የክርስትና ሃይማኖቶች ወደ ታሂቲ የገቡበት ሁኔታ
ታሂቲ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
በ18ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ በአውሮፓ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ሚስዮናዊ የመሆን ፍላጎት አድሮባቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ ሚስዮናዊ የሆነው ዊልያም ኬሪ በብሪታንያ የሚገኙ ፕሮቴስታንቶችን፣ ታሂቲን ጨምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ወዳልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ወንጌላውያን ሆነው እንዲሄዱ አነሳስቷቸው ነበር። ኬሪ እንዲህ እንዲያደርግ ያነሳሳው ኢየሱስ ለተከታዮቹ ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ የሰጠው ትእዛዝ ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) በተመሳሳይም ፍራንስዋ ኦገስት ሬኔ ደሸቶብሪዮ የተባሉ ፈረንሳዊ ጸሐፊ በ1802 ያዘጋጁትና በብዙ ቅጂዎች የተሸጠው ለ ዤኒ ዱ ክሪስቲያኒስም (ዘ ጂኒየስ ኦቭ ክሪስቺያኒቲ) የተሰኘ መጽሐፍ በርካታ ካቶሊኮችን ቀናተኛ ሚስዮናውያን እንዲሆኑ አነሳስቷቸዋል።
ከዚያም የካቶሊክና የፕሮቴስታንት ሚስዮናውያን ማኅበራት መቋቋም ጀመሩ። በ1797 የለንደን ሚስዮናውያን ማኅበር 29 ሚስዮናውያንን ወደ ታሂቲ ላከ። በ1841 ፒክፖየስ ፋዘርስ የተባለ ሃይማኖታዊ ማኅበር አባላት የሆኑ ካቶሊኮች ወደ ታሂቲ የመጡ ሲሆን ከሦስት ዓመት በኋላ ደግሞ የሞርሞን ቤተ ክርስቲያን አባላቱን ወደ አካባቢው ላከ። ብዙም ሳይቆይ ግን በርካታ ሚስዮናውያን መንፈሳዊ ተልእኳቸውን በመዘንጋት በፖለቲካ ጉዳዮችና በንግድ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ ጀመሩ። እነዚህ ሚስዮናውያን ተልእኳቸውን ወደ ጎን ገሸሽ ያደረጉት ለምን ነበር?
ከአሪ ጋር ጥምረት መፍጠር
መጀመሪያ ላይ የፕሮቴስታንቶች ትምህርት በሕብረተሰቡ ዘንድ እምብዛም ተቀባይነት አላገኘም ነበር። አንድ ጸሐፊ እንደገለጹት ከሆነ “መልእክታቸው የሚናገረው ስለ ርኅራኄና ሰዎችን ስለ መውደድ ሳይሆን ስለ ገሃነመ እሳትና በዚያ ስለ መሠቃየት ነበር።” ከዚህም ባሻገር ሚስዮናውያኑ፣ አሪ ተብለው ከሚጠሩት የጎሳ አለቆች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ተጠምቀው ክርስቲያን ለመሆን ፍላጎት እንደሌላቸው ማስተዋል አልተሳናቸውም። እነዚህ የጎሳ አለቆች የሃይማኖት መሪዎችም ነበሩ። በመሆኑም ሚስዮናውያኑ ትኩረታቸውን በጎሳ አለቆች ላይ ለማድረግ ወሰኑ።
ከእነዚህ የጎሳ አለቆች አንዱ የሆነው ዳግማዊ ፖማሪ በኢኮኖሚና በውትድርና መስክ ድጋፍ እንደሚሰጡት በማሰብ ሚስዮናውያኑን በጥሩ ሁኔታ ተቀበላቸው። ሚስዮናውያኑም ፖማሪ ግባቸውን ለማሳካት እንደሚረዳቸው ተሰምቷቸው ነበር። ከዚህም በላይ ሚስዮናውያኑ ወደ አካባቢው ከመጡበት ጊዜ አንስቶ የታሂቲን ነዋሪዎች፣ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን ለመሸመት ወደ አካባቢው ከሚመጡት መርከበኞች ጋር ያገናኙ ስለነበር በሕዝቡ ዘንድ የተወሰነ ተቀባይነት አግኝተው ነበር።
ፖማሪ፣ ሚስዮናውያኑ የፖለቲካ ግቦቹን ለማሳካትና የሚፈልገውን የጦር መሣሪያ ለማግኘት እንደሚረዱት ተስፋ በማድረግ ለመልእክታቸው ፍላጎት ያሳየ ከመሆኑም በላይ በ1811 ለመጠመቅ ጥያቄ አቀረበ። በቀጣዩ ዓመት ይህን ፍላጎቱን በደብዳቤ ገለጸ። ይሁን እንጂ ሚስዮናውያኑ፣ ፖማሪ ከመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ እየኖረ መሆኑን ለማረጋገጥ ሲሉ ለስምንት ዓመታት ያህል ጥያቄውን ለመቀበል ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ።
