“ኧረ አፍንጫ!”
ብዙውን ጊዜ ሰዎች ተባዕቱን ፕሮቦሲስ ጦጣ ሲያዩ አግራሞታቸውን በዚህ መንገድ መግለጻቸው የተለመደ ነው።a እንደ ኩንቢ ጠልጠል ያለው የዚህ ጦጣ አፍንጫ በአንዳንድ ተባዕቶች ላይ እስከ 18 ሴንቲ ሜትር ገደማ ሊያድግ ይችላል፤ ይህም የጦጣውን ቁመት (ጦጣው በአራት እግሮቹ ሲቆም) አንድ አራተኛ ያህላል ማለት ነው። የጦጣው የተንዘረፈፈ አፍንጫ አፉንና አገጩን ስለሚሸፍነው በሚበላበት ጊዜ አፍንጫውን ወደ ጎን ገፋ ማድረግ ይኖርበታል! የሰው ልጆች አፍንጫ ልክ እንደዚህ ጦጣ የቁመታቸውን አንድ አራተኛ የሚያህል ቢሆን ኖሮ ደረታቸው ጋ ይደርስ ነበር።
ፕሮቦሲስ ጦጣ እንዲህ ያለ አፍንጫ ያለው መሆኑ ምን ይጠቅመዋል?b በዚህ ረገድ የተለያዩ መላ ምቶች ተሰንዝረዋል። ለምሳሌ አንዳንዶች፣ አፍንጫው ከሰውነቱ ውስጥ ሙቀት እንዲወጣ በማድረግ ሰውነቱን ለማቀዝቀዝ እንደሚረዳው አሊያም ኃይለኛ ድምፅ ለማውጣት እንደሚያስችለው ይገልጻሉ። አፍንጫውን ሌሎች ተባዕት ፕሮቦሲስ ጦጣዎችን ለማስጠንቀቅ እንደሚጠቀምበት የሚናገሩም አሉ። በእርግጥም የቡድኑ መሪ የሆነው አውራ በሚቆጣበት ወይም በሚፈራበትና በሚደነግጥበት ጊዜ አፍንጫው ይነፋና ቀይ ይሆናል። የተባዕቱ አፍንጫ፣ የእንስቷን ጦጣ ልብ ለመማረክም ሊያገለግል ይችላል። በጥቅሉ ሲታይ ግን የጦጣው አፍንጫ ገና ያላወቅናቸውን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሳይሆን አይቀርም።
የተቆዘረ ሆድ
ተባዕቶቹም ሆኑ እንስቶቹ ፕሮቦሲስ ጦጣዎች ሆዳቸው ቁዝር ያለ ነው። የሆድ ዕቃቸው መጠን የሰውነታቸውን ጠቅላላ ክብደት አንድ አራተኛ ይሆናል። በዚህ ምክንያት ተባዕቶቹም ሆነ እንስቶቹ እርጉዝ ይመስላሉ! ይሁንና የእነዚህ ጦጣዎች ሆድ የተቀበተተው ለምንድን ነው?
