሃቅ አምነህ መቀበልህ የወላጆችህን ስህተት በተመለከተ ያልተዛባ አመለካከት እንድትይዝ ሊረዳህ ይችላል። ለምሳሌ አባትህ የጋብቻ መሃላውን ቢያፈርስ በአምላክ ዘንድ ተጠያቂ የሚያደርገውን ከባድ በደል መፈጸሙ ነው። (ዕብራውያን 13:4) ይሁን እንጂ አባትህ መሃላውን ማፍረሱ አንተን ጠልቶሃል ወይም አይወድህም ማለት ላይሆን ይችላል።
ሁሉም ባለትዳሮች “በሥጋቸው ላይ መከራ” አለባቸው። (1 ቆሮንቶስ 7:28) ይህ ሰበብ ሊሆናቸው ባይችልም አንዳንድ ወንዶችና ሴቶች በመከራ የተሞላው ይህ ዓለም በሚያሳድረው ተጽእኖ በመሸነፍ መጥፎ ተግባር ይፈጽማሉ። ሮበርት እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “አባባ የተሻለውን ነገር ሁሉ እንድናገኝ ምኞቱ ነበር። ጥሩ ቤት እንዲኖረንና ደስተኛ እንድንሆን ለማድረግ ሲል የተሻለ ገቢ አገኛለሁ ብሎ ወዳሰበበት ቦታ ሄደን እንድንኖር አደረገ።” ሆኖም የሮበርት አባት የቤተሰቡን ሕይወት ለማሻሻል ከቅን ልቦና ተነሳስቶ ያደረገው ጥረት ወዲያው አቅጣጫውን ቀየረ። ሮበርት እንዲህ በማለት ያስረዳል:- “አባባ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ችላ ማለት ጀመረ። ከዚያም ከሥራው ወጣ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ እናቴንና እህቴን መስደብ ጀመረ።” ብዙም ሳይቆይ ነገሮች በጣም ከመበላሸታቸው የተነሣ የሮበርት እናትና አባት ተፋቱ።
ሮበርት የአባቱ ስህተቶች በቀላሉ በምሬት እንዲዋጥ ሊያደርጉት ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ አባቱ ስለሚገኝበት ሁኔታ የተሻለ ግንዛቤ ማግኘቱ ንዴቱን ለመቆጣጠር ረድቶታል። የወላጆቹ ትዳር መፍረሱ የሚያሳዝን ቢሆንም ሁኔታው ሮበርትን አንድ ትልቅ ነገር አስተምሮታል። እንዲህ ብሏል:- “ቤተሰብ ስመሰርት መንፈሳዊ ነገሮች የመጀመሪያውን ቦታ መያዝ ይኖርባቸዋል።”
በተመሳሳይም አስቀድሞ የተጠቀሰው ማይክል የሚሰማውን መጥፎ ስሜት መዋጋት አስፈልጎት ነበር። “ባደረገብን ነገር ስለተናደድሁ አባቴን ማበሳጨት እፈልግ ነበር” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። ሆኖም ከአባቱ ጋር የነበረውን ዝምድና ጠብቆ ቆይቷል። እንዲያውም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ መበሳጨቱን ትቶ ሕይወቱን በተረጋጋ ሁኔታ መምራት ችሏል።
አንተም ሁኔታው የሚፈቅድልህን ያህል ከአባትህ ጋር ጤናማ የሆነ የአባትና የልጅ ግንኙነት እንዲኖራችሁ ትፈልግ ይሆናል። እርግጥ፣ አባትህ አንተንና እናትህን ጎድቷችሁ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አንተ ስለ ጉዳዩ የተሟላ መረጃ ላይኖርህ ይችላል። አባትህ ጥፋተኛ እንደሆነ ብትገነዘብም እንኳ አሁንም ቢሆን አባትህ ነው። ለእርሱ ቢያንስ በተወሰነ ደረጃ አክብሮት የማሳየት ግዴታ አለብህ። (ኤፌሶን 6:1-3) ከአባትህ ጋር በምትነጋገርበት ወቅት ‘ንዴትን፣ ቊጣን፣ ጩኸትንና መሳደብንም’ አስወግድ። (ኤፌሶን 4:31) ከተቻለ ግን በወላጆችህ ትዳር ውስጥ የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ ገለልተኛ ሁን። ወላጆችህን እንደምትወዳቸው በማረጋገጥ ከሁለቱም ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመስረት ትችል ይሆናል።