በዚህ መሃል ፖማሪ፣ ታሂቲንና በአቅራቢያዋ የሚገኙ ሶሳይቲ አይላንድስ ተብለው የሚጠሩትን ደሴቶች ያለ ተቀናቃኝ ማስተዳደር ችሎ ነበር። ፖማሪ ጥያቄውን በድጋሚ በማቅረቡ ሚስዮናውያኑ በ1819 እንዲጠመቅ ተስማሙ።
ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ውጤቱ መታየት ጀመረ። አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሶሳይቲ አይላንድስ እና በቱዋሞቱ አርኪፔላጎ ምዕራባዊ ክፍል የሚኖሩ ሰዎችን ጨምሮ ከኦስትራል ደሴቶች መካከል ግማሾቹ ክርስቲያን መሆናቸውን አወጁ።
የፖማሪ ሕግ
የደሴቲቱ ነዋሪዎች በጅምላ “ወደ ክርስትና በመለወጣቸው” ምክንያት ቀደም ሲል የነበሩትን ደንቦች፣ ልማዶችና ሕጎች በአዲስ መተካት አስፈለገ። ፖማሪ ይህን ለማድረግ ሚስዮናውያኑ እንዲረዱት ጠየቀ። ሚስዮናውያኑ ቀድሞውንም ቢሆን የአካባቢውን ወግ ለመለወጥና የንጉሡን ሥልጣን ለመገደብ ይፈልጉ ስለነበር የፖማሪን ጥያቄ ተቀብለው አዲስ ሕግ አረቀቁ። አንድ ጽሑፍ እንደገለጸው ከሆነ አዲሱ ሕግ “የብሪታንያን ሕገ መንግሥት፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ ሕጎችንና ክርስቲያን የሆኑ አገሮች የሚከተሏቸውን ልማዶች ያካተተ ነበር።” ሕጉ በርካታ ማስተካከያዎች ከተደረገበት በኋላ በንጉሡ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን የታሂቲ የመጀመሪያው በጽሑፍ የሰፈረ ሕግ ለመሆን በቃ። በኋላም የፖማሪ ሕግ ተብሎ መጠራት ጀመረ።
ይህ የፖማሪ ሕግ በአጎራባች ለሚገኙ በርካታ ደሴቶች ሞዴል ሆኖ ያገለገለ ሲሆን እነዚህ ደሴቶችም ተመሳሳይ ሕጎችን አርቅቀዋል። ሕጉ ሰንበትን በጥብቅ ማክበርን ያዝዝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ምንዝር፣ ከአንድ በላይ ማግባት፣ ሌብነትና ዓመጽ የመሳሰሉትን ድርጊቶች መፈጸም እንደሚያስቀጣ ይደነግጋል። ከዚህም ባሻገር ሕፃናትን መግደልን ጨምሮ ነፍስ ማጥፋት የሞት ቅጣት እንደሚያስከትል ይገልጻል። በተጨማሪም የጾታ ብልግናን የሚያበረታታን ማንኛውንም ዓይነት መዝናኛ ይከለክላል።
በፖለቲካዊ ጉዳዮች መካፈል
ዌር ዘ ዌቭስ ፎል የተባለው መጽሐፍ ስለ ፕሮቴስታንት ሚስዮናውያን ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “በደሴቲቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ከመጠን በላይ ተጠላልፈው ነበር። በተጨማሪም ከወንጌላዊነት ተልእኳቸው ጎን ለጎን ወታደራዊ ንድፍ አውጪዎች፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አማካሪዎች ብሎም ሕግና ሕገ መንግሥት አርቃቂዎች ሆነው ያገለግሉ ነበር።” በተመሳሳይም የሞርሞንና የካቶሊክ ሚስዮናውያን በተላኩባቸው ደሴቶች ሕዝባዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ይዘው ነበር። ከኦስትራል ደሴቶች መካከል አንዷ በሆነችው በቱብዋዪ ደሴት የሚኖር አንድ የሞርሞን ሚስዮናዊ “መንግሥት በቤተ ክርስቲያኒቱ ቁጥጥር ሥር ነው። . . . የደሴቲቱ ጠቅላይ ሚኒስትርም እኔ ነኝ” በማለት ተናግሮ ነበር። በጋምቢየር ደሴቶችም ካቶሊኮች ተመሳሳይ ተጽዕኖ አሳድረው የነበረ ሲሆን አንድ የካቶሊክ ቄስ የመንግሥት ባለሥልጣን ሆኖ ይሠራ ነበር።
ክሌር ሎ የተባሉ ታሪክ ጸሐፊ እንደገለጹት፣ ሚስዮናውያኑ ሕዝቡን መጽሐፍ ቅዱስ ከማስተማር ይልቅ “መልእክታቸውን ለማድረስ ፖለቲካን መጠቀም መርጠዋል።” ይህን ዘዴ የተጠቀሙት፣ ይዘው የመጡትን መልእክት በፍጥነትና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማሰራጨት እንደሚያስችላቸው ስለተሰማቸው ነበር። ሚስዮናውያኑም ይህን በማድረግ የቤተ ክርስቲያኑ ኃላፊዎች የሰጧቸውን መመሪያ ተላልፈዋል። አሁን ድረስ በፍሬንች ፖሊኔዥያ፣ ሃይማኖትና ፖለቲካ እጅና ጓንት ናቸው።