እንደ ላሞች ሁሉ በፕሮቦሲስ ጦጣዎች ሆድ ዕቃ ውስጥም ተፈጭተው የላሙ ዕፅዋትና ባክቴሪያዎች ይገኛሉ። ባክቴሪያዎቹ ምግቡ እንዲብላላ በማድረግ ሴሊውለስ የተባለው ንጥረ ነገር እንዲሁም አንዳንድ መርዛማ ዕፅዋት እንዲፈጩ ያደርጋሉ፤ እነዚህ መርዛማ ዕፅዋት ሌሎች እንስሳትን ሊገድሉ የሚችሉ ናቸው። በእርግጥም ፕሮቦሲስ ጦጣዎች ምግብ የሚፈጩበት መንገድ አስደናቂ ነው፤ በዚህም ምክንያት ከሌሎች የጦጣ ዝርያዎች በተለየ መልኩ ቅጠሎችንና ጣፋጭነት የሌላቸው ፍራፍሬዎችን፣ ጥራጥሬዎችን፣ ተምር እንዲሁም ሌሎች ዕፅዋትን ብቻ እየበሉ መኖር ይችላሉ።
ፕሮቦሲስ ጦጣዎች ምግብ የሚፈጩበት መንገድ አስገራሚ ቢሆንም የራሱ የሆነ ጉዳትም አለው። እንስሳቱ ስኳርነት ያላቸውን ቶሎ የሚፈሉ ፍራፍሬዎች መመገብ የለባቸውም። እንደነዚህ ያሉት ጣፋጭ ፍራፍሬዎች የጦጣዎቹን ሆድ በመንፋት ተሠቃይተው እንዲሞቱ ሊያደርጓቸው ይችላሉ።
ፕሮቦሲስ ጦጣዎች በሴሊውለስ የበለጸጉ ምግቦችን ስለሚመገቡና የሆድ ዕቃቸው አሠራር ውስብስብ ስለሆነ ምግባቸውን ለመፍጨት ብዙ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህ ቁርሳቸውን ግጥም አድርገው ከበሉ በኋላ እንደገና ከመመገባቸው በፊት ለበርካታ ሰዓታት ያርፋሉ።
ማኅበራዊ እንስሳ
ፕሮቦሲስ ጦጣዎች ሲበሉም ሆኑ ሲያርፉ ብቻቸውን አይሆኑም። አንድ አውራ፣ እስከ ስምንት የሚደርሱ እንስቶችንና ልጆቻቸውን ያቀፈ ቡድን ሊመራ ይችላል። በዚህ ቡድን ውስጥ የሚወለዱ ተባዕቶች ራሳቸውን የሚችሉበት ዕድሜ ላይ ሲደርሱ ይባረራሉ። እነዚህ ጦጣዎች ከሌሎች ለአካለ መጠን ያልደረሱ ተባዕት ጦጣዎች ጋር ይቀናጁና በዕድሜ ተለቅ ያሉ አንድ ወይም ሁለት ተባዕት ጦጣዎች ያሉበት ቡድን ይመሠርታሉ። ስለ እነዚህ ጦጣዎች ብዙም ለማያውቅ ሰው እንዲህ ያለው ቡድን አውራና እንስቶች ያሉበት ቡድን ሊመስል ይችላል።
ፕሮቦሲስ ጦጣዎች እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ረገድ ያልተለመደ ባሕርይ አላቸው፤ በተለይ ምሽት ላይ በወንዝ ዳርቻዎች ላይ ሲሰባሰቡ የአንዱ አውራ እንስቶች ከሌላው አውራ እንስቶች ጋር ሊቀላቀሉ ይችላሉ። እንዲህ ባሉት ጊዜያት አንደኛው አውራ፣ ሌላኛው አውራ በእንስቶቹ ላይ ዓይኑን እንደጣለ ከተሰማው ጥንካሬውን ማሳየት ይጀምራል። አብዛኛውን ጊዜ እንስቶቹን ለመከላከል የተነሳው አውራ (እስከ 20 ኪሎ ግራም የሚደርስ ክብደት ሊኖረው ይችላል) በአራት እግሮቹ ቆሞ አፉን በሰፊው ይከፍትና በተፎካካሪው ላይ ያፈጥበታል። ፕሮቦሲስ መንኪስ ኦቭ ቦርኒኦ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ይህ እርምጃ ተፈላጊውን ውጤት ካላስገኘ አውራው በድንገት ከዛፍ ዛፍ እየዘለለ ድምፁን ከፍ አድርጎ ማጓራት ይጀምራል፤ ብዙውን ጊዜ ጦጣው እየዘለለ ደረቅ ቅርንጫፎች ላይ ስለሚያርፍ የቅርንጫፎቹ መሰበር የሚፈጥረው ድምፅ ሁካታውን ያባብሰዋል።” ከስንት አንዴ ቢሆንም ግብ ግብ የሚነሳበት ጊዜም አለ።
ከላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ “የፕሮቦሲስ ጦጣዎች መልክ ብቻ ሳይሆን የሚያወጧቸው የተለያዩ ድምፆችም አስገራሚ ናቸው” ይላል። እነዚህ እንስሳት፣ በተለይ ምሽት ላይ በወንዝ ዳርቻዎች ሲሰባሰቡ ያጓራሉ፣ ያናፋሉ፣ እንደ አንበሳ ያገሳሉ እንዲሁም እንደ ፉጨት ዓይነት ድምፅ ያሰማሉ። የሚገርመው ግን በዚህ ሁሉ ሁካታ መሐል እናቶቹ ምንም ሳይረበሹ ልጆቻቸውን የሚያጠቡና የሚያሰማምሩ መሆኑ ነው። በመጨረሻም ጀምበሯ ስትጠልቅ ጦጣዎቹ ወንዙ አጠገብ ባሉ ረጃጅም ዛፎች ላይ ተመቻችተው ይተኛሉ።
ለየት ያለ እግር ያላቸው ጦጣዎች
ፕሮቦሲስ ጦጣዎች ከአፍንጫቸው በተጨማሪ ትኩረት የሚስብ ሌላም ነገር አላቸው፤ የተወሰኑ ጣቶቻቸው በከፊል የተያያዙ ናቸው። ይህ ደግሞ ለመዋኘት ብቻ ሳይሆን በወንዝ ዳርቻዎች ላይ ባለው ረግረጋማ መሬት ላይ ያለ ችግር ለመሄድም ያስችላቸዋል። እርግጥ በሐሩር አካባቢ ስለሚገኙ ረግረጋማ የወንዝ ዳርቻዎች ሲነሳ አዞዎችን ማሰብህ አይቀርም። ፕሮቦሲስ ጦጣዎች በሚኖሩበት አካባቢ በርካታ አዞዎች አሉ። ታዲያ እነዚህ በወንዝ ዳርቻዎች የሚኖሩ ጦጣዎች በአዞ ከመበላት የሚያመልጡት እንዴት ነው?
አንደኛው ዘዴያቸው አንዳች ድምፅ ሳያሰሙ በቀስታ ውኃው ውስጥ ከገቡ በኋላ ውኃውን ሳያናውጡ በአንድ መስመር ሆነው እየዋኙ ማለፍ ነው። ወንዙ ጠበብ ያለ በሚሆንበት ጊዜ ግን በሌላ ዘዴ ሲጠቀሙ ታይተዋል። ከፍ ያለ ዛፍ ላይ ይወጡና እስከ 9 ሜትር የሚደርስ ከፍታ ካለው ቅርንጫፍ በመዝለል ወንዙ ላይ በሆዳቸው ካረፉ በኋላ የቀረውን ርቀት በከፍተኛ ፍጥነት ዋኝተው ይሻገራሉ። እናቶችም ሳይቀር ልጆቻቸውን አቅፈው በዚህ ዘዴ ይጠቀማሉ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በብዛት ወንዙ ውስጥ ዘለው ይገቡና ወደሌላኛው ዳርቻ ለመሻገር በተቻላቸው ፍጥነት ይዋኛሉ! ከሁሉ የከፋው ጠላታቸው ግን አዞ አይደለም።
ሊጠፋ የተቃረበ ዝርያ
ፕሮቦሲስ ጦጣዎች ከምድር ገጽ ለመጥፋት የተቃረቡ ዝርያዎች ዝርዝር ውስጥ ገብተዋል፤ ዋነኛ መኖሪያቸው በሆነው አካባቢ ያሉት ጦጣዎች በጥቂት ሺህዎች የሚቆጠሩ ሲሆኑ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ነው። ለዚህም በዋነኝነት ተጠያቂ የሆኑት የሰው ልጆች ናቸው። ለእነዚህ ጦጣዎች አስጊ ከሆኑት ነገሮች መካከል የሰው ልጆች የሚያስነሱት ሰደድ እሳት፣ የደን መጨፍጨፍ፣ ተገቢ ቁጥጥር ያልተደረገበት ቱሪዝም እንዲሁም የፓልም ተክልን ለማስፋፋት ሲባል ደኖችን መመንጠር ይገኙበታል። ሌላው ደግሞ አደን ነው። አንዳንዶች ለመዝናኛ ብለው እነዚህን ጦጣዎች ይገድላሉ። ለምግብነት ወይም ለባሕላዊ መድኃኒትነት ሲባልም ይታደናሉ። ብዙውን ጊዜ እንስሳቱ የሚተኙት በወንዞች ዳርቻ ባሉ ዛፎች ላይ በቀላሉ ሊታዩ በሚችሉበት ሁኔታ ስለሆነ ለጉዳት የተጋለጡ ናቸው። እንዲያውም በሞተር ጀልባ የሚጠቀሙ አዳኞች በሚያዘወትሩት አንድ አካባቢ የጦጣዎቹ ቁጥር በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ 50 በመቶ ቀንሷል!
የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ይህ ዝርያ ስለተጋረጠበት አደጋ ሕዝቡ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ እየጣሩ ነው፤ በተጨማሪም ቦርኒኦ ውስጥ ፕሮቦሲስ ጦጣዎች ሕጋዊ ጥበቃ እንዲያገኙ ተደርጓል። ይሁን እንጂ እነዚህ እርምጃዎች በቂ ናቸው? ይህን ጊዜ ያሳየናል። እንግዳ የሆኑ ብዙ ነገሮች ያሉት ይህ ፍጡር ከዱር ቢጠፋ ምንኛ አሳዛኝ ይሆናል! ደግሞም ይህ ጦጣ በእንስሳት መጠበቂያ ቦታዎች መኖር ብዙም አይመቸውም።
እርግጥ ነው፣ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው ፍጥረታት ፕሮቦሲስ ጦጣዎች ብቻ አይደሉም። ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዝርያዎች ከምድር ገጽ ጠፍተዋል። ደስ የሚለው ነገር ግን አምላክ ምድርን ሙሉ በሙሉ የማስተዳደር፣ ክፉዎችን የማስወገድና ሕዝቦቹ ምድርን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የማስተማር ዓላማ አለው። (ምሳሌ 2:21, 22) ይሖዋ አምላክ “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ጕዳት ወይም ጥፋት አያደርሱም፤ ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና” በማለት ቃል ገብቷል።—ኢሳይያስ 11:9
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ፕሮቦሲስ ጦጣ የሚኖረው በቦርኒኦ ደሴት ነው። የአገሩ ነዋሪዎች ይህን እንስሳ ኧራንግ ቤላንዳ ወይም “የደች ሰው” ብለው ይጠሩታል።
b እንስቶቹም የተባዕቶቹን ያህል ባይሆንም ትልቅ አፍንጫ አላቸው።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፕሮቦሲስ ጦጣዎች ለየት ያለ አፍንጫና ሆድ አላቸው
[የሥዕሉ ምንጭ]
© Peter Lilja/age fotostock
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተባዕቱ አፍንጫ አፉን ስለሚሸፍነው በሚበላበት ጊዜ ወደ ጎን ገፋ ማድረግ ይኖርበታል
[የሥዕሉ ምንጭ]
© Juniors Bildarchiv/Alamy
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፕሮቦሲስ ጦጣዎች ሲበሉም ሆኑ ሲያርፉ ብቻቸውን አይሆኑም
[የሥዕሉ ምንጭ]
© Peter Lilja/age fotostock