የአንተ ጥፋት አይደለም
አባትህ ጥሏችሁ ሲሄድ ማየት ምናልባት በሕይወትህ ውስጥ ሊያጋጥሙህ ከሚችሉ በጣም አሳዛኝ ነገሮች አንዱ ነው። አባትህ ትቷችሁ እንዲሄድ ያደረጉትን ምክንያቶች ሙሉ በሙሉ ባታውቅም እንኳ የእኔ ጥፋት ነው ብለህ የምትደመድምበት ምንም ምክንያት የለም። እውነት ነው፣ ሁኔታው በግል እንደተጠላህ እንዲሰማህ ሊያደርግ ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ በአብዛኛው ለትዳር መፍረስ መንስኤ የሚሆኑት ልጆች አይደሉም። ወላጆችህ አብረው ለመኖር በአምላክ ፊት ቃል ገብተዋል። ከገቡት ቃል ጋር ተስማምቶ መኖር ደግሞ የእነርሱ እንጂ የአንተ ኃላፊነት አይደለም።—መክብብ 5:4-6
ይሁን እንጂ አሁንም ግራ የመጋባት፣ የጥፋተኝነት ወይም የተጠያቂነት ስሜት ከተሰማህ ለምን ሁኔታውን ለወላጆችህ አትነግራቸውም? ምናልባት ግልጽ ውይይት በማድረግ የሚያስፈልግህን ማጽናኛ ሊሰጡህ ይችሉ ይሆናል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ጄምስ እንዲህ በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “አባቴና እናቴ ቁጭ አድርገው እስካነጋገሩኝ ጊዜ ድረስ ተጠያቂው እኔ እንደሆንኩ አድርጌ አስብ ነበር።” ወጣቷ ናንሲም እንዲሁ አባቷና እናቷ ሲለያዩ ጥፋቱ የእርሷ እንደሆነ ተሰምቷት ነበር። ከእናቷ ጋር ብዙ ውይይት ካደረገች በኋላ እንዲህ የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሳለች:- “ልጆች ወላጆቻቸው ለሚፈጽሙት ስህተት ራሳቸውን ተጠያቂ ማድረግ አይኖርባቸውም።” አዎን፣ ወላጆችህ ‘የገዛ ራሳቸውን ሸክም በመሸከም’ ኃላፊነቱን እንዲወስዱ ጉዳዩን ለእነርሱ መተዉ የስሜት ጫና እንዳይደርስብህ ሊከላከልልህ ይችላል። (ገላትያ 6:5) ይሁን እንጂ አባት በሌለበት ቤተሰብ ውስጥ በተሳካ ሁኔታ ሕይወትህን መምራት የምትችለው እንዴት ነው? ወደፊት የሚወጣው ርዕስ ለዚህ ጥያቄ አንዳንድ መልሶች ይሰጣል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
b በየካቲት 2000 ንቁ! መጽሔት ላይ “ያለ አባት የቀሩ ቤተሰቦች—ለችግሩ መቋጫ ማበጀት” በሚል ዋና ርዕስ ሥር የወጡትን ተከታታይ ርዕሶች ተመልከት።
c ይሁን እንጂ ሁለቱም ወገኖች ትዳራቸውን አፍርሰው ሌላ ለማግባት የሚያስችላቸው ብቸኛ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ምንዝር እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል።—ማቴዎስ 19:9
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆችህ በትዳራቸው ውስጥ ላጋጠማቸው ችግር ራስህን አትውቀስ