የንግዱ እንቅስቃሴ የነበረው ሚና
በአውስትራሊያ የሚገኘው የካንቤራ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ኒል ገንሰን፣ አንዳንድ ሚስዮናውያን “በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ እጃቸውን ያስገቡት በንግድ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ ከነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ” እንደሆነ ገልጸዋል። በርካታ ሚስዮናውያን የንግድ መርከቦችን በመሸጥ፣ በማከራየት ሌላው ቀርቶ በመሥራት በንግዱ እንቅስቃሴ ይካፈሉ ነበር። አንዳንዶቹ ደግሞ አሮውሩት የተባለ ተክል፣ ቡና፣ ጥጥ፣ ሸንኮራ አገዳና ትንባሆ ያመርቱ ነበር።
ሚስዮናውያኑ የሚያደርጉት የንግድ እንቅስቃሴ በጣም የተደራጀ ስለነበር በአውስትራሊያና በታሂቲ መካከል የነበረውን የንግድ ልውውጥ ለ25 ዓመታት መቆጣጠር ችለው ነበር። በተለይ በአሳማ ሥጋና በኮኮናት ዘይት ንግድ በጣም ተሳክቶላቸዋል። ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ሚስዮናውያን ሁኔታው ተገቢ እንዳልሆነ ስለተሰማቸው ጉዳዩን ለለንደን የሚስዮናውያን ማኅበር አሳወቁ። ሌሎቹ ግን ይህ ዓይነቱ ንግድ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴያቸውን ለማራመድ ጠቃሚ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። እንዴት?
ሚስዮናውያኑ ታሂቲ ከገቡ ጀምሮ በሙያቸውና በአንዳንድ ምርቶቻቸው አማካኝነት የደሴቲቱን ነዋሪዎች ቀልብ ለመሳብ ይጥሩ ነበር። ሚስዮናውያኑ፣ ነዋሪው ይበልጥ “መሠልጠኑ” ደስታ ያስገኝለታል የሚል እምነት ስለነበራቸው ጠንክሮ መሥራትንና ቁሳዊ ሃብት ማካበትን ያበረታቱ ነበር። እንዲያውም አንድ ሰው ሀብታም መሆኑ አምላክ እንደባረከው የሚያሳይ እንደሆነ ይናገሩ ነበር።
ያደረጉት ለውጥ በእርግጥ እውነተኛ ነበር?
የለንደን ሚስዮናውያን ማኅበርን በተመለከተ ጥናት ያካሄዱ አንድ የታሪክ ምሑር፣ ክርስትናን በፍጥነትና በጅምላ ከተቀበሉት የደሴቲቱ ነዋሪዎች መካከል አብዛኞቹ ይህን ያደረጉት “ትክክለኛውን ነገር ለመፈጸም ወይም ከአምላክ ጋር ዝምድና ለመመሥረት ፍላጎት ስለነበራቸው አለመሆኑን” ከጊዜ በኋላ ጽፈዋል። ገንሰን፣ የታሂቲ ነዋሪዎች ክርስትናን የተቀበሉት “ዳግማዊ ፖማሪ እንዲህ እንዲያደርጉ ስለፈለገ ሲሆን ራሱም ቢሆን ክርስትናን የተቀበለው በእንግሊዝ ሚስዮናውያን (ሃይማኖታዊ ትምህርት ሳይሆን) ሃይማኖታዊ ልማድ ተስቦ ነው” በማለት ጽፈዋል።
በርካታ የታሂቲ ነዋሪዎች ክርስቲያን የነበሩት በስም ብቻ ሲሆን በጥቂት ዓመታት ውስጥም ማማያ ተብሎ በሚጠራ የሃይማኖት ንቅናቄ አማካኝነት ትተውት ወደነበረው የባዕድ አምልኮ ተመልሰዋል። ሌላው ቀርቶ አልጋ ወራሾቹ እንኳ ክርስትናንና የአካባቢውን ልማድ ቀላቅሎ የያዘውን እንዲሁም ለሥነ ምግባር ደንታ የሌለውን የማማያን አምልኮ ይከተሉ ነበር።
አንግሊካን፣ ካልቪኒስትና ሜቶዲስት በተባሉት የፕሮቴስታንት ቡድኖች መካከል ከፍተኛ ሽኩቻ የነበረ ሲሆን ከካቶሊኮች ጋርም በጥላቻ ዓይን ይተያዩ ነበር። ዘ ካምብሪጅ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ፓሲፊክ አይላንደርስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል:- “የደሴቲቱ ነዋሪዎች በሃይማኖት ድርጅቶች መካከል ያለው የመሠረተ ትምህርት ልዩነት ሊገባቸው ያልቻለ ከመሆኑም ሌላ ወንድማማች ነን የሚሉት ክርስቲያኖች የሚፎካከሩት ለምን እንደሆነ ግልጽ አልሆነላቸውም።” ለምሳሌ ያህል፣ ሁለት የካቶሊክ ሚስዮናውያን ወደ ታሂቲ በመጡበት ወቅት አንድ የፕሮቴስታንት ሚስዮናዊ ባስተላለፈው ትእዛዝ መሠረት ወዲያውኑ ከደሴቲቱ እንዲባረሩ ተደርገዋል። ይህ ድርጊት ብሪታንያንና ፈረንሳይን ዲፕሎማሲያዊ ግጭት ውስጥ የከተታቸው ሲሆን በሁለቱ አገራት መካከል ጦርነት ሊነሳ ምንም አልቀረውም ነበር። በመጨረሻም ፈረንሳይ፣ ታሂቲ በእሷ “ጥበቃ” ሥር እንድትሆን ያነሳችውን ጥያቄ መቀበሏን ብሪታንያ አሳወቀች።
ጠቃሚ አስተዋጽኦ አበርክተዋል
በሌላ በኩል ግን በርካታ የጥንት ሚስዮናውያን መሃይምነትን በማጥፋት እንዲሁም የሕፃናት ግድያን፣ የሰው ሥጋ መብላትንና ሰውን ለመሥዋዕትነት ማቅረብን የመሳሰሉ ልማዶችን በማስቀረት ረገድ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ከእነዚህ ሚስዮናውያን መካከል አንዳንዶቹ ከመጠን በላይ ጥብቅ የነበሩ ቢሆንም የደሴቲቱ ነዋሪዎች መልካም ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው ለማድረግ የተቻላቸውን ያህል ጥረዋል።
ሚስዮናውያኑ ካበረከቱት አስተዋጽኦ ሁሉ የላቀው መጽሐፍ ቅዱስን በታሂቲ ቋንቋ መተርጎም መቻላቸው ነው። እንዲህ ማድረጋቸውም የአካባቢው ነዋሪዎች መለኮታዊውን ስም እንዲያውቁ ረድቷቸዋል። የደሴቲቱ ነዋሪዎች ይህንን ስም አሁንም ድረስ በሚገባ ያውቁታል።a—ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በሐምሌ 1, 2003 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ተራ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ተረጎሙ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
‘ከዓለም አይደላችሁም’
የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች በዚህ መሠረታዊ ሥርዓት ይመራሉ። (ዮሐንስ 15:19) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ኢየሱስ “እኔ ከዓለም እንዳልሆንሁ ሁሉ፣ እነርሱም ከዓለም አይደሉም” በማለት ወደ አምላክ ጸልዮአል። (ዮሐንስ 17:16) ኢየሱስም ቢሆን ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ የነበረ ሲሆን ደቀ መዛሙርት ለማፍራትም ፖለቲካን መሣሪያ አድርጎ አልተጠቀመም። ከዚህም በተጨማሪ የዓለም መንፈስ የሚንጸባረቅበት ድርጊት በመሆኑ ቁሳዊ ሀብት ማሳደድን አውግዟል። ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊ ሀብትን በመሰብሰብ ላይ ያተኮረ ቀላል ሕይወት መምራትን አበረታቷል። (ማቴዎስ 6:22-24, 33, 34) በመሆኑም እውነተኛ ተከታዮቹ ምሳሌውን ይኮርጃሉ።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን በ1797 ወደ ታሂቲ ደሴት ሲመጡ
[ምንጭ]
The Granger Collection, New York
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1845 ገደማ፣ አንድ ሚስዮናዊ ወደ ክርስትና ከተለወጡ የታሂቲ ነዋሪዎች ጋር
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ንጉሥ ዳግማዊ ፖማሪ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታሂቲ እና ዋና ከተማዋ ፓፒዬቴ
[ምንጭ]
Photo courtesy of Tahiti Tourisme
[በገጽ 14 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
በስተ ግራ:- Photo by Henry Guttmann/Getty Images; በስተ ቀኝ:- Collection du Musée de Tahiti et de ses Îles, Punaauia, Tahiti